የአባቴ ስንብት (ሚሚ ከፋለ-ከሆላንድ አምስተርዳም)

45ትንሽ ስለ አባቴ እና ስለ ባህሪው እንዲሁም ከእኔ፣ ከቤተሰብ፣ ከጉዋደኞቹ ጋር ስላለው ግንኙነት አውርቻችሁ፣ ከዚያ ወደ ምስጋና መሄድ እፈልጋለሁ። በቅድሚያ አባቴን እና ቤተሰቡን አክብራችሁ የመጣችሁ ውድ የከፋለ ውዶች አመሰግናለሁ።

ከፋለ ከቤተሰብ ጋር ያለው ግንኙነት፦ በቤተሰቡ ዘንድ በጣም የሚወዱት እና የሚያከብሩት ወንድማቸው ነው። በጣም ይኮሩበታል፤ ለቤተሰብ ሶስተኛ ልጅ ነው፤ ግን እናቱም አባቱም አንደ መጀመሪያ ልጅ ከልጅነቱ ያከብሩታል፤ ይሰሙታል። በቤተሰብ መሃል የመጣን የርስትና የጉልት ጭቅጭቅ ገና ወጣት ሆኖ እሱ በፈቀደው መንገድ መፍትሄ እንዲሰጥ አድርገዋል።

ከፋለ እና ጉዋደኞቹ፦ ከጓደኞቹ ጋር ያለው ፍቅር የተለየ ነው። ከአገሩ እስኪወጣ ድረስ፣ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት – አምሃ ደስታ አብረውት የተማሩ ጓደኞቹ ሁሌም ውድ ወንድሞቹ ነበሩ። እስክስታ ሳትችል እንዴት ከሰባት ጊዜ በላይ አንደኛ ሚዜ ልትሆን ቻልክ? እያልኩ አሾፍበት ነበር። በስራ አለም ደግሞ፣ ከጋዜጠኞች እና ከደራሲዎች፤ ከጋሽ ማዕረጉ በዛብህ፣ ከበዓሉ ግርማ፣ ከብርሃኑ ዘሪሁን፣ ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ ከጋሽ ከበደ አኒሳ፣ ከአሳምነው ገብረወልድ፣ ከአጥናፍሰገድ ይልማ፣ ከገብረክርስቶስ ደስታ፣… ጋር ጓደኝነት ብቻ ሳይሆን፣ ለነፍስ ይዋደዱ ነበር ብል አላጋነንኩም።

45eከፋለ ማሞ ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድጅጅን ጋር

ከፋለ በጓደኞቹ ስኬት ከእንሱ በላይ የሚደሰት ቅን ጓደኛ ነበር፤ ጋዜጠኞች ያልሆኑ ጓደኞቹ፣ እነ ጋሽ ወጋየሁ ተክለማርያም፣ ጋሽ በቀለ ኃይሌ፣ ጋሽ ስለሺ ዘሪሁን፣ መንግስቱ፣ ጋሽ አድማሱ አጥናፍሰገድ፣ ጋሽ መስፍን ቢነጋ፤ ጋሽ ሠረቀብርሃን፣ ፕሮፌሰር ታምራት.. ከመሳሰሉት ጋር አብረው እስከ መኖር ለብዙ ጊዜ በፍቅርና በመከባበር አሳልፏል።

ከፋለ በስራ ቦታው፦ ከፋለ በጣም ታታሪ ሰራተኛ ነበር፤ ስራ ሳይጨርስ አይተኛም። እኔ ሳልወለድ የነበረ ታሪክ ሲነግረኝ፣ ያዘጋጀው ጽሁፍ በትክክል መውጣቱን ለማየት እንዳንዴ ሌሊት ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲሄድ፣ ከበዓሉ ግርማና ከብርሃኑ ዘሪሁን ጋር ይገጣጠሙ ነበር። ስራው ዝንፍ እንድትል አይፈልግም። በዚህም ምክንያት ሰርቶ ያሰራል። መተሃራ ስኳር ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ሆኖ፣ ሌሊት ሙሉ ቁጭ ብሎ የሚሰራባቸው ጊዜያት ብዙ ነበሩ። በስራውም ትልልቅ ድሎችን አግኝቷል። ሁሌም እሱ ስራ አስኪያጅ የሆነባቸው ፋብሪካዎች፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አንደኛ ይወጡ ነበር። አባቴ ሃቀኛና ግትር ነው። ዘረፋንና አድልዎን አይፈቅድም ነበር። በዚህም የተነሳ ‘ወይ አይበላ ወይም አያስበላ’ የሚል ስም ወጥቶለት ነበር። በአንድ ወቅት ለአጭር ጊዜ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር የነበሩት የተከበሩ ተስፋዬ ዲንቃ የህንን ጉዳይ ሰምተው ነግረውታል። “ከፋለ አንተ ሃቀኝነትህና ግትርነትህ ያው እንደዊንጌቱ ጊዜ ነው። ታዲያ ዘመኑ ደግሞ ከበደ..” ብለው ፣ አላስበላ ሲላቸው ሊበሉት ከነበሩት አድነውታል።

