ሚዛኑን ከሳተ ውዳሴ እና ስሜታዊነት ከሚነዳው የፖለቲካ አባዜ እስካልወጣን ድረስ … – ጠገናው ጎሹ

December 20, 2020
ጠገናው ጎሹ

 

ውዳሴን (ምሥጋናን) በትክክል ወይም በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ለተሻለ ሥራና ውጤት ማበረታቻ መሆኑ ይቀርና ማባለጊያና መባለጊያ ይሆናል ። ይህ አይነቱ በትክክለኛና ፅዕኑ መርህ ላይ ያልቆመ ፣ ከተፈላጊው ግብ ጋር ያልተቆራኘ ፣ በግልብ ስሜት የሚነዳ እና ሚዛናዊነት በእጅጉ የሚጎድለው ውዳሴ (አድናቆት) ፈጣሪያቸው፣ አሳዳጊያቸውና የበላይ አለቃቸው የነበረውን ህወሃትን ከትክሻቸው ላይ በማውረድ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ተዘፍቀው የነበሩበትን አስከፊ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ሥርዓትን እያስቀጠሉ “የዴሞክራሲዊ ለውጥ ሐዋርያት ነን” በሚል በመከረኛው ህዝብ ላይ ለሚሳለቁ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ሲውል ደግሞ አስከፊነቱ እጅግ ግዙፍና መሪር ነው። ከክስተቶች የሙቀት መጠን ጋር ልጎም በሌለው ግልብ ስሜት እየተነዱና እራሳንን ለሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ማድመቂያ አሻንጉሊትነት አሳልፎ እየሰጡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ወይም ዴሞክራሲያዊት አገርን መናፈቅን የመሰለ ክፉ አባዜ የለም ።

ለዘመናት ከመጣንበት በእጅጉ ከተሳከረ ፣ ግልብና ጎጅ ከሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለመማርና ሰብሮ ለመውጣት ፈቃደኞች፣ዝግጁዎችና የተግባር ውሎ ኢትዮጵያዊያን ሆኖ የመገኘት የፖለቲካና የሞራል አርበኝነቱ ዛሬም እንኳን ያለንበትን ፈተና በሚመጥን ደረጃ ገና በቅጡ የተጠጋንም አንመስልም። አዎ! በፅዕኑ መርህ ላይ ለተመሠረተ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ግብ እውን መሆን በጋራ ፀንተን የምንቆም የተፎካካሪነት ፖለቲካ መሪዎች ወይም አክቲቪስቶች ወይም የሙያና የሠራተኛ ማህበራት መሪዎች ወይም ትውልድን በእውነተኛ የመማር ትርጉም ቀራፂ መምህራን (ምሁራን) ወይም የኪነ ጥበብ ጥበበኞች ወይም የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎችና አስተማሪዎች ወይም የአገር ሽማግሌዎች፣ ወዘተ ሆነን ለመገኘት ባለመቻላችን ግዙፍና መሪር ዋጋ የተከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ትግል ለሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች አሳልፈን በመስጠት መልሰን እንነሱኑ “እግዚኦ አድኑን!” እያልን ከመማፀን የከፋ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ቀውስ ጨርሶ የለም።

አዎ! የገንዛ እራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ በግልፅና በቀጥታ መጋፈጥ ሲያቅተን ወይንም ፍርሃት ሲያሸንፈን የምንመርጠው ልፍስፍስ ሰበብ በመደርደር እራሳችንን መሸንገል (ማታለል) ስለሚቀናን ነው እንጅ ለዘመናት መሬት ላይ ተዘርግቶ የኖረውና አሁንም የቀጠለው ግዙፍና መሪር እውነት ይኸው ነው።

በዚህ ግዙፍና መሪር የፖለቲካ እውነታ ውስጥ በምንገኝበት ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህወሃት ደናቁርትና እብሪተኛ መሪዎች ብቻ የሰጠውን የጁንታነት ስያሜ ሌላ ቃል ጨርሶ ያጣንለት እስኪመስል ድረስ የህወሃት ብቻ በማድረግ እንደ በቀቀን እየተቀበልን እስኪ ሰለች ድረስ በማስተጋባት ክፉ አባዜ ተጠምደናል። ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የህወሃት ታማኝ መሣሪያ በመሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በአያሌ ንፁሃን ዜጎች የቁም ስቃይና ደም የተዘፈቀውን እጃቸውንና ህሊናቸውን በቅጡ (በህዝብና በፍትህ አደባባይ) ለመናዝዝና ተጠያቂነትን ለመውሰድ ቢያንስ የሞራል ዝግጁነት ያላሳዩትንና ይልቁንም እርስ በርሳቸው እየተሸላለሙና እየተሿሿሙ የቀጠሉትን ብልፅግናዊያን ፖለቲከኞች “እንደ ማቱ ሳላ እድሜያችሁን ያርዝምልን” የሚል አይነት እጅግ የወረደ ውዳሴ ቅኔ ከመቀኘት የሚከፋ የፖለቲካና የሞራል ኮስማናነት ከቶ የለም ።

ለዚህ እጅግ የወረደና አስቀያሚ “የእድሜ ያርዝምልን” ውዳሴ እንደ ወ/ት ብርቱካን ሜደቅሳ የመሰሉና እኩይ የሆነው ህወሃት/ኢህአዴግ ሠራሹና መራሹ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ተወግዶ በእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይተካ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ወገኖች የማሰቢያ ጊዜ እንኳ ሳይጠይቁ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ መጫወቻ ካርድ የሆነው ምርጫ ቦርድ ተብየ የመሪነት ሹመትን የመከራና የውርደት ምንጭ በሆነው ህገ መንግሥት ምለውና ተገዝተው በመቀበል “የመልካም ገፅታ” ሽፋን ሲሰጡት መታዘብ ደግሞ የህሊና ህመሙ ከባድ ነው ።

 

