የኢትዮጵያ መንግሥት ከእስካሁኑ አገሪቱን ውድ ዋጋ ካስከፈለው ድክመቱ ትምህርት መውሰድ ይኖርበታል፡፡

obama
የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መንግሥት፣ በተለይም የዴሞክራቲክ ፓርቲው ‹ኢስታብሊሽመንት› በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም እጅግ አደገኛ ነው፡፡ የዴሞክራቲክ ፓርቲው አመራሮች እና በእነሱ ዙሪያ ያለው የሚዲያና የቢዝነስ ኢምፓር በተለያዩ አገሮች የመንግሥት ለውጥ (regime change) የማድረግ እና አገራቱን ትርምስ ውስጥ የመክተት ልምድ አለው፡፡ ዴሞክራሲን በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋትና ለመደገፍ፤ እንዲሁም ሰብአዊ መብትን ለማስከበር በሚል ሽፋን በብዙ አገሮች የውስጥ ጉዳይ እየገቡ ከፍተኛ ምስቅልቅል ሲፈጥሩ የቆዩ አካላት ናቸው፡፡

እነዚህ፤ ራሳቸው የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ከለውጡ በኋላ በግልጽ እንዳመኑትና የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ እንደሚገነዘበው በተጭበረበረ ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ያለውን የአፈና አገዛዝ “በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት” ብለው ያሞካሹት ሰዎች (ፕሬዚዳንት ኦባማንና ሱዛን ራይስን መጥቀስ ይቻላል) የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ጠበቃ ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ ቢሆንም፤ በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት ሽፋን ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ እየወጓት ይገኛሉ፡፡ ይህም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡

የዚህ ሁሉ ውርጅብኝ አንደኛው ምክንያት ከኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ውድቀት የሚመነጭ ነው፡፡ ያለ ጥርጥር በሕዝብ ግንኙነትና በዲፕሎማሲው መስክ በእጅጉ ተበልጠናል፡፡ አሜሪካ ውስጥ ፖለቲካና የፖለቲካ ድጋፍ ከገንዘብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነገር መሆኑን ባለመረዳታችን ብዙ ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን፡፡ በአሜሪካ የፖለቲካ ድጋፍና ተቃውሞ ልክ እንደ እቃና አገልግሎት ይሸጣል፤ ይገዛል፡፡ አሸባሪው ቡድን ደጋፍ እንዲያገኝና የኢትዮጵያ መንግሥት መጥፎ ገጽታ እንዲኖረው የሚሠሩ የሎቢ ድርጅቶች፣ በኢትዮጵያ ላይ ይህን ሁሉ መዓትና ውድርጅብኝ ሲያወርዱ የሚውሉት ሕወሓትን ስለሚደግፉ ወይም አሸባሪው ቡድን ሕዝባዊ ነው ብለው ስለሚያምኑ አይደለም፡፡ እነዚህ አካላት በዚህ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ የሚረባረቡት ስለሚከፈላቸው ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ መረባረብ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ጥላሸት መቀባት፣ አሸባሪውን ቡድን ተበዳይና ተጠቂ አድርጎ ማቅረብ ገንዘብ ያስገኝላቸዋል፡፡ አሸባሪው ቡድን በሥልጣን ላይ በደነበረበት ዘመን በዘረፈው የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት ሎቢ ቀጥሮ ገጽውን እየገነባ ይገኛል፡፡ ሕወሓትና ደጋፊዎቹ አሜሪካ ውስጥ የፖለቲካ ድጋፍ የሚሸጥ የሚለወጥ መሆኑ ገብቷቸዋል፡፡ ይህንን ሐቅ ተረድተው በመንቀሳቀሳቸውም አትራፊዎች ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ለብዙ ዘመናት ዝናብና በረዶ ሳይበግረው አዳባባይ እየወጣ ሲሰለፍ ከርሞ ማሳካት ያልቻለውን በወራት ውስጥ ማሳካት ችለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ እየደረሰ የሚገኘው በእነሱ ትግል ምክንያት ጭምር ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Sport: የጎደለው ሊቨርፑል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት በሕዝብ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ትግሉ ላይ ከፍተኛ ብልጫ እንደተወሰደበት፣ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነትና የኮምኒኬሽን ስብስብ/ቡድን ማቋቋም እንደሚገባው፣ ከዚያም አልፎ አሜሪካ ውስጥ ሎቢ ድርጅቶችን መቅጠር እንዳለበት ወዘተ… ቢነገረውም በጄ የሚል አልሆነም፡፡ ሰሚ አልተገኘም፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ አላስፈላጊ ዋጋ ከፍላለች፤ እየከፈለችም ነው፡፡ ይህ ችግር መፍትሔ ካልተሰጠው ወደፊትም የኢትዮጵያ መከራ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡

