በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄራዊ መግባባት ወይም ምክክር የምንለው ሃሳብ ከጦርነት አቁም ስምምነት ሁሉ በላይ ነው። ሃገራችን ወደ ለውጥ መሄድ ካለባት አሁን ያለው ጦርነት ባይኖርም ብሄራዊ መግባባት ያስፈልጋል። ብሄራዊ መግባባት አስፈላጊ ጉዳይ የሆነበት ምክንያት ሃገራችን ኢትዮጵያ የረጋ ቅርፀ መንግስት የሌላትና እንዲሁም በአያሌው ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት መተሳሰሪያ መርሆዎችን ታቅፋ የምትኖር ሃገር ስለሆነች ነው። ስለሆነም የሽግግራችን ምክክሮች በአብዛኛው መተሳሰሪያ መርሆዎቻችንን ሁሉ እንደገና እየከለስን በፅሞና እንድናይ በር የሚከፍቱ መሆን አለባቸው።
የመተሳሰሪያ ዋና ዋና መርሆዎቻችንን እያነሳን ስንወያይ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያዎችን እንድናደርግ የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ ያስገባናል። ችግሮቻችን ሁሉ ከዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎች በታች ቢሆኑ ኑሮ ውይይታችን ሁሉ በህገ መንግስቱ ማእቀፍ ስር ብቻ ይወድቅ ነበር። ነገር ግን ህገ መንግስቱ ላይ ያሉ አንዳንድ ገዢ መርሆዎች ራሳቸው ጥያቄ ውስጥ የወደቁ በመሆናቸው ህገ መንግስቱ ለሃገራዊ ምክክሩ መውጫ ሆኖ አይታይም። ለዚህ ነው ሃገራችን ወደ ተሻለ ምእራፍ እንድትገባ ሁሉን አቀፍ ምክክር ያስፈልጋል የሚያሰኘን። ምክክሩ ፈጭቶ አሳምሮ ያመረተው ሃሳብ ለህገ መንግስት ማሻሻያ ዋልታና ማገር እያቀበልን የጋራ ቤታችንን ጥሩ አድርገን እንድንሰራ ያደርገናል። በመሆኑም ብሄራዊ መግባባቱ ሁሉን አቀፍ ሆኖና ሃቀኛ ሆኖ ፍሬ ካፈራ በውጤቱ በተሻለ መተሳሰሪያ መርሆ በተከሸነና በፀዳ ህገ መንግስት ወደፊት ሊያራምደን ይችላል። ለዚህ ምክክር አጀንዳ ናቸው ያልኳቸውን ሃሳቦች እንደገና ከዚህ ቀጥሎ ላንሳቸው። ጠቃሚ ናቸው።
1. በህብረታችን ወይም በአብሮነታችን ፍፁምነት ላይ። ህብረታችንና የጋራው ቤታችን በምን ያህል አቅም ወይም በምን ያህል የአብሮነትና የወዳጅነት የቃልኪዳን ልክ ይታተም? የሚለው ዋና የምክክር አጀንዳ ነው። አሁን ያለው መተሳሰሪያ መርሆ የህብረታችንን ልክ በመገንጠል የወሰነው ሲሆን አሁን ይህንን የህብረት ልክ እንዴት እናሳድገው የሚለውን ቁልፍ ጉዳይ ነው :: ለዚህ ነው Towards a More perfect Union እያልኩ የፃፍኩት:: ውይይታችን የጋራውን ቤት ፍፁም ወደ ማድረግ እንዲሆን መወያየት ያስፈልጋል ::
2. በቅርፀ መንግስት ላይ ምክክር ያስፈልጋል ። ቅርፀ መንግስት በምርጫ መንግስት ሲመጣና ሲሄድ የሚቀየር አይሆንም። በዚህ አንድ ኢትዮጵያን የመሰለ ቅርፀ መንግስት መስፋት አለብን። ይህ ጉዳይ ሀገሪቱ ፓርላመንታሪ ትሁን ወይስ ፕሬዝደንሺያል? የፌደራል ሥርዓቱ ምን መልክ ይያዝ? የመንግስት ቅርፁ ምን ይጨምር ምን ይቀንስ? ለምሳሌ የህገመንግስት ዳኛ ይኑር ወይስ እንዴት እንቀጥል ወዘተን ይመለከታል ::
3. ብሄራዊ ማንነትንና የብሄር ማንነትን እንዴት እንንከባከብ። በምን አይነት ምህዋር ይዙሩ? እንዴት ሳይጠላለፉ ይኑሩ በሚለው ላይ ምክክር ያስፈልጋል።በማንነቱ ፖለቲካ ላይ ውይይት ያስፈልጋል ::
4. ብሄራዊ ምልክቶችን በተመለከተ መመካከር ያስፈልጋል። ባንዲራን መዝሙርን ወዘተ ይመለከታል።
5. የመሬት ላራሹ ጥያቄ ምክክር ውስጥ መግባት አለበት። የፓሊስ ቀጭን ጉዳይ አይደለም ይህ አጀንዳ።
6. ያለፈ መጥፎ ትውስታዎች እንዴት ይታዩ? (Past bad memories) የሚለውን ማንሳት ተገቢ ነው።
7. ቋንቋና ተግባቦትን በሚመለከት ውይይት ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ፓሊሲ ሳይሆን የቋንቋ አያያዛችን ላይ የጋራ አቋም መያዝ ይቻላል።
እነዚህ ናቸው አጀንዳዎቻችን። በነዚህ ላይ የምናደርገው ስምምነት ህገ መንግስት የሚያሻሽሉ ሃሳቦችን ያመርትልንና ወደ ህገ መንግስት መሻሻል ስራ እንገባለን ስምምነቱ በጋራ ቃል ኪዳን ይፀናል ማለት ነው። ህዝቡም በዚህ ስምምነት ላይ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።