አዎ! ከሁለት ዓመታት በላይ

  • የጎሳና የቋንቋ ማንነትን መሠረት ባደረገ እና እንኳን በገንዛ አገር ልጅ በሰው ፍጡር ላይ ይደርሳል የማባይል የቁም ሰቆቃና የግድያ ዘመቻ ያለማቋረጥ በቀጠለበት
  • የቤተ መንግሥት ፖለቲካውን የተቆጣጠሩት ብልፅግና ተብየዎች መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ በማካሄድና ሰፊ የህዝባዊ ንቅናቄ ድጋፍ በማግኘት የህወሃቶችን እብሪት ወይም እብደት ዋጋው ባነሰ ሁኔታ ማስወገድ እየቻሉ በተረኝነት አባዜ በመጠመዳቸው የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እጅግ አስቀያሚ ደም መፋሰስ ባስተናገደበትና ቀሪው አሉታዊ ተፅእኖውም ቀላል በማይሆንበት
  • በህወሃት ሠራሹ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ህገ መንግሥት ፣ የፓርቲና የመንግሥት አወቃቀር ላይ በተረኝነት የተዘፈቁና ብልፅግና በሚል የለየለት የማታለያ ስያሜ እራሳቸውን የሰየሙ ኢህአዴጋዊያን ህወሃትን የትግራይ ብልፅግና ብለው በሰየሙት አሻንጉሊት ተክተው ዴሞክራሲ እየጎሞራ ስለመሆኑ በተለመደና እጅግ አሰልች በሆነው የርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መከረኛውን ህዝብ እጅግ በሚያሰለቹበት
  • አብዛኛው ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ተብየ የሸፍጠኛና ሴረኛ ርካሽ የመደመር ፖለቲካ ሰለባ በሆነበት
  • የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ግድ ይለዋል በሚል የታገሉ እንደ እስክንድር ነጋ የመሰሉ ንፁሃን ወገኖች ከበሰበሰውና ከከረፋው የፖለቲካ ሥርዓት አገልጋይነት ያልተላቀቀው የፍትህ አካል ተብየ ሰለባ በሆኑበት
  • እንኳን በክልልና ዞን በመዲናዋ አዲስ አበባም በአደባባይም ሆነ በአዳራሽ ተሰባስቦ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለዘመናት ከተዘፈቀበት የመከራና የውርደት አዙሪት እንዴትና መቼ ማውጣት እንደሚቻል ያለ ሥጋትና በነፃነት መነገጋጋር ጨርሶ በማይቻልበት
  • የዓለምን ህዝብ ሁለንተናዊ ህይወት በእጅጉ እየተፈታተነ ያለው የኮሮና ቫይረስ የሁለንተናዊ ድህነት ሰለባ በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት ላይም ከባድ ሥጋት እየደቀነ ባለበት፣
  • ከጎሳ ፖለቲካ ንግድ እናተርፋለን ባይ እኩያን የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች የክልል መንግሥታትን ለመፍጠር የሚያካሂዱት የሞት ወይም የሽረት አይነት የፖለቲካ ጨዋታ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው በሚባልበት
  • ኢትዮጵያዊያን ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ፀጉረ ልጥ በማሰኘት ለቁም ስቃይና ለግድያ እየዳረጋቸው ያለውን የዘርና የቋንቋ አጥንት ስሌት እያሰሉ ለመንቀሳቀስ በተገደዱበት ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ እነ ወ/ት ብርቱካን የተሳካ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቱን እንዳጧጧፉት የሚነግሩን “የምሥራች” በግልፅ የሚያሳየን የሥርዓት ሳይሆን የሥልጣን ተረኝነት ፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱትን ፖለቲከኞች በማስመሰል ምርጫ ሥልጣናቸውን እንዲያደላድሉ ማስቻልን ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ይህ አይነት እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ሰብእና የሚመነጨው ደግሞ ብርቱ ከሆነ የአድር ባይነት (severe oportunism) ልክፍት ካልሆነ ሌላ ከየት ሊሆን ይችላል?

“የእኛና የእኛ ብቻ ነው” በሚሉት ክልል ውስጥ የሆነውና እየሆነ ያለው ንፁሃን ዜጎችን ከደመ ነፍስ እንስሳት እጅግ ባነሰ ሁኔታ በቁም ስቃይና በግድያ መድረሻ የማሳጣት ዘመቻ እና ቤንሻንጉል ድረስ ተሻግረው እንዲፈፀም እያደረጉት ያሉት ለማየት ቀርቶ ለመስማት በእጅጉ የሚከብድ ግፍና መከራ አልበቃ ብሎ ወደ ወሎ እየዘለቁ ያዘጋጁትን ግዛት የማስፋፋት እኩይና አደገኛ ቅዠት ሊያለማምዱን ለሚሞክሩት የኦሮሙማ (orromization) ፖለቲከኞች በምርጫ ይሁንታ (legitimacy) ለማላበስ የሚደረገው የምርጫ ትርክትና ዝግጅት የመከረኛውን ህዝብ ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዘመን ከማራዘም ውጭ ከቶ ሌላ ትርጉም አይኖረውም።

ከሰሞኑ የተካሄደውንና በህወሃት ተሸናፊነት ተቋጨ የተባለውን ጦርነት ተከትሎ የምንሰማቸውና የምናያቸው ሚዛናዊነትና አርቆ አሳቢነት የሌላቸው ውዳሴዎች የአገራችንን የፖለቲካ ባህልና አስተሳሰብ ለሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ምቹ ሰለባ ሆኖ መቀጠሉን ነው የሚነግሩን።

የህወሃት ፖለቲከኞች እብሪት ወይም እብደት ከልክ በላይ ገንፍሎ በመደበኛ ወታደራዊ ሠፈር (ካምፕ) በነበሩ የአገሪቱ ወታደሮች ላይ እጅግ አስነዋሪና አሰቃቂ እርምጃ መውሰድ እና የአዲስ አበባዎቹ ደግሞ ከዚህ በላይ መታገስ ነገ ቤተ መንግሥታቸውም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንደሚገጥመውና ሥልጣናቸውም ወደ የማይመለስ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ሲያውቁ ጦርነቱ ታወጀ። የመከላከያ ሠራዊት ቅጥ ባጣውና ጭካኔ በተሞላበት የህወሃቶች እኩይ ድርጊት ላይ ለምን እርምጃ ወሰደ የሚል ጤናማ ህሊና ያለው የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነው የምንለው የመከላከያ ሃይል በተለይ በኦሮሚያ ክልልና ቀጥሎም በቤንሻጉል ክልል የጎሳ/የቋንቋ ማንነትን መሠረት አድርጎ የተፈፀመውንና እየተፈፀመ ያለውን የአያሌ ንፁሃን ዜጎች የቁም ሰቆቃና የግፍ ግድያ ሲሆን ቀድሞ ለመከላከል ቢያንስ ደግሞ ፈጥኖ ለመድረስ ያለመቻሉን ወይም ያለመፈለጉን መሠረታዊ ምክንያት አጥብቆ መጠየቅ ግን እጅግ አስፈላጊና ትክክል ነው። ለዚህ ተገቢ ጥያቄ ተገቢ መልስ ለመስጠት አለመፈለግ በህወሃት ላይ አስገኘ በሚል የምናዥጎደጉደውን ውዳሴ በእጅጎ ጎደሎ ያደርገዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የት ናችሁ የትግራይ ልሂቃን? - ከአንተነህ መርዕድ

