የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንኳር ስህተቶች – አንድነት ይልቃል

የሐገራችን የወቅቱ የሠላም ሁኔታ መፍትሄ ካልተበጀለት በገደል አፋፍ ላይ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው ፡፡ መንስኤን በተመለከተ ብዙ ትንታኔያዎች ተሰጥተዋል፤ እየተሰጡም ነው፡፡ የኢኮኖሚ ኢፍትሃዊነትና፣ የህዝብ ቁጥር እና እድገቱ ባለመጣጠኑ የሥራአጥ ቁጥር የትየለሌነት የህገመንግስታዊ መብቶች አተገባበር ችግሮች ወዘተ…፡፡ ሌሎች ደግሞ በራሱ በህገመንግስቱ ላይ ችግሮችን ሁሉ መደፍደፍ ይቀናቸዋል፡፡ ችግሮች ሁሉ ከህገመንግስቱ የመነጩ ናቸው ለማለት በቂ ጥናት ማድረግ ቢጠይቅም የወቅቱ አንኳር ችግሮች ከህገመንግስቱ የሚወለዱ መሆናቸው ግን የማይካድ ሐቅ ነው፡፡

ሕገ-መንግስቱ በመግቢያው ላይ “ዘላቂ ሰላም፤ ዋስትና ያለው ዶሞክራሲ እንዲሰፍን” ሲል የጀመረበት ራእይ ምኞት ሆኖ ቀርቷል፡፡ ምክንያቱም እራሱ ሕገ-መንግስቱ ራሱን በራሱ እየጠለፈ ፤ ሰላምና ዲሞክራሲንም እስከወዲያኛው ህልም አድርገው በሚያስቀሩ ጽንሰ ሃሳቦች የተሞላ ነውና፡፡

ከመግቢያው ላይ ሃሳቦችን ነቅሰን እያወጣን ስህተቶችን እንቀጠቁም:-

1. “እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች” የመግቢያው መነሻ ሀረግ ነው፡፡ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 5 ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ሕዝብ ለሚለው የሚከተለውን ድንጋጌ ይሰጣል፦

ሀ/ “ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባረቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፤

ለ/ “ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፤

ሐ/ “የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፤

መ/ “የሥነልቦና አንድነት ያላቸውና፤

ሠ/ “በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓምድር የሚኖሩ ናቸው”፡፡

ይህ በራሱ በሐገሪቱ ለማያባራ ሰለም እጦትና ጦርነት፤ ለሚሊዮኖች መብት መነፈግ በር ከፋች ነው፡፡ ለምን ቢባል ገና ከጅምሩ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባትን አገር በሽግግር መንግስት ዘመን በ9 ክልሎች ብቻ ላይ የተመሰረተ የፌደራል አስተዳደሮችን በማዋቅር ራሱን ጠልፎአል፡፡ በጉልህ መብት ያገኙት ብሔር ብሔረሰቦች ትግሬ ፣ አማራ ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ሱማሌ እና ሐረሪ ሲሆኑ ከ74 በላይ ብሔረሰቦች በዘጠኙ ክልሎች ውስጥ ተጨፍልቀዋል (አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 1)፡፡

አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 ደግሞ ሌሎች “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል ማቋቋም መብት አላቸው” ይላል ፡፡ ስለዚህ በማንነትና በመልክዓምድር ጥያቄ ላይ ገና የማያባሩ ጦርነቶችና ግጭቶች ይጠብቁናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የክልሉ መሥራች ናቸው ተብለው የማይታሰቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እና መጤ ተብለው በሁለተኛ የክልሎች ዜግነት የሚፈረጁ ለመብቶቻቸው በሚያነሱት ጥያቄ የእርስበርስ አውዳሚ ግጭቶች ይጠብቁናል፡፡

2. “የየራሳችን መልክዐምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በመግቢያው ውስጥ የሚገኝ ሌላ ሐረግ ነው፡፡

