የከሸፈ ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት – ኢ.ሀ.ሥ.አ.

ዜመ_ኢ-1_20130428_ዐማርኛ
ዜና ፡ መግለጫ ።
ለንደን ፥ ታኅሣሥ ፡ 28 ፡ ቀን ፥ 2013 ፡ ዓ.ም. ።
ካፈጣጠሩ ፡ ሀገር ፡ ኢትዮጵያን ፡ የከዳው ፡ የውንብድና ፡ እና ፡ የጥፋት ፡ ኀይል ፡ ሕ.ወ.ሐ.ት. (ሕዝባዊ ፡ ወያኔ ፡ ሐርነት ፡ ትግራይ) ፥ ጥቅምት ፡ 24 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፥ ጨለማን ፡ ተገን ፡ በማድረግ ፥ በሰሜን ፡ ጐንደር ፣ በመላ፟ ፡ ትግራይ ፡ እና ፡ በሰሜን ፡ ወሎ፟ ፡ ክፍላተ ፡ ሀገር ፡ የሰፈረውን ፥ የኢትዮጵያ ፡ ክንድ ፡ የኾነውን ፡ ሀገራዊ ፡ ጦር ፡ ሰራዊት ፥ እንዲሁም ፡ ያካባቢውን ፡ ሰላማውያን ፡ ኗሪዎች ፡ በቀቢጸ ፡ ተስፋና ፡ የሕይወትን ፡ ቅድስና ፡ በካደ ፡ በተለየ ፡ አረመኔነት ፡ ጨፍጭፏል ። ይህ ፡ የወንጀለኞች ፡ ድርጅት ፥ ዅሉም ፡ በዅሉ ፡ በሺሕ ፡ የሚቈጠሩ ፡ ሀገራውያንን ⁽1⁾ ፡ ገድሏል ፥ ዐያሌ ፡ ንብረትንና ፡ መሠረተ ፡ ልማትን ፡ አውድሟል ፥ ሀገርን ፡ ለውጭ ፡ ጠላት ፡ ጥቃት ፡ አጋልጧል ፥ የርኵሰትና ፡ የክዳት ፡ ድርጊቶቹንም ፡ በይፋ ፡ አምኗል ።
ድርጅቱ ፥ ሕ.ወ.ሐ.ት. ፥ በሕግ ፡ ይፍረስና ፡ ይወገዝ ፥ ኀላፊዎቹም ፡ ተይዘው ፥ በሀገር ፡ ክዳት ፣ በፀረ ፡ ስብኣዊነት ፡ ወንጀልና ፡ በጦር ፡ ወንጀል ፡ አንቀጾች ፡ ተከሰው ፡ እሀገራዊ ፡ የፍርድ ፡ ችሎትም ፡ ፊት ፡ ቀርበው ፡ በወንጀለኛ ፡ መቅጫ ፡ ሕግ ፡ መሠረት ፡ ይቀ፟ጡ ፡ ከማለት ፡ በቀር ፥ ይህን ፡ ለመሰለው ፡ ርኵሰትና ፡ ክዳት ፡ ምንም ፡ ዐይነት ፡ የሐዘንም ፡ የውግዘትም ፡ ቃላት ፡ አይገኙለትም ።
ኾኖም ፥ ከክዳቱና ፡ ከጭፍጨፋው ፡ ዠርባ ፡ ምክንያቶች ፡ የኾኑት ፡ ባዕድ ፡ ተከ፟ል ፡ የአፓርትሀይድ ፡ ሥርዐቱና ፡ ሌሎች ፡ ይፋ ፡ ያልወጡ ፡ ተሳታፊዎችና ፡ ተመሳጣሪዎችም ፡ ስላሉ ፥ ጠቅላላው ፡ ጕዳይ ፡ በመሸጋገሪያ ፡ መንግሥት ፡ ወቅት ፡ በዝርዝር ፡ የሚመረመርና ፡ በሀገራዊው ፡ ፈታሒ ፡ ሥልጣን ፡ ሕጋዊ ፡ ፍጻሜውን ፡ የሚያገኘ ፡ ስለሚኾን ፥ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ (ኢ.ሀ.ሥ.አ.) ፡ የፍርድ ፡ ኺደቱን ፡ በተመለከተ ፥ አቋሙን ፡ ወደ ፡ ፊት ፡ ያስታውቃል ።
ይህ ፡ ሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ የተባለ ፡ የውንብድና ፡ ድርጅት ፥ ከሀገር ፡ ወዳ፟ዱና ፡ ጨዋው ፡ የትግራይ ፡ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ ነዋሪ ፡ አንዳች ፡ ውክልና ፡ አልነበረውም ፤ የፈጸማቸው ፡ የሀገር ፡ ክዳት ፡ ወንጀሎች ፡ ዅሉ ፥ ድርጅቱንና ፡ ከኀምሳ ፡ ዓመታት ፡ በፊት ፡ የፈጠሩትን ፣ የነወዩትን ፣ ያደራጁትንና ፡ ከሩቅ ፡ ኾነው ፡ የዘወሩትን ፡ የምልክዮሽ ፡ ኀይሎችንም ፡ የሚመለከቱ ፡ ወንጀሎች ፡ ናቸው ። የትግራይ ፡ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ ነዋሪ ፡ ከደሙ ፡ ንጹሕ ፡ መኾኑን ፡ ራሱም ፡ ያውቀዋል ፥ መላ፟ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብም ፡ ያውቅለታል ፥ የዓለም ፡ ሕዝብም ፡ ሊያውቅለት ፡ ይገ፟ባ፟ል ። ይህም ፡ ሊታመን ፥ የሕ.ወ.ሐ.ት.ን ፡ ጥሪ፟ ፡ ካለመቀበሉ ፡ ሌላ ፥ ሀገራዊው ፡ ሰራዊት ፡ በተሰማራባቸው ፡ የትግራይ ፡ ቀበሌዎች ፡ ዅሉ ፥ ነዋሪው ፡ የሰራዊቱን ፡ መመ፟ሪያ ፡ በማክበር ፡ ለ”ሕግን ፡ የማስከበር ፡ ዘመቻ”ው ፡ ድጋፉን ፡ አሳይቷል ። ባስፈለገም ፡ ጊዜ ፥ ሲጨቍነው ፡ የኖረውን ፡ የውንብድና ፡ ኀይል ፡ ከሀገራዊው ፡ ሰራዊት ፡ አባላት ፡ ጐን ፡ ተሰልፎ ፡ ወግቷል ።
ይህን ፡ ፋሺስታዊ ፡ የክፋት ፡ ኀይል ፡ ድል ፡ አድርገው ፡ ሕይወታቸውን ፡ በሠዉት ፡ ዠግኖችና ፡ በተገደሉት ፡ ሰላማውያን ፡ ኢትዮጵያውያን ፥ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ (ኢ.ሀ.ሥ.አ.) ፡ የተሰማውን ፡ መሪር ፡ ሐዘን ፡ ይገልጻል ፤ የሞቱትን ፡ ነፍስ ፡ እግዚአብሔር ፡ እንዲምርለትም ፡ ይጸልያል ። ለተጐዱት ፡ ቤተሰቦቻቸውና ፡ ወዳጆቻቸው ፡ ዅሉ ፡ እንዲሁም ፡ ለመላ፟ው ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ጽናቱን ፡ እንዲሰጥለት ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ይለምናል ። ኢትዮጵያ ፥ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ መንግሥቷን ፡ መልሳ ፡ ስታቆም ፥ የሕይወት ፣ የአካል ፡ እና ፡ የንብረት ፡ ጕዳት ፡ የደረሰባቸውን ፡ ልጆቿን ፡ ዅሉ ፡ ትክሳቸዋለች ፡ ሲል ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ እምነቱን ፡ ይገልጻል ።