አዎ! ምንም እንኳ ጦርነቱ በአንድ ሥርዓት ውስጥ የነበሩና በሁለት አንጃ ተሰንጥቀው የሥልጣን ትንቅንቅ (power struggle) በማድረግ መከረኛውን ህዝብ ለዘመናት ካወረዱበት የሞትና የቁም ውርደት አዙሪት እንዳይላቀቅ ባደረጉ ሃይሎች ምክንያት የተካሄደ ቢሆንም የዋናው ሰይጣናዊ ፖለቲካ ሥርዓት ወላጅ የሆነው ህወሃት መመታት ስለነበረበት ጦርነቱን መደገፍ ትክክል ነበር። ይህ ግን እጅግ አያሌ ንፁሃን ዚጎች ከሁለት ዓመታት በላይ እያስቆጠረ ባለው በይፋ ያልታወጀ ፣በማንነት ላይ ያነጣጠረና እጅግ ዘግናኝ የሆነ አፈና እና ግድያ ሰለባ ሲሆኑ ሃላፊነታቸውን ያልተወጡትን ከፍተኛ የሲቭል ባለሥልጣናትንና ወታደራዊ አዛዦችን ከተጠያቂነት ከቶ ሊያድናቸው አይችልም ። ከዚህ ተጠያቂነት ነፃ እንዲሆኑ መፍቀድ በንፁሃን ወገኖች የቁም ስቃይና የግፍ አሟሟት መቀለድ ነው የሚሆነው። ለዚህም ነው ውዳሴያችን ሚዛናዊ እና ስሜታዊነታችን በቅጡ ማድረግ አለብን ማለት ትክክል የሚሆነው።

ጦርነቱ ጁንታ የተሰኙትን በማስወገድ (ከባድ ዋጋ ማስከፈሉ ሳይዘነጋ) ሥርዓቱን ግን በተረኝነት ለማስቀጠል እንዲያስችል ተደርጎ የተጀመረበትንና ተጠናቀቀ የተባለበትን የፖለቲካ ጨዋታ ለምንና እንዴት ብሎ አለመጠየቅም ለሌላ ረጅም ዘመን የሸፍጠኛ ሴረኛ ፖለቲከኞች ሰለባነት እራስን አሳልፎ መስጠት ነው የሚሆነው።

ህወሃት መመታት ነበረበት ወይም አለበት ስንል የዜግነት መሠረታዊ መበትን መሠረት ያደረገ እና የቡድን (የብሄረሰብ/የጎሳ ወይም ሌሎቼ ማንነቶች) የሚከበሩበት መሠረታዊና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ መንገድ ይከፍታል በሚል ፅእኑ እምነት እንጅ በህወሃት የተለከፉበትን የፖለቲካ ካንሰር ልክፍት እንደተሸከሙ ኢህአዴግነታቸውን የኦሮሞ ብልፅግና፣ የአማራ ብልፅግና፣ የደቡብ ብልፅግና ፣ የሲዳማ ብልፅግና፣ ገና ወደፊት የሚወለዱ ብዙ የማንነት ብልፅግናዎች እና የዚህ ወይም የዚያ ክልል ነፃ አውጭ ድርጅቶች ብሎ በመሰየም ተጨማሪ (ቀጣይ) የመከራና የውርደት ዘመናትን ያስቆጥሩን ዘንድ እንድንፈቅድላቸው በፍፁም አልነበረም ።ሊሆንም አይገባውም ።

በአንድ በኩል ህወሃትን ብቻ ማስወገድ የትግሉ አልፋና ኦሜጋ አስመስለውና በሌላ በኩል ደግሞ በተረኝነት ተተክተው የህወሃት/ኢህዴግን ሥርዓተ ፖለቲካ ከነ ህገመንግሥቱና አወቃቀሩ እጅግ በተፋጠነና በከፋ አኳኋን ለማስቀጠል ሌት ተቀን በመሥራት የተጠመዱትን ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ሳይመሽ በጊዜ ለሁሉም የሚበጅ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ወደ የሚሆንበት መስመር ግቡ ማለት የግድ ነው። በእውን የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን መሆንን የምንፈልግ ከሆነ ክስተትን እየተከተሉ ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችንና ግብረ በላዎቻቸውን ከማሞካሸት ወይም ከማማረር ክፉ የፖለቲካ አባዜ ሰብሮ መውጣትን ግድ ይለናል።

የሥልጣንና የግል ዝና አፍቃሪነት (narcissism) ፣ በጎሳ እና በዜግነት (በኢትዮጵያዊነት) ፖለቲካ መካከል የመደነስ ( dancing hypocritical/cynical political dance )፣ መሬት ላይ ወርዶ ህይወት የማይዘራ ዲስኩር አብዝቶ የመደስኮር (highly inflated and impractical rhetoric)፣ በሳል የሚመስል ግን እጅግ እንጭጭ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ (deceivingly matured but actually infantile political thinking) ችግር ያለበትን ጠቅላይ ሚኒስትር በትክክልና በአግባቡ በመተቸት ተገቢውን እውቅና ከመስጠት ይልቅ ከእውነታው ጋር በማይገናኝ ውዳሴ ማሞካሸት ማቆሚያ ባጣው የሚሊዮኖች ንፁሃን ዜጎች የቁም ሰቆቃ የግፍ አሟሟት መሳለቅ ስለሚሆን ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ መታረም ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ ባመፈለጋችን ወይም ባለመቻላችን ለውጥ መጣ በሚል ጮቤ ረግጠን ሳንጨርስ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ለማየትና ለመስማት በእጅጉ የሚከብድ የአያሌ ንፁሃን ዜጎችን የቁም ስቃይና የግፍ አሟሟት ከምር ሊፀፅተንና ታዲያ እኛስ ምን አደረግን ? አሁንስ ምን እያደረግን ነው? ነገና ከነገ ወዲያስ ? ብለን እራሳችንን እንድንጠይቀው ግድ ይለናል። ተያይዞ መዳንን እንጅ ተያይዞ መተላለቅን ከምር የምንፀየፍና የምንቃወም ከሆነ ተያይዞ የመዳኛው መንገድ የየራስን ህሊና ጠይቆና ወቅሶ የሚበጀውን ማድረግ ነው።