እውን በኢትዮጵያ ምድር የብሔረሰቦች አሰፋፈር በዘመናት ሁሉ በአንድ ሥፍራ የተወሰነ ነበር? እንግሊዝኛው “ለረዥም ጊዜ የሰፈርንበት ሥፍራ የነበረን” ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህ ዘመን ቁጥሩ ምን ያህል ነው? ኦሮሞ የዛሬ 500 ዓመት የት ነበር እውነተኛ ወሰኑ? የአማራስ? አዲስ አበባ የኦሮሞ ግዛት የነበረችው መቼ ነው? ከዚያ በፊትና አሁንስ ? ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ራያ ሙሉ በሙሉ የትግራይ አካል የሆኑት መቼ ነው? የብሔር ብሔረሰቦችን ወሰን ለይተንና አንጥረን ታሪክን ፈትሸን ነው በሽግግር መንግስቱ 9 ክልሎችን የፈጠርነው? ባድመ ላይ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ውዝግብ የዛሬ 20 አመት ምን ያህል ሰው እንደሞተ ማስተዋል ይገባናል- 70,000፡፡ በዚህ ረገድ ህገመንግስቱ የኢትዮጵያን ህዝብ የእሳት እራት የሚያደርግ ትልቅ ወጥመድ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ - መላ መላ ብለው ኅሊናዎን አበርትተው ለንሥሃ ይብቁ! - ከበየነ

የሚገርመው ይህ ባልታየበት ሁኔታ አንቀጽ 39 መሰንቀሩ ነው፡፡ ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው” ሲል የኢትዮጵያን ህዝብ የመጠፋፊያ የጊዜ ቦንብ ይቀብራል፡፡ ማን የማንን መሬት ይዞ ሲሄድ እያየ ዝም ይላል? ትግራይ ቢገነጠል አማራ ስለ ወልቃይት፣ ጠገዴና ራያ እያለቀሰ ዝም ሊል? በሕዝብ ቁጥር የበላይነትና በህዝበ-ውሳኔ በኦሮሞ ተወሰዱብኝ ስለሚለሏቸው አዋሳኝ ወረዳዎች ሶማሌዎች በቁጭት ያሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በአዲስ አበባ ላይ መቆራቆስ አይቀሬ ነው። የደቡብ ክልል ክፍፍል እስከ ወረዳና ዞን የዘለቀ መሆኑም ትልልቅ አደጋዎችን የቋጠረ ነው፡፡

አንቀጽ 48 የአካላለል ወሰን ጥያቄዎችን ወይም የክልሎች ወሰንን በሚመለከት አለመግባባት ቢሰከት በፌደሬሽን ምክር ቤት “የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወሰናል” ይላል ( ንዑስ አንቀጽ1)፡፡ ታሪክስ ለምን ገሸሽ ይደረጋል? አንድ ብሔር የአንድ አካባቢ ታሪካዊ ባለቤት ሆኖ ሳለ ከጊዜ በኋላ በተፈጠረ የህዝብ ንቅናቄ ወይም ወረራ የህዝብ ቁጥር ብልጫ ቢወሰድበት ታሪካዊ ይዞታውን መነጠቅ አግባብነት አለው? 500 ዓመታትን ወደ ኋላ ብንሄድ የአሁኑ አካሄድ ሁሉ ፍሩሽ ይሆናል፡፡

3. “ከታሪካችን የወረስነውን የታዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ”

ይህም መግቢያው ላይ የሚገኝ ሀረግ ነው፡፡ ታሪክ የሚጠቀሰው የተዛባ ግንኙነትን ለማረም ብቻ ነው? ጠቃሚና መልካም የነበሩ ግንኙነቶችን ለማጠናከር አይጠቀስም? የተዛባ ግንኙነት የሚለው እንዴት ይፈታል? ጨቋኝ ተጨቋኝ ? ወራሪ ተወራሪ ከሆነ ማን ነበር ወራሪው? የአማራ ብሔር በላይነት ለማለት ተፈልጎ ይሆናል፡፡ በአማራ ስም የተሰለፉ መሪዎች የዘር ግንድ፣ የሰራዊቱ መዋቅር በደንብ ተፈትሾአል? የዛሬ 120 ዓመት የሚኒሊክ ተስፋፊነትን ታሪክ ከጻፍን የዛሬ 500 ዓመት የኦሮሞ ገዳ ተስፋፊነትንም በመጻፍ ሚዛንን መጠበቅ ይገባናል፡፡ ስለ Amharization አውርተን መቼም በገዳ ስለተፈጸመው Oromization ታሪክን መካድ አይገባም፡፡ የተዛባ ግንኙነትን በዚህ መልክ ሚዛን ጠብቆ መተንተን ተገቢ ነው ፡፡

