ባለቄራው ፓስተር – አሁንገና ዓለማየሁ

የባለቄራው ፓስተር የገና መልእክት በጣም አስገራሚ ነው።

የቄራው ፍጡራን የታረዱት ወገኖቻቸው ደም ጠረን አፍንጫቸውን፣ የፓስተሩ ረዳቶች የሚስሉት ካራ (ቢላ) የፉጨት ድምጽ ደግሞ ጆሮዎቻቸውን እየረበሸው ደንዝዘው ሳሉ ፓስተሩ ግን ከወንጌል እያጣቀሱ ፍልስፍናዊ ዲስኩር ያደርጉላቸዋል።

ፓስተሩ በቄራ ውስጥ ለታጎሩት ሰንጋዎች ስለሚነጋው ጨለማ ስብከት ያደርጋሉ። መሸ ያለ ይተኛ፤ ነጋ ያለ ይነሳ። ብለዋቸዋል። መሸ ብለው ተኝተው ታርደው ይነጋል። (የሰሜን እዝ ወታደሮች፣ የመተከል፣ የጉሊሶ ነዋሪዎች፣ የሻሸመኔ የአርሲ ክርስትያኖች)። ነጋ ብለው ተነስተው በገመድ ተጠልፈው ይጣላሉ (እነ እስክንደር ነጋ፣ እነ አስቴር ቀለብ፣ እነ ልደቱ፣ እነ ይልቃል ወዘተ)። መሸ ብለው ሲተኙ በልዩ ኃይል በሳንጃ ይወጋሉ። ነጋ ብለው ሲነሱ ወደ ማጎሪያ ይነዳሉ።

ባዶ ንግግርዎ

ምን ተስፋ ያመጣል ለቄራዎ ሰንጋ
እርድ ሆኗል እጣቸው ቢመሽም ቢነጋ።

ይልቅ አይሻልም ቢሰማራ ከብቱ
ተከፍቶ በረቱ
ማረጃውም ካራ ተሰብሮ ስለቱ?

(በረት = ክልል፤ ካራ = ሕገመንግሥት)

ለተለጎሙና በቄራ ውስጥ ለተቀየዱ ሰንጋዎች ንግግር ማድረግ ምንኛ መዘባነን ነው? ጦርነቱ በድል መቋጨቱ አያጠያይቅም*። የሥልጣን ማስከበሩ ጦርነት። ከፍተኛ እልቂት እንዳስከተለ ግን የሚናገር የለም (ዲጂታሎች እንኳን በምስክርነት አይቆጠሩም)። ወር ባልሞላ ጊዜ የማይካድራ፣ ሰሜን አዝና የሁመራን ጭፍጨፋዎች ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ሰው እንዳለቀ ይገመታል። ይህንን ሰብአዊ ውድመት አስቀድሞ በኃላፊነት ስሜት በተሠሩ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሥራዎች መከላከል አይቻልም ነበርን?

“መሸ ያለ ይተኛ” የሚል ፌዝ። ማነው ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ የሰላም እንቅልፍ ተኝቶ ያደረ? ይልቁንም ባላፉት ሦስት አመታት ምን እንቅልፍ አለ? የተኛም ሲነጋ ታርዶ ይገኛል፣ ያልተኛም አልቀረለት። እንኳን በቄራ ውስጥ ያለ በሩቅም ያለ ወገን በሰቀቀን ናላው ዞሯል፣ ገላው አልቋል። አንድ ወንድሜ መንገድ ላይ የእግዜር ሰላምታ ለሚሰጡት ሰዎች የሚመልሰው አባባል ነበረው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

“እንዴት አደርክ? የሰላም እንቅልፍ አገኘህ?” ለሚለው ሰላምታ መልሱ

“ሃያ አመት ሞላኝ (ከተኛሁ)። ኢህአዴግ እያለ ምን እንቅልፍ አለ!” የሚል ነበር። የሚሰማው ሁሉ “ኧረ አንዳታስፈጀን!” ብሎ ይሸሽ ነበር።

