December 10, 2020
55 mins read

የሁለት ማህበራዊ አንቂዎች ወግ – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ደራሲ መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
     ታህሣሥ 1/2013 /

ታክሲዋ ሙሉ ሰው ጭናለች።የኮሮና የአሥቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመነሳቱ እና ከኋላ ሦሥት ሰው ብቻ እንዲጫን በመባሉ ተጋፍቼ ፣ተሳፋሪውን በመቅደም፣ የኋላ መቀመጫውን የበሥተቀኙን ጥግ ወንበር ሥለያዝኩ፣የሁሉም ተሣፋሪ ግማሽ ፊት ይታየኛል።
እያንዳንዱ ተሳፋሪ ምን እንደሚያሥብ፣በግማሽ ፊቱ ብቻ ማወቅ አይቻልም።ግማሽ ፊት የተገመሰ ሃሳብን እንጂ ሙሉ ሃሳብን በምሥሉ አይከሥትለህም።ይህ እወነት ቢሆንም ከሀገሬ ተጨባጭ ሁኔታ ተነሥቼ በዚህ ታክሲ ውሥጥ ያለ ሰው ከኮሮና ይልቅ የእለት ጉርሱ እንደሚያሥጨንቀው አሥባለሁ።መቼም የሆድ ጥያቄ እንደተመለሰላቸው የበለፀጉት ሀገራት ጠቢቦች ሥለ ዓለም ሥነ _ምህዳር እና ፍፃሜ እየተመራመረ ራሱን የሚያሥጨንቅ ሰው በዚህ ታከሲ ካለ ታምር ይሆንብኛል።
ከአለም የሥልጣኔ እድገት አንፃር የእኛን ሰው ከፖለቲካ ይልቅ እሥከዛሬ ምንነቱ ያልታወቀው” ዳርክ ኢነርጂ “ሊየሥጨንቀው ፣ በተገባ ነበር።ይሁን እንጂ ዓለምን ሥለሚሰለቅጣት የእሳት ክምር ሰው ባለማወቁ ሲነጋ ሲጠባ ዳቦ ብቻ ነው ጭንቁ።ምቾትና ድሎት ነው፣ጭንቁ።የዓለም ሰው ጭንቅ ሱፐር ማሲቭ ብላክ ፣ ሆል፣አይደለም።
እዚህ ታክሲ ውሥጥ እንኳን የማየው ሰው፣ፀዳ ያለ ልብሥ በመልበሱ፣ሥለዓለም ይጨነቃል ብዬ አላሥብም።ሥለ ዓለም ከሚጨነቅ ይልቅ ፖለቲካው ሃያ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ሢጠዘጥዘው ሥለከረመው ሥለ ቋንቋውና እሱን ተከትሎ ሥለመጣው ጎሣዊ ዘመዱ ነው የሚያሥበው። ፖለቲካው ሃያዘጠኝ ዓመት አንቆ እየጋተ ባሳደገው ቋንቋውና ብሔር፣ብሔረሰቦች ነው ፣የሚያሠላሥለው። ” ብሔር ብሔረሰቦች ኑ! ኑ ! የኢትዮጵያ ልጆች ” እያለ ሰውነቱን እና ዜግነቱን ረሥቶ ነው የሚጨፍረው።እድሜ ላሥጨፋሪው ና ባለፉት ሃያሰባት ዓመታት ከሰውነትና ከዜግነት ይልቅ ቋንቋ መሆኑንን ያልተቋረጠ ፕሮፓጋንዳውን እየጋተ ላሳደገው። ዕድሜ በቡድን እንጂ በግለሰብ ደረጃ በዜግነቱ እንዲያሥብ ለከለከለው።ዕድሜ ‘ በቋንቋህ ማምነትህ ብቻ ፣ ዜጋ መሆንህ ይረጋገጣል።’ እያለ በቡድን ዙሪያ ተሰባስቦ እንጂ እንደ እንድ ግለሰብ ማሰብ ለከለከለው።ዕድሜ “ብሔር ብሔረሰቦች ኑኑ!የኢትዮጵያ ዜጎች እንዳይል ፣በሥታሊናዊ ቅኝት ላዘመረው። እድሜ አቋራጭን እንጂ ጥረትን፣ግረትን፣ላብና ደምን የሚጠይቅ ሥራ እንዲጠላ ላደረገው።
በአቋራጭ አሥተሳሰብ ሰበብም ፣ ‘ እገሌ ቋንቋ በማወቁ በቻ በምላሱ ጉልበት ፣ ባልተፈጠረበት ጎሳ ቱባ ባለሥልጣን ሆነ።እገሊት በድፍረቷ ና በአይን አውጣነቷ ብቻ የክልሉ ዋና ሰው ለመሆን በቃች። እኔ ግን በቋንቋ በለመቧደኔ ይኸው ዘለአለሜን እከኬን ሳክ እኖራለሁ።’ ይላል።…እያለ በአእምሮ የሚመነዠግ ሃሳብን በራሱ እሳቤ ልክ ሲያነሳ ና ሲጥል ፣ሲያወርድና ሲያወጣ ሲያደቅና ሲያምሥ ፣ ድንገት በኮቱ ደረት ኪሥ ያያዝው የሞባይሉ ሥልኩ ሲጮኽ ከሹፊሩ በሥተቀር ሁሉም ተሳፋሪ ወደ እሱ ላይ አይኑን ለአፍታ አሳረፈ። ተሳፋሪዎቹ በሙሉ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ነበር። ”