አባቴ ከእኔ ጋር ፦ ለኔ አባቴ የቅርብ ጓደኛዬና አክባሪዬ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ ልክ እንደ ትልቅ ሰው ነበር ተራ እየሰጠኝ፣ ለእገራችን ብርቅዬ ከሆኑት ከእነ ጋሽ ጸጋዬ፣ ከነ ጋሽ ማዕረጉ.. ጋር አወራ የነበረው። ባገሪቷ ላይ ባሉ ትልልቅ ሆቴሎች፣ ለምሳ ይዞኝ ይወጣና ለረጅም ሰዓት ያወራኛል። የእኔን ምርጫም ያከብር ነበር። ገና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ጀምሮ፣ አሰገዱ የምትባል ባንክ የምትሰራ የአክስቴ ልጅ ዘንድ የኪስ ገንዘብ አስቀምጦልኝ እየሄድኩ እወስድ ነበር። ሰውን እንዳከብር፣ የሃሳብ ልዩነትን እንዳከብር፣ ሰው በሃሳብ ስለተለየኝ እንዳልጠምደው፣ በተግባር እያሳየ ያስተምረኝ ነበር። ላመንኩበት ነገር፣ በተለይ ፍትህ ሲጓደል ካየሁ ዝም እንዳልል፣ የድሃ ጠበቃ እንድሆን፣ እንዲሁም የቤት ሰራተኞቻችንን ከማክበር ጀምሮ በተግባር አስተምሮኛል። ጓደኝነትም እስከ ህይወት ፍጻሜ መሆኑን ሁሌም ይነግረኛል። ከሁሉም በላይ ከሰዎች ጋር ስትጣዪ፣ ድልድይ አታፍርሺ ያለኝ በህይወቴ ብዙ ረድቶኛል። በጣም ፈጣን አንባቢም እንድሆን አስተምሮኛል፤ ሃሳቤን ባጭር መግለጽን እንደልቤ እንድከራከረው በማድረግ አስተምሮኛል። ካለን ቅርበት ብዛት ስለ ጓደኞቹ ባህሪ እና የህይወት ስኬት ፣ ከልጆቻቸው በላይ እኔ አውቅ ነበር። እንዲሁም ሆላንድ ያላችሁ ውዳጆቹን ሁሉ በመልክ ሳላውቃችሁ በፊት በዝና አውቃችሁ ነበር። ለምስሌ ያህል ጋሽ ብስራት፣ ጋሽ ተፈራ፣ ዶ/ር ገነት፣ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ፣ ማርታ ነጋሽ፣ አቤ እና ዝኑ፣ ብርቱካንና አቶ ፍቅሬ፣ ዳኜ፣ መንክር፣ ፋሲል ኩራባቸው፣ ነጃ ዓሊ፣ ቦጋለ ካሳዬ፣ መሃመድ፣ ጉልህ ወርቅ፣ እና የመሳሰላችሁትን ሳላውቃችሁ በፊት ስለ አመላችሁ፣ ስለ መልካምነታችሁ አውቃለሁ። ጌች፣ ገኒ፣ ክንፍሽ፣ ቲጂ፣ አፈወርቅ አግደው አና መስፍኔ (መስፍን አማን)፣ ደግሞ የአፉ ማሟሻ ነበራችሁ። የክንፍሽን ስም ሲጠራ ፊቱ ሁሉ በደስታ ይቀየር ነበር። መስፍኔ እና ዳኜን አንቺ ነው የሚለው።

 

ምስጋና፦ በመጀመሪያ አባቴን እድሜ እና ጤና ሰጥቶ እስካሁን ላቆየው፣ ነፍሱን በሰላም ላሳረፋት ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን። በመቀጠል፣ የስደት ኑሮው እንዲጣፍጥለት ላገዛችሁት፤ አሁን እዚህ ለሌለው ለጌታቸው አበራና ለገኒ፤ ጌችዬ ለእናቴም ለአባቴም አለኝታ ነበር። አገር ያስለመዳቸው ታዛዥ ልጃቸው ነበር። እናቴ ሁሌ ጌች እንደ ግርማዬ ወንድምሽ ነው ትለኝ ነበር። እንዳለችውም በአሜሪካን አገር ወንድሜም ሜንቶሬም የምለው፣ ብዙ የአገር መውደዴ እና የፖለቲካ እውቀቴ እንዲዳብር የረዳኝ ወንድሜ ነው። ጌችዬ አመሰግናለሁ!