ኢትዮጵያ ለብዙዎች መታረጃቸው ቄራ የሆነችበት የኢህአዴግ/ብልጽግና አስተዳደር የበላይ ጠባቂ ፓስተራችን (ጠ/ሚ) የዚህ ሕዝብ እርድና ሰቆቃ ይቅርና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና የመኖር መብቱ በሽብር የታጠረ መሆኑ የማይሰማቸው የማያሳቅቃቸው ናቸው። እሳቸው ባስፈላጊው አጀብ ተከብበው ያሰኛቸው ቦታ በነጻነት ስለሚንቀሳቀሱ ከአዲሳባ ጣፎ፣ ከአምቦ ነቀምቴ፣ ከደጀን ጎሐ ጽዮን፣ ከአዋሳ ዝዋይ መጓዝ፣ ከጋዛ ቴል አቪቭ እንደመሄድ የጭንቀትና የሽብር፣ በሞት ጥላ ውስጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ መሆኑ አይሰማቸውም። አያማቸውም። የነቡለንን፣ የነጉሊሶን፣ የነሻምቡን፣ የነማንዱራን፣ የነድባጤን፣ የነሆሮን ሥራ የማይቦዝኑ፣ እርድ የማያስተጓጉሉ፤ የምድር ሲዖል የአማራ ቄራዎችማ እዚህ ላይ አናነሳም። ፓስተራችን ስቅስቅ ብለው እንዳያለቅሱበን ብንተወው ይሻላል።

ዛሬ በመተከልና በኦሮሚያ የቀስት፣ የገጀራና የክላሽ ሰለባ በመሆን ሥጋት ውስጥ ለሚኖር ሕዝብ፣ ልባዊ፣ መንግሥታዊ፣ ሕጋዊና መዋቅራዊ መፍትሄ እንጂ ባዶ ንግግር ሰላም አያመጣለትም። ኑሮው በሽብር፤ ቀብሩ በዶዘር ለሆነ ሕዝብ ተረት ተረት ማውራት በሰብአዊነቱ ላይ መሳለቅ ነው።

የገናን በዓል በየጫካው፣ በየመጠለያው በየእርዳታ ካምፑና በሞቱ ቤተሰቦቻችሁ የሐዘን ጥላ ሥር ለምታሳልፉ ወገኖቻችን ፈጣሪ ብርታቱን ይስጣችሁ፣ የመከራ መጨረሻ ያድርግላችሁ።

የገናን በዓል ያለበደላችሁ በወህኒ ቤት እንድታሳልፉ የተፈረደባችሁ ወገኖቻችን የነጻነታሁ ቀን የቀረበች ትሁን።

ቀጣዩን የገና በዓል ከዚህ ሁሉ ጨለማ ነጻ ሆነን በሰላም የምናከብረው ያድርግልን።

ፈጣሪ የኛንም ሆነ የቀደምቶቻችንን በደል አያስብብን። በምህረቱ ይጎብኘን። (ኢትዝክር ለነ አበሳነ ዘትካት። ፍጡነ ትርከበነ ሣህልከ እግዚኦ እንዳለ ቅዱስ ዳዊት)

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ጦርነት እንኳን ገና በልቶ ላልጠገበ ሕዝብና ለጥጋበኞቹም አይመችም" ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

ተረኞቹ እንበላለን ብለው አበላልተውን ሀገራችንን ለባእዳን በዪዎች እያመቻቹ መሆናቸውን አላስተዋሉምና፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብለን እንጸልይ።

አሁንገና ዓለማየሁ

______

* ለሕወሃት ውድቀት ላደረጉት ታላቅ አስተዋጽኦ ጠ/ሚ ዐቢይን ሳላመሰግን አላልፍም። ለነዚያ አሸባሪ አዛውንትና የግፍ ድርጅታቸው ሕወሃት ውድቀት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እግዚአብሔር ይስጣችሁ ለማለት እወዳለሁ። በተለይ የደሃው ገበሬ ልጆች የከፈላችሁት መስዋእትነት ትውልድ የማይዘነጋው ነው።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share