“ለአፍ ዳገት የለውም” ይሉት አባባል በተለይ ለወያኔው አፈ ቀላጤ ለጌታቸው ረዳ በልኩ የተሰፋ ሥነ ልሣናዊ የምላስ ቡታንታ ነው ቢባል በትክክል ያስማማል፡፡ ጌታቸው ረዳና አጎቱ አቢይ ረዳ ማነው አቢይ አህመድ የድምጽ ማጉያ እጀታ (ማይክ) ከጨበጡ ይሉኝታንና ሀፍረትን በቲራ ዘርረው ይጥሏቸዋል፤ እንዲያውም ካልዋሹ በሕይወት የሚኖሩ አይመስላቸውም ይመስለኛል – መዋሸት ለነሱ ARV (antiretroviral drug – የሕይወት ማቆያ ክኒን) ሳይሆን አይቀርም፡፡ “ሰው ምን ይለኝ? አሁን የምለው ነገር ውሸት ቢሆን ጓደኞቼና የቅርብ ቤተሰቤስ ምን ይታዘበኝ? የ‹ሾርት ሜሞሪ› ምርኮኛው አብዛኛው ኢትዮጵያዊስ ምንም አያመጣም – ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በምቀላምደው ነገር ምን ይለኝ ይሆን…?” ብለው እነዚህ የታሪክ ጉዶች በፍጹም አይጨነቁም፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ጌቾ ምላሱና ሃሳዊ መሲሑ አቢይሻ ማሰብ ከማይችሉት የቻይና ሮቦቶች ጋር ይመሳሰሉብኛል፡፡ የጃፓን ሮቦቶች ቢሆኑ ሳይሻለን አይቀርም ብዬ እገምታለሁ ደግሞ፤ ለምን ቢሉ ኦሪጂናሎቹ የጃፓን ሮቦቶች ከቻይኖቹ ይልቅ ጥቂት የሰው ሽታ ሳይኖራቸው አይቀርም ብዬ እገምታለሁ – መቼም ግምት ነውና ብሳሳት ይቅርታ አድርጉልኝ፡፡ ሰው ውሸት ብቻ ለመናገር ይፈጠራል??….
“ሒሳብ ማወራረድ” ምን ማለት ነው? አማራው ጌታቸው ረዳ ትግሬ ሆኖና ትግሬን ወክሎ ከአማራ ጋር ሒሣብ እንደሚያወራርድ በፊትም አሁንም በተደጋጋሚ ይፎክራል፡፡ አማራው ሴኩትሬ ጌታቸውም ልክ እንደጌቾ ምላሱ በአማራ ላይ እንደፎከረና እንደዛተ የራሱን ሒሣብ በቅርቡ አወራርዶ ከዚህች አስጠሊታ ምድር ተሰናበተ – የርሱ ተሻለ – በስንት ጣሙ ወንድማለም! ይሄ ጌታቸው የሚባል ስም ግን አንዳንዴ ነገር አለው ማለት ይሆን? ጌታቸው አሰፋ፣ ጌታቸው በላይ፣ ጌታቸው ረዳ፣ ሴኪቱሬ ጌታቸው….፡፡ በዚያን በወዲያኛው ሰሞን ነገዳዊና ብሔራዊ ማንነቱን በሶልዲ የሸጠው ሴኩትሬ ጌታቸው “በ45 ደቂቃ ኦፕሬሽን ትግራይ ውስጥ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ዐመድ አደረግነው” ብሎ ከመናገሩ የኢትዮጵያ አምላክ ራሱን ዐመድ አደረገው፡፡ ሒሣብ ማወራረድ ብሎ ነገር እንዴት ያስጠላል ግን!