ለክንፉ አሰፋ፤ ክንፍሽ ሁሌም ከፋለ እኔ ዘንድ ደጋግሞ ሲመጣ፤ ቲኬቱን አዘጋጅቶ፣ ፓስፖርት አሳድሶ፣ የሚያስፈልጉ እቃዎችን ገዛዝቶ የሚሸኘው ልዩ ልጁ ነበር። በኋላም ሙሉ ውክልና ወስዶ የከፋለ ተጠሪ ሆኖ ሲያገለግለው ኖሯል። ሁሌ እንደምልህ፣ የአባቴ ልጅ ወንድሜ ነህ። ቲጂም ያማረውን ምግብ እየሰራች፣ ጋሽ ከፌ እያለች እያማከረችውም እየመከረችውም የኖረች ልጁ ነች።

አፈወርቅ አግደው፣  ከፋለ- አፍሽ ሲል ያምርበታል፤ አፈወርቅም ጋሼ ጋሼ እያለ በሳቅ ‘እስኪወድቅ’ ያጫውተውና አብሮት ረጅም ዎክ ከብዙ ጨዋታ ጋር ለብዙ ዓመታት ያረጉ ነበር። እግዚአብሔር ልጆችህን ላንተም ጓደኛ ያርግልህ። በእሱ አማካኝነት ያወቀችው ጉልህ ወርቅ፣ ጉልዬ ባለቤቱ፣ ከፋለን በእስተርጅናው ያማረውን እያበላች አቀማጥላ ይዛዋለች፤ አንችንም እግዚአብሔር በልጆችሽ ይካስሽ።

መስፍን አማን፤ መስፍኔ ከፋለን በጣም እንደቆሎ ጓደኛ ከሚያወሩት ወጣት ፖለቲከኞች አንዱ ነው። ከፋለም ብሪሊያንት ነው ይለኝ ነበር። ክንፍሽም ሆነ መስፍኔም እና ጌች ለእኔም ከፋለ ያተረፈልኝ ጓደኞቼ ስለሆኑ፣ እኔም ብቃቱን አውቀዋለሁ። መስፍኔ፣ በከፋለ የህይወት መጨረሻ ምዕራፍ ላይ በተለይ ይሄ ስንብት እንዳይበላሽ በሰው አገር ላይ ከዳኜ ጋር እየተሯሯጠ ትልቅ ውለታ የሰራ ወንድሜ ነው። ዳኝዬም በጣም አመሰግናለሁ። ዝንሽ እና አቤ፤ ብርቱካን፤ ማርታ፤ ከፋለን ደጋግማችሁ እየሄዳችሁ የሚወደውን ምግብ ይዛችሁ የምታጫውቱት መልካም ሰዎች ናችሁና አግዚአብሔር መልካም ነገር ቤታችሁን አያሳጣው።

ጋሽ ብስራት ኢብሳ፤ አቶ ተፈራ(አዲስ አበባ ፌስቶራንት)፣ ደ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ዶክተር ነገደ ጎበዜ፣ አቶ አበራ የማነአብ፣ ዶ/ር ግርማ አሰፋ፣ ዶ/ር ወንድሙ መኮንን፤ ከእናንተ ጋር ትልልቅ ቁም ነገሮችን ማውጋት ለከፋለ በስደት ላይ ሀሴት ከሚያደርግበት መንገድ አንዱ እንደሆነ ስነግራችሁ በደስታ ነው።

በመጨረሻም የምወዳችሁ እህቶቼ ህይወቴ፤ ማሜ፣ኒናዬ፣ መሰረት(መስዬ)ስላጽናናችሁኝ አመሰግናለሁ!