እስከዚያው ፡ ድረስ ፦
1) ከሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ የ30 ፡ ዓመት ፡ ጭቈና ፡ ነጻ ፡ ለወጡት ፡ የክፍለ ፡ ሀገር ፡ ትግራይ ፡ ነዋሪዎች ፦ እንኳን ፡ ለዚህ ፡ የነጻነት ፡ ቀን ፡ አበቃችኹ ፤ ለዚህ ፡ ዅሉ ፡ መከራና ፡ ሞት ፡ ዳርገዋችኹ ፥ አኹን ፡ ደግሞ ፡ በውስጣችኹ ፡ ተደብቀው ፡ ዐዲስ ፡ ዙር ፡ መከራን ፡ የሚደግሱላችኹን ፡ ጥቂት ፡ ወንጀለኞች ፡ እያወጣችኹ ፡ ለሕግ ፡ አስከባሪው ፡ ኀይል ፡ አስረክቡ ፤
2) አላግባብ ፡ ወደ”ትግራይ ፡ ክልል” ፡ ተዛውረው ፡ ለነበሩት ፡ የጐንደር ፡ ክፍለ ፡ ሀገርና ፡ የወሎ፟ ፡ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ ወረዳዎች ፡ ነዋሪዎች ፦ እናንተንም ፥ እንኳን ፡ ለዚህ ፡ የነጻነት ፡ ቀን ፡ አበቃችኹ ! “ክልላዊው ፡ የአፓርትሀይድ” ፡ ሥርዐት ፡ ፈርሶ ፥ ኢትዮጵያ ፡ በዐዲስና ፡ በሕጋዊ ፡ አስተዳደራዊ ፡ አወቃቀር ፡ በሥልጡንሕዝባዊ ፡ መንገድ ፡ እስክትዋቀር ፡ ድረስ ፥ በታላቅ ፡ መሥዋዕትነት ፡ ባስከበራችኹት ፡ መብታችኹ ፡ የያዛችኹትን ፡ ግዛታችኹን ፡ ሳትለቁ ፡ ጸንታችኹ ፡ እንድትቈዩ ፤
3) መላ፟ው ፡ የኢትዮጵያ ፡ ነጻ ፡ ሕዝብ ፡ ሆ�� ፦ እንኳን ፡ ለዚህ ፡ የድል ፡ ቀን ፡ አደረሰኽ ! ምንም ፡ ውጊያው ፡ በወንድማማቾችና ፡ እትማማቾች ፡ መኻከል ፡ መኾኑ ፡ ዕጥፍ ፡ ድርብ ፡ ሐዘን ፡ ቢኾንብን ፡ ቅሉ ፥ ድል ፡ የተመታው ፡ ወንድምን ፡ ከወንድሙ ፥ እኅትን ፡ ከእኅቷ ፡ የሚያለያይና ፡ የሚያፋጅ ፡ ከምዕራቡ ፡ ዓለም ፡ የመጣ ፡ የንኁልዮሽ ፡ ርኩስ ፡ መንፈስ ፡ በመኾኑና ፥ ድሉ ፡ የወደፊቱንም ፡ የኢትዮጵያ ፡ ዕጣ ፡ ፈንታ ፡ መቃናት ፡ ገና ፡ ካኹኑ ፡ በማመልከቱ ፥ ዳግመኛ ፡ እንኳን ፡ ደስ ፡ ዐለኽ ! ባዕድ ፡ ሠራሹ ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ የአፓርትሀይድ ፡ ሥርዐት ፡ ከኢትዮጵያ ፡ ምድር ፡ ፈጽሞ ፡ እንዳይነቀል ፥ «ሕገ ፡ መንግሥቱን ፡ እናስቀጥላለን» ፡ የሚሉ ፡ አታላዮች ፡ በሚዋሹልኽ ፡ ግብዝ ፡ ምርጫና ፡ ማንኛውም ፡ ማዘናጊያ ፡ እንዳትዘናጋ ። የኢትዮጵያን ፡ ሀገራዊ ፡ አንድነትና ፡ ብሔራዊ ፡ (ምድራዊ ፡ ወይም ፡ ግዛታዊ) ፡ ሙሉነት ፡ በማስጠበቅና ፡ በማረጋገጥ ፥ ዐዲስ ፡ ሕገ ፡ መንግሥትኽንና ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ የርትዕ ፡ መንግሥትኽን ፡ ትመሠርት ፡ ዘንድ ፥ አስቀድሞ ፡ መላ፟ ፡ ሀገርኽ ፡ ኢትዮጵያን ፡ መልሰኽ ፡ እእጅኽ ፡ ለማስገባት ፡ በአንድነት ፡ ተነሥ ፥
ሲል ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ጥሪ፟ውን ፡ ከመልካም ፡ ምኞቱ ፡ ጋራ ፡ በሀገር ፡ ፍቅር ፡ ያስተላልፋል ።
1 ፤ የምልክዮሽ ፡ እጅ ፡ ደም ፡ አለ፟በ፟ት !
ደቡብ ፡ አፍሪቃ ፡ የተፋችውን ፡ የ”አፓርትሀይድ” ፡ ሥርዐት ፥ የተባበሩት ፡ ያሜሪካ ፡ ኹነቶች ፡ መንግሥትና ፡ ጥቂት ፡ ምዕራባውያን ፡ መንግሥታት ፥ በቀልን ፡ በሚያመለክት ፡ አደራረግ ፥ በግንቦት ፡ ወር ፡ 1983 ፡ ዓ.ም. ፡ በቀንደኛዋ ፡ የፀረ ፡ ቅኝ ፡ ግዛት ፣ የፀረ ፡ ምልክዮሽና ፡ የፀረ ፡ “አፓርትሀይድ” ፡ ተዋጊት ፡ ኢትዮጵያ ፡ ላይ ፡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ (የኢትዮጵያ ፡ ፌዴራላዊ ፡ ዴሞክራሲያዊ ፡ ሪፓብሊክ) ፡ የ”አፓርትሀይድ” ፡ ይዘት ⁽2⁾ ፡ መልክ ፥ “ፐርል ፡ ሀርበር”ን ፡ በሚያስንቅ ፡ ክዳት ፥ በጕልበት ፡ ጫኑባት ። ይዘቱንም ፡ በከሓዲው ፡ ሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ እጅ ፡ ውስጥ ፡ አደረጉት ።
በዚህ ፡ መሠረት ፥ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ይዘት ፡ ዋና ፡ ተጠሪ ፡ ሕ.ወ.ሐ.ት. ፥ 29 ፡ ዓመት ፡ ሙሉ ፡ ይህ ፡ ነው ፡ የማይባል ፡ በደልን ፡ በኢትዮጵያ ፡ ላይ ፡ ፈጸመ ። ሊገለጹ ፡ የማይችሉ ፡ የስርጀታ ፣ የጭቈና ፣ የአመሳሶ ፣ የሙስ፟ና፟ ፡ ዐይነቶች ፡ በገቢር ፡ ታዩ ፤ ባጠቃላይ ፡ ያስተዳደር ፡ ብልሹነት ፥ አንዳች ፡ ከልካይ ፡ ሳይኖርበት ፥ የ”mean”-stream ፡ ማወራኛዎችም ፡ አይተው ፡ እንዳላዩ ፣ ሰምተው ፡ እንዳልሰሙ ፡ እየኾኑለት ፥ በእየዓመቱ ፡ በቢልዮን ፡ ዶላር ፡ የሚገመትን ፡ የሀገር ፡ ሀብት ፡ በውጭ ፡ ምንዛሪ ፡ መዝብሮ ፡ ወደቀረው ፡ ዓለም ፡ በሕገ ፡ ወጥ ፡ መንገድ ፡ አሸሸ ። በዚሁ ፡ ጊዜ ፥ “mean”-stream ፡ ማወራኛዎች ፡ የኢትዮጵያ ፡ ጥርየት ፡ በ”ባለኹለት ፡ አኃዝ ፡ እድገት” ፡ መጠን ፡ ማደጉን ፡ በሰፊው ፡ ከመንዛት ፡ አላቋረጡም ፤ ኾኖም ፥ ይህ ፡ የ”ባለኹለት ፡ አኃዝ ፡ እድገት” ፡ መጠን ፡ ስማዊ ፡ (nominal) ፡ እንጂ ፡ እውናዊ ፡ (real) ፡ የእድገት ፡ መጠን ፡ ባለመኾኑ ፥ ስማዊው ፡ እድገት ፡ በባሰ ፡ “ባለኹለት ፡ አኃዝ” ፡ የዋጋ ፡ ንረት ፡ ፈጽሞ ፡ መበ፟ላቱንና ፡ የሀገሪቱ ፡ ጥርየት ፡ መቀንጨሩን ፡ አልተናገሩም ።
በሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ የሚ፟መ፟ራ፟ው ፡ ይዘት ፥ በዋነኛነት ፡ እንዲፈጽማቸው ፡ የተመደቡለትን ፡ ሀገር ፡ ኢትዮጵያን ፡ የመደምሰስ ፡ መደምደሚያ ፡ ተልእኮዎች ፦
1) ኢትዮጵያን ፡ የባሕር ፡ በር ፡ የማሳጣት ፡ የምልክዮሽ ፡ እኩይ ፡ ዐላማን ፡ በሕገ ፡ ወጥ ፡ ፈረዳ ፡ እዳር ፡ ለማድረስ ፥ የባሕር ፡ ምድርንና ፡ የደንከልን ፡ ኢትዮጵያዊ ፡ ከፊል ፡ ሕዝቧን ፣ ከፊል ፡ ምድሯንና ፡ የቀይ ፡ ባሕር ፡ ዳርቻዎቿንም ፡ በሙሉ ፡ ለጠላት ፡ አሳልፎ ፡ በመስጠት ፤
2) የኢትዮጵያን ፡ ሕዝብ ፡ እንዲሁም ፡ ብሔሯን ፡ (ምድሯን) ፡ በ”ዘር” ፡ መክፈልት ፡ ከፋፍሎ ፥ ሀገራዊ ፡ አንድነቷንና ፡ ብሔራዊ ፡ ሙሉነቷን ፡ ለአደጋ ፡ በመዳረግ ፤
3) በባዕድ ፡ ሠራሹ ፡ “ሕገ ፡ መንግሥት” ፡ መሠረት ፥ አንዱን ፡ የኢትዮጵያ ፡ እግዚእ ፡ ሕዝብ ፡ “ሕዝቦች” ፡ ብሎ ፡ ከፋፍሎ ፡ በመጥራትና ፡ ኢትዮጵያን ፡ ባለቤት ፡ አልባ ፡ ለማድረግ ፡ በመሞከር ፤
4) ሀገራዊ ፡ ልሳን ፡ ዐማርኛን ፡ በእንግሊዝኛ ፡ አንጻር ፡ ለማዳከም ፡ በመሞከር ፤
5) ሀገራዊነትን ፡ በውልደተኝነት ፡ ለመተካት ፡ በመሞከር ፥ እንዲሁም ፡ ማኅበረሰብን ፡ ከማኅበረሰብ ፡ ከፋፍሎ ፡ በማገዳደርና ፡ በማጋጨት ፡ በእየዕለቱ ፡ ዕልቂትን ፣ መፈናቀልንና ፡ ስደትን ፡ በማከታተል ፤
6) የተቃወመውን ፡ ዅሉ ፡ አላንዳች ፡ ርኅራኄ ፡ ባሠቃቂ ፡ መንገድ ፡ በማሳደድ ፣ በመሣቅየትና ፡ በመግደል ፤
7) የሀገሪቱንና ፡ የመንግሥቷን ፡ ሀብት ፡ በመመዝበር ፥
8) ሌላ ፡ ሌላም ፡ የረከሱ ፡ ግብሮችን ፡ በመፈጸም ፤
ጠላትነቱን ፡ አረጋግጧል ።
ነገር ፡ ግን ፥ ሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ አልተሳካለትም ፤ መጨረሻውን ፥ ሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ ራሱ ፡ እንሆ ፡ ተደመሰሰ ።
ከመደ፟ምሰሱ ፡ ሦስት ፡ ዓመታት ፡ በፊት ፥ በ2010 ፡ ዓ.ም. ፡ በተቀጣጠለው ፡ ሕዝባዊ ፡ ዐመፃ ፡ የራሱ ፡ መጨረሻ ፡ ታይቶትና ፡ ተጨንቆ ፥ በሆዱ ፡ ያባው ፡ ቀሪ ፡ የጥፋት ፡ ተልእኮው ፡ እንዳይታጐል ፡ ማምለጫን ፡ ለማግኘት ፡ ሲል ፥ በትረ ፡ ውንብድናውን ፡ ለቀሩት ፡ የቅሬታው ፡ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ይዘት ፡ አጋሮቹ ፡ አቀብሎ ፥ ወደመሸሸጊያው ፡ “የትግራይ ፡ ክልል” ፡ ሾለከ ። ሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ እስከ ፡ ዛሬ ፡ ድረስ ፡ ለበደለውም ፡ በደል ፦በክተናል ፡ ከማለት ፡ በቀር ፡ አንዳችም ፡ ጸጸት ፡ አላሳየ ። ቅዱስ ፡ መጽሐፍ ፦ውሻ ፡ ወደ ፡ ትፋቱ ፡ ይመለሳል ፡ (2ኛ ፡ ጴጥ. ፥ 2 ፥ 22) ፡ ሲል ፡ እንዳመለከተው ፡ ዅሉ ፥ ዐዲስ ፡ አበባን ፡ ለቆ፟ ፡ ወደትግራይ ፡ “ክልል” ፡ ምሽጉ ፡ ከተመለሰ ፡ በዃላ ፥ ያልተለወጠውን ፥ እውነተኛውን ፡ የከሓዲነት ፣ የፋሺስትነትና ፡ ያጥፊነት ፡ ብልሹ ፡ ጠባዩን ፡ በሚያሠቅቅ ፡ ኹኔታ ፡ በመላ፟ ፡ ሀገሪቱ ፡ በመድገም ፡ ለዓለሙ ፡ ዅሉ ፡ መልሶና ፡ ገልጦ ፡ አሳየ ። ሕ.ወ.ሐ.ት. ፥ ይህን ፡ ወንጀሉን ፡ ሲፈጽም ፥ ዐዲስ ፡ አበባ ፡ እሥልጣኑ ፡ ሰገነት ፡ ላይ ፡ ከቀሩት ፡ አንጋፋዎች ፡ አጋሮቹ ፡ ውስጥ ፥ ኢትዮጵያን ፡ “በዘር ፡ ማጽዳት” ፡ ዘመቻ ፡ ወደ ፡ “ዩጎስላቪያነት” ፡ በመቀየር ፡ አጥፊ ፡ ስያስ ፡ የሚስማሙለትን ፥ የከፊሉን ፡ ተመሳጣሪነት ፣ ወይም ፡ ተባባሪነት ፣ ወይም ፡ ደግሞ ፡ የዐቅም ፡ ድጋፍ ፡ ሳያገኝ ፡ እንዳልቀረ ፡ በገቢር ፡ ተመስክሯል ።
በወልቃይት ፣ በጠገዴ ፡ (ጸገዴ) ⁽3⁾ ፣ በካፍታ ፡ ሑመራ ፡ እና ፡ በጠለምት ፡ (ጸለምት) ፡ ወረዳዎች ፥ በተለይ ፡ በማይ ፡ ካድራ ፡ ከተማ ፡ አካባቢ ፥ ከጥቅምት ፡ 24 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፡ አንሥቶ ፡ እስከተባረረበት ፡ ቀን ፡ ድረስ ፡ ከ1’500 ፡ ያላነ፟ሱ ፡ ንጹሓንን ፡ ያጠፋ፟ው ፡ አረመኔያዊ ፡ የወያኔ ፡ ጭፍጨፋ ፥ መሠረቱ ፡ የዚሁ ፡ በ1933 ፡ ዓ.ም. ፡ የተሸነፈው ፡ የፋሺዝም ፡ ቂም ፡ በቀልና ፡ ፋሺስታዊ ፡ አስተሳሰብ ፡ ስለ ፡ መኾኑ ፡ ምንም ፡ ጥርጥር ፡ የለውም ። የዩጎስላቪያውን ፡ የ”ስሬብሬኒሽካ” ፡ ጭፍጨፋ ፡ በሚያስታውስ ፡ ኹኔታም ፥ የኢትዮጵያን ፡ መበ፟ታተን ፡ እንዲያስከትል ፥ ኾነ ፡ ተብሎ ፡ ተፈጽሟል ።