ሒሣብ እናወራርድ ቢባል እኮ ትግራይ አትችለውም፡፡ እውነቱን እንነጋገር ካልን በትግራይ ሕዝብ ደምና አጥንት ከ46 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ሕወሓት በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ላይ የሠራው ግፍና በደል አንዲት ትግራይ ብቻ ሣትሆን መቶ ትግራዮችም ከፍለው አይጨርሱትም – ስማኝ ወንድሜ – ሰባራ ክላሽ የታጠቁ ሰባት ወጣቶች ብቻ አይደሉም ኢትዮጵያን ያፈራረሷትና ለዚህ መሳይ ውርደት የዳረጓት፡፡ ይሄ “ሕዝብን ከድርጅትና ከቡድን (ከሕወሓት) ለዩ” የሚባል የፖለቲካ ሎተሪ ማስተዛዘኛ ከእንግዲህ ብዙም አይጥመኝም፡፡ እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ማደርን የመሰለ ነገር የለም፡፡ በግርድፍ ግምት 95 በመቶ የሚደግፈውን ድርጅት አምስት በመቶውን ለማዳን ሲባል የሚደረግ ማንቆለጳጰስ እንድንደግፍ አታስገድዱን፡፡ እነዚህ ጉዶች ብዙውን ትግሬ በፕሮፓጋንዳና በታላቅነት ስሜት አንጀቱን በልተውታል፤ ሥነ ልቦናውን ሰርቀውታል፡፡ በተዘረፈ መሬት ሆዱን ሞልተው አሁን ባዶ ሲሆን አሳብደውታል፡፡ የሰው ወርቅ አያደምቅም ሞኜ፡፡ የሰው የሆነ ወደመጣበት ይመለሳል፡፡ ያኔ ታዲያ ያስተክዛል፡፡ ለዚህም እኮ ነው በትግራይ እንኳንስ የዱሮዋ ልሙጥ ባንዲራ የሰይጣን ዓርማ ያለበት ወያኔ ሠራሹ “የኢትዮጵያ ባንዲራ”ም የማይውለበለበለበለበው (ኤርምያስ ለገሠ ትዝ አለኝና ማውለብለብን መጻፍ አቃተኝ – እርሱ ደግሞ መናገር – ስቀልድ ነው)፡፡ ወያኔና ተጋሩ አንድ ባይሆኑ ኖሮማ ሕወሓት ከደደቢት ባልወጣ፡፡ አንዳንዴ ሰውን ያስፈግግልኛል ብለህ የምታወራው ቀልድ ገደቡን ያልፍና መሪር ሀዘን የሚፈጥር የጠነዛ ቀልድ ይሆናል፡፡ ደርግን ለመጣል የሞተው 60 እና 70 ሽህ ትግራዋይ በተባበሩት መንግሥታት የተመዘገቡ የሁለትና የሦስት ትናንሽ ሀገራትን ሕዝብ ሊሆን ይችላል፡፡ ….
ለማንኛውም ሒሣብ ማወራረድን በተመለከተ በነጌታቸው የሚወተወተው ጉዳይ በመስተዋት ቤት ውስጥ የሚኖር ድንጋይ ለመወርወር ቀዳሚ ሆኖ መገኘቱን ለሌሎች እንደመጠቆም ያህል የሚቆጠር ነው፡፡ ጌታቸው ረዳ አማራ መሆኑን ረስተን በተውሶም ቢሆን ትግሬ ሆኖ አማራን ለማጥፋት እንዲህ ከደነፋ አማራጩ ላለመጥፋት መዘጋጀት ብቻ ነው፡፡ አማራ ይህን ሒሣብ የማወራረድ ሕወሓታዊ የዘወትር መዝሙር ለመቋቋምና ኅልውናውን ለማስቀጠል ከዳር እዳር መነጋገርና መስዋዕትነትን ለመክፈል መዘጋጀት አለበት – ልክ እንደሰሞኑ፡፡ ብአዴንንም ሆነ ፌዴራል ተብዬውን ደግሞ ማመን የለበትም፡፡ የተለዬ ሥልት መቀየስ አለበት፡፡ “አለበለዚያ ውኃ ቢወቅጡ እምቦጭ” እንዲሉ ይሆንና ከችግሩ አዙሪት መቼም አይወጣም፡፡ ብአዴንና ኦህዲድ ከወያኔ ጽዋ የጠጡት ፀረ አማራና ፀረ ኢትዮጵያ መርዝ ስላለ በነዚህ ኃይሎች አማራው ለተወሰነ ጊዜ መቸገሩ አይቀርም፡፡ ግን የነዚህ ወገኖች ሤራ እየተነቃባቸው በመሆኑ ብዙም አይቀጥልም፡፡ ኅልውናውን የሚያስጠብቅ ኃይል ይመጣል፡፡ እንግዲህ በቁጥርም ሆነ በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ማን