የሂትለራዊያን ሴራ በኢትዮጵያ ሲገለጥ ንቃ ኢትዮጵያዊው ወገኔ – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

“The very first essential for success is a perpetually constant and regular employment of violence.”
“Kill, Destroy, Sack, Tell lie; how much you want after victory nobody asks why?

― Adolf Hitler

በአንድ ሉዐላዊ አገር  ውሥጥ  የሚኖር ዜጋ  ሁሉ፣ ዘረኝነት  ከፍጥረቱ  አጥፊ  መሆኑንን  ካልተገነዘበ  በሥተቀር  በቀላሉ  ሰው ሁሉ አንድ ፍጥረት መሆኑንን በካዱ ጥቂት  የተማሩ  ሆኖም ያበዱ  ግለሰቦች  በሥሜት እየተነዳ ፣  የራሱን  ቋንቋ ና ባህል  በማግዘፍ  የሌላውን  በማኮሰስ  ብቻ  ሳይሆን ፣ ሌላ ቋንቋ የሚናገረውን  እንደ  ሰው  ባለመቁጠር  ኢ- ሰብዓዊ  ድርጊት  ሊፈፅም  ይችላል ። እብድን  የሚከተል ሰው ሀሉ   ከእብድ የባሰ ነውና ። ይህንንም  እውነት  ዛሬ  በአገራችን  እየደረሰ  ባለው  የጭካኔ  በትር  ፣ ሞት ና መፈናቀል ፤ ሰቆቃና  ሥደት   ለመገንዘብ ችለናል።

ይህንን መቻሉን ደግሞ ይኸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ እያየነው ነው ። ይህ ፀሃፊ ሳይታክት ጎሠኝነት ፣ ቋንቀኝነት እና የፖለቲካ ኢሌቱ የፈጠረው ሰውን ከሰው የሚለይ ፣ የሚያጣላ ፣ የሚያጨራርሥ ሂትለራዊ የአንድ ዘር ብቻ ታላቅነት ማንገሥ ፣ አገራችንን ማውደሚያ አውዳሚ ቦንብ ነው በማለት ደጋግሞ በዚህ የድረ ገፅ ጋዜጣ መፃፉ ይታወቃል ።

እንደሌሎቹ ቅን ፀሐፍት ፀሐፊው ፣   የፃፈው እውነት ቢሆኑም ፣ ፅሑፉ  ሃሳብ  ብቻ  በመሆኑ  ሃሳቡን  የሚተገብር  የሥልጣን  ሃይል  ባለመኖሩ ፣  አገሪቱ ወያኔ ለ27 ዓመት ከሚመራበት የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካዊ መንገድ ዘሬም ” ሙሉ ለሙሉ  ባለመልቀቋ  ” ይኸው ያበዱ ዘረኞች ሌላው ዘር ከምድረ  ገፅ መጥፋት አለበት በማለት ቆርጠው በመነሳት ፣ እንሆ የዚችን አገር የዋህ ዜጎች የሚጠብቀን መንግሥት አለን በማለት በተዝናኖት በተኙበት እያረዷቸው ነው ። በዚህ ሤራ ሰበብም  በክልል የተከፋፋሉት ዜጎች ክልላዊ ጦርነት እንዲጀምሩ  እየገፋፉ ነው ።

ይህ ብቻም አይደለም ። አንደአንድ ሰውነታቸውን የዘነጉ እና በዘረኝነት ያበዱ ጥቂት  ሆዳም ዜጎቻችን ፣ በታላቅ ምሥጢር ከግብፅ የደህንነት ኃይሎች ገንዘብ በመቀበል ፣ በኢትዮጵያ ከጫፍ እሥከጨፋ ሁከት ፣ ያለመረጋጋት ና ሽብር እንዲፈጠር   ሌት ተቀን በህቡ እንደሚሰሩ ና እንደሚያሴሩ  ይታወቃል ። ልብ በሉ ትላንት ኤርትራ እንድትገነጠል ያደረጉት እነዚሁ ናቸው ። ለሆዳም ጀነራሎች  ሴት ና ሥጋ ብቻ ሳይሆን ረብጣ ዶላርም በማሥታቀፍ ነበር ፣ የኢትዮጵያን ጦር እጅ እና እግሩን አሥረው ለእርድ በማቅረብ ኤርትራን ያስገነጠለው  ።

