“ከውስጥ ኾነው የተላላኪነት ሥራ በሚሠሩ የሕዝብ ጠላቶች ላይ ሕጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው” የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን

224629419 1600523423455979 7272856893701324970 n
ባሕር ዳር:ሐምሌ 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን በወቅታዊ ጉዳይ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም አሸባሪው ትህነግ የትግራይ አርሶ አደሮች የክረምት የእርሻ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መንግሥት የሠጠውን የጥሞና ጊዜ ወደ ጎን በመተው በተለያዩ አካባቢዎች ትንኮሳ እየፈጸመ ነው፤ ዓላማውም ቢሳካለት ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው ብለዋል።

አሸባሪው ከተከዜ ማዶ በተለያዩ ጊዚያት ትንኮሳዎችን አድርጓል ያሉት አቶ ያለዓለም የአደርቃይና የማይጠብሪ አካባቢዎችን ለመውረር ባደረገው ትንኮሳም በወገን ጦር የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደበት ነው ብለዋል።

“ከአማራ ሕዝብ የማወራርደው ሒሳብ አለኝ፤ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ብሎ ለተነሳው ጁንታ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የጸጥታ ኀይሉና ከሁሉም ጫፍ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እየሰጡ ያሉት ምላሽም እጅግ የሚበረታታ ነው፤ ተጠናክሮም መቀጠል አለበት ብለዋል። አሸባሪው ቡድን ዕድሜያቸው ለጦርነት ያልበቁ ህጻናትን ከፊት በማሠለፍ ንብረት ይዘርፋል፤ የንጹሓን ሕይወት ያጠፋል፤ የአርሶ አደሮችን በሬ፣ ላምና ፍየል አርዶ ይበላል፤ ዜጎችን በማጎሳቆል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሁሉን ነገር እየሞከረ ነው ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።

የኢትዮጵያ ጠላት መኾኑን የተረዱት ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በነቂስ በመውጣት ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ እውነትንና ሕዝብን የያዘ ወገን አሸናፊ ነው፤ እናሸንፋለንም ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ማኀበረሰቡም አሸባሪው በትግራይ ውስጥ በኢ-ፍትሐዊ መንገድ ለጦርነት የሚማግዳቸውን ሕጻናት በማየት ለፍትሕ መጮህ አለበት፤ እውነቱን በመረዳትም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል ነው ያሉት።

እንደ ሕዝብ ለመኖርም አሸባሪው ቡድን ከምድረ ገጽ ሊጠፋ ይገባል የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው ማንኛውም ሰው የሚታገለው የመኖር ህልውናውን ለማረጋገጥ ነው፤ ጠላት ቢሳካለት አጎራባች ከኾኑት ከአማራና አፋር ሕዝቦች ባለፈ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እቅድ ያለው መኾኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል ብለዋል።

የውስጥ ተላላኪዎችን ለማክሰም ወጣቱ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው “ከውስጥ ኾነው የተላላኪነት ሥራ በሚሠሩ የሕዝብ ጠላቶች ላይ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ርምጃ እየተወሰደ ነው” ብለዋል። የባንዳነት ሥራ የሚሠሩ ሰዎችም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፤ የተላላኪነት ሥራ ሲሠሩ በተገኙት የሕዝብ ጠላቶች ላይም የማያዳግም ርምጃ እየተወሰደባቸው እንደኾነ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ ያንብቡ:  ረዳት ፓይለቱ ኃይለመድህን አበራን በመደገፍ በስዊዘርላንድ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠራ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share