ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝቦቿ በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍለው ወይም ተመድበው የኖሩበት ዘመን ቢኖር በዘመነ ኢሕአዲግ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አዎ በዘመነ ኢሕአዲግ ሕዝቧ ሕዝቦች ተብለው የበዙበት፣ የተበተኑበት ነው፡፡ አበዛዙ ሥነ ልሳናዊ ትክክለኛነቱ ሲያጠራጥር ፖለቲካዊ ይዘቱ ብዙኃዊነት የሚል ቅብ የሆነ አገላለፅን የያዘ ሲሆን ውስጡ ግን አብዝቶ ማሳነስ፣ ከነበረበት ደረጃ ማውረድ፣ ማዝቀጥ የሚሉ ተግባራዊ ትርጉምን ያስተዋልንባቸው፣ እያስተዋልንም ያለንባቸው እሳቤዎች እና ተግባራት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ዘመነ ኢሕአዲግ እንደሚባለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሳይሆን ወያኔያዊ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ነበር፡፡ ወያኔያዊ የሚለውን ቅጽል የተጠቀምኩት ከዛ በኃላ የተገለፁት ቃላት በሙሉ የይስሙላ፣ የሸርና የድንቁርና የዝቅጠትና የውርደት የቁልቁለት አካሄድን መርህ ያደረጉ በተግባር ደረጃ ሲፈተኑ ሐሰተኛ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡
ፌዴራላዊ ሲል እውነተኛ ፌዴራላዊ ያልሆነ በተግባር ሲፈተሸ አሓዳዊ ወይም የሞግዚት አስተዳደርን ያነገሠ፣ ዲሞክራሲያዊ ሲባል በወረቀት እንጂ በተግባር ከዲሞክራሲ ጋር ዓይንና ናጫ የሆነ፤ ሪፐብሊክ ማለት ትርጉሙ ሕዝባዊ መንግስት ሲሆን ወያኔያዊው ሪፐብሊክ ሕዝባዊ መሠረት የሌለው፣ ወያኔ መንጃ ፍቃድ ሳይኖረው ለሃያ ሰባት ዓመታት ያሽከረከረው መንግስት፤ ኢትዮጵያ የሚለውን ታላቅ የክብርና የነፃነት መገለጫ ቃል እንኳ በወያኔያዊው ኢትዮጵያ ክብሩንና ማንነቱን የጣለ ያጣ የተዛባ አመለካከትና ጥላቻ በመርዝ የተላወሰ ትርጉምና ታሪካዊ ሴራና ደባ ሲሰጠው የኖረ ሁኖ ታይቷል፡፡
የወያኔያዊው ፌዴራላዊ ሥርወ መንግስት የማፍያዎች ስብስብ ስለሆነ በመልካም እርሻ ላይ እንክርዳድ የዘራ አሳዛኝና የባከነ የዝቅጠት ታሪካዊ ጊዜ እውን ሁኖ ታይቶበታል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም እንክርዳድ ተዘርቶበት ስንዴ ሁኖ የበቀለውን ይህን ትውልድ ለመግለፅና ለማወደስ ነው፡፡ ያባቶችን የሥነ-ልቦና ከፍታ የታጠቀ ዛሬም የታሪክ ውሃ ልክ መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል፡፡ ለዚህም ዕውቅና እና ምስጋና ይገባዋል፡፡
ከ1983 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ በተለይም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የተወለደው ትውልድ ዓይኑን የገለጠውና ጆሮውን የከፈተው ወይም የተማረው ብሔር ተኮር የሆነ ርዕዮት ዓለምን እንዲያቀነቅን ተደርጎ ነው፡፡ ስለ ብሔር ማወቅ መማር ችግር የለበትም፤ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ወያኔያዊው ብሔርና ዘር ተኮር እሳቤ በመርዝ የተላወሰ ማር ሆኖ ቀርቦ የወጣቱን ወይም የሕዝቡን እሳቤ ወደ ዝቅጠትና ውድቀት በእጅጉ አዋርዶታል፡፡ ከፋይዳው ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ብሔርህ ይህ ነው ሌላው ብሔር ባንተ ብሔር ላይ ይህን በደል ፈጽሟል፣ ዘርፏል፣ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል፣ እሱ ላንተ ታሪካዊ ጠላትህ ነው፣ አሁንም ሊያጠፋህ ይችላል በሚል የቅኝ ግዛት የከፋፍለህና የአጋጭተህ አገዛዝ የተጫነበት ትውልድ ነው፤ ይህ ትውልድ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ላይ ሳይሆን ክልላዊነት ላይ ብቻ እንዲያቶክርና እንዲያስብ የተደረገ ወይም የተገደደ ትውልድ ነበር ፡፡ ልክ እንደ ጋሪ ፈረስ አንድ አቅጣጫ ብቻ ይዞ እንዲጓዝ ግራውንና ቀኙን እያየ እንዳይሄድ የተደረገ ትውልድ ነበር፡፡ (አንዳንድ ቦታዎች ላይ የጋሪ ፈረስ የሚጎትተውን የጋሪ ክፍል እንዳያይና እንዳይበረግግ ዓይኑ አካባቢ ወደኃላ እና ግራ ቀኙን እንዳያይ በፕላስቲክ ይሸፈናል)