ተሳፋሪው፣እንደተመካከረ ሁሉ አፍጥጦ እንዲያየው ያደረገው የሥልኩ መጥሪያ ሙዚቃ ነበር።”አይንሽ ለምን በጎን ይመለከተኛል፣አንቺን የፈጠረ እኔንም ፈጥሮኛል።…”የሚል ነበር።የጥሪው ድምፅ። የድሮ የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን ነው።ዘመን የማይሽረው ።የ1960 ዎቹ ትሩፋት ።” ፍንዳታ !!ዱርዬ !! “ ለሚዘፈንለት ለዚህ የ2013 ዓ/ም ፈጣጣ ተውልድ ፣በጎን አየሺኝ ብሎ ዘፈን ቢያሥደነግጠው አይገርምም።
“ሄሎ ማን ልበል?” ሲል በቁጥሩ ሥላለየው ፣የደዋዩን ማንነት ለማረጋገጥ ጠየቀ።
“የአክቲቪሥት፣ አክሱም ዘ ላሊበላ ሥልክ አይደለም እንዴ?”
“ነው።አንተን ማን ልበል?”
” ኦ! ሥላገኘሁ በጣም ደሥ ብሎኛል።በዜጋ መፅሔት በፃፍከው ሥለማንንነት በሚተነትነው ፅሑፍህ፣’ እኔ ራሴ ማነህ ብትለኝ ?ወይም ሥለማንነቴ ብትጠይቀኝ እንደአንተ ሰው ነኝ።ነው መልሴ።በዘመን ቅብብሎሽ ድንገት በተፈጠረ ቋንቋ የቀደመውን ሰውነቴን አልቀይርም። ‘ ያልከውና ግብዝነትን እንደምትኮንን በመግለፅ፣’ ማንም ይሁን ማ አንተ ብዬ የመጥራት መብቴን ማንም አይነጥቀኝም።በምድር በሰማይ አቻ የሌለውን ፈጣሪያችንን ‘አንተ’ እያልን፣ አንቱ ካላላችሁኝ እያሉ ቡራ ከረዩ የሚሉ ሰዎች ይገርሙኛል።’ በመላትህ ነው አንተ ያልኩህ።ለማንኛውም ከአባይ ወንዝ ቲቪ ነው የምደውልልህ።ጋዜጠኛ ኪሩቤል እባላለሁ ።ቴሌቪዢናችን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከአንተና ከእንተ ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ ካለው፣ ከኦደአት አበሻ ጋር ‘ጮራ!’ በተሰኘው፣ብዙ ተመልካች ባተረፈልን ግልፅ መድረክ እንድትወያይ ልጋብዝህ ነው፣ የደወልኩት።”በማለት የደወለለትን ምክንያት ገለፀለት።
“መቼ ነው፣ለውይይቱ ፕሮግራም ለመያዝ ያቀዳችሁልን?”
” የፊታችን እሁድ ከሰዓት በኋላ፣ልክ 9 ሰዓት ላይ።ይመችሃል?”
“አዎ ይመቸኛል።”
“የቴሌቪዥን ጣቢያችን ፣ከታወቀው ‘ቴዎድሮስ’ ባንክ አጠገብ ከሚገኘው፣’አብዲሳ አጋ’ ህንፃ ላይ ነው።”
“አውቀዋለሁ።”
“አመሠግናለሁ።መልካም ቀን ይሁንልህ።”
“ለአንተም።”
ሥልኩን ዘጋና፣ሰዓቱን ተመለከተ።ገና 2:40 ነው።መሥራዬ ቤቱ በ3:10 ይደርሳል።
መሥሪያ ቤቱ የውጪ ድርጅት ሲሆን ፣ለተለያዩ ፋብሪካዎች የሚያገለግሉ የምርት ግብአቶችን የሚያሥመጣ ነው ።በኮሮና ሠበብ ሥራው በመቀዛቀዙ ቢሮ ዘግይቶ ቢገባ ችግር የለውም። ሥራው፣የተላኩ ኢሜሎችን አንብቦ በመርከብ ወይም በካርጎ አውሮፕላን የተጫኑ እቃዎች እንዳሉ ማረጋገጥ እና ከሚመለከተው ጋራ ሂደቱን ማከናወን ነው።መልእክት ከሌለ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሣልፈው ኢንተርኔት ላይ አፍጥጦ ነው።
ዛሬ ከወንዝ ቲቪ የደረሰው መልእክት ኢንተርኔቱን በደንብ እንዲገለገልበት እንደሚያሥገድደው ተረድቷል።
‘ ለመሆኑ በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ውሥጥ ወግ ና ሥርዓት ያለው ፖለተካ ነበረ ወይ?ሲጀመር ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት መንግሥታት የተለየ ታሪክ ነበራት እንዴ?ሰዎች በመራባት ምድርን ሳይሞሏት በፊት የትኛውም ሀገር ሥምሥ ነበረው ??? ዘመናዊ ፖለቲካ የአሥራ ዘጠነኛው ክ/ዘ ታሪክ አይደለም እንዴ?ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ተገዢነት የተላቀቁት በ20ኛው ክ/ዘ አይደለም ወይ ???