4. “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች ሕዝቦች ይህ ሕገመንግስት ከዚህ በላይ ለገለጽናቸው ዓላማዎችና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን፣ እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት በሕገመንግስት ጉባኤ ህዳር 29 ቀን 1987 አጽድቀነዋል”፡፡

‹‹መርጠን በላክናቸው›› የሚለው ይሰመርበት፡፡ እውን በብሔርሰቦች እውነተኛ ውክልና፣ ጥያቄ፣ ውይይትና ምሁራዊ ግምገማ የጸደቀ ህገመንግስት ነው? ከሆነ የተሰባሰቡት ሀይሎች ለሀገር ውድመትና ለእርስበርስ መጠፋፊያ ምክንያት የሚሆኑ ጽንሰሃሳቦችን የያዘ ቦንብ ለራሳቸው አጥምደው ነበር የተለያዩት ማለት ድፍረት አይሆንም፡፡

ማጠቃለያ

ቢያንስ አማራው ይህ ህገመንግስት ሲጸድቅም ሆነ ሲረቀቅ ውክልና አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ‹‹እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው›› የሚለው ለእርሱ አይሰራም፡፡ ብዙ ምርጥ አናቅጽን የያዘ ይህ ሕገመንግስት አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ታርሞ ካልተሸሻለ እነሆ በቅርብ ጊዜ ሶርያን እዚሁ አገራችን እናያታለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:   ከይሁዳዊ ፀባይ እንፋታ ፡፡ በበርባን ፀባይ መጓዛችን ያብቃ! - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

በይቅርታ ሊፈቱ ከሚችሉ የታሪኮቻችን ውጥንቅጦች በላይ ይህ ህገ-መንግስት የመጠፋፊያ ጽንሰ ሃሳቦችን በውስጡ የሰነቀ መንግስታዊ የመርዝ ሰነድ ነው፡፡

የህገመንግሥቱና የታሪክ ግጭት

“ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር ፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባሕሉን የመግለጽ ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡” ( አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 2 )

‹‹ ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው›› የሚለው ይሰመርበታል፡፡ ግን ታሪክ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ታዬ ቦጋለ አረጋ የተባሉ ምሁር መራራ እውነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 36 ላይ እንዲህ ብለዋል፡፡

“ታሪክ ፡- የሰው ልጅ ባሳለፋቸው ረጅም ዘመናት ውስጥ በተወሰነ ጊዜ (ዘመን) ፣ ቦታ፣ የአኗኗር ዘይቤ የተፈጸሙ ክንውኖች በምን አኳኋን ፣ እንዴት ባለ አውድ ፣ ለምን ዓላማ ፣ በእነማን አስተባባሪነትና ተባባሪነት እንደተፈጸሙ ቢቻል ታሪካዊ ማስረጃዎችን በማጣቀስ ባይቻል የተሰበሰቡ መረጃዎችን በማገላበጥ እና በሚጠናው ድርጊት አቅጣጫ ከተገኙ ሌሎች ሰነዶች አኳያ በማመሳከር ወደ እውነታው ለመድረስ የሚጥር ነው፡”

ታሪክ በጊዜ (ዘመን) እና ቦታ የሚፈጸም ነው፡፡ ይህንን እሴቱን መንከባከብ ለየትኛውም ብሔረሰብ ሕዝብ የተሰጠ መብት ነው፡፡ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱ ታሪክ የተገነባበት ቦታ አለው፡፡ ይህ ቦታው ከጊዜ በኋላ ወይ በመስፋፋት አሊያም ከአጎራባች አካባቢዎች በጊዜ ውስጥ በፈለሱ የሌላ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አባላት ቢያዝና የቁጥር ብልጫ ቢወሰድበት እና ወደ ሌላ ክልል ቢገባ እንዴት ይዳኛል? ወደ ሌላ መካለሉ የመሬት (ቦታ) ቅሚያ አይሆንም?