የአገረ መንግስቱ ለልማት ሥራ መነቃቃት እጅግ ያስደነገጣቸው ፣  የኢትዮጵያ ብልፅግናን  ጭላንጭል በማየት ፣ጭላንጭሉ ፣ወደ ብርሃን እንዳይቀየር   ና አባይ ለልማት ሳይሆን ባለበት እንዲቆም ለማድረግ ለነውጥ ፣ ለሁከት ፣ ለሽብር ፣ ለግድያ ፣ወዘተ።  በቢሊዮን ብር  መድበው ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬም  እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይህ ፀሐፊ ያምናል ።

የአጣዬ ና የአካባቢው ዘግናኝ ሽብር ዓላማም ይኸው ነው ፡፡   በአብን ውሥጥ የተሰገሰገው ፀረ ኢትዮጵያ ሆዳም ኃይል ፣ ኢትዮጵያን ለማብነን የሚጥር መሆኑንንም በሰልፉ ላይ ያንፀባረቃቸው መፈክሮች ያሳበቃሉ  ። የአብን ፖርቲ  ትክክለኛ ሥሙም “አብን”  እንደሆነ በዚህ ዘረኝነትን በሚያረጋግጥ መፈክሩ ተረጋግጧል ። ኢትዮጵያዊነትን አብንኖ አማራ የሚባል አንድ ሉአላዊ አገር ለመመሥረት የሚፈልግ ቅዠታም ፖርቲ እንደሆነም ለኢትዮጵያኒዝም ኃይሎች ግልፅ ሆኗል ።

የኢትዮጵያኒስቶች ዓላማ ና ግብ ግልፅ ነው ።ዓላማና ግባቸው  ዜጎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል የሚዳኙበት ፤ በቋንቋቸው የማይበላለጡበት ፤ በማንኛውም ሥራ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተሰማርተው የሚሰሩበት ፤ ተፈጥሯዊ ና ሰብአዊ መብታቸው በእኩል ደረጃ የተረጋገጠበት  ፤ በፖለቲካ ፣ በማህበራዊ ፣እና በኢኮኖሚ ውድድሯች ያለአድሎ የሚሳተፉበት አገረ መንግሥት መገንባት ነው ። ይህንንም ዓላማቸውን ለማሳካት ይቻላቸው ዘንድ ፣ ሂትለራዊ አመለካከት ና አስተሳሰብ ያላቸው ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ገለል እንዲሉላቸው ይፈልጋሉ ።

እነዚህ ሂትለራዊ  ኃይሎች  ትላንት በኢህአዴግ ፣ ዛሬ ደግሞ   በብልፅግና ውሥጥ  አሉ  ። አገሪቱ በለውጥ ላይ እንደመሆኖ  የለውጡን  በጎ ሂደት በነውጥ  ለመቀየር የሚፍጨረጨሩ  የቀበሮ  ባህታዊያን  በብልፅግና ውሥጥ መኖራቸው የሚያሥገርም አይደለም ። እጅግ የሚያሥገርመው ትላንት ከኢህአዴግ ጋር አብረው ሲፈተፍቱ የነበሩ ና ጥቅማቸው በሠቋረጡ ከብልፅግና ጋር የተጣሉ ፣ ዛሬ በየሶሻል ሚዲያው  ሂትለራዊ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት አገር ወደማያባራ ጦርነት ውሥጥ እንድትገባ መጣራቸው ነው ።

አንዳንድ  ሂትለራዊ  ፀረ ኢትዮጵያ ተከፋይ  ዩቲዮበሮችም …( በነፃ የሚደሰኩር ዩቲዩበረኛ እንደሌለ ይታወቃል ። ) ዜጎች እያንዳንዷን የዓመቷን  365 ቀን  በሠላም እንዳይውሉና እንዳያድሩ ፣ በቀፋፊ ፕሮፖጋንዳቸው አማካይነት ከመጣራቸውም በላይ ፣  ለአንድ ቀን እንኳ  ኢትዮጵያ እንድትኖር የማያፈልጉ ፣ ከወዲሁ” ኢትዮጵያ ሞታለች።” ብለው የሚያውጁ እብዶች ናቸው  ።