እንደሚበልጥ ለማየት ፉከራውን ጋብ አድርጎ ወደተግባር መግባት ነው፡፡ አንዳንዴ አፍ ፍርሀትን ለመሸፈን ይውላል፡፡ በነገራችን ላይ ከአማራው ጎን የሚሰለፉ ኃይሎች ከአጥፊዎቹ በእጅጉ ይበልጣሉ – የዘመናት መርዛማ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከሆኑት ከተጋሩና ከኦሮሞው ማኅበረሰብም ጭምር፡፡ የአማራው መጥፋት የነሱም መጥፋት መሆኑን የተረዱና ወደፊትም በስፋት የሚረዱ ወገኖች ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸው የኅልውና ጉዳይ በመሆኑ የሚጠበቅም የዘገዬም ነው፡፡
“እንደውነቱ ከሆነ እታች ሆኖ ለላይ ድንጋይ መወርወር ለላይኛው ማሳየት ነው” እንዲሉ ከ6 ሚሊዮን ሕዝብ የወጡ ቀን የከዳቸው ወያኔዎች 40 እና 50 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ላይ በበደል ላይ በደል ለመጨመር አሁንም ከተቁነጠነጡ የአባታቸውን የመለስ ዜናዊን ትዕቢታዊ ንግግር ተውሰን “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው” ከማለት ባለፈ የምንለው ሌላ ነገር የለም፡፡ አማራ ያን ሁሉ የዘመናት ግፍና በደል ዝም ብሎ ማለፉ ለዚህ ከሞቱም በኋላ ለሚያሳዩት ዕብሪትና ለሚያሰሙት የቀቢጸ ተስፋ ዲስኩር የልብ ልብ ሳይሰጣቸው አልቀረም፡፡ የአማራን ጩኸት ቀምተው ሒሣብ ማወራረዱን በነሱም ብሶ ከተናገሩት መልሱ ቀላል ነው፡፡ መከራ የመከረው አማራም መቼ ምን እንደሚደርግ ያውቃል፡፡
ወያኔ በለስ ቀንቶት የኢትዮጵያን መንግሥት ለብቻው በሚባል ደረጃ በተቆጣጠረባቸው 27 የግፍ አገዛዝ ዓመታት ውስጥ ብዙ በደሎችን ማድረሱ ገና የቅርብ ጊዜ ትውስታ በመሆኑ አንረሳውም፡፤ እዚህም አናነሳውም፡ በዚህ ቡድን የተነሣ ኢትዮጵያ በሞትና በሕይወት መካከል መገኘቷ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ሀገር በታኝ የጎሣ ፖለቲካ በህገ መንግሥት ቀርፀው ከማስቀመጣቸውም በተጨማሪ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንደሚባለው ለም መሬቶችንና የጨው ማምረቻ ሥፍራዎችን ከአማራውና ከአፋር ወደራሳቸው በማካተት ከ1983 ዓ.ም በፊት ያልነበረ የአስተዳደር ወሰን መሥርተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ወልቃይትንና ራያን ጨምሮ በርካታ የሌሎች ጠቅላይ ግዛቶችን መሬቶች ወደትግራይ ጨምረው ለትግራይ ሕዝብ በቀላሉ ሊድን የማይችል ብርቱ ራስ ምታት ሰጥተውታል፡፡ ብዙ ሞኝና ጉጉታም የትግራይ ዜጋም ወያኔ የሚለው ሁሉ እውነት እየመሰለው “ከወልቃይትና ራያ ውጪ ወደ ውጪ” በሚል ፈሊጥ እንደእሳት እራት እየዘለለ እቶን ውስጥ ለመግባት ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ይህን በሀሽሽና በከንቱ ፕሮፓጋንዳ ሰክሮ የሚተም ዜጋ አንድ ቦታ ማስቆም ያስፈልጋል፡፡ “አጋምን የተጠጋ ቁልቋል ዝንታለሙን ሲያለቅስ ይኖራል” የሚባለው ሃቅ ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ራሳቸው