የአሸባሪው ህወሓት ሊቀመንበሩ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በኩል ለተባበሩት መንግሥታት በጻፈው ደብዳቤ ኃይሎቹ ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለሱ ማዘዙን ገለጸ።
የህወሓት ኃይሎች ካለፈው ዓመት ሰኔ ወዲህ ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በመግባት በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ውጊያ ሲደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
ኅዳር ላይ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱን፣ የክልል ልዩ ኃይሎችንና ሚሊሻዎችን በማቀናጀት ባካሄደው መጠነ ሰፊ ዘመቻ በርካታ አካባቢዎችን መልሶ ለመቆጣጠር ችሏል።
በህወሓት መሪዎች በኩል ግን ኃይሎቻቸው እንዲወጡ የተደረገው “በስልታዊ ውሳኔ” መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ለቢቢሲ “አማጺው ሽንፈት ገጥሞት” ይዟቸው ከነበሩ ቦታዎች እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማን ጨምሮ በርካታ የሰሜን ወሎ አካባቢዎችን ከአማጺያኑ ስር በማውጣት መቆጣጠሩን መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፤ የቀሩ አካባቢዎችን መልሶ ለመያዝ ዘመቻው እንደቀጠለ በተነገረበት ጊዜ ነው የህወሓት ሊቀ መንበር ደብዳቤ መጻፋቸው የተሰማው።
ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ለመንግሥታቱ ድርጅት ትናንት እሁድ ታኅሣሥ 10/2014 ዓ. ም. ጻፉት በተባለው ደብዳቤ ላይ ኃይሎቻቸው ከትግራይ ክልል ውጪ ከነበሩባቸው አካባቢዎች “ለሰላም ዕድል ለመስጠት” ለቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን አመልክተዋል።
ይህም ውሳኔ “ወዲያው ተግባራዊ” እንደሚሆን በደብዳቤያቸው ላይ አመልክተው፤ በአስቸኳይ ግጭቶች ቆመው ድርድር እንዲጀመር ጠይቀዋል።
BBC
http://amharic.thehabesha.com/debretsion-appeal-to-un-secretary-general-anthony-gutierrez-for-peace-negotiation-with-ethiopia/