መንግሥት ለመሆን ወይም በሀገር እና በህዝብ መሪነት በዓለም መንግሥታት ፊት ለመታወቅ ገለልተኛ፣ፍትሐዊ፣ነፃ፣ተአማኒ ምርጫ አካሂደው በህዝብ የተመረጡ፣ የተመሠከረላቸው፣እፁብ ድንቅ አሥተዳዳሪ ወይም አገልጋይ መንግሥታት ዛሬሥ በ 21ኛው ክ/ዘ አሉ እንዴ ?
እርግጥ ሀገራት መንግሥቶቻቸውን በህዝብ ይሁንታ ለመመሥረት ግልፅ ምርጫ ያካሂዳሉ።…’ታክሲው የመጨረሻ ፊርማታው ላይ በመድረሱ ከሃሳቡ አናጠበው።ከታክሲው ወርዶ ቀጥታ ወደ ቢሮው አመራ።
እንደተለመደው ሥራ አሥኪያጁ እና ፅዳት ሠራተኛዋ ቀድመውታል።ፅዳት ሠራተኛዋ እንኳ ቢሯዎቹን ሰው ሳይገባ ለመፅዳት ነው በጠዋት መግባቷ፣የሥራ አሥኪያጂ ሁሌም በጠዋት መግባት ግን የእሱን ሁሌም ማርፈድ ሣለሚያሳብቅበት አይወደውም። በኮረና ምክንያት እንኳን የሥራ ዲሲፕሊናቸው አልተለወጠም።
ቢሮው እንደወትሮው ፀድቶ ነው የጠበቀው።በተለመደው የቫይረሥ አምካኝ ሣንታይዘር ጠረጴዛው ተወልውሏል።ጭምብሉን አውልቆ በማሥቀመጫ ከረጢቱ ውሥጥ በጥንቃቄ አሥቀመጠው።የሸሚዙን እጅጌ ሰበሰበና ኮምፒውተሩን ለኩሶ እሥክሪኑ ላይ አፈጠጠ።

2
የሞባይሉ ሥልክ ጥሪ ድምፅ፣ለሦሥተኛ ጊዜ የጀምስ ሃይፒን ኖ ድራማ (no drama ) የተሠኘውን ዘፈን ያሠማል።ከጠዋቱ ሦሥት ሰዓት ነው።ሰው በዚህ ሰዓት እንዴት ይተኛል?በጤናው ነው?ይባል ነበር ድሮ።ኮሮና ወይም ኮቪድ 19 ከቤት ያለመውጣትን ያበረታታል። እድሜ ለኮሮና ዘንድሮ በመኝታ ብዛት ሥንቱ ሣር በቀለበት? “ለምን ትተኛለህ?ሰነፍ ገና ሙጃ ይበቅልብሃል ።”ብሎ በነገር የሚሸነቁጥህ የለም።”ሰነፍ ! “ብሎ የሚወቅሥህ ሥለሌለም ሃሳብህን ጥለህ ትተኛለህ።
የሥልኩ ጩኸት ሢደጋገም ፣የግዱን አየተነጫነጨ ከብርድ ልብሥ ውሥጥ እጁን እንደ እባብ መዞ ሞባይሉን አነሳው።ብርድልብሱን በአንድ እጁ ከፊቱ ላይ ገለጠና ሥልኩን ከፈተ።ወደ ጆሮውም አሥጠግቶ “ማነህ እንደ መርዶ አርጂ በጠዋት የምትቀሰቅሰኝ?”በማለት ኮሥተር ብሎ ጠየቀ።
“ኦደአት አበሻ ነህ?”
” አዎ ነኝ።ማን ልበል?”