የወልቃይት ፣ የጠገዴ ፣ የጠለ፟ምትና ፡ የካፍታ ፡ ሑመራ ፡ ወረዳዎች ፡ [ቢጋር ፡ 1ን ፡ ይመለከቷል፥ PDF] ፡ ከጐንደር ፡ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ ግዛትነት ፡ በውንብድና ፡ ውሳኔ ፡ ወደ ፡ “ትግራይ ፡ ክልል” ፡ ወረዳነት ፡ በ1983 ፡ ዓ.ም. ፡ የተዛወሩባቸው ፡ ምክንያቶች ፦
• አንደኛ ፥ ነዋሪዎቹ ፥ በጠቅላላው ፥ በፋሺስት ፡ ኢጣሊያ ፡ ወረራ ፡ ዘመን ፡ (1928-1933 ፡ ዓ.ም.) ፡ እንደ ፡ ቢትወደድ ፡ አዳነ ፡ መኰንን ፡ ባሉ፟ ፡ ሀገራውያን ፡ ዠግኖች ፡ መሪነት ፡ በፈጸሙት ፡ ታላቅ ፡ የዐርበኝነት ፡ ተጋድሏቸው ፥ አካባቢያቸውን ፡ “የፋሺስት ፡ መቃብር” ፡ ያሠኙበትን ፡ የዠግንነት ፡ ዝና፟ቸውንና ፡ የሀገራዊነት ፡ ሟያቸውን ፡ ለመበ፟ቀል ፤
• ኹለተኛ ፥ የምልክዮሽ ፡ ኀይሎች ፡ በ”ሪፓብሊክነት ፡ ትገነጠላለች” ፡ ብለው ፡ ለወሰኑባት ፡ የትግራይ ፡ “ክልል” ፥ በሱዳን ፡ በኩል ፡ መጋ፟ቢያን ፡ ለመስጠት ፤
• ሦስተኛ ፥ ለ”ሪፓብሊክነት” ፡ የታጨው ፡ የትግራይ ፡ “ክልል” ፥ ከወሎ፟ ፡ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ ግዛትነት ፡ በ1983 ፡ ዓ.ም. ፡ አላግባብ ፡ የተዛወሩትን ፡ የራያ፟ ፡ እና ፡ የአላ፟ማጣ ፡ ወረዳዎች ፡ አክሎ ፥ በምግብ ፡ ራሱን ፡ ከመቻልም ፡ ዐልፎ ፡ መጀለቻው ፡ የሚኾነውን ፡ ሰፊ፟ ፡ እና ፡ ለም ፡ የዕርሻ ፡ መሬት ፡ ባለቤት ፡ ለማድረግ ፡ ነበር ።
ጥቅምት ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፡ አጋማሽ ፡ ላይ ፡ በሺሕ ፡ የሚቈጠሩ ፡ ንጹሓን ፡ ሀገራውያንን ፡ (ዐማራዎችን) ፡ ያጠፉ፟ትና ፡ [ቢጋር ፡ 2ን ፡ ይመለከቷል፥ PDF] ፡ በተለመደው ፡ የሐዘን ፡ መግለጫ ፡ ሊታለፉ ፡ የነበሩት ፦
• የ”ኦሮሞ ፡ ክልል” ፡ (በወለ፟ጋ፟ ፥ ጉሊሶ ፣ ቂልጡ ፣ ጃርሶ ፣ ሆሮ፟ ፣ ጕድሩ ፡ … ፡ ወረዳዎች) ፣
• የ”በኒ ፡ ሻንጉል ፡ ጉምዝ ፡ ክልል” ፡ (በመተከ፟ል ፡ አውራጃ ፥ ማንዱራ ፣ ቡሌን ፣ ድባጤ ፣ ካማሺ ፡ … ፡ ወረዳዎች) ፣
• የ”ደቡብ ፡ ክልል” ፡ (ሰሜን ፡ ቤንች ፣ ማጂ ፣ ኮንሶ ፣ ዐማሮ ፣ ማሌ ፡ … ፡ ወረዳዎች) ፡ ወዘተርፈ ፡ … ፡
ሀገራውያንን ፡ ወይም ፡ ዐማራዎችን ፡ ከእየ”ክልሉ” ፡ የ”ማጽዳት” ፡ ጭፍጨፋዎችን ፥ እስካኹን ፡ ችላ፟ ፡ ሲላቸው ፡ የነበረው ፡ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.-ብልጽግና ፡ ፓርቲ ፡ የሚመ፟ራ፟ው ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፥ ድንገት ፥ የሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ ጥቃቶች ፡ በሰራዊቱ ፡ ክፍለ ፡ ጦሮች ፡ ላይ ፡ በትግራይ ፡ “ክልል” ፡ ውስጥ ፡ በመደ፟ገማቸው ፥ እንደውጭ ፡ ጕዳይ ፡ “ሚኒስቴር” ፡ ቃል ፡ አቀባይ ፡ አገላለጽ ፥ «ቀዩ ፡ መስመር ፡ ታለፈ» ፡ ብሎ ፥ አኹን ፡ የምንመለከተውን ፡ “ሕግን ፡ የማስከበር ፡ ዘመቻ” ፡ ከዘገየ ፡ ሊያውጅ ፡ ተገደደ ። በጦር ፡ ሰራዊት ፡ ክፍለ ፡ ጦሮች ፡ ላይ ፡ ጥቃት ፡ እስከተፈጸመበት ፡ እስከ ፡ ጥቅምት ፡ 24 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፡ ድረስ ፥ በእየወረዳው ፡ በ”ዘር ፡ ማጽዳት” ፡ ሽፋን ፡ የተፈጸሙትን ፡ ፀረ ፡ ሀገራዊ ፡ (ፀረ ፡ ዐማራ) ፡ ጭፍጨፋዎች ፡ ዅሉ ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ በሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ እያመካኘ ፡ ሕግን ፡ ከማስከበር ፡ እስካኹን ፡ መታቀቡ ፥ የፀረ ፡ ሀገራዊ ፡ (ፀረ ፡ ዐማራ) ፡ ጥቃቶቹን ፡ ውጤት ፡ (ማለት ፥ በዘር ፡ ላይ ፡ የተመሠረቱ ፡ “ክልሎችን” ፡ ለማጠናከርና ፡ ለግንጠላ ፡ ለማብቃት) ፡ ስለሚፈልገው ፡ እንደ ፡ ነበር ፡ በብዙ ፡ ማስረጃዎች ፡ ተረጋግጧል ። ይህን ፡ መግለጫ ፡ አሰናድተን ፡ በምናጠናቅቅበት ፡ ሰዓት ፥ ታኅሣሥ ፡ 16 ፡ ቀን ፡ 2020 ፡ ዓ.ም. ፥ በ”በኒ ፡ ሻንጉል ፡ ጉምዝ ፡ ክልል” ፡ ባንድ ፡ መንደር ፡ ብቻ ፡ ከ200 ፡ ያላነ፟ሱ ፡ ሀገራውያን ፡ (ዐማራዎች) ፡ ተጨፍጭፈው ፡ መገደላቸውን ፡ በታላቅ ፡ ሐዘን ፡ ተረድተናል ። ይህም ፡ የደረሰው ፥ ዶክተር ፡ ዐቢይ ፡ አሕመድ ፡ “ክልሉን” ፡ በጐበኙ ፡ ማግስት ፡ ነው ።
በዚህ ፡ ምክንያት ፥ “ፕሬዚደንቷ”ን ፡ ወይዘሮ ፡ ሣህለ ፡ ወርቅ ፡ ዘውዴን ፡ እና ፡ “ጠቅላይ ፡ ሚኒስትሩ”ን ፡ ዶክተር ፡ ዐቢይ ፡ አሕመድን ፡ ጨምሮ ፥ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ ዋና፟ ፡ ዋና፟ ፡ ኀላፊዎችና ፡ የክልል ፡ ኀላፊዎች ፥ ከሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ ኀላፊዎች ፡ እኩል ፥ በሀገር ፡ ክዳት ፡ አንቀጽና ፡ በፀረ ፡ ስብኣዊነት ፡ ወንጀል ፡ ተባባሪነት ፡ አንቀጽ ፡ በሕግ ፡ ይጠየቃሉ ፡ ሲል ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ዳግመኛ ፡ ያስታውቃል ።