የዋህ ጋዜጠኞችም ፣ አሪፍ የፖለቲካ ተንታኝነታቸው ባይካድም ፣ ሳያውቁት ሂትለር ሆነዋል ። “እንዴት ?” ቢባል  በውሥጣቸው የሚተራመሰውን  የግላቸውን “በቀል” አብይ አህመድ ” በእስታሌን በትር ” (በመንግሥቱ ኃይለማርያም በትር ፤ ልትሉትም ትችላላችሁ … ) እንዲበቀልላቸው የሚፈልጉ ሆነው በመገኘታቸው ነው ።

እነዚህ በበቀል ጥም  መቀወሳቸው የማይታወቃቸው ሂትለራዋ  ግለሰቦች  “አብይ አህመድ  ሱሪ  በአንገት አውልቅ ።” በማለት ፈፅሞ  የማይሆን ና ለዲርጊት የሚከብድ ምክር  ሲለግሱም  ይደመጣሉ ።   አንዳንድ የፖለቲካ  ነብይ  ወይም ሰባኪ ወይም ቄስ ነን ባይ  ዩቲውበሮችም ፣  እኛ አሜሪካ ሥላለን ወላፈኑ አያገኘንም በማለት በእሳት ላይ ቤንዚል ሲያርከፈክፉ ይሥተዋላሉ።

በጣም እጅግ በጣም  መሰሪ የሆኑት ሂትለሮችም   ፣ ከምንም ነገር እንደሌሉበት ሁሉ ፣  እንደጲላጦስ ” ከደሙ ንፁህ  ነን ።  ” በማለት በውሥኪ እጃቸውን እየተለቃለቁ ፣ ” የገሃዱን  ዓለም ሆረር ፊልም ፤ ”  በአምሥት ኮኮብ  ሆቴል ቁጭ ብለው ያያሉ ። በህቡ  የሚመሩት  ሂትለራዊ  ጦርነት  በወከሉት  ነፍሰ ገዳይ  አማካኝነት ፣  ግብ  እሥኪመታ  የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ  ሆቴላቸው ውሥጥ  በተዝናኖት ይቀመጣሉ ።

ከሁሉ የሚያሥከፋው ደግሞ ፣ ሂትለራዊ አሥተሳሰብ ያላቸው አንዳንድ የደህንነት አባላትም ደብል ኤጀንት በመሆን ኢትዮጵያን ለማጥፋት መተባበራቸው ነው ።እነሱ ብቻ አይደሉም በህግ አሥፈፃሚው ውስጥ ያሉ ቁልፍ ሰዎች የሂትለር ዴሉዢን ያጠቃቸው ከሆኑ አገር መፍረሱ አይቀርም ። ገንዘብ ሲናገር ህግ ዝም ፣ ጪጭ ይላልና  !!

አገሬ በእነዚህ ሁሉ   ህሊና ቢስ ሂትለራዊያን   እየተተራመሰች ጉልበቷ ዝሎ ተልፈሥፍሳ እንድትወድቅ እየተሴረባት ነው ።  ከብልፅግና መንገዶም እንድታፈገፍግ    በሂትለራዊ  ዘረኝነት  መንፈስ  በሰላማዊ ሰልፍ ሥም  ለእርስ በእርስ ጦርነት እንድተመቻች እያደረጉ ነው ፡  ።

ሂትለርን ፣ በዘረኝነቱ  የዛ ትውልድ  ጀርመኖች በአደባባይ ደግፈውታል ። ጀርመኖቹ    ” ልክ ነህ  ሂትለራችን እንዳልከው ፣  እኛ ምርጥ ዘር ነን ።አለምን መግዛት አለብን ።እነዚህን መተተኛና ሰው በላ የሆኑትን ይሁዲዎችን ማጥፋት ና የቀረውን የዓለም ህዝብ ማሥገበር  ይኖርብናል ፤ አለብንም ። ”  በሚል የዘረኞች የልብ እብጠት  የሂትለርን ፖርቲ ፣ እኩይ ዓላማ  ደግፎ  በአደባባይ የወጣው ህዝብ ፣ ለ 11 ሚሊዮን በአሰቃቂ ሁኔታ ማለቅ   (5 ሚሊዮኑ ይሁዳዊያን ናቸው ፡፡ ) አይነተኛ ድግፍ አድርጓል ።