ከአሸባሪው ቡድን በተጨማሪ የግብጽ እና የግብጽ ደጋፊዎች ተጽዕኖም ቀላል አይደለም፡፡ ብዙዎቹ የዐረቡ ዓለም አገሮች ከሕዳሴው ግድብ ጋር አያይዘው ኢትዮጵያን እረፍት መንሳትና ማዋከብ የየእለት ተግባራቸው አድርገውታል ማለት ይቻላል፡፡ የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያንን እያሰረ የሚያሳቃየውና ጠርዞ ወደ ኢትዮጵያ የሚልከው በሌላ በምንም ምክንያት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን የማዋከቡ አንደኛው መንገድ ስለሆነ ነው፡፡ የጎረቤት ሱዳን መንግሥት ኢትዮጵያ በራሷ የውስጥ ጉዳይ ላይ በተወጠረችበት ወቅት ጠብቆ የአገራችንን መሬት መውረሩም ከዚኸው ኢትዮጵያን የማዋከብና እረፍት የመንሳት መንገዱ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተወጥራና ተዋክባ እጇን እንድትሰጥ ይፈለጋል፡፡ በሕዳሴው ግድብ እና በዓባይ ጉዳይ ላይ አስገዳጅ ውል እንድትፈርም መጠነ-ሰፊ ጫና እየደረሰባት ይገኛል፡፡ የአብዛኛው ጫና ምንጩ ከሕዳሴው ግድብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በዚህ ረገድም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳየው የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ድክመት ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፤ ወደፊትም ያስከፍለናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሎቢ ድርጅቶችን ቀጥሮ የአሜሪካንን ፖለቲከኞችን (በተለይም የኮንግረስ አባላትን)፣ ሚዲያውንና ታዋቂ ሰዎችን መያዝ ሲገባው፣ ይህ ነው የሚባል የረባ ሥራ ሳይሠራ ቀርቷል፡፡

በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች በቅርቡ ከአሜሪካ አካባቢ የዐቢይን መንግሥት ከሕዝብ የመነጠል፤ ከዚያም አልፎ የመንግሥት ለውጥ አጀንዳን የማቀንቀን አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡ እነዚህ እጅግ አደገኛ አዝማያዎች በጠንካራ የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራ ካልተቀለበሱ መዘዛቸው የከፋ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ጦር (አየር ኃይል) ሊቢያን እንዲደበድብና ሞሐመድ ጋዳፊን እንዲያስወግድ የወሰንኩት ውሳኔ በፕሬዚዳንትነት ዘመኔ ከወሰንኳቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎች አንዱና የምቆጭበት ነው ብለውናል፡፡ ግን ኦባማ ይህን የተናገሩት ሞሐመድ ጋዳፊ ከተገደሉ፤ ሊቢያም የጦር አበጋዞች መፈንጫ ከሆነች በኋላ ነው፡፡ የኦባማ ተፀፅቻለሁ ማለት ሊቢያን አይመልሳትም፡፡ አሜሪካዊያን በብዙ አገሮች በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት ጥበቃ ሽፋን እየገቡ አገራቱን አፈራርሰዋቸዋል፡፡ የመሣሪያ ንግድ የሚያጧጡፉ ድርጅቶቻቸው ጦርነት እንደሚፈጥሩ ዓለም ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በፍራንክፎርት የኢትዮጵያዊያን የነፃነትና እኩልነት ለኢትዮጵያ ግብረ ኅይል መግለጫ

እንዲህ ዓይነቱ አደገኛ መንግሥት የመቀየር እርምጃ በኢትዮጵያ ላይ እንዲወሰድ እና በአሜሪካ ተጽዕኖ የመንግሥት ለውጥ እንዲደረግ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችንና ዘገባዎችን እያየን ነው፡፡ እነዚህ ዘገባዎች እንዲሁ በቀላሉ መታለፍ የለባቸውም፡፡ የተሻለው መፍትሔ በጠንካራ የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራ የተቀነባበረብንን መጠነ-ሰፊ ውርጅብኝ መመከት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከእስካሁኑ አገሪቱን ውድ ዋጋ ካስከፈለው ድክመቱ ትምህርት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራው ተገቢውን ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገር ወዳድ ዜጎችም ብንሆን እንዲህ ዓይነቱን በተከበረች አገራችን የውስጥ ጉዳይ እየገቡ የመፈትፈት ታላቅ ድፍረት በጽናት መቋቋም ይገባናል፡፡ ከኢትዮጵያ የሚበልጥ ምንም ነገር የለም!

(ዳዊት ዋበላ)

 

2 Comments

  1. The picture of a man called Yohanes Abrham should have been included. I believe he is the primary source of the above law makers.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share