እጅግ ሸፍጠኛና ጨካኝ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ማንነት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴ ገዥ ቡድኖች (ህወሃቶች/ኢህአዴጎች) ሩብ መቶ ክፍለ በአያሌ ንፁሃን ዜጎች የቁም ስቃይና ደም የተጨማለቀው የፖለቲካ ማንነታቸው እረፍት በነሳቸው ቁጥር ይኸውና ዛሬም የሁለንተናዊ ውድቀት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን ህገ የመንግሥት ተብያቸውን በማስከበር ስም እየተጠዛጠዙ (እየተነካከሱ) አልፈታልህ ያለው አስከፊ ችግር (ፈተና) የዴሞክራሲ እጦት እንጅ በአብሮነትና በመከባበር አብሮ መኖር ያልሆነውን መከረኛ ህዝብ ቁም ስቅሉን እያስቆጠሩት ቀጥለዋል።

በእነዚህ የአንድ ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብና መዋቅራዊ አገዛዝ ውላጆች በሆኑ አንጃዎች መካከል የተካሄደውና ከፍፃሜው በኋላ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተፅእኖ (the lingering negative imact) በቃል እንደምንለው ቀላል የማይሆንውን ደም አፋሳሽ እና አያሌ ንፁሃን ዜጎችን ለመፈናቀልና ለስደት የዳረገውን ጦርነት ልኩን ከሳተ የድል አድራጊነት ጮቤ ረገጣና እርስ በእርስ የመሞካሸት አባዜ ታግሰን በጥሞና ልናስብና ልንጨነቅ ግድ ይለናል። መከራና ውርደት በዚህ ትውልድ እንዲያበቃ ከምር የምፈልግ ከሆን ትክክለኛውና አዋጭው መንገድ ይኸው ነው።

አዎ! እያልኩ ያለሁት እኩያን የህወሃት መሪዎችን ያለምንም የንብረትና የሰው ህይወት መስዋእትነት በእጅ ሥር ማስገባት የግድ መቻል ነበረበት አይደለም። እያልኩ ያለሁት ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የተከፈለበትን ወርቃማ የለውጥ እድል ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የለውጥ አቅጣጫና ግብ በሚወስደን አገራዊና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ አውድ (political space/environment) አማካኝነት ማስኬድ የነበረብንን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ፈሩን እንዲስት ስላደረግነው ይኸውና አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለን ነውና አሁንም ልብ እንግዛ ነው።

 

በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ጨርሶ የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ

ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት እያስቀጠሉ ህወሃትን ከፖለቲካ ምህዋሩ ማስወጣት የትግሉ አልፋና ኦሜጋ አድርገው ከእነሱ ጋር የተደመረ የለውጥ አካል እና ያልተደመረ ግን ፀረ ለውጥ (አፍቃሬ ህወሃት) የሚል እጅግ የተለመደና አሰልች የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ከተዘፈቅንበት የመከራ አረንቋ (horrifying quagmire) አያወጣንምና ቆም ብለንና ትንፋሽ ወስደን እናስተውል ነው እያልኩ ያለሁት።

አዎ! እያልኩ ያለሁት በወቅቱ ለለውጥ ዝግጁ እንደሆኑ የሰበኩንን (የደሰኮሩልንን) ሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያንን ወይም የዛሬዎቹ ብልፅግናዊናንን ገንቢነት ባለው እና ግልፅና ቀጥተኛ በሆነ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ለመታገል ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ሆነን ባለመገኘታችን ዛሬም ከመግደልና ከመገዳደል የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን ከእራሳችን ጉዳት በላይ የዓለም መሳለቂያ ሆነናልና ልብ ገዝተን የሚበጀውን እናድርግ ነው።

አዎ! እያልኩ ያለሁት ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በጎሳ/በቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ በክላችሁ የብልግና ፖለቲካ ሥልጣናችሁ ተከላካይ (ዋስትና) ያደረጋችሁትን የመከላከያ ሠራዊት ከዚህ ክፉ ደዌ አላቃችሁ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ህይወትና ደህንነት የሚገደው አድርጉት ነው።

ኢህአዴግነታቸውን ብልፅግናዎች በሚል ስያሜ የለወጡ ፖለቲከኞች የፖለቲካ መጫወቻ ማእከሉን በበላይነት ይዘውረው የነበረውን (ህወሃትን) በማስወገድ እራሳቸውን በተረኝነት ከመተካት ያለፈና ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የሚወስድ መሠረታዊ እርምጃ ጨርሶ ባልወሰዱበት ሁኔታ ውስጥ “ ብሶት የወለደን የለውጥ ሃዋርያት ነን” ሲሉን “ብሶት የወለዳችሁ ምድራዊ ሃይል ሳትሆኑ ከሰማየ ሰማያት የላከልን ሙሴዎቻችን ናችሁ” ብለን የተቀበልን እለት ነው ለሆነውና እየሆነ ላለው የመከራና የውርደት ዶፍ ሰፊውን በር በርግደን የከፈትንለት ።

እንዲህ አይነቱ ለዘመናት የመጣንበት እጅግ አስከፊ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ አዙሪት (political vicious cycle) በሚመጣው ሳይሆን በዚህ ትውልድ ፍፃሜ ሊያገኝ ይገባል በሚል ፅእኑ መርህና ዓላማ ላይ ፀንተን አልተገኘንም። ይህንም ባለማድረጋችን በጋራ አገራዊ ግንዛቤና አቋም ላይ የተመሠረተ እና በፅዕኑ መርህ ላይ የቆመ ዴሞክራሲያዊ ሃይል (ድርጅት) እውን ለማድረግ አልተቻለንም። ይባስ ብለን ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የሚወስዱ መሠረታዊ እርምጃዎች ጨርሶ በሌሉበት ከርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ጠቀሜታቸው አንፃር እየታዩ የሚወሰዱ ክስተቶችን እየተከተልን በስሜታዊነት ፈረስ ከመሸምጠጥና ተፈትነው መላልሰው ለወደቁት ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች የውዳሴ ገፀ በረከት ከማዥጎድጎድ ክፉ ልማድ ለመውጣት ከየራሳችን ህሊና ጋር ትግል ማድረግ ይኖርብናል። በሚያሳዝን መልኩ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን አጥብቀን ከምንመኘው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተቃራኒው እየሆነብን ተቸግረናልና ለምንና እንዴት ብለን እራሳችንን እንጠይቅ ፤ እርስ በርሳችንም እንጠያየቅ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አዳፍኔንም መክሸፍንም ነው ያየሁበት - ዳዊት ዳባ