ወንድሞቼ፤ ጌትሽ፣ ግርምሽ፣ እና ዘገየ፤

ጌትሽ፤ ከፋለ ከእኔ በላይ ይወድህ እንደነበር ታውቃለህ? አንተም እሱ የሚወዳቸውን የወይን ጠጆች፣ ቆሎ እና ልብሶች እያመጣህ ታስደስተው ነበርና ተባረክ።

ግርምሽ፤ ከፋለ ግርምዬ ሲልህ፣ አንተም ከፍሽ ስትል በጣም ያምርባችሁ ነበር። መተሃራ፣ ወንጂ፣ እና ሶደሬ በምንሄድ ጊዜ፣ ከከፋለ ጋር ያሳለፍናቸው ውብ ጊዜዎች አይረሱም። ጥልቅ የሆነ የፖለቲካ እውቀትህ እና ቀልዶችህ ያስደስቱት ነበር። በጣም ይኮራብህም ነበር።

ዘገየ፤ ከፋለ አሜሪካ ደጋግሞ በመጣበቸው ወቅቶች፣ ሁሌም መጥቶ እስኪመለስ እያንዳንዱን ቀናት ሳትለየው ጊዜህን፣ ፍቅርህን፣ ገንዘብህን ሳትቆጥብ አብረኸው ዎክ እያረክ ታወጉ የነበረው፣ የከፋለን ህይወት ጣፋጭ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጸዖ አድርጓልና አመሰግንሃለሁ!

በመጨረሻም ባለቤቴ፣ አመለ-ሸጋው ታዴ፤ ከፋለ እየመጣ ሁሌ ሶስት ወር ከእኛ ጋር ሲያሳልፍ፣ ባንተ በጣም ከመደሰቱ የተነሳ ይሄ ልጅ እናቴና እነዚያ ወዛደሮች ይመርቁኝ የነበረው ውጤት ነው ይልህ ነበር። ሲገልጽህም፣ ታዴ ረቂቅ ውብ ሰው ነው ይልህ ነበር። ሴት ልጁን ለሚወድ አባት፤ ትዳሯን ከወደደ ሌላ ምንም በህይወቱ አይፈልግምና አባቴን ሳላስደሰትክ አመሰግንሃለሁ።

ውድ ልጆቼ፤ የአባቴ አድናቂዎች፤ አንደ ‘ፓፓ’ ሃይለኛ አንባቢ መሆን እንፈልጋለን የምትሉኝ። ግሩምዬ ሁሌ ጥሩ ውጤት ስታመጣ፣ “ሚሚ እንደ ፓፓ የምሆን ይመስልሻል?” የምትለኝ፤ ብሩክዬ፤ አራተኛ ክፍል ሆነህ ሃይለኛ አንባቢ ነህ ስትባል፣ አስተማሪዋን “አያቴን ባየሽው በጣም ብዙ ይበልጠኛል” ያልካት። “አድጌ፣ አያቴን አገሩን ለቆ እንዲወጣ ያረገውን መንግስት እከሳለሁ” ያልከኝ ውድ ልጄ! በእናንተ ውስጥ ከፋለን ህያው ሆኖ አየዋለሁና ክብር ምስጋና ለፈጣሪ ይሁን። አገሩን በቅንነት በታማኝነት ያገለገለው አባቴ የሰማዩ አባቴ በአቅፉ እንዳረገው አምናለሁና አባቴ እወድሃለሁ ሁሌ እንደምትለው አግዚአብሔር በምድር ላይ ሁለት ስጦታዎችን ሰቶኛል። ሚሚዬን እና እንቅልፍ ትል ነበር። ሁለተኛው አሸንፏል፤ በስራዎችህ ሁሌ ህያው ነህ፤ እስካገኝህ በሰላም አንቀላፋልኝ።

ሚሚ ከፋለ

ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ/ም

ሆላንድ-አምስተርዳም

3 Comments

  1. ሚሚ ከፋለ ላባትሽ እረፍተ ነብስ ይስጥልን ግዳጃቸውን ተወጥተው ከሚወዱት አገራቸው ተገፍተው የወጡ ይመስላል። በተለይም ከሳቸው ጋር የተጠቀሱት ግለስቦች በመልካም ኢትዮጵያዊነት የምናውቃቸው በመሆኑ አባትሽ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆናቸው ማስረጃ ነው። ለማንኛውም አንችም ኢትዮጵያዊነትን አጠናክሪ ያባትሽን አገር መውደድ ለተከታዮችሽ አስቀጥይ።

