ደጉ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያ ከጠላቶችዋ ጥቃት ሲዘነበርባት ከሌላው ሕዝብ ጋር ተባብሮ የተከላከለ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ አጼ ዮሃንስን ተከትሎ ደርቡሽን መልሷል, በራስ አሉላ አባነጋ እየተመራም ኢጣልያን ተፋልሟል። ፋሺስቶችን ከተፋለሙት አርበኞች መካለል እነ ደጃዝማች ገብረሕይወት መሸሻ፣ ደጃዝማች አባይ ካህሳይ፣ ደጃዝማች ተስፋይ መደባይ፣ ፊታውራሪ ተሰማ ተስፋይ፣ ደጃዝማች ግዛው፣ ደጃዝማች ተፈሪ፣ አጋፋሪ ብሩ፣ ካሳ ስብሃት፣ ቀኛዝማች አበራ አዳሌ፣ ከሴቶችም እነ ከበደች ስዩምና ወይዘሮ ደስታ ገብረ ሚካኤል ምንጊዜም ታሪክ ያስታውሳቸዋል። ትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶና የእስልምና እምነት ተከታዮችን አጣምራ የያዘች የርህሩህና ተዋዶ የሚኖር ሕዝብ መሬት ነች። እጅግ የሚያሳዝነው እነዛ አርበኞችን ያፈራች ምድር ባንዳዎችንም ወለደች። የባንዳዎች ልጆች ጊዜ ጠበቀው ኢትዮጵያን ተበቀሉ።
ደጉ የትግራይ ሕዝብ ከገዛ አብራኩ በወጡት እነ ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ ስዩም መስፍን፣ በመሳሰሉ ድቅድቅ ጨለማዎች እጅግ ለከፋ ጥቃት ተዳረገ። ትህነጎች የትግራይን ሕዝብ – ወርቅ ሕዝብ፣ ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ፣ ወዘተ፣ እያሉ እየደለሉ ለእሳት ማግደውት ወደ ሲዖል ሄዱ።
በሻዕቢያ እርዳታ ቁምጣ ለብሰው በደርግ የውስጥ ችግር መዳከም ምክንያት አዲስ አበባ ሰተት ብለው የገቡት እነ መለስ – በብዙ ሺህ የሚቆጠር የትግራይ ልጆችን ለጥይት አረርና ፈንጂ፣ ለታንክና መድፍ፣ ለጦር ጄቶችና ሄሎኮፕተሮች ጥቃት ሰለባ አድርገዋቸዋል። አንዳች መልካምነት እውስጣቸው ያላደረው የዲያብሎስ ስብስቦች ይህን ሁሉ ያደረጉት ወርቅ ለማካበት፣ ኤፈርትን አቋቁሞ ለመዝረፍ፣ ሜቴክ የተባለውን ድርጅት ፈጥሮ ቅሚያንና ዘረፋን ለማካሄድ ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የትህነግን ማንነትን እንዲረዳና የትግራይ ሕዝብ ለነዚህ መሠሪዎች ድጋፉን እንዲያቆም የወተወቱት አቶ ገብረመድህን አርዓያና አቶ አብርሃም ያየህ እጅግ ቅን አስተዋዮች ናቸው። እነዚህ ሰዎች እጃቸውን ከደሙ ንጹህ አድርገው የታጠቡት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን የሶስት አስርት ዓመታት ስቃይና ዛሬ በትግራይ ሕዝብ ላይ የተከሰተውን አሳዛኝ ሁኔታ ገና ድሮ በብሩህ ዓዕምሯቸው ተገንዝበው ነበር። እነ ስብሃት ሲያሾፉ፣ እነ መለስ ሲፈላሰፉ፣ እነ ስዩም ሲንደላቀቁ፣ እነ አባይ ጸሃዬ ገንዘብ ሲንተራሱ –አቶ ገብረመድህንና አቶ አብርሃም ስደት ላይ ናቸው። ወያኔ እራሷ በቆፈረችው ጉድጓድ ስትቀበር ግን አቶ ገብረመድህንና አቶ አብህራም በሕይወት አሉ። እንኳን እነዚህ አስተዋዮች ይቅርና የትህነግን መሠሪነት ገና ከጠዋቱ ተረድተው ሲፋለሟቸው የነበሩት ኮሎኔል መንግሥስቱ ኃይለማርያም በህይወት አሉ። የእግዚአብሄር ፍርድና ሚዛን እኛ እንደምናስበው አይደለም።
