ለቸኮለ! ሰኞ ሐምሌ 26/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ኮምንኬሽን ባለሥልጣን ሁለተኛውን የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ ጨረታ በቀጣዩ ወር እንደሚያወጣ ሮይተርስ ዘግቧል። ዓለማቀፍ ኩባንያዎች ለጨረታው የሚያቀርቡትን ዋጋ ለማሳደግ፣ በጨረታው የሚወጣው የአገልግሎት ፍቃድ የሞባይል ገንዘብ መገበዬን እንዲጨምር እንደተደረገ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ ተናግረዋል። በኬንያው ሳፋሪኮም ኩባንያ የተመራው ዓለማቀፍ ጥምረት ያሸነፈው የመጀመሪያው የቴሌኮም አገልግሎት ጨረታ የሞባይል መገበያያ ፍቃድን አይጨምርም።

 

2፤ የሕወሃት ተዋጊዎች ውጊያ ከማቆማቸው በፊት፣ ፌደራል መንግሥቱ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ እንዲፈታ፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ይፈጸማሉ የተባሉ ጥቃቶችን እንዲያቆምና ለሀገሪቱ አካታች የፖለቲካ መፍትሄን እንዲቀበል የሕወሃት ተዋጊዎች አዛዥ ናቸው የተባሉት ጀኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳይ ለቢቢሲ በሰጡት ቃል አሳስበዋል። የሕወሃት ተዋጊዎች በአፋር እና አማራ ክልሎች አዲስ ጥቃት የከፈቱት መንግሥት ያገደውን የሰብዓዊ ዕርዳታ መስመር ለማስከፈት ነው- ብለዋል ጻድቃን። መንግሥት ሰብዓዊ ዕርዳታ መስመሮችን የዘጋው ሕወሃት ራሱ ነው ይላል

 

3፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከባድ ጦር መሳሪያ እና ወታደሮችን ወደ ትግራይ ክልል ያመላልሳል በሚል በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ ወሬዎችን መሠረተቢስ ሲል በድረገጹ አስተባብሏል። ከኅዳር ወዲህ ያደረጋቸው ጥቂት በረራዎች ሙሉ በሙሉ የንግድ በረራዎች እንደሆኑ የገለጸው አየር መንገዱ፣ አንዳንድ ግለሰቦች የሚያሰራጯቸው ፎቶዎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዳልሆኑ አክሎ ገልጧል። አየር መንገዱ መለዮ ለባሾችን ማመላለሱ በዓለማቀፍ ሕግ የተፈቀደ ቢሆንም፣ ወደ ግጭት ቀጠናዎች ግን አመላልሼ አላውቅም ብሏል። ክልሉ የሚያደርገውን በረራ ከአንድ ወር በፊት በድጋሚ ማቋረጡ ይታወሳል።

 

4፤ የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረ ጺዮን ገ/ሚካዔልን ጨምሮ በሽብር ወንጀል በተከሰሱ 62 የሕወሃት አመራሮች ላይ የተመሠረተውን ክስ ፍርድ ቤት ነሐሴ 11 በንባብ ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። ተለዋጭ ቀጠሮው የተሰጠው ዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን አሟልቶ ባለማቅረቡ ሲሆን፣ ዓቀቤ ሕግ የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃዎቹን በቀጣዩ ቀጠሮ አቀርባለሁ ብሏል። ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው ለተከሳሾቹ ክሱን ለማንበብ ቢሆንም፣ ለዛሬው ግን ስብሃት ነጋ እና ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ እስር ቤት ላሉትና በችሎቱ ለተገኙት 19 ተከሳሾች በጽሁፍ ሰጥቷቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግብፅ የማያባራ ተንኮል !!!! - ተድላ አስፋው

 

5፤ በሱዳኗ ከሰላ ግዛት 40 አስከሬኖች ተከዜ ወንዝ ውስጥ እየተንሳፈፉ እንደተገኙ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣን መናገራቸውን ዓለማቀፍ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። አስከሬኖቹ ከኢትዮጵያው የትግራዩ ክልል ግጭት ይሸሹ የነበሩ ሰዎች ሳይሆኑ እንደማይቀር ባለሥልጣኑ የተናገሩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ በጥይት የተመቱበት ምልክት ያላቸውና እጃቸውን ለፍጥኝ የታሰሩ እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ሆኖም ሰዎቹ የሞቱበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ የአስከሬን ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል። አስከሬኖቹ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተገደሉ ሰዎች ስለመሆናቸው አስከሬኖቹን አይተናል ካሉ በሱዳን ከሚገኙ ስደተኛ የትግራይ ተወላጆች ውጭ ዘገባውም ሆነ ባለሥልጣኑ ሌላ ማረጋገጫ አላቀረቡም።

 

6፤ የሕወሃት ደጋፊዎች ሑመራ ከተማ ላይ ቀደም ሲል በትግራይ ተወላጆች ላይ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል የሚለውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳቸውን በድጋሚ እየጀመሩት እንደሆነ የመንግሥት ወቅታዊ ሁኔታዎች መረጃ ማጣሪያ በትዊተር ገጹ አስታውቋል። የሐሰት ፕሮፓጋንዳው እየተሰራጨ ያለው የሐሰት ምስሎችንና ስዕላዊ ቅንብሮችን በመጠቀም እንደሆነ ተገልጧል። ማንኛውም ሰው ይህንኑ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እንዲከላከል መረጃ ማጣሪያው አክሎ ጠይቋል።

 

7፤ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ቱርክ ለኢትዮጵያ ማናቸውንም ዓይነት ድጋፍ ታደርጋለች ማለታቸው ተገልጧል። ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን በበኩላቸው ቱርክ ለኢትዮጵያ ደኅንነት እና መረጋጋት ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጠዋል።

 

8፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለገቢ ንግድ የውጭ ምንዛሬ እንደገና ማቅረብ እንደሚጀምር ከባንኩ መስማቱን ሪፖርተር ዘግቧል። ባንኩ በውጭ ሀገራት ያሉብኝን ክፍያዎች በቅድሚያ ማጠናቀቅ አለብኝ በማለት ከአንድ ዓመት በላይ ለገቢ ንግድ የውጭ ምንዛሬ ማቅረብ አቁሞ ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግልጽ ደብዳቤ ለሃይሌ ገብረሥላሴ -ከአበበ ገላው

 

9፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በአፋር እና ሱማሌ ጎሳዎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ ጅቡቲ መጋባቱን አንታገሰውም ሲሉ የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ሰዒድ ሐሰን በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው አስጠንቅቀዋል። የጅቡቲ መንግሥት ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው፣ በጅቡቲ ከተማ ትናንት በአፋር እና ሱማሌ ተወላጆች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ነው። በግጭቱ ሕይወት እንደጠፋና ንብረት እንደወደመ የገለጹት ሚንስትሩ፣ ግጭቱ ባስቸኳይ እንዲቆም አሳስበዋል። በጅቡቲ ግጭት የተቀሰቀሰው በኢትዮጵያው ሱማሌ ክልል የአፋር እና ሱማሌዎች ግጭት በርካታ ሰዎች በሞቱ ማግስት ነው።

 

[ዋዜማ ራዲዮ]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.