በቁጥር ቀላል ያልሆኑ በእድሜ ተሞክሮና በእውቀት የአንጋፋነትን ስም ያተረፉ ምሁራንን ጨምሮ ፊደል የቆጠሩ ወገኖች የለውጥ ሐዋርያት ነን ባይ ፖለቲከኞችን ወደ አምልኮ የሚጠጋ የፖለቲካ ሰብእና (cult of political personality) በማላበስ ከመከራው ስፋትና አስከፊነት የተነሳ በለውጥ ስም ወደ መንበረ ሥልጣን ላይ በሚወጣ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኛ የሚነገረው (የሚሰበከው) መልካም ቃል ሁሉ እውነት እየመሰለው የተቸገረውን የአገሬ ህዝብ ይበልጥ ግራ በማጋባት ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ከከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዓላማ፣ አቅጣጫ ፣መርህና ግብ ተንሸራቶ ይኸውና ከእራሱ ጉዳት አልፎ የዓለም መሳለቂያ እንዲሆን ጉልህ አስተዋፅኦ አድርገዋል ።

 

  • የሸፍጥና የሴራ ውላጅ የሆነውና በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውና የከረፋው የህወሃት/ኢህአዴግ ሥርዓተ ፖለቲካ ከሥረ መሠረቱ ተነቅሎ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እስካልሆነ ድረስ ትግላችንን ላለማቋረጥ ቃል ለምድርና ለሰማይ ይሁንብን ” እያሉ በየአደባባዩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲነግሩን (ሲሰብኩን) የነበሩት አብዛኛዎቹ “የተፎካካሪ” ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች ነን ባዮችም ህወሃትን ከትከሻቸው ላይ አውርደው የዚያው ሥርዓት ተረኛ የበላይ ገዥዎች የሆኑትን ፖለቲከኞች የሸፍጥና የሴራ ተሃድሶ አወዳሾችና ፍርፋሪ ለቃሚዎች በመሆን እጅግ ውድ ዋጋ የተከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ወርቃማ ዓላማና ግብ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሰውበታል። በሚሳዝን ሁኔታ አሁንም እንኳን ከስህተት ሊማሩና ሊታረሙ “የለውጥ ሐዋርያትን” የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ለመከላከል የማይደርቱት የትንታኔ ድሪቶ የለም።

አዎ! አሁንም አብዛኛዎቹ ምሁራንና “ተፎካካሪ” ፖለቲከኞች በአብዛኛው የተጠመዱት የህወሃት ጁንታዎች የተሰኙት በጦርነት መሸነፍ የህወሃት ህልውና እንዲያከትም በማድረግ በኢህአዴጋዊያን/በብልፅግናዊያን እየተመራ ያለውን

የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ሂደት ድል በድል ያደርገዋል በሚል የትርክት ድሪቶ ላይ እንጅ የዚህ ሁሉ አገራዊ መከራና ውርደት ዋነኛ ምንጭና ምክንያት የሆነው ህወሃት/ኢህአዴግ ሠራሽ ሥርዓትን አስወግዶ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሶያዊ ሥርዓት የሚወስድ አስተሳሰብና አሠራር አሁንኑ መጀመር አለበት የሚል አይደለም። ይባስ ብለው አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ መጭውን ምርጫ “እንደሚያሸንፉ” ለሚጠበቁት ብልፅግናዎች ታማኝ ድጋፍ ሰጭ በመሆንና ለዚህ ውለታም ጥቂት ወንበሮችን በመቀበል የተከበሩ የፓርላማ አባል እየተባባሉ ቀሪ እድሜያቸውን ለመኖር (መኖር ከተባለ) ከወሰኑ ሰንብተዋል። ከርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ መጫወቻ ካርድነት ለመውጣት ያልሆነለት የምርጫ ቦርድ ተብየው ሹመኞችም እየነገሩን ያለው መሪር ሃቅ ይኸው ነው።