ይህ ወያኔያዊ ኅቡዕ አገዛዝ የበደል ጥዋው ሞልቶ ሲፈስ በሕዝብ ትግል ከሕዝብ ጫንቃ ላይና ትከሻ ተወርውሮ ሲጣል በደሉን፣ ያደረሰውን ግፍ አምኖ ተቀብሎ ይቅርታ ጠይቆ መኖርን እምቢ በማለት በትህቢት ተወጥሮ እኔ ያላስፈጨዃትና እኔ ያላቦካዃት ያልጋገርኳት ሀገር እንድትኖር አልፈቅድም ብሎ ሲመሠረትም ጀምሮ ሊያጠፋት የሰነደላትን ሀገር በተግባር አወድማታለሁ ብሎ ጀርባዋን ወጋ! የማይነካውን፣ የማይደፈረውን፣ የተከበረውንና ለሕዝቡ ክብርና ቃል ኪዳን ያለውን ለዛም የደከመውንና የተሰዋለትን ኢትዮጵያዊነትን የተሸከመ መከላከያ ጦራችንን ወጋ፡፡ መውጋት ብቻ አይደለም በዓለም መድረክ ተደርጎ በማይታወቅ ደረጃ በሀገሪቱ ጦር ላይ ጥቃት ፈጸመ፡፡ በዚህም ብዙኃን አዘኑ፣ ተሰዉ ሀገር ማቅ ለብሳ አዘነች፡፡
ይህ ወያኔያዊ ግፍ ድርጊት ኢትዮጵያዊ የአፀፋ ምላሽ ተሰጠው፤ አይቀጡ ቅጣትን ቀመሰ፡፡ መቃብሩን አርቆ ስለቆፈረ ግብዓተ መሬቱን ለማፋጠን ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተመው ተነሱ፡፡ ወያኔ ከፋፍዬዋለሁ፣ የጎሪጥ እንዲተያይ ፈጽሞ እንዳይስማማና እንዳይተማመን አብሮም እንዳይቆም አድርጌዋለሁ ያለው ሕዝብ በተቃራኒው ሆኖ መቆም ጀመረ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ቢዳፈን እንጂ የማይጠፋ ረመጥ መሆኑን አስመሰከረ፡፡ የታሪክ ገጾች የሚነግሩንም ይሄንኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ሲመጣባቸው እንደ ብረት ምሶሶ ጠንክረው አንድ ልብ፣ ዋልታና ማገር ሁነው መነሳት ታሪካዊ ባህላቸው መሆኑ የታወቀ የተረዳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን ዳግም የአኩሪ ታሪክም ባለቤት መሆኗን ያሳየችበት ጊዜና ትውልድ ስላገኘን ደስ ሊለን ይገባል፡፡
ይህ ትውልድ እንክርዳድ ተዘርቶበት ነበር፤ የራሱን ብሔር እንዲቆጥርና ለይቶ እንዲቆም ሌላውን እንደጠላቱ እንዲመለከት ተደርጎ የተቀረፀ ነበር፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለውና ታሪካዊ ባህሉን በመገንዘብ ዘቅጦ ከመቅረት በከፍታ መዋኘትን መርጦ መዋኘት ባለበት ገንዳ ውስጥ ለመዋኘት ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ( “Swim in the pool you are expected to swim” እንደሚሉት) ለሀገሩ ህልውና ዘብ ለመቆም ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደ ሰርዶ ሳር ተያይዞ እንደ ሸረሪት ድር አብሮ ሀገሩንና ሕዝቡን ታሪኩንና ትውልዱን ለማስቀጠል ያለማንም አስገዳጅነት ሆ ብሎ ተነስቷል፡፡ አዎ በተለይ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ያለን አንድና አንድ አማራጭ አብሮ መቆም ብቻ ነው፤ ከዚህ ውጭ ያለው ወያኔያዊው መንገድ ያሳንሰን ከሆነ እንጂ ትልቅ አያደርገንም፣ ሊያዳክመን እንጂ አያጠናክረንም፣ ሊበትነንና እንደ አራዊት ያባላናል እንጂ አያዋድደንም ፣ አብሮ አያኖረንም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኩራትና አይነኬነት መሆኑን ለእነዚህ ሀገርና ሕዝብ ብሔርና ታሪክ አልባ ለሆኑ የምዕራባውያን እና የግብፅ ስትራቴጅክ ጥቅም አራማጆች ተላላኪዎች በቂ ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ስለዚህ ይህ እንክርዳድ ተዘርቶበት ስንዴ ሆኖ ለበቀለ እና ለቆመ ትውልድ ወደር የለሽ ምስጋና ይገባል!!! ፡፡ ለወደፊቱም ሀገሩንና ሕዝቡን ለመበታተንና ለማጥፋት ከሚጣደፉ ተላላኪ ፖለቲከኞች ጠብቆ እንደ አባቶቹ የታፈረችና የተከበረች ሀገርን ለማቆየትና ከነ ሙሉ ክብሯና ማዕረጓ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የማያወላውል አቋም ይዞ እንደሚቀጥል እምነታችን የፀና ነው ፡፡ ዘቅጠን እንድንዋኝ ቢያደርጉንም ከፍ ብለን መዋኘትን ልናሳያቸው ጉዞ ጀምረናል፡፡ አሁንም በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያዊነት ያልገባው ወገን ካለ « በበዛብህ ጊዜ የደነቆረ በበዛብህ አምላክ ሲል ይኖራል» እንደሚባለው ዓይነት እንዳይሆን የተጫነበትን ቀንበር እንዲያራግፍ ይህ ትውልድ በተግባር እየመከረው ይገኛል፡፡ ታሪክን የሚያከብሩ ክብር ታሪክን የሚያዋርዱ ውርደት ይገባቸዋል! አዎ እንክርዳዶች ይነቀላሉ!!! ግብዓተ መሬት ለጉጅሊ ወያኔ!!! ኢትዮጵያ ለዘላለም ተከብራና ታፍራ ትኑር!