ለብዙ ፡ ዓመታት ፡ በኤርትራ ፡ ሠልጥነውባቸው ፣ ታጥቀውባቸውና ፡ ሰፍረውባቸው ፡ ከነበሩት ፡ ከሕዝባዊ ፡ ግንባር ፡ ሐርነት ፡ ኤርትራ ፡ (ሕ.ግ.ሐ.ኤ. ፡ ወይም ፡ “ሻዕቢያ”) ፡ የውንብድና ፡ ኀይል ፡ የጦር ፡ ሰፈሮች ፥ በ2010-11 ፡ ዓ.ም ፥ በዶክተር ፡ ዐቢይ ፡ አሕመድ ፡ የውንብድና ፡ አገዛዝ ፡ ፈቃድ ፥ ወደ”ኦሮሞ ፡ ክልል” ፡ ከእነሙሉ ፡ ትጥቃቸው ፡ ገብተው ፡ እንዲሰፍሩ ፡ የተደረጉት ፡ “የኦሮሞ ፡ ነጻነት ፡ ግንባር” ፡ ተዋጊዎች ፥ በእንቅስቃሴያቸውም ፡ ኾነ ፡ በሥራቸው ፡ አንዳች ፡ ገደብ ፡ ሳይደረግባቸው ፥ ዓመት ፡ ባልሞላ ፡ ጊዜ ፡ ውስጥ ፥ በብዙ ፡ ሺሕ ፡ የሚቈጠሩ ፡ ንጹሓን ፡ ኢትዮጵያውያንን ፡ መግደላቸውና ፡ በሚልዮን ፡ የሚቈጠሩትንም ፡ ማፈናቀላቸው ፡ ይታወቃል ። ለዚህ ፡ ዅሉ ፡ ወንጀል ፡ የዶክተር ፡ ዐቢይ ፡ አሕመድ ፡ የውንብድና ፡ አገዛዝ ፡ ተጠያቂ ፡ መኾኑን ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ያውቃል ፤ “የሞት ፡ ነጋዴዎች”ም ፡ ይህኑ ፡ ሰው ፡ “የሰላም ፡ ኖቤል”ን ፡ ሸልመውታል ።
በሠኔ ፡ ወር ፡ 2012 ፡ ዓ.ም. ፡ በ”ኦሮሞ ፡ ክልል” ፡ ታጣቂዎችና ፡ በኦ.ነ.ግ. ፡ ታጣቂዎች ፡ በተደራጁና ፡ በተሰማሩ ፡ ዱርዬዎች ፡ በግፍ ፡ የተጨፈጨፉትንና ፡ ንብረቶቻቸው ፡ የተዘረፉባቸው ፣ የወደሙባቸው ፡ በዐሥር ፡ ሺሕ ፡ የሚቈጠሩትን ፡ ጕዳተኞች ፡ ደግሞ ፥ ምንም ፡ ዐይነት ፡ ካሳ ፡ እንደማይክሳቸው ፡ ይህ ፡ ዐምባ ፡ ገነን ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ በዕብሪት ፡ ማስታወቁ ፡ ይታወሳል ።
ኅዳር ፡ 19 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፥ “ሕግን ፡ የማስከበር ፡ ዘመቻ”ው ፡ በታወጀ ፡ በ25ኛ ፡ ቀኑ ፥ የኢትዮጵያ ፡ ሀገራዊ ፡ ሰራዊት ፥ የወያኔ ፡ ከሓዲ ፡ ኀይልን ፡ መደምሰሱንና ፡ ማዘዣው ፡ ያደረጋትን ፡ መቀሌ ፡ ከተማን ፡ ሙሉ ፡ በሙሉ ፡ መቈጣጠሩን ፡ ያበሠረውን ፡ የድል ፡ ዜና ፡ በመስማቱ ፡ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ (ኢ.ሀ.ሥ.አ.) ፡ ከፍ ፡ ያለ ፡ ደስታ ፡ ተሰምቶታል ። የኢትዮጵያ ፡ ሀገራዊ ፡ ሰራዊት ፡ አባላት ፡ የኢትዮጵያ ፡ ጥንታዊ ፡ የርትዕ ፡ ሥልጣኔ ፡ የ«ሥልጡንሕዝብና» ፡ ምርቶች ፡ ናቸውና ፥ ምንም ፡ ላለፉት ፡ 50 ፡ ዓመታት ፡ የማያቋርጥ ፡ ንኅለተኛ ፡ ስብከትና ፡ የአእምሮ ፡ ዕጥበት ፡ ቢሞ፟ከ፟ርባቸው ፥ ሀገራቸው ፡ ኢትዮጵያ ፡ የተመሠረተችባቸውን ፡ ዘላለማውያን ፡ ኅልያዎች ፡ ከፍ ፡ አድርገው ፡ በመያዝ ፡ እስከ ፡ ዛሬ ፡ ጠብ፟ቀው ፡ ማቈየታቸውን ፡ በድል ፡ አረጋግጠዋል ። በዚህ ፡ ዕለት ፡ ፋሺዝምን ፡ በ80 ፡ ዓመት ፡ ለኹለተኛ ፡ ጊዜ ፡ ድል ፡ አድርገውታል ።
እዚህ ፡ ላይ ፡ ሳናነሣው ፡ የማናልፈው ፡ ለሤራው ፡ ዅሉ ፡ ማብረሻ ፡ የኾነው ፡ ያልተጠበቀ ፡ ድርስ ፡ አለ፟ ። ጥቅምት ፡ 24 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፥ የሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ የውንብድና ፡ ኀይል ፡ በሰሜን ፡ ኢትዮጵያ ፡ የሰፈረውን ፡ የኢትዮጵያ ፡ ጦር ፡ ሰራዊት ፡ ድንገት ፡ ባጠቃበት ፡ ወቅት ፥ ጦሩ ፡ ክፉኛ ፡ ተጐድቶ ፡ ላጠቃላይ ፡ ድምሳሴ ፡ ተጋልጦ ፡ ነበር ። ማዘዣውን ፡ ባሕር ፡ ዳር ፡ ያደረገውና ፡ አረንጓዴ ፣ ብጫ ፣ ቀይ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሰንደቅ ፡ ዐላማን ፡ ያነገበው ፡ የጐንደር ፣ የወሎ፟ ፣ የጐዣምና ፡ የሸዋ ፡ ክፍላተ ፡ ሀገር ፡ ሕዝባዊ ፡ ሰራዊት ፥ ማንም ፡ ባልጠበቀው ፡ ፍጥነት ፥ በእልኽና ፡ በዠግንነት ፡ ተወርውሮ ፡ ለተከበበው ፡ ሰራዊት ፡ ስለ ፡ ደረሰለትና ፥ የሕ.ወ.ሐ.ት.ን ፡ የሽፍታ ፡ ኀይል ፡ እጅግ ፡ ባነሰ ፡ ትጥቅና ፡ የሰራዊት ፡ ቍጥር ፡ ስላሽቀነጠረው ፥ ይደርስ ፡ የነበረውን ፡ የከፋ፟ ፡ ሀገራዊ ፡ አደጋ ፥ ተኣምር ፡ በሚያሠኝ ፡ ክንዋኔ ፡ አስወግዶ ፥ ከመቀሌም ፡ ከዐዲስ ፡ አበባም ፡ ይጠ፟በ፟ቅ ፡ የነበረውን ፡ ጥፋት ፡ አርክሶታል ። የዚህ ፡ ሕዝባዊ ፡ ሰራዊት ፡ ሟያ ፡ ዃላ ፡ “ሕግን ፡ የማስከበር ፡ ዘመቻ” ፡ ለተባለው ፡ ግብረት ፡ መሳካት ፡ ያንበሳውን ፡ ድርሻ ፡ ይዟል ።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ ኀላፊዎች ፥ ኹኔታው ፡ ከቍጥጥራቸው ፡ በመውጣቱ ፡ ተገደውም ፡ ቢኾን ፥ በመጨረሻ ፡ ይህን ፡ “ሕግን ፡ የማስከበር ፡ ዘመቻ” ፡ ያሉትን ፡ ግብረት ፡ ማወጃቸውና ፥ የውጭ ፡ ኀይሎችን ፡ ተጽዕኖ ፡ ተቋቁመው ፥ በስኬት ፡ ማስፈጸማቸው ፡ ያስመሰግናቸውም ፥ በታሪክም ፡ ለሀገር ፡ እና ፡ ለሕዝብ ፡ እንደዋሉት ፡ ውለታ ፡ ይቈጠርላቸውም ፡ ይኾናል ።
