አይዞን ወሎ (አሁንገና ዓለማየሁ)

አይዞን ወሎ
በውበትም በባሕርይ
ከማርም ማር ወለላ
ጣፋጭ የወይን ዘለላ
የሥልጣኔው እምብርት
የእውቀት ጭማቂው ጠለላ
የአለት ቅኔሽ ላሊበላ
የቃላት ቅኔሽ ሳይንት ዋድላ
የአክሱም ነገሥታት መሸሻ
የዛጔ ጻድቃን መንገሻ
የበሬንቱ ጦር መድረሻ
የሙእሚን አገር የኡለማ
የወዳጃ የመንዙማ
የአምባሰል ባቲ ዜማ
ባጥሽን ዘልቆ የሚሰማ
የትዝታችን መዲና
ያንቺወዬአችን ቃና
ኧረ ምኑ፣ የቱ ጎድሎ?
የደም ኅብር ነበርሽ ወሎ
የፈጠረሽ ተቀላቅሎ
አማራ አገው አርጎባ
ከትግሬ ኦሮሞ ሲጋባ
እና ግን
የእንክርዳዱ ሊጥ ሲጋገር
ባምናው ምጣድ አክንባሎ
የአድዋችን ጦስ ጭዳ ሲሻ
እሳት ላይሽ ተከንብሎ
የትህነጉ የእሮብ ሴራ
አሳልፎሽ ለመከራ
የአቢይ አህመድ ረጅሙ ቀን አርብ ሆኖብሽ የጎልጎታ
ችንካር በራ/ስጌ በግርጌሽ/ በቀኝ በግ/ራሽ ሲመታ
በጎንሽ ጦር ተሽጦ
ለጥም የሰጡሽ ሆምጥጦ
በእሾህ አክሊልሽ ስቀው
በኤሎሄሽም ተሳልቀው
የቂም እሳት ሲንቀለቀል
ለአይሁድ ሮማዊው በቀል
ደጀኔ ብሎ ስሞሽ
አሳልፎ ሰጭ ይሁዳ
ጴጥሮስሽም ክዶሽ ማልዳ
መከራ አይተሽ እንደጌታ
በጊሸን ትከሻ መርከብሽ
ግማደ መስቀል አርፎብሽ
የሃጂ አገር የመነኩሴ
የአዛና ምድር የቅዳሴ
የነካሌብ የነሙሄ
ምልእት ነበርሽ በኩለሄ
ዛሬ ታጭተሽ ለኤሎሄ
የጭንቅሽ ሬቱ ቢመርም
እንዲህ ሆኖ ግን አይቀርም
አይዞሽ ሲሞላ ሱባኤ
የሕዝብሽ ዱአ ጉባኤ
ሞታለች ቢሉሽ ቅዳሜ

ቀጣዩ እሁድ ነው — ትንሣኤ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተጠየቅ (ዘ-ጌርሣም)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share