“ጋዜጠኛ ክሩቤል እባላለሀ።ከአባይ ወንዝ የቴሌቪዢን ጣብያ ነው የምደውለው።ከአክሱም ዘላሊበላ ጋር ፣የፊታችን እሁድ ፣ልክ በ9 ሰዓት ፣በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳባችሁን በሚዲያችን በኩል እንድታሥተላልፉ ለመጋበዝ ነው፣የደወልኩልህ።”
“ኦ! ክሩቤል።የፕሮግራምህ አድናቂ ነኝ።እሁድ ይመቸኛል።ግብዣችሁን ተቀብያለሁ።”
“አመሠግናለሁ።”
ሥልኩን ዘግቶ ከአልጋው ተንሥቶ ቁጭ አለ።ሥለመጪው እሁድ የቴሌቪዥን ውይይት አሠበ።አክሱም ዘ ላሊበላ ጋር የሚያደርገው ውይይት በመግባባት የሚቆጭ መሆኑንን ልቡ ያውቃል።ሰው ሁሉ የግሉን ሃሳብ እንደሚያንፀባርቅ ቢገምትም እርሱን በሰላ ሂሥ የሚተቹት የመሐልን መንገድ በመምረጡ ነው።
“ የኢትዮጵያ ህዝብ ህልመኛ በመሆኑ በቀላሉ ሥሜት ኮርኮሪ በሆኑ ቃላቶች እንደሚነዳ ያምናል።ሰው መሆኑንን በለማሥተዋል ፣ሰው የሚያሥብ ፍጡር እንደመሆኑ ድንገት ሃሳቡን እንደሚቀይር ያልተገነዘበ ማህበረሰቡን ወደጥፋት እንዲሠማራ የሚቀሰቅሥ ማህበራዊ አንቂን ይጠላል።
“ጦርነት እንዳይለኮስ ያደረኩት ቅሥቀሳ ባለመሳካቱ አዝኛለሁ። እየኖርኩ ያለሁት በደህና ጊዜ ቤተሰብ ባወሰኝ ሀብት ነው።ይህ ሀብቴ የሚኖረውም አገር ሥትኖር ብቻ ነው።እኔ በአጋጣሚ የተደላደለ ኑሮ እየኖርኩ ነው። ለውይይት ከእኔ ጋር የተጋበዘው በደሞዙ ብቻ የሚኖር ሃቀኛ እንደሆነ አምናለሁ። የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ተቆርቋሪ ጋር ለውውይይት በመጋበዜ ደሥተኛ ነኝ።
“ ጋዜጠኛው ‘ ይህ ጦርነት ፍትሃዊ ነው? ወይሥ አይደለም ? በእርቅ መቆም አለበት ወይሥ በኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል አሸናፊነት ጦርነቱ መቋጨት አለበት? ‘ የሚል ቦንብ የሆነ ጥያቄ በማንሳት ሊያሟግተን ያሥብ ይሆናል።እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ሲጠይቅም እኔ ወደ እርቅ እንደማደላ ፣ከሶሻል ሚዲያው በመረዳቱ በሁለታችን መካከል የጦፈ ክርክር እንደሚነሳ አሥቦ ከሆነ ተሳስቷል።
ይህ ጋዜጠኛ እጅግ በሳል እና ለሙያው ሟች እንደሆነ አገር ያውቃል።ጥያቄዎቹ ማፈናፈኛ የላቸውም።እናም ለዚህ ውይይት ጥንቃቄ ያለው ዝግጅት ማድረግ አለበኝ።”
በማለት ልብሱን ለባበሰና ወደ አከራየው ኢንተርኔት ካፌ አመራ።
3
እሁድ ጠዋት።አባይ ወንዝ የቴሌቪዥን ጣብያ ሥቲዲዮ ግርግዳ ላይ የተሰቀለው ሰዓት 9 ሰዓት እንደሆነ ያመለክታል። በቀጠሯቸው ሰዓት ሁለቱም ማህበራዊ አንቂዎች በቴሌቪዢን ጣብያው ተገኝተዋል።
“እንኳን ደህና መጣችሁ።” በማለት” የፍጥጫ ” ፕሮግራም አዘጋጅ ሰላምታ ካቀረበ በኋላ ውይይቱ ተጀመረ።….
” አቶ ላሊበላ ዘ አክሱም ፣ ዛሬና አሁን ያልተቋጨው በህወሓት ጥቂት ኃይሎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ መንሥኤው ምንድነው ብለህ ታሥባለህ?”
