የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ለአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል የእግር እሳት መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ ነው

255978811 1677345615773759 1626689158306306666 n
ሕዳር 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኪንፋዝ በገላ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ በለሳ ወረዳ ሕዝባዊ ሠራዊት ከሌሎች የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ጋር በመሆን በተናበበ መንገድ በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ላይ ከባድ የማጥቃት እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ።
ለሀገሩ መሞት ክብርና ኩራቱ የሆነው ይህ ሕዝባዊ ሠራዊት “ለዘመቻ ወደ ኋላ የቀረህ ጥቁር ውሻ ውለድ” ብሎና ተማምሎ ተነስቷል።
በቆራጥነት እና አይበገሬነት ወኔ የተመመው ሕዝባዊ ሠራዊት ቀፎው እንደተነካ ንብ ከሁሉም አካባቢዎች ወደ ግንባር በመትመም የጠላትን አንገት እያስደፋ ነው።
የኪንፋዝ በገላ ወረዳ ሕዝባዊ ሠራዊት ከዋግ ጀግኖች ጋር በመሆን ወራሪ ኃይልን መውጫ መግቢያ አሳጥቶታል።
የኪንፋዝ በገላ ወረዳ የሕዝባዊ ሠራዊቱ አባል አቶ እሸቴ ዳኛው “የወረዳው ሕዝብ የክልሉን መንግሥት የክተት ጥሪ ተቀብሎ ዋግኽምራ ግንባር ዘምቷል፤ በግንባሩም ጠላትን እየደመሰሰ ለከፍተኛ ድል እየገሰገሰን ነው” ብለዋል።
ሕዝባዊ ሠራዊቱ ትጥቁን እና ስንቁን ይዞ መዝመቱን የገለጹት ዘማች እሸቴ ሕዝባዊ ሠራዊቱ ለዘመቻ ሲሄድ ቀያቸው እንዳይደፈር ተጠባባቂ ኃይል መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራ ላይ ላይ እያደረሰ ያለው ጭፍጨፋ፣ዝርፊያ እና ውድመት እጅጉን ያንገበገባቸው ዘማቾቹ በሽብር ኃይሉ የተወረሩ አካባቢዎችም በቅርብ ቀን ነፃ ይወጣሉ ነው ያሉት።
256556034 1677344815773839 3845256839510968635 n
ከልጃቸው ጋር ወደ ግንባር መዝመታቸውን የገለጹት ሌላኛው የኪንፋዝ በገላ ወረዳ ዘማች አማረ ምስጋናው ከዚህ በፊት ወራሪው ኃይል በጋይንት ግንባር ወረራ ለመፈጸም ሞክሮ ሳይሳካለት ተሰባብሮ በተመለሰበት ዘመቻ መሣተፋቸውን ተናግረዋል። በዚያን ጊዜ ጠላት ደብረታቦር ከተማን ለመያዝ አሰፍስፎ ሲመጣ አከርካሪውን ሰብረን መልሰናል የሚሉት አቶ አማረ ዛሬም በዋግ ግንባር ልጃቸውን ይዘው ታላቅ ጀብድ እየፈጸሙ መሆናቸውን ነግረውናል።
የኪንፋንዘ በገላ ወረዳ የሕዝባዊ ሠራዊቱ መሪ ሻምበል ተስፋየ አዛለው ከሌላው ሕዝባዊ ሠራዊት ጋር በመሆን በአንድነት፣ በጀግንነት እና ወኔ ጠላትን እየቀጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሻምበል ተስፋየ በግንባር የተገኘው ሕዝባዊ ሠራዊት ኢትዮጵያ ልጆቿ እያሉ የማትፈርስ ሀገር መሆኗን ያስመሰከረ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው – ከዋግኽምራ ግንባር
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.