ክርስቶስ የሚፀየፋቸውንና በተለይም ለሥልጣናቸው ጨርሶ ገደብ ባልነበራቸው ገዥዎችና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ይፈፀሙ የነበሩ ኢፍትሃዊነትን፣ የሰብአዊ መብት ረገጣን፣ መገዳደልን ፣ጭቆናን፣ ስግብግብነትን፣ ሃሰትን፣ ጥላቻን፣ ሸፍጥን፣ ሴረኝነትን፣ ምቀኝነትን፣ አድርባይነትን ፣ የሞራልና የመንፈስ ድህነትን ፣ ወዘተ ግፉአን ወደ ሚኖሩበት ሁሉ እየተዘዋወረ ያስተማረውና በመጨረሻም የተሰቀለበትን መስቀል እስከሚሰቀልበት ቦታ አሸክመው እያዳፉና እያንገላቱ በመውሰድ “ስቀለው፣ ስቀለው ፣ ስቀለው ” ብለው ሲያሰቅሉት በፀጋ የተቀበለበት ሚሥጥር በገሃዱ ዓለማችን ክፉ ነገርን የመቃወምና ለበጎ ነገር ፀንቶ የመቆም ፈተና ከቶ ተመን የማይገኝለትን የህይወት ዋጋ እስከማስከፈል ሊያደርሰን እንደሚችል አውቀን ዝግጁዎች እንደንሆን ሊያስተምረን ጭምር እንጅ መሰቀሉንና መነሳቱን እናምናለን ስላልን ብቻ ተስፋ የምናደርገውን የሰማይ ቤት እንድንወርስ አይደለም። ታዲያ በዚህ ክርስቶስ የሰው ልጅን ከኋጢአት ለመታደግ (ኋጢአት ከላይ ለማሳየት የሞከርኳቸው ክፉ ባህሪያትና ሥራዎች ማለት እንጅ ሌላ ሚሥጥርነት የለውም) የሠራውን እጅግ ድንቅ ሥራ ተመረንበታልና ተመራምረንበታል የሚሉን እንደ ሙአዘ ጥበባት (መቸም የተግባር እንጅ የሹመት አይነት እያነሱ መለጠፍ ችግራችን አይደለም) ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አይነት ወገኖች ለምን የቤተ መንግሥት ፖለቲከኛች አማካሪዎችና የውዳሴ ቅኔ ደርዳሪዎች ሆኑ የሚል ደምሳሳ (ምክንያት አልባ) ትችት ለመሰንዘር አልሻም ። ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ተዘፍቀው የኖሩበትን የጎሳ/የቋንቋ ማንነት ስሌት የፖለቲካ ሥርዓት እንዲቀጥል በማድረግ እስከ አሁኗ ጊዜ ድረስ ንፁሃን ዜጎች የቁም ስቃይና የአሰቃቂ ግድያ ሰለባዎች ሲሆኑ ሃላፊነታቸውን አለመወጣት ብቻ ሳይሆን እንመረዋለን የሚሉት መንግሥት አካላት የድርጊቱ አነሳሽና ተሳታፊ በሆኑበት የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና መሰሎቹ ምንና እንዴት ብለው እንደሚያማክሩ መጠየቅ ግን ቢያንስ የሞራል ግዴታ ነውና በግልፅና በቀጥታ መጠያየቅን ግድ ይላል የሚለው ግን ፅእኑ እምነቴ ነው። የቤተ መንግሥት ፖለቲካ አማካሪና የሥነ መለኮት “ጠበብቱ” ዲያቆን ሙአዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ከአሁን በፊት ንፁሃን ዜጎች በተገኙበት ማህበረሰብ ማንነትና በሚከተሉት ሃይማኖታዊ እምነት ምንነት እየተለዩ ለቁም ሰቃይ ሲዳረጉና ከደመ ነፍስ እንስሳት አሟሟት በከፋ ሁኔታ ሲገደሉ ለማስቆም ይቅርና ትርጉም ያለው የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ ያልቻለውን ጠቅላይ ሚኒስትር “ኢትዮጵያን ባነሱ ቁጥር በእንባ ጎርፍ ይታጠባሉ” የሚለውን የአማካሪነቱን ምሥክርነት በየቀኑ ከምናየውና ከምንሰማው መሬት ላይ ያለ መሪር እውነታ በላይ አምነን እንድንቀበለው ሊያሳምነን ሲቃጣው አንድችም አይነት የይሉኝታ ስሜት አይታይበትም። መቸም ይህች ጉደኛ አገርና መከረኛው ህዝቧ በየጊዜው ከገጠሟቸውና ከሚገጥሟቸው ፈተናዎች መካከል አንዱ የዓለማዊው ቤተ መንግሥትና የሰማያዊው ቤተ ህይወት መቀላቀል መሆኑ አዲስ ነገር ባይሆንም እውነተኛውን የሰማያዊ ጌታ እና ሸፍጠኛና ሴረኛ የምድሩን ፖለቲከኛ በእኩልነት አገለግላለሁ የሚል ግልፅ የአድርባይነት ባህሪ ግን ጨርሶ አደገኛ ነው። ለሙአዘ ጥበባት ዲያንቆን ዳንኤልና መሰሎቹ ግን ይህ ትክክልና የሚቻልም ነው። ከሰሞኑ ደግሞ ጁንታ የተሰኙት የህወሃት መሪዎች ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ ላባረሯቸው የቀድሞ አሸከሮቻቸው በነበራቸው ጥላቻና ንቀት በለኮሱት ጦርነት መሸነፋቸውን ተከትሎ እነማንን እንደሆነ በግልፅና በቀጥታ ለመናገር ባልደፈረው ዲስኩሩ “…እባካችሁ ወደ ላይ ከወጣንበት ከፍታ ወደ ታች አትጎትቱን” በሚል ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገኙበትን አስከፊና አሳዛኝ ሁኔታ የማያሳይ የዲስኩር ድሪቶ መደረቱን ተከታተልኩት። ግን ጨርሶ አልገረመኝም። መከረኛው የአገሬ ህዝብ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከኖረበት (መኖር ከተባለ) የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት ተገላግዬ በእኔና ከእኔ ተሠርቶ ለእኔ የሚበጅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆንልኛል የሚለውን ራዕዩን ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች አኮላሽተውበት ስለዴሞክራሲ ሳይሆን በህይወት ስለመሰንበትና እንደ አገር ስለመቀጠል ወይም ስላለመቀጠል የሚጨነቅበትን ግዙፍና መሪር እውነት “ከፍተኛው የኩራት ማማ ላይ ወጥተናልና ወደ ታች አትጎትቱን” በሚል ሲገልፀው ጨርሶ ህሊናውንም ሆነ አንደበቱን አልጨነቀውም። እንግዲህ ልብ በሉ! በእጅጉ የተወሳሰበውንና የተጎሳቆለውን የአገሬን ህዝብ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እውነታ መርምረውና ተንትነው ለቤተ መንግሥት ፖለቲከኞች የፖሊሲ ቀረፃ የሚበጅ ሃሳብ የሚያቀርቡት እንዲህ አይነት አማካሪዎች ናቸው። መውረድን መውጣት፣መውደቅን መነሳት፣ መጠላትን መፈቀር፣ ኢፍትሃዊነት ፍትሃዊነት፣ የንፁሃን ዜጎች እንግልትንና እሥራትን የፀባይ ማረሚያ፣ የህወሃት መሪዎችን የጦርነት ውሎ ሽንፈት የነፃነትና የዴሞክራሲ አልፋና ኦሜጋ (ከፍታ የሚለው ይህን ሳይሆን አይቀርም)፣ ወዘተ የሚሉ አማካሪዎች እኮ ናቸው ይህች አገርና መከረኛ ህዜቧ ከዘመናት የመከራና የውርደት ኦዙሪት ሰለባነት ወጣን ሲሉ ተመልሰው እንዲዘፈቁበት ያደረጉትና በማድረግ ላይ የሚገኙት። እንዲህ አይነት ግለሰቦች እኮ ናቸው ናቸው ታላቁ መጽሐፍ “እውነትን እውነት እና ሃሰት ደግሞ ሃሰት በሉ ብሏልና እንደቃሉ አድርጉ” እያሉ በቅጥፈትና ለቅጥፈት ባሰለጠኑት አንደበታቸው የሚሰብኩን ።