” ጥያቄህ ግልፅ መሆን አለበት ” በማለት ንግግሩን ገታ በማድረግ አቶ ኦደአትን እና ጋዜጠኛውን ክሩቤልን ትኩር ብሎ ተመለከተ ና ነግግሩን ቀጠለ።
“ይህ ቡድን በግልፅ በአደባባይ ፣ጭራቅነቱን ያሥመሠከረ የሥልጣን አረቄ ሥካር ‘የዞረ ድምር ‘ ያሳበደው ፣’ እኔ የማልመራትን ኢትዮጵያ ሺ ቦታ እንድትከፋፈል በማድረግ ሥሞን ከምድረ ገፅ እደመስሰዋለሁ። ‘ በማለት ከውጪ ጠላቶቻችንን ጋራ ያበረ ና የተባበረ ነው።
የዚህ ጦርነት መንሥኤ ጭራው ነው እንጂ እዚህ ያለው ጭንቅላቱ ውጪ ነው።እናም ይህንን ጦርነት እንደዋዛ መመልከት አይቻልም።
ይህ ታሪካዊ እውነት ነው። የዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን ሴራ ጅራቱ ነው ትግራይ ውሥጥ ያለው እንጂ ጭንቅላቱ በውጪ ጠላቶቻችን አገር ነው። እነዚህ ኃይሎች ለጥቅማቸው ብቻ ሳይሆን ለሥልጣናቸው ሲሉ የአባይን ወንዝ የፖለቲካ መሣሪያ በማድረግ በየጊዜው ከህዝባቸው የሚነሳባቸውን ፣የፍትህ ና የዴሞክራሲ ጥያቄ የሚያረግቡት እኛን አሥቀድሞ ባጠመዱት የቋንቋ ና የጎሳ ፈንጂ በማተራመሥ ነው ።
ይህ ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን ከእነዚህ አገራት ትላንትም ሆነ ዛሬ ምሥጢራዊ ድጋፍ አለው። እናም ህወሓት የተሰኘ ሥሙን የሙጥኝ ያለው ከአራት አሥረተ ዓመታት በፊት ከእነዚህ አገሮች ጋር በዶለተው ሴራ የተነሳ ነው። የትግራይ ህዝብ እንዳይበለፅግ ለ27 ዓመት በአንድ ለአምሥት እጅና እግሩን አሥሮ የገዛውም ፣ሁል ጊዜ በችጋር እያሳበበ ፣በሆድ እየደለለ ባርያ በማድረግ ሊገዛው አሥቦ ነው። እናም የጦርነቱ ሰበብ የላሚቷን ወተት እኔ ብቻ ልጠጣ የሚል ሥግብግብ ፍላጎት ነው።
የወደፊት ፍላጎቱ ፣ የነፃ አውጪነትን ትርክት መልሶ በመፍጠር የህዝብን ሥነልቡና በማህበራዊ ድረ ገፅ በሚያቀርበው ደራማ በማነሳሳት ዛሬም እንደትላንት ድልድይ በማፍረሥ አለሁ በማለት ከፀረ- ኢትዮጵያ ኃይሎች ረብጣ ዶላር እያገኘ አውሮፓና አሜሪካ መንፈላሠሥ ነው።
የህውሓት ጥቂት አንጃ መፈናፈኛ ሲያጣ ፣ ሞቶ መቃረቡን ሲረዳ ሳይቀድሙኝ ልቅደማቸው።በድህነት ያማቀቅሁትን ህዝብንም ከ30 ዓመት በፊት በነበረው ትርክት መልሼ ሽምቅ ተዋጊ ላድርገው ።በዚህም ውጥኔ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ድጋፍ ሥለማገኝ ፣በአገራቸው እየተንፈላስኩ እኖራለሁ ብሎ ማለም ነው። ጦርነቱን የቀሰቀሰው ከዚህ አንፃር ነው።…”
“አቶ ኦደአት አበሻ አንተስ ምን ትላለህ ? ”
“ጦርነቱን የጫረው ትህነግ ነው።ይህንን እራሱም አምኗል። እኔ ይህ ጦርነት ለሁለቱም የሚረባ አይደለም ባይ ነኝ። ።አገርን አጥፊ ሰውና ንብረትን አውዳሚ ጦርነት መሆኑ የታወቀ ነው።ሁሌም የጦርነት ፍፃሜ ይህ ነው። በመሆኑም ሁለቱም ወገኖች ቶሎ ብለው ጠመንጃ ጥለው ወንበር ሥበው በጠረጴዛ ዙሪያ ቢቀመጡ ዳግም ጦርነት እንዳይፈጠር ይረዳል ብዬ አሥባለሁ። በጦርነት ትርፍ እንደሌለ ሁለቱም ወገኖች ተገንዝበው ገዳይ መሣሪያቸውን ጥለው፣ወንበር ሥበው በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት ካልመጡ የሚዳ ውጊያው እዛና እዚህ መቀጠሉ አይቀርም። ጦርነቱ የሚቀጥለውም ድህነት በተንሰራፋባት አፍሪካ በቀላሉ ሰላም ማሥፈን ሥለማይቻል ነው። በተለይም ገንዘብ ያላቸው ኃይሎች በአፍሪካ እንደ አልሻባብ ፣ቦኩሐራም ወዘተ የተባሉ ፅንፈኞችን እና አክራሪ ኃይማኖተኞችን በመፍጠር ባሻቸው ሰዓት እያደቡ እሳት እንደሚጭሩ ና እዛና እዚህ ቃጠሎ እንደሚያደርሱ ማስተዋል የሰላም ውይይት ሃሳቤን ያጠናክርልኛል ።