ነገር ፡ ግን ፥ እነርሱ ፡ “ሕግ” ፡ የሚሉት ፡ የኢትዮጵያን ፡ ሕዝብ ፡ የካደና ፡ እግዚእናውን ፡ የረመረመ ፡ ሕገ ፡ ወጥ ፡ አቋማቸውን ፡ ነው ። እውነተኛው ፡ ሕግን ፡ የማስከበሩ ፡ ዘመቻ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ እግዚእናን ፡ እስከ ፡ ማክበርና ፥ ለዚህ ፡ ዅሉ ፡ ፍጅት ፡ ምክንያት ፡ የኾነውን ፡ ባዕድ ፡ ሠራሹንና ፡ ሕገ ፡ ወጡን ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ “ሕገ ፡ መንግሥት” ፡ በመሻር ፥ ለሽግግር ፡ መንግሥት ፡ ቦታውን ፡ እስከ ፡ መልቀቅ ፡ ስለሚኼድ ፥ ኀላፊዎቹ ፡ ይህኑ ፡ ለማድረግ ፡ እንዲዠግኑ ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ በሀገር ፡ ፍቅር ፡ ዳግመኛ ፡ ያሳስባቸዋል ። በዚህ ፡ ምስቅል ፡ ስያሳዊ ፡ ወቅት ፥ ለሀገርና ፡ ለሕዝብ ፡ ተብሎ ፡ በተፈጸመ ፡ በታላቅ ፡ ወሮታነት ፡ ታሪክ ፡ የሚዘክርላቸው ፡ ይህን ፡ የመጨረሻ ፡ አድራጎታቸውን ፡ ይኾናል ።
2 ፤ ቢፍገመገምም ፥ ቆዳውን ፡ የገለፈፈ ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ።
ከስድስት ፡ ዓመት ፡ በፊት ፥ የተባበሩት ፡ ያሜሪካ ፡ ኹነቶች ፡ ርእሰ ፡ ሀገርና ፡ “የሰላም ፡ ኖቤል ፡ ተሸላሚ” ፡ ባራክ ፡ ኦባማ ፥ በሐምሌ ፡ ወር ፡ 2007 ፡ ዓ.ም. ፡ ኢትዮጵያን ፡ በጐበኙበት ፡ ወቅት ፥ መቶ ፡ በመቶ ፡ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ፡ አባላት ፡ ብቻ ፡ በሚመክሩበት ፡ በአሻንጕሊቱ ፡ የተወካዮች ፡ ምክር ፡ ቤት ፡ ፊት ፡ ቆመው ፥ በኢትዮጵያ ፡ የ”ዴሞክራሲ” ፡ ማበብን ፡ እንዳደነቁለትና ፡ የቢልዮን ፡ ዶላር ፡ ዓመታዊ ፡ ርዳታን ፡ ለውንብድና ፡ ይዘቱ ፡ እንዳስቀጠሉለት ፡ ይታወሳል ። ዘንድሮ ፡ ደግሞ ፥ ኅዳር ፡ 21 ፡ ቀን ፡ 2013 ፡ ዓ.ም. ፥ የዚያ ፡ ዘመን ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ጨቋኝ ፡ ይዘት ፡ የጸጥታ ፡ ኀላፊ ፥ ያኹኑ ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ ዋና ፡ ተጠሪና ፡ ሌላው ፡ “የሰላም ፡ ኖቤል ፡ ተሸላሚ” ፥ ዶክተር ፡ ዐቢይ ፡ አሕመድ ፥ በዚሁ ፡ አሻንጕሊት ፡ ጉባኤ ፡ ፊት ፡ በሰጡት ፡ ቃል ፥ «ለቀባሪው ፡ አረዱት» ፡ በሚያሠኝ ፡ ኹኔታ ፥ እስከ ፡ ዛሬ ፡ ድረስ ፡ “ምስጢርነቱ” ፡ ተጠብ፟ቆለት ፡ የነበረውን ፡ የይዘቱን ፡ ጨቋኝ ፡ ጠባይና ፡ አሠራር ፡ በዝርዝር ፡ ከሥተውበታል ። ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ንግግራቸውን ፡ በጥንቃቄ ፡ አድምጧል ፤ እስካኹን ፡ የነበረውን ፡ መረጃም ፡ ኾነ ፡ ድምዳሜ ፡ አጠናክሮለታል ፡ እንጂ ፡ ዐዲስ ፡ መረጃን ፡ አላገኘበትም ። ዋና ፡ ተጠሪው ፡ ይነግሩናል ፡ ብሎ ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ የጠበቀው ፡ በ2010 ፡ ዓ.ም. ፡ ሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ በትረ ፡ ውንብድናውን ፡ ለርሳቸውና ፡ ለቡድናቸው ፡ ሲያስረክብ ፡ በምን ፡ ስምምነት ፡ መሠረት ፡ እንደ ፡ ነበር ፥ ምስጢረኛ ፡ ስምምነቱንስ ፡ የትኛው ፡ ወገን ፡ መዠመሪያ ፡ እንዳፈረሰውና ፡ ለዚህ ፡ ስብራት ፡ እንዳደረሰው ፡ ዝርዝር ፡ መረጃን ፡ እንዲሰጡ ፡ ነበር ። ይህ ፡ ለጊዜው ፡ ስላልተገለጠ ፥ በሽግግር ፡ መንግሥት ፡ ወቅት ፡ በሚቋቋመው ፡ መርማሪ ፡ ድርገት ፥ ዶክተር ፡ ዐቢይ ፡ አሕመድ ፡ እና ፡ ቡድናቸው ፥ እንደተረፉት ፡ የሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ መሪዎች ፡ ዅሉ ፥ ተጠይቀው ፡ በእነርሱ ፡ በኩል ፡ የሚያውቁትን ፡ ይመልሳሉ ፡ ሲል ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ በተስፋ ፡ ይጠብቃል ።
የተወሰኑ ፡ የውጭ ፡ መንግሥታት ፡ ኢትዮጵያን ፡ በረዥም ፡ ዘመን ፡ ሤራ ፡ ለመደምሰስ ፥ በእጅ ፡ አዙር ፡ ይዘቶቻቸው ፡ አማካይነት ፥ ያከታተሉባትን ፡ አጠቃላይ ፡ የጥፋት ፡ ናዳ ፥ እንዲህ ፡ ከይዘቱ ፡ ተጠሪ ፡ ከዶክተር ፡ ዐቢይ ፡ አሕመድ ፡ ገለጻ ፡ በማያጠራጥር ፡ ኹኔታ ፡ ለማረጋገጥና ፡ ለመደምደም ፡ ተችሏል ። ምልክዮሽ ፥ ላለፉት ፡ 30 ፡ ዓመታት ፥ ላይ ፡ ላዩን ፡ ለሰው ፡ ልጅ ፡ መብትና ፡ ለ”ዴሞክራሲ” ፡ ተሟጋች ፡ መስሎ ፡ በመመጻደቅ ፥ ለፍጹም ፡ የንጥቂያ ፡ ዐላማው ፥ ጨቋኙንና ፡ ንኅለተኛውን ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ይዘት ፡ ሲያቋቁመው ፣ ሲደግፈውና ፡ ሲከባከበው ፡ ኖሯል ። የዓለም ፡ ኅብረተሰብ ፡ ሌላ ፡ ማስረጃን ፡ ሳይጠይቅ ፥ የኢትዮጵያን ፡ መበ፟ደ፟ል ፡ እንዲያውቅለት ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ድምፁን ፡ በዚህ ፡ ረገድ ፡ ዳግመኛ ፡ ያሰ፟ማ፟ል ።