እናም ይኸውና ዛሬም ለዚህ አይነቱ እጅግ አስከፊ የፖለቲካ አዙሪት እና የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ምክንያታዊነትን፣ ሚዛናዊነትን ፣ ዘላቂነትንና ገንቢነትን በተላበሰ አቀራረብና የአስተሳሰብ ይዘት መፍትሄ ከማመንጨትና ከመቅረፅ ይልቅ በዚያው በለመደብን ግልብና ቅርብ አዳሪ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ መጥመልመሉን ቀጥለንበታለን። ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችንና ግብረ በላዎቻቸውን በመሬት ላይ ካደረጉትና እያደረጉት ካለው አገራዊ መሪር እውነታ አንፃር ሳይሆን በተረኝነት በሚዘውሩት የፖለቲካ ሥልጣናቸው ላይ ሊደቀን የሚችለውን ሥጋት (አደጋ) እያሰሉ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች (የሚያሳዩንን ክስተቶች) እየተከተልን በስሜት ከመነዳትና ጨርሶ ሚዛኑን የሳተ ውዳሴ ቅኔ ከመቀኘት ክፉ አባዜ መቸና እንዴት እንደምንላቀቅ እንኳን ለማወቅ ለመገመትም በእጅጉ ያስቸግራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአሜሪካ እና የቻይና ላም ልዩነት (የለቅሶ ቤት ወግ) - መኮንን ሻውል ወልደጎርጊስ

መሬት ላይ እያየነውና እየታዘብነው ያለነው እጅግ እኩይ የፖለቲካ ጨዋታም የምንፈራው እንዳይሆንና የምንፈልገው እንዲሆን የሚያሳይ አይደለም። በአንድ በኩል እጅግ ግዙፍና መሪር ዋጋ ከተከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ፍለጋ ትግል እየተንሸራተተ የሸፍጥ፣የሴራና የተረኝነት ተሃድሶ ፖለቲካ ፍርፋሪ ለቃሚ (ምፅዋዕተኛ) የሆነ ተቀዋሚ ፖለቲከኛ ተብየ በሚተራመስበት እና በሌላ በኩል ደግሞ ህልውናቸውን ገደብ ከሌለው ሥልጣን ጋር ባቆራኙ የገዥው ቡድን ፖለቲከኞች ጫና እና በእራሱም ድክመት ምክንያት አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ባልቻለው የእውነተኛ ፌደራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ፖለቲከኛና ደጋፊ ምክንያት የፈራነው ነገር እውን ሆኖ ብናገኘው ከቶ ሊገርመን አይገባም።

አንቅቶ፣ አደራጅቶና መርቶ ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን እንዲበቃ የሚያስችለው የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት) ለማፍራት ያልተሳካለት መከረኛ ህዝብ የለውጥ መሪ ነኝ በሚል መንበረ ሥልጣን ላይ የሚወጣውን ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኛ ሁሉ ካለፈው ሳይሻል አይቀርም በሚል ለማወደስ ቢገደድ ምን ይገርማል?

መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ አልፉና ኦሜጋ ጁንታ የተሰኙትን የህወሃት ፖለቲከኞች ከፖለቲካ ጨዋታው ውጭ ማድረግ እንደሆነ ሲነገረው ለምንና እንዴት? ብሎ ከመሞገት ይልቅ አሜን ብሎ በመቀበል ሌላውን አሜን ለማሰኘት የትንታኔ ድሪቶ የሚደርት ምሁር ነኝ ባይ በበዛበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ፊደል የመቁጠር እድል የተነፈገው የአገሬ ህዝብ አሜንና እልልል ብሎ ቢመቀበል ለምን ይገርመናል?

መቸው የፖለቲካ ባህላችንና አስተሳሰባችን ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር ምን አይነት ለውጥ? በነማን? ከነማን ? ለነማን? ለምን? በየት በኩል አድርጎ የት ለመድረስ? ከዚያስ? የሚሉ እጅግ ፈታኝ ጥያቄዎችን (ጉዳዮችን) በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ከመጋፈጥና ትክክለኛ መልስ ለመስጠት ጥረት ከማድረግ ይልቅ የሚቀለን ወይም የሚቀናን የመሪ ነን ባዮችንና የግብረ በላዎቻቸውን የሸፍጥና የሴራ ዲስኩር ወይም ስብከት እየተከተልን እልልታውን ማቅለትና ውዳሴውን መቀኘት ሆኖብን ነው እንጅ ለዘመናት የመጣንበትና አሁንም የምንገኝበት መሪር እውነት ይኸው ነው።

ለዚህ ደግሞ መንበረ ሥልጣን ላይ የወጣ ፖለቲከኛን ሁሉ በመሬት ላይ ከነበረውና ከሚኖረው (ካለው) መሪር ሃቅ አንፃር ሳይሆን በሰላ አንደበቱ የሚሰብከውንና የቤተ መንሥት ፖለቲካው በተናጋበት ቁጥር የሚወስዳቸውን ቅንጭብጫቢና ከዘለቄታ መፍትሄ ጋር ያልተጣመሩ የፖለቲካ ፍጆታ (fragile and short term political consumption) እርምጃዎችን ብቻ በመመልከት ጀግናው ፣ አስደናቂው ፣ የዘመናችን ሙሴ ፣ አሸብራቂው ፣ አይበገሬው ፣ ታላቁ፣ ወዘተ እያልን ከምናዥጎደጉደው ወደ አምልኮነት የተጠጋው የፖለቲካ ሰብእና ፈጠራ ( cult of political personality) ውዳሴያችን በላይ ግልፅና ግልፅ ማሳያ የለም ።

በመሬት ላይ ግልፅና ግልፅ የሆነ መሪር እውነት ማለትም በህወሃት/ኢህአዴግ የተተከለ (የተመሠረተ) እና በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓተ ፖለቲካ ላይ ተዘፍቀው (ብልፅግና ተብየዎችን መለቴ ነው) ጁንታ የሚሏቸውን የቀድሞ አለቆቻቸውን በግድም ይሁን በውድ ከፖለቲካ ጨዋታ ሜዳው ማስወገዳቸው ብቻውን የትም እንደማያደርስ ለማወቅ መሬት ላይ የሆነውንና እየሆነ ያለውን መሪር እውነት ከመረዳት በላይ ምርምር አይጠይቅም። እየተነጋገርን ያለነውና መነጋገርም ያለብን እጅግ አስከፊውን የሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ማንነት ስሌት የፖለቲካ ሥርዓት እንደ ሥርዓት አስወግዶ እውነተኛ (መሠረታዊ) ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ስለማድረግ እንጅ የተወሰኑ ፖለቲከኞችን ወይም ቡድንን ከፖለቲካው ጨዋታ ሜዳ ውጭ ስለማድረግ ብቻ ፈፅሞ አይደለም። መሆንም የለበትም።

