እንዳንዘናጋ (ዘ-ጌርሣም)

እንጠብቅ በራችን
እንሙላ ውኃችን
የአባይን ተፋሰስ
ዙሪያውን በማሰስ
ኬላችን እንዝጋ
ጠላት የለም ብለን
በጊዜው ተታለን
አደጋን በማቅለል እንዳንዘናጋ
በህብረት እንመክት መጭውን አደጋ
የእባብ ጭንቅላቱ
መሬት ውስጥ መግባቱ
መርዙን እየተፋ
ባይታይ በይፋ
እንደገና አድብቶ
እኛን አዘናግቶ
ኃይሉን አጎልብቶ
በሌሎች ተረድቶ
ብቅ ማለቱ አይቀርም
ጊዜው ውሎ ቢያድርም
ሲመታ መልፈስፈስ
ሲተውት በመንከስ
ሲሽነፍ ሰላምን
ጊዜ አድብቶ ጠብን
ደጋግሞ አሳይቷል
ለአንዴም ዘንጋ ሳንል
ያለማወላወል
ይገባል መጠበቅ
ቀድመን በመጠንቀቅ
ሞቶ አገር ማዳንን ያውቃል ያገሬ ሰው
ወዳጅ ብቻ ሳይሆን ጠላት ምስክር ነው
እናስታውስ አድዋን
እናስታውስ ማይጨውን
እንዘክር ወልወልን
እናስብ መተማን
የቅርቡን ወረራ
ጀግኖች ያፈራውን በተራ በተራ
ምስክር ነውና ሐረር ካራማራ
የእንኛ መታወቂያ ዓለም ያደነቀው
የመጣውን ጠላት ድባቅ የመታነው
በመልክ ስብጥር
ጥርስና ከናፍር
እንደ ጠንካራ ቤት ጨፈቃና ማገር
ሆነን በመቆም ነው
ሀገር አስከብረን በጋራ የኖርነው
የመጣ ቢመጣ ከቶ እማንበገር
በአገራቸን ጉዳይ የማንደራደር
ስለሆን እኮ ነው
የደፈረን ሁሉ አጉራ ጠናኝ ያለው
እንኳንስ ዛሬና ጀግና ኃይል እያለን
የምድር የየብሱ መከላከያቸን
እራሱ እየሞተ እኛን ጠባቂያችን
ቀደምት ተመስክሯል ያባቶቻችን ጀብድ
በቁሙ ሲያዝሉት የጠላታችን ክንድ
የሉሄ እያሰኙ በፍርሃት ሲርድ
እያርበተበቱ አገር ለቆ እስኪሄድ
እኛም በድርሻችን ካለፈው ተምረን
በአንድ ላይ በመቆም ዘብ መሆን አለብን
አደጋን በማቅለል እንዳንዘናጋ
በህብረት እንመክት መጭውን አደጋ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያመኑት ፈረስ ከፈሩት ፈረስ - መስፍን አረጋ

1 Comment

  1. የህዳሴ ግድብ ተርባይን
    ተጋልጥዋል ለመደፈን
    ነበረ የእኛ ምኞት
    ተርባይኑ ውሀ እንዲገባበት
    የአማራ ደም ገብቶ ረግቶበት
    ግድቡ ተጋልጥዋል ለመኮላሸት
    ረግረግ ቆሻሻ ነው የገባበት
    በመጀመሪያው የውሀ ሙሌት
    የገደብነውን አንጀታችንን በማሰር
    በውሸት ማጣሪያ አደረጉብን የጅምላ መቃብር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share