የሂትለር ጭካኔና ግፍ ፣ የወቅቱን ትውልድ ተጠያቂ ያደረገ   የትላንት አስቀያሚ ታሪክ  መሆኑ ይታወቃል ።  ደግሞም በአንድ አጋጣሚ ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠር ወጣትን በፍላሎቱ ተጠቅመህ ለሂትለራዊ እኩይ ዓላማህ ከጎንህ ልታሰልፈው ትችላለህ ። ገንዘቡ ካለህ ፣ የማደራጀት ልቅ ፈቃድ ከተሰጠህ በቀላሉ ወጣቱን የከንቱ ዓላማህ ነዳጅ ልታደርገው ትችላለህ ።

ወጣትን ሥሜት ሊነዳው እንደሚችል የታወቀ ነው ። መንጌ በ11 ኛው ሰዓት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሥቲ ወጣትን ወደ ብላቴ የጦር ማሠልጠኛ ጣብያ እንዲከት ያደረገው  ፣ ማንም በሚያውቀው ወኔ ቀስቃሽ  ንግግሩ ነበር ፡፡ ” ኢትዮጵያ ልትሞት ነውና ድረሱላት። ” በማለት በአገር ወዳድነት በጋለ   ንግግሩ እንደሆነ  አሥታውሱ ።

የሰሞኑንን በሰልፍ ሥም በተቃውሞ ሥም በአማራ ክልል በተለይም በባህር ዳር እየተደረገ ያለው ሴራ የውጪ ጠላቶቻችን እጅ ያለበት መሆኑን መጠርጠር አስፈላጊ ነው ፡፡ በመንጌ ቅስቀሳም እንዘምታለን ብለው በወኔ ከተነሱትም ወጣቶች ጋራ ድርጊታቸውን ሥናነፃጽር ድርጌታቸው የወራዳ ተግባር ነው ፡፡ድርጊቱን  ከእነዚህ ቆረጥ የኢትዮጵያ ልጆች ወኔ ጋር ማሥተያየት ከቶም አልሻም ። ዛሬ እኮ ጥቂት የማይባለው ወጣት ከወሬ የዘለለ አገር ወዳድነት  የለውም ። ሽለላውን ፉከረውን በመድረክ ለማሰማት አንደኘ ነው ፣ ና ጠመንጃ ያዝና አገርን ከጠላት ተከላከል ብትለው ግን ወገቤን ይልሃል ። ቅሌን ፣ ጨርቄን ፣ ማቄን ፣ ይልሃል ።

በጣም የሚገርመኝ ደግሞ ፣ የዛሬው ጥቂት ወጣት ተሳዳቢነቱ  ነው ። ብልግናው ።   95 ፐርሰንቱን  የኢትዮጵያን ወጣት የማይወክል ቢሆንም ፣ ዕድሜ ለአብን ይህ ወጣት በዘረኝነት ህሊናው መበረዙ  እጅግ ያሳዝናል ።

ለአለፉት 3 ኣመታት ፣ ሰውነትን በዚች አገር እናንግሥ ። ዘረኝነት ፣ ቋንቋ አምላኪነት ፤ ተረኝነት ፤ የእነሱ እና የእኛ ማለትን አስወግደን ሥልጡኑን  የዓለም ፖለቲካ እንከተል ።  ተብሏል ፡፡ምን ያልተባለ በጎ ነገር አለ ?