አለመግባባት ቢፈጠርና የአካላለል ለውጥ ፍላጎት ቢከሰት ሕገ-መንግስቱ በአንቀጽ 48 ንዑስ አንቀጽ 1 ‹‹ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወስናል›› ይላል? በትግራይ ፍልሰተኞች የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ቀደምት የወልቃይትና ጠገዴ አማሮችና የራያዎች ጥያቄ አፈር በላ ማለት ነው፡፡ ታሪክ ቦታም ጭምር ነው፤ ስነ-ልቦናዊ ትስስር እና የባህል መስተጋብሩ ከአቆራኘው ወገኑ በድምጽ ብልጫም ሆነ በፖለቲካዊ ውሳኔ ሊነጠል አይገባውም፡፡ ሕገመንግስቱ ፌደራል አከላለልን በተመለከተ ከታሪክ ጋር ይጣረሳል፡፡ ታሪክ መረጃና ማስረጃ ላይ ይደገፋል። የኢፌዴሪ ሕገመነንግሥት ግን በፖለቲካ ውሳኔ ኢትዮጵያን አንኮታኩቷቷል።

የሶማሌና የኦሮሞ አጎራባች ወረዳዎች እና ሌሎችም ታሪክን ባላገናዘበ መልኩ በድምጽ ብልጫ መነጠቅ አይገባቸውም፡፡ ድሬደዋ፣ሞያሌ፣ አዲስ አበባና ሌሎችንም በዚሁ አንጻር ካላየናቸው ውሎ አድሮ የእልቂት መንደሮች ይሆናሉ፡፡ ሕዝበ-ውሳኔ ታሪካዊ ዳራዎችን ካላገናዘበ በፍጹም ችግሮቻችንን አይፈታም፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛ ልሂቃን “የምንሊክ ሰፋሪ” ብለው ለማሸማቀቅ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በኦሮሚያ የሚኖሩ ሕዝቦችን መብት እንዳይጠይቁ አንገት ለማስደፋት ሰርተዋል፣ እየሰሩም ነው፡፡ ኒውተን በአንድ የዳይናሚክስ ሕጉ ለእያንዳንዱ ድርጊት ተመጣጣኝ እና ተቃራኒ አጸፋ (for every action, there is an equal and opposite reaction) እንዳለው በኦሮሞ መስፋፋት ታሪክ ላይ ያተኮሩ ዘመቻዎች ተጀምረዋል፡፡ የታሪክ ግጭቶችን የሚያስተናግድበት መንገድ ያላበጀው ሕገመንግስት አንድነትን አደጋ ላይ መጣል ብቻ ሳይሆን መተናነቂያ እና መተላለቂያ ሜዳ የሚያመቻች ነው፡፡ሊሻሻል ይገባዋል!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጥንታዌት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  አጭር ታሪክና ሥርዓት

ድሬደዋን፣ሞያሌን፣ጭናክሰንን፣ ባቢሌን ወዘተ… ያለ ታሪካዊ ዳራ ምልከታ በሪፈረንደም ለሱማሌ ወይም ለኦሮሞ ብንሰጥ ጣጣው ይከፋል፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው ተበትኖ የሚኖር ሌላ ብሔረሰብ በሁለተኛ ዜግነት እየታየ መቀጠል ይዋጥለታል?