” ዛሬ ሁላችንም እንደተመለከትነው፣ ትህነግ ባለው ገንዘብ ና መሣሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን ያሰለጠነው ያሥታጠቀውና ደሞዝ የሚከፍለው ሚሊሻና ፣ልዩ ኃይል እንደ ቴዎድሮስ ና ገብርዬ እሥከ መጨረሻው ደም ጠብታ ይዋጋልኛል ብሎ በማሰብ የእብደት ጦርነት በአገር መከላከያ ላይ ከፍቶ እንደተዋረደ ሥናሥብ ነገም ያደራጁትን ሚሊሻ ና ልዩ ኃይል ደሞዝ ሥለሚከፍሉት ብቻ እንደ ግል አሽከራቸው በመመልከት ጨፍጭፍ፣ግደል፣እረድ ቁረጥ፣ፍለጥ ወዘተ የሚሉ እንደሚፈጠሩ ወይም እንደማይከሰቱ ምንም ማረጋገጫ የለንም።የህወሓት ጭራቅ ቡድን የፈፀመውን ዘግናኝ ድርጊት ነገ ሌላው የጎሳ ፖለቲከኛ አይፈፅመውም ብሎ ለማሰብ እኛ ምደር ላይ ያለው ፖለቲካዊ አደረጃጀት አይፈቅድልኝም። የደቆነውን ሤጣን ካላጠፋኸው መቀሰሱ አይቀርም። ዛሬ ወይም ነገ ሞታቸው መከሰቱ እንደማይቀር የማይገነዘቡ ለአገር ና ለህዝብ የማያሥቡ ግብዝ ባለሥልጣኖችን ከከፍተኛው የመንግሥት አመራር ላይ ዞር እሥካልተደረጉ ጊዜ ድረሥ የቋንቋና የጎሣ ተረኝነት አባዜ ይቀጥላል።
” የህወሓት መሪ የነበረው ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን በቋንቋና በጎሣ ከፋፍሎ ጥቅምን ለከፍተኛ አመራሩ በከፍተኛ ደረጃ እየሰጠ ፣በተዋረድ ደግሞ እያቃመሰ ኢትዮጵያን በጥቂት ቱጃር መንደርተኞችና የቋንቋ ነጋዴዎች ሲበዘብዝ መቆየቱ እሙን ነው።
“የትግራይንም አጠቃላይ ሀብትና የድርጅቱን የኢኮኖሚ ተቋማት የሚቆጣጠር ቱጃር እንደነበረም መዘንጋት የለበንም። በአውሮፖና አሜሪካም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላርና ፖውንድ ያለው ዓለም አቀፍ ከበርቴ ነው።ይህ ከበርቴነቱ ደግሞ የከበርቴ አገራትን ድጋፍ ያሥገኝለታል።መቼም እነሱም ለጥቅማቸው ያደሩ ሥለሆኑ ነው የማይካድራ ጭፍጨፋውን በማጉለት አለማቀፍ ውግዘት እንዳይደርሥበት የተከላከሉለት። ይሁን እንጂ ይህ ባካበተው ሀብት በትእቢት የተወጠረው የገዘፈ የጭራቅ ባህሪውን በማይካድራ ላይ በማሳየቱ ከትግራይ ልብ ውሥጥ እንደወጣ መታወቅ አለበት።በዚህ ድርጊቱ ነው፣ ከባድ የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰበት ብዬ አምናለሁ።
“እርግጥ ነው፣ከሞራል አንፃር መንግሥት ኪሳራ ባይደርሥበትም በንብረት፣በሰው ሀብት በገንዘብ ህወሓት ከከሰረው በባሰ ኪሳራ ደርሶበታል።ነገም ወደ ጠረጴዛ ውይይት ካልተመጣ ኪሳራው እያበዛ መሄዱ የታወቀ ነው።ህወሓት እንዲህ በቀላሉ የምትጠፋ አይደለችም።አሥተሳሰቧ በሌሎች ቋንቋዎች ውሥጥ የተተከለ ነውና።እናም ነገ ከሌሎች ተገንጣይ ሃሳብን ከሚያቀነቅኑ ገንጣዮች ጋራ አብራ ብቅ ማለቷ አይቀርም። ነገ ተነገወዲያ በሽምቅ ውጊያ መንግሥትና ህዝቡን ማክሰሯን ትቀጥላለች።ብዬ ለማሰብ የአፍሪካ የሴራ ፖለቲካ ታሪካዊ እውነት ያሥገድደኛል።
“ደግሞም ፣ በአፍሪካ ትርምስ፣ ግጭት፣ ያለመግባባት፣ የጎሳ ና የነገድ ጥላቻ እንዲሥፋፋ በገንዘብ የሚደግፉ ሤጣናዊ ኃይሎች እሥካልጠፉ ድረሥ በትግራይ ሙሉ፣ለሙሉ ሰላም ይመጣል ብዬ አላሥብም።..”