  • የእኛ አገር የመንግሥት ማዋቅር ፣ ወይም አገረ መንግሥቱ የቆመበት ምሰሶ ሰውን አግላይ እንጂ አቃፊ አይደለም ። ዜጎች በአገራቸው ግዛት እንደልባቸው እየተዘዋወሩ በየመግሥት መሥሪያ ቤቱ ተቀጥረውም ሆነ ፣ በግላቸው ለመሥራት ከቶም አይችልም ። ምክንያቱም የቋንቋ አጥሩ ይከለክላቸዋል ።
  • ይህ በቋንቋ አጥር የተዋቀረ አገረ መንግሥት ፣ ከዓለም ህዝብ ቅቡልነት ያለው አኗኗር  ጋር የሚያጋጭ ነው ። የእውቀት ሽግግርን የሚገድብ ከመሆኑም በላይ ፣ ከፖለቲካ ፖርቲ  ጋር ያልተዛመደ  የየክልል  መንግሥትን  በማዋቀር እውነተኛ ና ሥልጡን የፊደራል ሥርዓትን የማያነበር መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል ።
  • ዛሬ በአገረ  መንግሥቱ  በእያንዳንዱ  ከተማ ና ገጠር የሚኖሩ ውህዳን ፣ በየክልሉ ምክር ቤት ውክልና የላቸውም ። የቋንቋ ክልላዊ መንግሥቱ ዘግቶ ለመብላት በወያኔ የተቋቋመ በመሆኑ ፣ ከወያኔ ውድቀት በኋላም ይህ የዘረኛ ሥርዓት ተሥማምቷቸዋል ።
  • ይህ በቋንቋ አማካኝተው ጥቂቶች ዘወትር ብፊ የሚበሉበት ፣ ዘወትር ቮድካ የሚጠጡበት ና በተቀናጣ ኑሮ  የሚምነሸነሹበት እና የቀኃሥን ታሪክ ለመድገም ባለሥልጣናቱ የሚቀዠቀዡበት ሥርዓት  ፣  ፈፅሞ ከዓለም የፖለቲካ መንገድም ሆነ ዓለም ካሏት  አማራጭ ርእዮተ ዓለም ጋር የማይመሣሠል እንደሆነ ለዶ/ር አብይ የተሰወረ አይደለም ።ይሁን እንጂ ለሁሉም በተሰጠው ይቅርታ ሁሉም ንሥሐ  በመግባት ራሱን ይቀይራል ብሎ ህዝብ ተስፋ አድርጎ ነበር ።…  በማለት የተለያየ ሃሳብን ብዙዎች በተለያየ አገላለፅ እውነቱን አቅርበዋል ፡፡

በነገራችን ላይ ፣  በይቅርታ በደላቸውና ግፋቸው በለውጡ መንግስት ሥርየት የተሰጣቸው ፣ የመንግሥት ዓባላት ብቻ አልነበሩም ። በኤርትራ በረሃ ያሉት መንግሥትን በጠመንጃ አፈሙዝ ከሥልጣን ለማውረድ የሚታገሉ እና በዘር ፖለቲካ እንደ ህውሃት ሥሙን ያለቀየረው ኦነግም ጭምር ነበር ። ያን ጊዜ በምክር ቤት ዓባል  ” እንዴት ለአሸባሪ ቡድን ይቅርታ ይደረጋል ? ”  በማለት አንድ የምክር ቤት አባል ሲጠይቁ “አሸባሪ እኛ ነበርን ። ” በማለት በሥርዓቱ ውሥጥ መንግሥታዊ አሸባሪነት እንደነበረ የለውጡ መሪ  መሥክረው ፣ በይቅርታ ለመሻገር እንጂ በበቀል ዜጎችን ለማሰቃየት ና በእሥር  ለማንገላታት እንደማይሹ ተናግረው እንደነበር እናሥታውሳለን ። ይህ ቅን የይቅርታ መንገድ  ግን ብዙም እርቀት አሻጋሪውን መሪ እንዳለስጓዛቸው አይተናል ። ጥቂቶች ሁሉም ዜጋ ሰው እና ከእነሱ እኩል እንደሆነ ለመቀበል የማይፈልጉ  ሂትለራዊ አመለካከትና አሥተሳሰብ ያሳበዳቸው ግለሰቦች ፤ በውጪ ጠላቶቻችን እና የኢትዮጵያ ወርቅ ባስጎመጃቸው ወርቅ ምራብውንና

አሜሪካውያን ቱጃሮች  ገንዘብ ፤ በጥቂት ጊዜ ውሥጥ አፈርጥመው አብይ አህመድ ምኒልክ ነው ። ነፍጠኛ ነው ። እኛን አይወክልም ። “ማለት ጀመሩ ።