በምቾት እየኖሩ የኦሮሞን ሰፊ ሕዝብ ለጦርነት የሚቀሰቅሱ ፀጋየ አራርሳን የመሰሉ ደናቁርት የአጋንንት ውላጆች ከአውስትራሊያና ከአሜሪካ የሚነዙትን የጦርነት ዐዋጅም እየሰማን ነው፡፡ ፀጋየ የተባለው ስድ ራሱንና ቤተሰቡን በአውስትራሊያ አቀማጥሎ እያኖረ እዚህ ያለው ኦሮሞ ከሌላው ወገኑ በተለይም ከአማራው ጋር በሰላም እንዳይኖር የሚያውጠነጥነውን ሤራ ብትሰሙት የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ባለበት ሄዳችሁ ግደሉት ግደሉት የሚል መንፈስ ይጠናወታችኋል፡፡ እጅግ ሲበዛ ባለጌ ነው፡፡ አሁን ሲናገር እንደምሰማው ከሆነ ከሃምሳ ሽህ የሚበልጥ ጦር እንዳዘጋጁና አዲስ አበባንና ሸዋን በቅርቡ እንደሚቆጣጠሩ ለመሰል አሸባሪ ወገኖቹ በኩራት እያበሠረ ነው፡፡ የጦር ብዛት የልብን የሚያደርስ መስሎት ከሆነ ሕወሓትን ዘወር ብሎ ይጎብኝ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ደግሞ እንኳንስ ከፎከረ ከወረወረም ያድናልና አይዞን ጎበዝ!! መጪዎቹ ጥቂት ወራት የፈተና ናቸው፡፡ በርሱ የፀና ግን ምንም አይሆንም፡፡
ወንድሞቼ – እንደጥጋብ ያለ መጥፎ ጠላት የለም፡፡ ሕወሓትን እንዲህ ጉድ እየሠራው ያለው ጥጋብ ነው – ካለስንቅ የሚያዘምተውን የዱባን ዓይነት ጥጋብ፡፡ ድንገት ሳያስበው የሆነ ዕድል በሆነ ወቅት ከደደቢት አዲስ አበባ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከተተው፡፡ ትንሽ ሰው ጥጋብ አይችልምና ያን ዕድል በአግባቡ እንደመጠቀም ሀገርን ለማፍረስ አዋለው፡፡ ሌላው ሕዝብም በተለይ አማራ ያ ሁሉ ግፍና በደል እየደረሰበትም አፉን በመዳፉ ይዞ እየተገረመ 27 ሲደመር 3 ዓመታትን በስቃይና በመከራ አሳለፈ፡፡ ሕወሓት በክፉ ሥራው ምክንያት ከአራት ኪሎ ሲባረር መባረሩን ማመን አልቻለም፤ በፋሲካ እንደተቀጠረችው ገረድ ሁሌም አዛዥ ናዛዥና ሹዋሚ ሻሪ እንደሆነ የሚቀጥል መሰለውና ከንግሥናው መውረዱን ለማመን ተቸገረ፡፡ አምባገነኖች እንዲህ ናቸው – የሊቢያው ጋዳፊ ከተደበቀበት የቆሻሻ ቱቦ ውስጥ አውጥተው በእንትኑ ሣንጃ ሊቀበቅቡበት የቸኮሉ ወታደሮችን እንደቀድሞ ሥልጣን ላይ ያለ መስሎት ሊያዛቸው ይንጠራራ ነበር – መውረዱን ረስቶት፡፡ ወይ የጁንታዎች ድንቁርናና መመሳሰል!! ሕወሓት ቀን ሰጥቶት ወደሜዳው የገባችዋን ኳስ እንዳሻው ሲጠልዛት ከርሞ አሁን ወደሌላ ሜዳ ስትገባ ዐይኑን ማመን አቃተው፡፡ ሞቶም ሞቱን የማያምን ገልቱ እንደወያኔ አይቼ አላውቅም፡፡ አፋቸው ባለመሞቱ ብቻ በሚሉት እየተገረምን አለን፡፡
ወያኔ ያ ሁሉ የሰሞኑ ውርጅብኝ ደርሶበት እንኳን ከአራት ኪሎው የሥልጣን ማማ መውረዱን ሊያምን አልፈለገም፡፡ እንደዱሮው መሀል አዲስ አበባ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያለ ይመስለዋል፡፡ ቱባ ቱባ አለቆቹ ሞተውበት ወይም ታስረውበት እያዬ አሁንም 1980 እና 1990ዎቹ ውስጥ ያህል እንደሚገኝ ሳይሰማው አልቀረም፤ ድርጊቶቹም ሁሉ የዚያን ዘመን ሁኔታውን የሚያስታውሱ ናቸው፡፡ ምን ዓይነት መታወር ይሆን!