  2. ሚሚና መላ ቤተሰብ ሃዘናችሁ የእውነተኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሃዘን ነው። እንደምታውቁት እንዲህ ዘመን ጠግቦ የልጅ ልጅ አይቶ ማለፍ ማለፊያ የድንኳን ዘመን ነው። ብዙዎች ይህን እድል አያገኙም። ያው እኛም በጊዜአችን ቀድመውን የተሻገሩትን ፍለጋ እንሄዳለን እንጂ እነርሱ ወደ እኛ አይመጡም። እንደ አባታችሁ ያለ ዘመን ተሻጋሪ ሰው ደግሞ ሲያልፍ ልክ አንድ ትልቅ ቤተ-መጽሃፍት (ላይብራሪ) እንደ ተቃጠለ ነው የሚቆጠረው። አሁን በዘርና በቋንቋው ደንበር ገተር እያለ የሚተመውን ፍጡር የሚያስተምሩት ስንት ነገር ነበርና። በዘመናት መሃል ሃገርን ወገንን ብለው በስደት፤ በድር በገደል፤ በረሃብና ጥማት የተንከራተቱ እልፍ ናቸው። የግፈኞች በተር በወረፋ እያረፈባቸው አንድን ሲሻገሩት ሌላው አፈር የመለሰባቸው ቁጥራቸው ብዙ ነው። አባታችሁ ከዚህ ሁሉ የህይወት ስንክሳር አልፈው እድሜ ጠግበው ማለፋቸው እሰይ ያሰኛል።
    Blair Thomson Ethiopia: The Country That Cut Off Its Head: A Diary Of The Revolution በተሰኘው መጽሃፉ ላይ የሚያመላክተን ይህኑ አፍራሽን አፍራሽ እየተካው የዝንተ ዓለም የፓለቲካ ግብግብ በሃገራችንና በህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን መከራና ችግር ነው። ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን፤ በዓሉ ግርማና ሌሎችም በጊዜአቸው ለሃገርና ለወገን ያላቸውን አካፍለው ያለፉ ወገኖች ናቸው። የአባታችሁ የአቶ ከፍያለ ማሞም ለሃገርና ለወገን ያደረጉት አስተዋጾ ዘመን ተሻጋሪ ነው። በዚህ ተጽናኑ። በርቱ።

  3. ሚሚ እግዚአብሔ ያጥናሽ።አባትሽን ከፋየለው ማሞ ለአራት ዓመታት ያህል ማስታወቂያ ሚንስተር አዲስ ተቀጣሪ ሆኜ ፣ ሁለቱን አመት በሬዲዮው ክፍል በከፋለው አለቃነት ሥር ሆኜ ነው የሳለፍኩት።በወጣትነት ዘመኔ በ20 የዕድሜ ክልል ውስጥ ስለነበርኩ፣አጉራ ዘለለንቱ፣ማን አለብኝነቱ፣ደረት መንፋቱን ከፋለው ተገንዝቦት፣እንደ አለቃ በቁጣ ሳይሆን ፣እንደ የተፈጥሮ ጉዞ ተመልካች ይስቅም፣ በራሴም እንድስቅ ያደርግ ነበር። አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ራዲዮ የበላይ ኃላፊ እያለ አንዲት የሻቢያ ይሁን የጀበሃ ምርኮ በአማሪኛ የሰጠችውን የቃለ መጠይቅ መልስ ከቴፕ እየሰማሁ በጽሁፍ እንዳዘጋጀው ይጠይቀኛል።ጨርሼ አስረከብኩት።” የተማራኪዋ የሕዝብ ግኑኝነት በመሆን ተዋጥቶልሃል” አለኝ።የሚገርመው በዛ የወጣትነት ዘመን ነፃ አውጪ ለተባለ ወገን ሁሉ ማጋደል ነበርና ከፊያለው ያስተዋለው ያንን ነበር።

    ከፍያለው ከሚወደው ከማስታወቂያ ሚንስተር ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ሲዛወር በጊዜ እንደ ገባኝ በግፊት ነበር።አግኝቼውም ሊያነሳው የሚፈልገው ርዕስ አልነበረም።በፈነታው እኔና የሥራ ባልደረባዬን ጋብዞና መክሮ መሸኘቱን አስቀድሟል።ከዚያ በኋላ ስደት ሆኜ እሱ ሆላንድ ሆኖ በስልክ ተገናኝተናል።

    ሁሌም ከከፋለው ትዝታ ከዓይነ ሕሊናዬ የማጠፋው ፈገግታው ነው። በአጭሩ ነፍስ ይማር።ከፍያለው የሁላችም ነበርና ፣ሁላችንንም መጽናናትን ይስጠን።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.