በሕ.ወ.ሐ.ት ፡ መደ፟ምሰስ ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ይዘት ፡ ምሰሶውን ፡ ዐጥቷል ፤ መፍረሱ ፡ የጊዜ ፡ ጕዳይ ፡ ኾኗል ። ዛሬ ፡ የትግራይ ፡ “ክልል” ፡ በገቢር ፡ ፈርሷል ፤ ሌሎቹም ፡ “ክልሎች” ፡ ይከተላሉ ። መላ፟ ፡ ኢትዮጵያ ፡ (ባሕር ፡ ምድርንና ፡ ደንከልን ፡ ጨምሮ) ፡ በዐዲስ ፡ የግዛት ፡ አወቃቀር ፡ በምትዋቀርበት ፡ ዋዜማ ፡ ላይ ፡ ትገ፟ኛለች ። መላ፟ው ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ እና ፡ ሰራዊቱ ፡ ለመሠረታዊ ፡ ለውጡ ፡ ይነ፟ሣ፟ሉ፟ ። የምልክዮሽ ፡ የ100 ፡ ዓመት ፡ ጥረትም ፥ የመኖር ፡ ምክንያቱን ፡ ዐጥቷል ፡ ባያሠኝም ፥ መዳከሙ ፡ ርግጥ ፡ ኾኗል ፤ በኢትዮጵያ ፡ ላይ ፡ ያጠላ፟ው ፡ አደጋ ፡ ግን ፡ ገና ፡ አልተወገደም ።
የተፍገመገመው ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፥ ቆዳውን ፡ እንደገለፈፈ ፡ እባብ ፥ ባዲስ ፡ ገጽታ ፡ ለመታየትና ፥ በረዥሙ ፡ ያቀደ ፡ በመምሰል ፥ ለመጪው ፡ “ምርጫ” ፡ ከመሰናዳትም ፡ ዐልፎ ፥ ስለጠቅላላው ፡ ያፍሪቃ ፡ ቀንድ ፡ አወቃቀርም ፡ ደፋ ፡ ቀና ፡ ማለትን ፡ ይዟል ። ስያሳ ፡ ግን ፡ የሚ፟ሠ፟ራ፟ው ፡ በእውን ፡ መሠረት ፡ ላይ ፡ እንጂ ፥ በምኞት ፥ ያውም ፡ በክፉ ፡ ምኞት ፡ መሠረት ፡ ላይ ፡ ሊኾን ፡ አይገ፟ባ፟ም ። የቅሬታው ፡ ይዘት ፡ መጨረሻ ፡ እንደማያምር ፡ ይህ ፡ ብቻውን ፡ ያስረዳናል ።
ምልክዮሽ ፡ በኢትዮጵያ ፡ ላለበው ፡ ፀረ ፡ ሥልጣኔ ፡ የንጥቂያ ፡ ዐላማው ፡ ፍጡሩን ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ይዘት ፡ ጠጋግኖ ፡ እስከተልእኮው ፡ ፍጻሜ ፡ ድረስ ፡ ሊሠራበት ፡ መሞከሩን ፡ በእልክ ፡ ተያይዞታል ። ይህም ፥ በተለይ ፡ ድልን ፡ በተቀዳጁትና ፡ የይዘቱን ፡ ንኅለተኛ ፡ ምኞት ፡ ፈጽመው ፡ በሚቃወሙት ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሰራዊት ፡ ከፍተኞች ፡ መኰንኖች ፡ ላይ ፡ ዐዲስ ፡ ዙር ፡ የወገዳ ፡ ዘመቻ ፡ በቅርቡ ፡ እንደሚዠ፟መ፟ር ፡ ያመለክታል ።
ሲኾን ፡ ቢውል ፡ ግን ፥ ጨለማ ፡ ብርሃንን ፡ አያሸንፈውምና ፥ ኢትዮጵያ ፥ በርትዕ ፡ ሥልጣኔዋ ፡ ብርሃን ፡ ተመርታና ፡ ጸንታ ፥ ይህንም ፡ የጨለማ ፡ ወቅት ፡ በነጻነቷ ፣ በአንድነቷና ፡ በሙሉነቷ ፡ ተሻግራው ፥ ወደ ፡ ብሩህ ፡ ነገዋ ፡ ትዘልቃለች ።
3 ፤ የውሳኔ ፡ ወቅት ።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ ኀላፊዎች ፥ እንደሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ ኀላፊዎች ፡ ዅሉ ፥ እነርሱም ፡ ይህን ፡ ሕገ ፡ ወጥ ፡ “ሕገ ፡ መንግሥት” ፦ «እናስቀጥላለን» ፡ በማለት ፡ ወደ ፡ ትፋታቸው ፡ እንዳይመለሱ ፥ ዛሬ ፡ በሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ ላይ ፡ የደረሰው ፡ መደ፟ምሰስና ፡ ዐመድ ፡ መኾን ፡ ትምህርት ፡ ይኹናቸው ፡ ሲል ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ በአጽንዖት ፡ ሊያመለክታቸው ፡ ይወዳል ።
ይልቅስ ፥ ቀና፟ውን ፡ መንገድ ፡ በመከ፟ተል ፥ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ የጠየቀውን ፡ የእግዚእናውን ፡ መከ፟በር ፡ በማረጋገጥ ፥ ዐዲስ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ ሕገ ፡ መንግሥት ፡ የሚረቀቅበትንና ፡ የሚጸድቅበትን ፡ ምዕራፍ ፡ ስለሚከፍተው ፡ የሽግግር ፡ መንግሥት ፡ መቋቋም ፡ ጕዳይ ፥ ከመላ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ተወካዮች ፡ ጋራ ፡ ለመነጋገር ፡ ሀገራዊ ፡ ጉባኤን ፡ ለመጥራት ፡ እንዲስማሙ ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ ኀላፊዎችን ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ በታላቅ ፡ ዐደራ ፡ ዳግመኛ ፡ ያሳስባቸዋል ።
መደምደሚያውን ፥ ከዚህ ፡ በላይ ፡ በተዘረዘሩት ፡ አንጻር ፡ የአዎንታዊ ፡ አቋማቸው ፡ መታመኛ ፡ ይኾንላቸው ፡ ዘንድ ፥ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ ኀላፊዎች ፦