ይህ ከእራሳችን እጅግ አስከፊ ሁለንተናዊ ጉዳት አልፎ የዓለም ህብረተሰብ መሳለቂያ ያደረገን ፖለቲካ ወለድ የርስ በርስ መገዳደል ( ጦርነት) ባአስተማማኝነት እንዳይቀጥል ወይም በሌሎች የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ማንነት ፖለቲካ አተርፍ ባይ ነጋዴዎች እንዳይደገም ለማድረግ ነገ ሳይሆን ዛሬ ምን መደረግ አለበት ? የሚለውን እጅግ ግዙፍና መሪር ጥያቄ የመጋፈጡ ወኔው ሲያጥረን እየመረጥን ያለነው አካሄድ ግልፅና ግልፅ ስለሆነው የህወሃት ወንጀል ማመንዠክ ሆነና ከፊታችን የተደቀነውን የእራሳችንን ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንረሰዋለን።

በመሠረቱ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመጣንበትን መግለፅ የሚያስቸግር አገራዊ የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት የተከሉት፣ያስፋፉትና ሥር እንዲሰድ ያደረጉት እኩይ የህወሃት ፖለቲከኞች አከርካሪ ቢሰበር እሰዬው የማይል ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

በሌላ በኩል ግን ክስተትን እየተከተሉ የመሞቅ ወይም የመቀዝቀዝ ፖለቲካና በጅምላ የመንጎድ አስተሳሰብ ፣አቀራረብና አካሄድ ክፉ ልክፍት (ልማድ) ስንት ጊዜና ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ከእኛው ከእራሳችን በላይ ማስረጃ ከቶ የለም። የዚህ ሁሉ መከራና ውርደት ዋነኛው ምክንያት (ምንጭ) ደግሞ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመጣንበትና በህገ መንግሥት ደረጃ ተደንግጎ ሥራ ላይ የዋለው የህወሃት/ኢህአዴግ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ማንነት ስሌት ሥርዓተ ፖለቲካ ነው ። በህግ መንግሥት ተብየው መሣሪያነት የተዘረጋው የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት ፣ የመንግሥት አወቃቀር እና በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠርና ሥርዓቱ ያባለገው የካድሬ ሠራዊት በነበረበት እንዲቀጥል ያደረገው ብልፅግና ተብየውም ከጁንታነት ነፃ የሚወጣበት ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት የለም። ጁንታነት እኮ ያለህዝብ ይሁንታ ወይም በሃይል ሥልጣን ላይ ወጥቶ ከህዝብ ፍላጎት ወጭ የሚገዛ ቡድን ማለት ነው።ይህ ጁንታነት ደግሞ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካን መሠረት አድርጎ ሥልጣን ሲይዝና ሲገዛ አደጋው በእጅጉ የከፋ ነው። ዴሞክራሲና ይህ አይነት የፖለቲካ ሥልጣን አያያዝና አገዛዝ ጨርሶ ተፃራሪዎች ናቸው። ለዚህ ነው እኮ የህወሃት መወገድ ከዚህ አስከፊ የፖለቲካ ጨዋታ ለመውጣት ለሚደረግው ትግል መንገድ ከሚከፍቱ አይነተኛ እርምጃዎች አንዱ ነው ማለት ትክክል የሚሆነው። እናም ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን መሠረታዊ አስተሳሰቦቹ፣ ህገ መንግሥቱና መዋቅሮቹ ጨርሶ ባልተነኩበት ሥርዓተ ኢህአዴግ ውስጥ እንደተዘፈቁ የቀጠሉት ብልፅግና ተብየዎች ከወራት በኋላ ምርጫ አካሂደው እራሳቸውን ህጋዊነትንና የህዝብ ይሁንታ ለማላበስ የሚያደርጉት ጥረት የሸፍጠኛና ሴረኛ ጁንታ ርካሽ የፖለቲካ ተውኔት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? እናም ለመከረኛው ህዝብ የሚያስብ እንጥፍጣፊ (ከብልሽት የተረፈ) ህሊና ካላቸው ትክክለኛውና ዘላቂው መንገድ የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓታቸውን ወደ ከርሰ መቃብር የሚሸኝና በምትኩ በእኩልነት የሚኖርባትን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል የሽግግር ጊዜ መንግሥትን ዴሞክራሲያዊ አርበኝነትን በተላበስ መሪነት ማዋለድ የግድ ነው።

ይህ እውን ይሆን ዘንድ ግን የፖለቲካ ባህላችን ፣አስተሳሰባችንና አካሄዳችን ክስተቶችን እየተከተልን መንበረ ሥልጣን ላይ የተሰየመውን ፖለቲከኛና ግብረ በላዎቹን ደስ ያለን ሲመስለን ልክ በሌለው ውዳሴና ግልብ ስሜታዊነት ከማሞካሸት እና ቅር ስንሰኝ ደግሞ ከማማርርና ከመቆዘም ክፉ አባዜ ወጥተን መለኪያችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደን ሥራ እየተሠራ ነው ወይስ እየተኮላሸ ነው ? ከሚል ተጨባጭ ፣ ግልፅና ቀጥተኛ ጥያቄ ላይ የተመሠረተ መሆንን አለበት። በሥራው ለሚሳተፉ ፖለቲከኞች የምንሰጠው የእውቅና ምሥጋናም ይህንኑ ተጨባጭ መለኪያ የሚመጥን መሆን ይኖርበታል። ይሀን አድርገን እስካልተገኘን ድረስ የሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑን የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት ያለአንዳች መሠረታዊ ለውጥ እንዲቀጥል ያደረጉት ፖለቲከኞችና ግብረ በላዎቻቸው በቅርቡ እንካሂደዋለን በሚሉ በሸፍጥና በሴራ የተበከለ ምርጫ “ምድር አንቀጥቅጥ ድል” ተጎናፅፈው ሌላ (ቀጣይ) የመከራና የውርደት ዓመታት እንደሚያስቆጥሩን አምነን መቀበል ይኖርብናል።

ክፉው ሳይሆን በጎው ያሸንፍ ዘንድ እየተመኘሁ አበቃሁ!

 

 

1 Comment

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.