“ህወሓትን በቀላሉ ማፍረሥ አይቻልም።ህውሓት አትፈርስም።ህወሓትን ፈፅሞ ለማፍረሥ ከተፈለገ መንግሥት የሚደግፋቸው የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ በአዋጅ እንዲፈርሱ ወይም ከፖለቲካ ጫወታ ወጪ እንዲሆኑ ማደረግ ያሥፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ይህ መንግሥት ተቋማዊ እና ህገመንግሥታዊ አቅም የለውም።
” ተቋማዊ እና ህገመንግሥታዊ መብት ቢኖረው በቀላሉ የጎሳና የቋንቋ ፖለቲካን ከጫወታ ውጪ ማድረግ ይችል ነበር።ዛሬ ና አሁን እየተጓዘበት ያለው መንገድ እንኳን በከፊል የወያኔ/ኢህአዴግ መንገድ መሆኑንን የተገነዘበ አይመሥለኝም። ለዚህም ይመሥለኛል በጊዜ አፈንጂ መቆጣጠሪያ እየታገዘ የሚፈነዳ በነፃ አውጪዎች ሥም የተዘጋጀ ፈንጂ ጉያው ውሥጥ አሥቀምጦ አገር የሚመራው።
ህገ መንግሥቱም በጎሳና በቋንቋ የፖለቲካ ፖርቲ መሥርቱ የሚል አንቀፅ ባይኖረውም ቅሉ ፣ የእገሌ፣የእገሌ ክልል በማለት ለተወሰኑ ጎሳዎች ብቻ እውቅና ሰጥቶ ከ85 ቱ ውሥጥ ለ11 ጎሳዎች ብቻ የመገዝት በሉት ሌላውን ጨፍልቆ የማሥተዳደር ሥልጣን በመሥጠት ፖለቲካው በቋንቋ እንዲቃኝ ማድረጉ ይታወቃል።ይህ እውነት ባለበት ህወሓት ወይም ትህነግን ብቻ ነጥሎ ከፖለቲካ ጫወታ ውጪ አደርጋለሁ ብሎ መፎከር ከንቱ ነው። ህገ መንግሥቱም የሚፈቅድ አይደለም።
“ህገ መንግሥቱ ዜጋንና ልጅነትን በውል ለይቶ አያሥቀምጥም። ሥለፊደራሊዝም ያወራል እንጂ ፊደራላዊ የሆነ ተቋም በየክልሉ የለውም። ያለው ቋንቋዊ ተቋም ነው። ዜጎች በዜግነታቸው በእኩል አይታዩም። በየትኛውም ክልል መብታቸው ከክልሉ መሥተዳድር ቋንቋ አንፃር ነው የሚከበረው።ቋንቋውን ከተናገርክ የበለጠ መብት አለህ።ካልተናገርክ ግን መብትህ የተሸራረፈ ነው።አየር፣ፀሐይ ና ዝናብ ከማግኘት የዘለለ ነፃነትና መብት የለህም።ከምርጫ አንፃርም ተወከይህን አትመርጥም ።ማጨብጨብ እና ማዠርገድ ግን ትችላለህ።ለዚህ አድራጎትህ ጥቂት ወይም ብዙ ይከፈልሃል ። በቃ።…”
” አቶ ኦደአት አመሠግናለሁ።የሚቀጥለው ጥያቄዬ የመጨረሻ ጥያቄዬ ነው።ካለኝ ሰዓት አንፃር። እንደምታውቁት ይህቺ አገር ለዘመናት በጦርነት ሥትታመሥ የኖረች አገር ናት። በይበልጥም ከ19 ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ግዛቷን በመሸራረፍ የበለጠ ትንሽ እንድትሆን ብቻ ሳይሆን እንዳትበለፅግ ቅጥረኛ የጎረቤት አገራት ጦረኞች ፣የግብፅ ማሃዲሥቶች በተደጋጋሚ በሰሜኑ የአገራችን ክልል በኩል እንደወጓት በታሪክ የሚታወሥ ነው ። ከጥቃቅን ጦርነቶች ባሻገርም ከባድ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ እንዳጋጠማት ና ጦርነቱ ውድ ልጆቿን እና ሀብቷን እንደበላ ይታወቃል። ዛሬም የአገራችንን ብልፅግና የማይሹ የውጪ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ይህቺን አገር ለማውደም በብርቱ እየጣሩ ነው። ይህንን እውነት በመገንዘብ ፖለቲካችንን የበለጠ በማዘመን ፣የኢኮኖሚ ፖሊሲያችንንም ተራማጅ በማድረግ ፣ህብረተሰባችንንም በማንቃት እንዴት ነው ፣በሥውር ያጠመዱትን ና በያዙት ሪሞት በፈለጉት ጊዜ የሚያፈነዱትን የትርምሥ ቦንብ ማክሸፍ የምንችለው? አቶ ላሊበላ ዘ አክሱም…”