በዚህም ምክንያት ነው እንግዲህ በምልዓቱ የትግራይን አምስትና ስድስት ዕጥፍ የሚሆንን ሕዝብ “ሒሣብ ታወራርዳለህ” እያለ የሥነ ልቦና ጭቅቅቱን በቃላት ጋጋታ እየተወጣ የሚገኘው፡፡ መድኃኒት የለሽ በሽታ፡፡
ከእንግዲህ ሒሣብ ማወራረድ ካለ የሚያወራርደው ወያኔና ጃዝ ብለው የላኩት ወገኖች ናቸው፡፡ ይህም ወደፊት በቅርቡ እውን ይሆናል፡፡ ተኝቶ የቆዬ አበያ በሬ ሲነሳ አቀብ ቁልቁል የለም፤ ሁሉንም እርሻ ቁጭት በተሞላበት አዲስ ጉልበት ገማምሶ ነው የሚጥለው፡፡ የጌታቸው ምላስና የአቢይ ሀሰተኛ አንደበት ወደ ማኅደራቸው የሚሸጎቡበት ቀን እየገሠገሠ ነው – ወዳለንበት እየመጣ፡፡ ትግራይ ላይ በስምንት ወር ውስጥ ለተካሄደ የጥፋትና ውድመት ጦርነት የወጣን የ“አንድ መቶ ቢሊዮን” ብርና በአንድ ክረምት ተተከለ የተባለን የ“አምስት ቢሊዮን” ችግኝ የሒሣብ ስሌት የማያውቀው ይህ አሰለጥ ጠ/ሚኒስትር ይህን መሰሉን ቧልታዊ የሒሣብ ቀመር የሚያሰላስልነበትና እውነትን የሚረዳበት ዘመን ሩቅ አይደለም፡፡ የሚገርመው ደግሞ ይህን መሰሉን ነጭ ውሸት ተቀብሎ የሚያራግበው ‹ውታፍ ነቃይ› አበዛዝ ነው፡፡ “ኧረ ጌታዬ፣ አንድ መቶ ቢሊዮን እኮ ትልቅ ቁጥር ነው፤ ቀነስ ያድርጉት”፣ “ጌታዬ፣ አምስት ቢሊዮን ችግኝ እኮ በመላው ዓለምም በአምስት ዓመታት የማይተከል ትልቅ አኃዝ ነው” ብሎ የሚመክር አንድ እንኳ ጤናማ አማካሪ ይጥፋ? ምሁሩም ማይሙም፣ ጋዜጠኛውም አክቲቪስቱም … ምድረ ተደማሪ ተደጋፊ ዝም ብሎ ማጨብጨብ፡፡
እንግዲህ አፍ አይሞትምና የነጌታቸው ሒሣብ ውርጃ ማለቴ ማወራረድና የነፀጋዬ በሪሞት ኮንትሮል የሚካሄደው ስንተኛው ዙር እንደሆነ የማላውቀው ኦነጋዊ ጦርነት በጉጉት የሚጠበቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ የሒሣብ ውርርዱ አቶ/ኦቦ/አይተ ዳኛ ታሪክም በተጠንቀቅ መቆሙን ማስገንዘብ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ በአማራ ላይ ወጥመድ ያጠመድሽ ተንከሲስ ሁላ የተንኮልሽን የዞረ ድምር ውጤት በጠጋ ለመቀበል ተዘጋጅ፡፡ ታቃለህ – የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት ያልተወረወረባቸው ቀስት፣ ያልተተኮሰባቸው የጥይት አረር፣ ያልተረጨባቸው የፕሮፓጋንዳ መርዝ የለም፡፡ የዚህ ሁሉ ዘመቻ አለቆች ለግብጽና ስለግብጽ ምለው ተገዝተው የተነሱ ምዕራባውያንና አውሮፓውያን መሆናቸው በታሳቢነት ተይዞልኝ የመጨረሻው ጦርነት ሲጀመር ግን አሸናፊዎቹ ባለፉት 30 እና 50 ዓመታት ክፉኛ የተጎዱት ወገኖች ስለመሆናቸው ቅንጣትም እንዳትጠራጠሩ አደራ ማለትን እፈልጋለሁ፡፡ አሸናፊው እውነትን የያዘ ወገን ነው፤ አሸናፊው ፍትኅን ባለማዛባት ለሃቅ የቆመና ግፍና በደልን በትግስት ያስተናገደ ወገን ነው፡፡ በጎመን ጥጋብ ሆዱ የተንቆረዘዘው ሌላው እንደጉም ሲበን፣ እንደጤዛ ሲረግፍ ታያላችሁ፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ሆነው ሊያጨራርሱን የሚቋምጡ እነሕዝቅኤልንና ፀጋየን የመሰሉ መሠሪ የጠላት ወኪሎችም ከደገሱት የዕልቂት ድግስ ገፈቱን ቀማሾች ናቸው፡፡ መጪዋን ጨለማ የሚያልፋት ጥቂት ቢሆንም የኢትዮጵያን ሰቆቃ የፈጠሩና ያራዘሙ ግን አይሻገሯትም፡፡ ይህ ትንቢት ሣይሆን ከታሪክ መዛግብት ማንበብ የሚቻል የተራ ዕውቀት ውጤት ነው፡፡