ሶስቱ ሙስኬቶች፣ ሶስቱ የማይለያዩት – የ 1844 ዓም ተውኔት ነው። ተውኔቱ በፈረንሳይ ፖለቲካ ጉዳዮች ተሳታፊ የሆኑ የሶስት ሰዎች ገጸ ባህርያትን ያሳያል። እኔ ሶስቱ ሙስኬቶች ያልኳቸው በትህነግ ፖለቲካ ጉዳይ ወሳኝ ቦታ የነበሩትን – አቶ ስዬ፣ አቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ፣ ዶክተር ቴዎድሮስን ነው። እነ አቶ ስዬን ከሶስቱ ሙስኬቶች የሚለያቸው ግን እነዛ ገጸ ባህርያት ናቸው እነዚህ ደግሞ በኅልውና፣ እነዛ አገራቸው ነበሩ እነዚህ ደሞ ሩቅ በስደት። እነ ስዬ ፈረንጅ አገር ሆነው ጓደኞቻቸው ሲሸሹ፣ ሲራወጡ፣ ሲያዙ – በቴሌቪዥን ተመለከቱ። በእርግጥ ዝም አላሉም – ሠርገኛ መጣ ሆነባቸው እንጂ –የቀጠሯቸውን ሎቢይስቶች ጠርተው ቶሎ ቶሎ እንዲጽፉ አዘዙ፣ ጦር አለን ብለው ፎከሩ። ያች በንዋይ ክምር ዙርያ ለም መስላ የምትታየው ደረቅ ቅጠል ወደ ትቢያ ተቀየረች፣ ሊይዟት ቢሞክሩ አልጨበጥ አለቻቸው። ትህነግ መነሻም መድረሻም የሌላት ለተውኔት እንኳን የማትመች የሠይጣን ድምጽ ነች። በክፋት የተጸነሰችዋ ትህነግ ፍጻሜዋ የሕዝብ መከራ ሆነ።
ጦርነት አስከፊ ነው። ለዝርፊያና ቅሚያ የሚደረግ ጦርነት ባህል አይሆንም። እናት አገርን ከጠላት መከላከል ነው ባህል። ቀማኛ ጥይት ሳይተኮስ ነው ብሩን ሰብስቦ የሚሮጠው። መድፍ ዒላማውን ሊያደበይ ሲወረወር የገንዘብ ክምር መከታ አይሆንም፣ ጄት በሠማይ ሲያጓራ ምሽግም ባዳ ነው። “ጦርነቱ ከተጀመረ ጉድ ይታያል” ብለው አሜሪካ የገቡት አቶ ስዬ ዛሬ ምን ይሰማቸው ይሆን? ዶክተር ቴዎድሮስስ ቢሆን – “በሃገሬ በትግራይ ያለው ነገር አሳዘነኝ” ብለው ለፈረንጆቹ አቤቱታ ሲያቀርቡ የመከላከያ አባላቱን ጨፍጭፈው ጦርነቱን የጀመሩት ጓደኞቻቸው መሆናቸውን ለምን ደበቁ? ምን ያደርጋል መቅለስለሱ። አስቀድሞ አልነበረም እንዴ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስቱን ጥዶ ማልቀስ። ህወሃት አስልታ ጦርነት ስትጀምር የአማራው ልዩ ኃይል ከእርሷ የባሰ ቆቅ መሆኑን እንደምን ዘነጋች? የስድስት ዓመቷ ሕጻን ቤተልሄም እናቷን ማጣቷ ሳያንሳት ሁለቱ እግሮቿ ተቆርጠው ወንበር ላይ ተቀምጣ – የፍቅር አይኖቿ ወድያና ወዲህ ሲንከራተቱ ከማየት የባሰ ሌላ ምን የሚያሳዝን አለ?
ለሶስቱ ሙስኬቶች – እነ አቶ ስዬ ሌላ ሶስት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላቅርብ። አንደኛ – የትግራይ ሕዝብ ወንድሙ ከሆነው የአማራ ሕዝብ ተናክሶ ኢትዮጵያ ዛሬ ለተዘፈቀችበት አሳዛኝ ሁኔታ መድረሷን ስታዩ በትዝታ ተመልሳችሁ – ያን ኢትዮጵያን ለመበተን የተደረገውን ክፉ የደደቢት ጉባዔ ትረግሙት ይሆን? ሁለተኛ – በባንዳ ልጆች የምትመራዋ፣ የግብጽ ሎሌዋ ትህነግ ዓላማዋ ቅሚያ፣ ስርቆት በተጓዳኝ ኢትዮጵያን ለሚያመሰቃቅለው ኦነግ ጥርጊያ መንገድ ማመቻቸት መሆኑን ተገንዝባችሁ ነበር? ሶስተኛ –ኢትዮጵያ በናንተ ምክንያት የዋይታ ምድር፣ የደም መሬት ሆና ስታዩዋት – እውን በሕይወት አለን ትላላችሁ?
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ሚክያስ