ራሥ ጎበና በሚኒልክ ዘመነ መንግስት ፣ ከኦሮሞ ተከታዮቻቸው ጋር የገነቧትን ታላቋን ኢትዮጵያ በመካድ እና ውህዱን የየከተማውን ህዝብ  ከምድረ ገፅ አጥፍተን ፣ ኦሮሚያ የምትባል አገር እንመሰርት ፤ ተነሱ ። ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ያገባችሁም  ፍቱ ና ከቋንቋችሁ ጋር ተጋቡ ፡፡ በማለት  ሂትለራዊ  ቅሥቀሳቸውን ተያያዙት ። ቢጨረሻም ሃጫሉን ገደሉ ። መጨረሻቸውም   እሥር ቤት ሆኖ አረፈው ። ዛሬም በሰው እኩልነት የማያምኑ ጥቂት እብድ የቋንቋ አምላኪዎች በሁሉም ክልሎች ውሥጥ አሉ ። እነዚህ ሰውነታቸውን የካዱ ፣ በሂትለራዊ  እብደት  ህሊናቸው የተሞላ አገር ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች ዛሬ የሚፈጠረው ሁከት ፣ ትርምሥ ፣ መፈናቀል ፣ ሞትና ሥደት ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አያገናዝቡም  ። እነሱ የሚታያቸው የማያቋርጠው የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍርፋሪ  ና የድሎት ኑሯቸው ነው ። እናም ዛሬም  የሚሰጧቸውን ፍርፋሪ እያለመጡ አገርን ወደእርሰ በእርስ ጦርነት ለመውሰድ ሌት ተቀን እያሴሩና እየሰሩ ነው ።

ትህነግ  አይነኬ  የሰሜን ዕዙን መከላከያ   በተለመደው ሽፍታነቱ  በመተንኮሱ ና ለማዋረድ በመሞከሩ  ፣ በመከላከያ ሰይፍ መቆረጡን እንኳን ቆም ብለው በማሰብ ወደ ሰውነት ቀልብ አልተመለሱም ። ዛሬም በማጀራቱ በኩል  መንግሥትን ለማረድ እያሤሩ ነው  ።

የመንግሥት ጀርባ ጠባቂ ህዝብ  ነው ። የለውጡን  ኃይል  አሻጋሪውን መንግሥት ከበሥተኋለው እንዳያርዱት መጠበቅ ያለበት የኢትዮጵያ ህዝብ  ነው ። የሱዳን ወይም የግብፅ ህዝብ አይደለም ። ይህንን እውነት ህዝቡ በቅጡ ያውቅ ዘንድ መገናኛ ብዙሃን የጎላ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት የማያሥተዳድራቸው የቴሌቪዢን ጣብያዎች የባላገሩ ቴሌቪዥን ፣የአርት ቴሌቪዥን የናሁን ወይንም  የአሃዱን  ፣ …ግማሽ ያህል እንኳን፣ ህዝብን የማንቃት ሚና ለመጫወት አልቻሉም ፡፡ በእኔ ግምገማ ፡፡ይህንን ለማረጋገጥ የሚስተላልፉትን የፕሮግራም ይዘትና ያላቸውን ታዳሚ ማስተያየት በቂ ይመስለኛል ፡፡

በኢትዮጵያ  ከተሞች  የሚሥተዋለውን  ዋልጌነት ፣ በጫት ና በሺሻ መጀዘብ  ቢያንስ  ለመቀነስ ፣ የበኩሉን አሥተዋፆ  የሚያደርግ አንድ የመልካም ዜጋ  ማፍርያ መንገድ ቴሌቪዢን ነው  ። ወጣቶቻችን ወደ  አክሳሪ  ሱስ  እንዳይገቡ  የሚያደርግ ፣ ሥራን ሳይንቁ  በመሥራት ራሥን  ለመቻልና ለሌሎች ሰዎችም  የሥራ ዕድል  መፍጠር  እንደሚቻል   በተግባር  የሚያሳይ ፕሮግራም  ከገሃዱ  ዓለም  ሰው ህይወት ጨልፈው ለማሳየት  ሚዲያዎቹ ሊገነዘቡ ይገባል ። በትይዩነት ፣ የጫት ቃሚ ወጣት መጨረሻ  እና  የመልካም  ምግባር  ወጣትን  መጨረሻ  በመዳሰስ  በንፅፅሩ  ወጣቱ  እንዲማር  ቢሰራ መልካም ነው ።

ዛሬ፣ዛሬ ከንቃተ ህሊና ዝቅተኝነት አንጻር ፣ በሱስ ና በስንፍና ተተብትበው ፣ ጥቂት የማይባሉ የከተማ ወጣቶች በጥራቃ ሆነዋል ። እንደ ተከፈተ ሬዲዮ ያለፋታ  ይናገራሉ እንጂ አያዳምጡም ። የንግግር ወጡ ማዳመጥ እንደሆነ እንኳን አይገነዘቡም ። ዝም ብለው ደረቅ እንጀራ ቢጎዘጉዙት ምን ይጠቀማል ?  እነዚህ በቀቀኖች ናቸው የሂትለራዊ ዓላማ ደጋፊዎች ፡፡