አትዋል ይዋሉብህ አትምከር ይምከሩ፤
በቆፈሩት ጉድጓድ ሳይገቡም አይቀሩ፤ የሚባለው ለጨዋታ አይደለም፡፡ ገበሬው ዘወትር የሚያወሳው እውነት ነው፡፡
ፍቅር ያልገዛውን ምን እንደሚገዛው ግልጽ ነው፡፡ ደህና የተኛውን አንበሣ ቀስቅሳችሁ ዐውሬ አድርጋችሁታልና ከእንግዲህ ውርድ ከራስ፡፡ የሚያዋጣው ግን – ከሚጠበቀው የመጨረሻው መጨረሻ ጦርነት ወዲህ ትንሽም ብትሆን ጊዜ ካለችን ማለቴ ነው – የሚያዋጣው ግን ሰላምና ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ሁልጊዜ ጌትነት የለም፡፡ አእምሮን እንጠቀም፡፡
“የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ፤ ያውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ” እያሉ መፎከር ቀላል ነው፡፡ “ለጠላት ወገን ውኃ ሰጣችሁ፤ ምግብ አጎረሳችሁ” ብሎ ንጹሓን ዜጎችን በአደባባይ በሰይፍ እየቀሉ ልክ እንደወያኔዎች ሕዝብን ማስፈራራትም ቀላል ነው፡፡ ለጥፋት ተሰልፎ ውድመትንና ጸጸትን ማስከተልም በጣም ቀላል ነው፡፡ እውነተኛ ሰላምንና ፍቅርን ለማምጣት መጣር ግን ከሁሉም ዓይነት የወልና የተናጠል ኪሣራ ያድናልና በዚያ ላይ መበርታቱ ለጤናማ ዜጎች አዋጭ ነው፡፡ ተያይዞ ከመጥፋትና አንዱ የአንዱ የኅልውና ሥጋት ከመሆን ይልቅ ቆም ብሎ ማሰብ ጠቃሚ ነው፡፡ ወልቃይትና ራያ የመጨረሻዎቹ የሕይወት እስትንፋሶቻችን አይደሉም፡፡ እልህን ተወት ካላደረጉት ያሳብዳል፤ ያሳውራል፤ ያደነቁራል፡፡ ያልተከለከልከውን የገዛ ሀብትህን በግድ የኔ ነው ብለህ ጦር ስትማዘዝ የሚባክነው ጉልበትና የሚጠፋው የሰው ነፍስ ቀላል አይሆንም፡፡ የስሙኒ ዶሮ የአሥር ብር ገመድ ይዛ ከጠፋች ዶሮን ማሰሩ ምን ጥቅም አለው? አጉል እልህ ካልሆነ በስተቀር ወልቃይትና ራያ በደርጉና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዘመን በነበሩበት ግዛት እንዲካለሉ ተደርጎ ያኔ ትግሬና አማራ በፈለገው ግዛት ይኖር እንደነበር ሁሉ ዛሬስ እንደዚያ ማድረግ ምን ይከብዳል? ሚኔሶታ መሬት ገዝቶ፣ ቤት ሠርቶ፣ ሀብት አፍርቶ እንደማንኛውም አሜሪካዊ በነፃነት የሚኖረው ደቻሣ፣ ሆሮ ጉድሩና ቱሉቦሎ ላይ ከወንድሞቹ ጋር በድህነት ግን በፍቅር ተቆራምዶ የሚኖረውን ስንሻውን በነሁንዴሣና ጫልቱ አንገቱን ለማስቆረጥ ነጋ ጠባ የሚቀሰቅስበት ምክንያትስ ምን ይሆን? ምን ዓይነት የደም ጥማት እንበለው? ብዙዎቻችን የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ለምን እስከዚህን ደረጃ ወርደን አበድን? ጤናማ ካህን ባይኖረን፣ ደህና ኢማም እንዲኖረን ባንታደል … በየአካባቢያችን በሚገኙ ጠበሎች ተጠብለንና በየቤታችን በሚገኝ ሙስባሃ ተደባብሰን ጸሎታችንንና ዱኣችንን ወደ ፈጣሪ በማድረስ ከተደገሰልን ዕልቂት ለዘርም ቢሆን ለመትረፍ እስኪ የተቻለንን ሁሉ እንሞክር፡፡ ሰላም፡፡