የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ የዘንድሮውን የገና በዓል በታሪካዊቷ ላልይበላ ከተማ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት ለማክበር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ

የቢሮ ኃላፊ አቶ ጧሂር መሐመድ ዛሬ በላልይበላ ከተማ በሰጡት መግለጫ አሸባሪውና ወራሪ ህወሓት በክልሉ በከፈተው ጦርነት ምክንያት የክልሉ የቱሪዝም ኢኮኖሚው ክፉኛ መጎዳቱን ገልጸዋል።

ጎብኚዎች ወደ አካባቢው እንዲመጡና ዘርፉን ለማነቃቃት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሽብር ቡድኑ በላልይበላ ከተማ በቆየባቸው ወራት ለቱሪዝም ዘርፉ የጎላ ሚና ያላቸውን የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ሆቴሎችንና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማውደሙንም ተናግረዋል።

በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሰረተ ልማቶችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ስራ ለማስጀመር ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን በመግለጫቸው አመልክተዋል።

በተለይም መንግሥት 1 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ላቀረበው ጥሪ በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለጎብኚዎች እየተመቻቹ መሆኑንም አብራርተዋል።

የገና በዓልን በታሪካዊቷ ላልይበላ ከተማ ታህሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም፣ ጥምቀት በዓልን ደግሞ በጎንደር በደማቅ ሥነስርዓት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ወራሪው ኃይል ያወደመውን የላልይበላ አየር ማረፊያ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በመጠገን ለጎብኚዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ከፌዴራል መንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ የሚከበር ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከራሳቸው ባለፈ የኢትዮጵያ ወዳጆችን በማስተባበር በመንግሥት ጥሪ መሰረት ወደ ሀገራቸው እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል።

“ኢትዮጵያ የውስጥና የውጪ ጠላቶቻችን እንደሚሉት የሰላም ስጋት ውስጥ ያለችና የፈረሰች ሀገር አለመሆኗን በዚህ አጋጣሚ ማሳየት ከሁላችንም ይጠበቃል” ብለዋል።

ኢዜአ

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሀገሪቱ ሕግ መሠረት የሚፈቱ ጉዳዮች

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share