1) እስካኹን ፡ በሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ ሲላከኩ ፡ የነበሩት ፡ በእየክልሉ ፡ የሚፈጸሙት ፡ ፀረ ፡ ሀገራዊ ፡ (ፀረ ፡ ዐማራ) ፡ ጥቃቶች ፥ ከሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ መወገድ ፡ ወዲህም ፡ መቀጠላቸውና ፡ በነገሩ ፡ የቅሬታ ፡ ይዘቱ ፡ ከፍተኞች ፡ ኀላፊዎች ፡ እጅ ፡ መኖሩን ፡ ማስረጃዎች ፡ ስላረጋገጡ ፥ እነዚህን ፡ የሀገራዊ ፡ ክዳት ፡ ወንጀሎች ፡ በፍጥነት ፡ ከማዘዣው ፡ እንዲያስቆሙ ፤ ለዚህም ፡ ተደጋጋሚ ፡ ጥፋት ፡ ዋናው ፡ ተጠያቂ ፡ “ጠቅላይ ፡ ሚኒስትር” ፡ ዐቢይ ፡ አሕመድ ፡ ስለ ፡ ኾኑ ፥ ከኀላፊነታቸው ፡ ተወግደው ፥ ምርመራ ፡ እስኪዠመር ፡ ድረስ ፥ በቁም ፡ እስርነት ፡ እንዲቈዩ ፤
2) በሠኔ ፡ ወር ፡ 2012 ፡ ዓ.ም. ፡ በሐሰት ፡ ተወንጅለው ፡ አላግባብ ፡ የታሰሩትን ፡ እንደ ፡ አቶ ፡ እስክንድር ፡ ነጋ ፡ ያሉ፟ትን ፡ የስያሳ ፡ ቡድን ፡ ኀላፊዎችንና ፡ የማወራኛ ፡ ባለሟያዎችን ፡ ከእስር ፡ ቤት ፡ በፍጥነት ፡ እንዲፈቱ ፤
3) የኢትዮጵያ ፡ አንድያ ፡ ባለቤት ፡ የኾነውን ፡ የኢትዮጵያን ፡ አንድ ፡ ሕዝብ ፥ በፋሺስታዊ ፡ እልኽ ፡ “ሕዝቦች” ፡ እያሉ ፡ ሀገሪቱን ፡ ባለቤት ፡ አልባ ፡ የሚያደርጉበትን ፡ ከፋፋይ ፡ የጠላት ፡ አነጋገር ፡ ከኀላፊዎቹና ፡ በቍጥጥራቸው ፡ ሥር ፡ ካሉት ፡ ማወራኛዎች ፡ ገለጻዎች ፡ ፈጽመው ፡ እንዲያስወግዱ ፤
4) በኢትዮጵያ ፡ አንድያ ፡ ሀገራዊ ፡ ቋንቋ ፡ በዐማርኛ ፡ ላይ ፡ እስካኹን ፡ በግልጽ ፡ ደባቸውን ፡ ሲፈጽሙ ፡ የቈዩባቸውን ፡ ነውረኞች ፡ የጠላትነት ፡ አቋምና ፡ አሠራር ፡ በይፋ ፡ አውግዘዋቸው ፥ ለሀገራዊው ፡ ቋንቋ ፡ የሚ፟ገ፟ባ፟ውን ፡ ክብር ፣ ጥንቃቄና ፡ ክብካቤ ፡ በገቢር ፡ እንዲያሳዩ ፤
5) ዛሬ ፡ ዳግም ፡ የተሰነከሉት ፡ የፋሺዝም ፡ የምልክዮሽና ፡ የአፓርትሀይድ ፡ ተምሳሊት ፥ ባለሰማያዊ ፡ መደብ ፡ ዐምስት ፡ እግር ፡ ኮከብን ፥ ቀደም ፡ ሲል ፡ እሰንደቅ ፡ ዐላማችን ፡ ላይ ፡ በውንብድና ፡ ዐዋጅ ፡ እንደለጠፉት ፡ ዅሉ ፥ መልሰው ፡ በራሳቸው ፡ ዐዋጅ ፡ በሰላም ፡ እንዲያስወግዱ ፥
እያለ ፥ ከመልካም ፡ ምኞቱ ፡ ጋራ ፥ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ያሳስባቸዋል ፥ ያበራታቸዋልም ።
ለመላ፟ው ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፥ ሰንደቅ ፡ ዐላማው ፡ የነጻነቱ ፣ የእግዚእናውና ፡ የአንድነቱ ፡ ተምሳሊት ፡ ነው ፤ ወይም ፡ በሌላ ፡ አነጋገር ፥ በራሱ ፡ ሥልጣኔ ፡ የቆመ ፡ ሐራ ፡ ሀገርነቱን ፡ በሰንደቅ ፡ ዐላማው ፡ ይመስ፟ልበታል ። በዚህ ፡ ረገድ ፥ ከማንም ፡ ፈቃድን ፡ መጠየቅ ፡ ወይም ፡ መቀበል ፡ ስለማያሻው ፥ ነጻነቱን ፡ የመዋጀት ፣ እግዚእናውን ፡ የማስከበርና ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ የርትዕ ፡ መንግሥቱን ፡ የመመሥረት ፡ የተቀደሰ ፡ ተግባሩን ፡ እዳር ፡ ለማድረስ ፥ ከእንግዲህ ፡ አረንጓዴ ፣ ብጫ ፣ ቀይ ፡ ሰንደቅ ፡ ዐላማውን ፡ ይዞ ፡ ከሰራዊቱ ፡ ጋራ ፡ በአንድነት ፡ ተነሥቷል ። ይህን ፡ በመፃረር ፡ ደፍሮ ፡ የሚመጣበት ፡ የጭቈና ፡ ኀይል ፡ ቢኖር ፡ ደግሞ ፥ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ በሰላማዊም ፡ ኾነ ፡ በማንኛውም ፡ መንገድ ፡ ሊከላከለው ፡ ሙሉ ፡ መብት ፡ አለ፟ለ፟ት ፤ የኢትዮጵያ ፡ ሰራዊትም ፥ ተገቢ ፡ መንግሥት ፡ በሌለበት ፡ ባኹኑ ፡ ኹኔታ ፥ ለሕዝብ ፡ እግዚእና ፡ የመታዘዝ ፡ ግዴታ ፡ አለ፟በ፟ት ፨
የጊዜያዊ ፡ ፈጻሚ ፡ ምክር ፡ ጽሕፈት ፡ ቤት ፥
ኢ.ሀ.ሥ.አ. ።
——-
[የኅዳግ ፡ ምልክቶች]
⁽1⁾ • ሀገራዊ፤ የነጻ፡ሕዝብ፡አባል፣ የሀገር፡ባለቤት፣ እግዚእና፡ያለ፟ው፣ ሿሚ፣ ሻሪ፡ኢትዮጵያዊ፡(citizen | citoyen)።
• ዐማራ፡(ዐም፡ሐራ)፤ ነጻ፡ሕዝብ፥ የመላ፟፡ኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡የሀገራዊነት፡ወይም፡የሀገር፡ባለቤትነት፡ስሙ፡(citizenry)።
⁽2⁾ ይዘት ፤ በግእዝ ፡ ‘እኅዘት’ ፥ አለሥልጣኑ ፥ መንግሥታዊ ፡ ኀይልን ፡ በእጀ ፡ መናኛ ፡ የጨበጠ ፡ ዐምባ ፡ ገነን ፡ አገዛዝ ፡ (“régime”) ።
⁽3⁾ ጠገዴ፡ወይም፡ጸገዴ፤ ‘ጸ’፡እና፡’ጠ’፡ባማርኛ፡ተወራራሽ፡ፊደሎች፡ስለ፡ኾኑ፥ ግዛቱ፡በኹለቱም፡አጠራሮች፡ይጠ፟ራ፟ል። እንዲሁም፡ጠለምት፡እና፡ጸለምት፥ ሞጣ፡እና፡ሞጻ፥ ጣና፡እና፡ጻና፥ ወዘተርፈ፡…።
=====================================================
የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ።
ETHIOPIANS’ CITIZEN DEMOCRATIC UNION

1 Comment

  1. የድርጂት ስም ጋጋታ እና ከ_ የማያድን መግለጫ ማንበብ እና መስምቱ ሰለቸን፡፡ ዘጠኝ ሱሪ ከእንትን አያድምንም እንደተባለው ከመግለጫ እሩምታ ይልቅ በትግባር የርስን ድርሻ መውጫቱ መልካም ነው፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.