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በአንድ የኦሮሚያ ክልል ዞን ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ነበር፡፡ በዚሁ አመት( 2011 ) የተደረገ የገበሬዎች ስብሰባ ነበር፡፡ የዞኑ ምክትል አስተዳደሪ ለንግግር ወደ መድረክ ተጋብዘ ፡፡ በንግግሩ ማገባደጃ ላይ ግን ድንገት ስለወቅቱ ሁኔታ መናገር ሊጀምር በካሜራ እንዳይቀረጽ ትዕዛዝ አስተላልፎ ንግግሩን ቀጠለ ፡፡

በኦሮምኛ ‹‹ ስለአዲስ አበባ ጉዳይ የሚናፈሰውን ወሬ ሰምታችሁ አትረበሹ፡፡ ድርጅታችን ኦዲፒ ጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡ በእኔ ዞን ብቻ 5000 የአዲስ አበባ መታወቂያዎች እንዲሰራጩ ተደርጓል፡፡ በየዞኑ በመላው ኦሮሚያ ይህ እየተደረገ ነው፡፡ የአሁኑ የህዝብ ቆጠራ ለኦሮሞ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ በቀናችሁ በሠፈራችሁ ተገኝታችሁ መቆጠር አለባችሁ፡፡ የኦሮሞ ትግል አሁን ጫፍ ደርሷል፡፡ አገሪቱን ወደፈለግነው ለመምራት ስልጣኑ በድርጅታችን ኦዴፓ እጅ ነው›› ሲል አጠቃለለ፡፡

የአዲስ አበባን ወይም የጠንቱንዋን በረራ ዲሞግራፊ (የህዝብ ቁጥር) ለመቀየር ከሚደረጉ ሴራዎች አንዱ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ታሪካዊ እሰጥአገባዎችን እና የህገ-መንግስቱን እንቀጽ 49 እንዴት መሻገር እንደታሰበ እና እስከመቼ እቅድ እንዲተያዘም አላውቅም ፡፡ ብቻ አዲስ አበባን የኦሮሞ ለማድረግ ህዝብ ቁጥር ላይ መተኮሩ አንድ ቀን ለአንቀጽ 48 የአከላለል ለውጥ ህዝባዊ ጥያቄ እንዲቀርብ መንገድ ለማመቻቸት በረዥም ጊዜ የተያዘ ዕቅድ መኖሩን ጠቋሚ ነው፡፡

እንደው እንበልና ሌላውን ሕዝብ በማፈናቀል፣ ኦሮሞን በማስፈር፣ በውሸት መታወቂያ በድብቅ በመላው ኦሮሚያ አያሰራጩ በአዲስ አበባ ነዋሪነት በማስቆጠር ኦሮሞ በልጦ ይገኝ፡፡ ግን ግን ታሪካዊ እና ሕገመንግስታዊ እውነታን ቸል ብሎ መብቱን ዝም ብሎ የሚያስረክብ ፈሪ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል? የሌላውን ቤት እያፈረሱ የራስን ቤት ለመገንባት የሚሮጥባት የሴራ አገር ሆናለች ኢትዮጵያ፡፡ የአዲስ አበባን የጥንት ታሪክ በተለይ የኦሮሞ ልጆች ሊማሩት ይገባል። እልባት ካልተገኘለት ግን መተላለቃችን ነው፡፡ ሕገመንግሥቱን ከፋፋይ ያደረጉት አንቀጾች ይሻሻሉ! ጆሮ ያለው ይስማ! (1) በታኝ አንቀፆቹ፣ (2) ታሪክን ገፊነቱ፣ እና (3) ጎዶሎ የሕዝብ ውክልናው። አንኳር ችግሮቹ እነዚህ ናቸው።

ሕገመንስቱ ኢትዮጵያ እና አማራ-ጠል የሆኑ ድርጅቶች ፕሮግራም ነው የሚለውንም መናቅ አይገባም፡፡ የፋሽሽት ጣሊያን መርዝን የተጋቱ ነገር ግን የትግራይን ህዝብ፣ የራስ የአሉላ አባነጋን፣ እና የአጼ ዮሐንስን ጥልቅ የሀገር ፍቅር፣ እንዲሁም በወያኔ ቅስቀሳ የተማገደ እና ነገሩን በጥልቀት ያልተረዳ ቅን ታጋይን ተጋዴሎ የማይመጥን የባንዳ ጥላቻ ወራሽ ልጆች የበታችነት ስሜት እልህ፣ የነዋለልኝ የስታንሊን የብሔር ፖለቲካ ጀብደኝነት፣ የኦነግ ታሪክን ያላገናዘበና የተለጠጠ የኮሎንያሊዝም ትርክት ያቦካው የጥፋት መሳሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share