ዛሬ ፣  እነዚህ ጥቂት ወጣቶች ፣  በበቀቀናዊ ህሊና እየተመሩ  የትላንት  አባቶቻችንን ኢትዮጵያዊነት በመካድ ፣ ለጠላቶቻችን ሴራ ተመቻምቸው   በሰላማዊ  ሠልፉ  ውስጥ ተቀላቅለው ግጭት ፣ ሁከትና ትርምስ  ፤ ያለመረጋጋት እና ሞት እነዲከሰት ፤ እነ ግብፅ  በገንዘብ  ያቀናበሩትን አገር የማፈራረስ  ሴራ  እንዲተገበር ሲጥሩ አስተውለናል ። በቀጥታ ሰውን በግፍ የገደሉና ያሥገደሉ ፤ የአቀዱ ና በፋይናንስ  እና በሎጀስቲክ  የደገፉ ፤ ለፍርድ እንዲቀርቡ ከመጠየቅ  ባሻገር ፤ አገረ መንግሥቱን የሚመራውን በቅን ልቡና እና በእውነት እየሰራ ያለውን መንግስት ማጣጣል ፤ በእውነቱ በህዝብ ውስጥ ውዥንብር መፍጠርን ነው የመረጡት ፡፡ በውዥብሩም ሳብያ ፣ በአገሪቱ ውስጥ ግጭት ተፈጥሮ   የአባይን ግድብ  የውሃ  ሙሌት በታቀደለት ቀን መሰረት እንዳይከናወን ማድረግ ነው ዋናው ዓላማቸው  ። ይህ ፍፁም ሂትለራዊ መንገድ ነው ፡፡ ሂትለራዊ መንገዱንም ያመቻመቹት ኢትዮጵያን ለመበዝበዝ አፋቸውን ከፍተው ሊውጡን ያሰፈሰፉ ሂትለሮች ናቸው ፡፡ የሰው ዘር ሁሉ በእኩልነት እንዲኖር የማይፈልጉ ፣ ሁሌም እነሱና የእነሱ ዘር ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆን ፣ ሌላው ሰው ተመፅዋችና ለማኝ ሆኖ በመኖር ህይወቱን እንዲገፋ  የሚጥሩ ግለሰቦች ሁሉ የትም ይኑሩ የትም የለየላቸው ሂትለሮች እነደሆኑ መታወቅ አለበት ፡፡ … የኢትዮጵያን ህልውና ለመደምሰስ የሚጥሩ ኃይሎች የሂትለር ዕብደት የተጠናወታቸው ናቸው ፡፡ እነዚህ ዕብዶች በውስጣችን ያሉ ና  በውጪ አገር የሚኖሩ ናቸው ፡፡  ኢትዮጵያዊያን ይህንን እውነት ለመገንዘብ ቆም ብለን እናንስብ ፡፡ ከመንጋ ህሳቤ እንውጣ ፡፡ በእብዶች ጭንቅላት ከምንመራ የራሳችን ጭንቅላት እንዲያስብና እንዲያሰለስል ብንፈቅድለት መልካም ነው  ፡፡

 

2 Comments

  1. cadre mekonnen: The whole garbage you scribbled is exactly like what I used to hear from cadres of Mengistu, Meles and the traitor ahmed. If you can lend me your ears, stop wasting your time here. This is the place for adults who have critical thinking skills-not for cadres.

  2. መኮንን ሻውል፣. በጥቅስ ያስቀመተጥከው የሂትለር ነው የምትለው የአሁኑ አብይ መግለጫ ነው። ህዝቡ የአጭር ጊዜ ማስታወሻ ስብእና ነው ያለው. እያለ ደጋግሞ ነግሮናል። ከሂትለሩ ሰበካ ጋር ልዩነቱ ምንድነው። ለመግደሉም አብይ እያስጨፈጨፈ ነው።
    በእርግጥም ለአብን ያለህ ጥላቻ ይገባኛል። እንዳልከው “አብን” ነው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.