አመሰግናለሁ።እንዳልከው በአገራችን ፖለታካም ሆነ ኢኮኖሚ ውሥጥ የውጪ ኃይሎች ትልቅ ሚና አላቸው። ሚናቸውም አልሚና አጥፊ ሆኖ ይገኛል ።እነዚህ አገሮች ከጥቅም አንፃር ከእኛ ጋር ሊቆሙ ይችላሉ። ጥቅም ካላገኙ ግን አይቆሙም።ለዚህ ነው ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅነትን የማይፈልጉት።መንግሥት አገራቸውን ና የአገራቸውን ቱጃሮች ተጠቃሚ ካደረገ ከመንግሥታችን ጎን ይቆማሉ።ይረዳሉ። ይህንን እያደረጉ ግን አንድ አገር አተራማሽ የሆነ የአገሬው መንግሥት ሙሉ ትኩረቱን በአገር ግንባታ ላይ ለማድረግ የማያሥችለው ኃይለኛ ሽምቅ ተዋጊ ወይም አክራሪ ኃይማኖተኛ ቡድን ይፈጥራሉ። በተለይም በቅኝ ገዢነት የሚታወቁ አገራት በዚህ የተካኑ ናቸው።
በየአንዳንዱ የቀድሞ ቅኝ ግዛት አገር ሰው ፣ሰው መሆኑንን አበክሮ እንዳያሥብ ፣ሰው ማለት ቋንቋ ና የተወለደበት ጎሳ ሥያሜ እንደሆነ እንዲያሥብ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጎሳ ውጪ ሌላው ሰው ሰው እንዳልሆነ እንዲያሥብ ቅኝ ገዢ የነበሩት አድርገዋል። በዚህም ሰበብ ለእድገቱ ና ለብልፅግናው በጋራ ከመሥራት ይልቅ የአንዱን ሥኬት ሌላው አፈር ለማልበሥ ና ከእርሱ እኩል ደሃ እንዲሆን ሲጥር ስኬታማው በድህነት ውሥጥ ሆኖ በችጋርና በእጦት የሚሰቃየውን የራሱን ወገን ካለበት የድህነት አረንቋ ለማውጣት እጁን አይዘረጋለትም።…እንዲህ አይነቱን ያለመረዳዳት መንገድ በዘመን እርዝመት በአእምሮው ያሰረፁትም ቅኝ ገዢዎቹ ናቸው። በሥጋ ጥቅም ጥቂቶችን በመደለለ የሥጋ ባርያ ያድርጓቸዋል። የምሥኪን አገራቸውን ወርቅና አልማዝ እየሰረቁ የሚያከማቹት እና ቤት የሚገዙት በበለፀጉት አገራት እንደሆነ ሥንረዳ ደግሞ ምን ያህል ለአገራችን እድገት እንደማያሥቡ በቀላሉ እንገዘባለን።
እየውልህ ፣ እንሥሣት እና አውሬዎች የየራሥሳቸው አንድ አይነት የማይለዋወጥ ሃሳብ እንዳላቸው እና ሰው ግን በአንድ ግዜ ብዙ አሳቦችን በአእምሮው ማውጠንጠን እና ማደራጀት ፣ እንደሁኔታው መተግበር የሚችል ቢሆኑም ፣ለሥጋዊ ጥቅሙ ሲል ብቻ የራሱን እና በውል የሚያውቃቸውን እንሥሣት ባህሪ ደምሮ በመላበሥ ፣ በቀላሉ በውሥጡ ያለውን የሞራል ህግ አሽቀንጥሮ እንደጣለ ተገንዝቤለሁ።
ከዚህ የራሴ ና የመሰሎቼ ግንዛቤ አንፃር ፣ ሥጋን የማሥደሰት ፍላጎቱን ያረካው የምእራቡ ዓለም ፣ መንፈሳዊ ፍላጎቱን ለማርካት ያለ ቅጥ እየተጋ ነው ቢባልም ገና ከሥጋ እርካታ ያለወጣ አይጠረቄ ና ሥግብግብ መሆኑንን ራሱም አይረዳውም። …
በተለይም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው አገሮች ፈረንሣይ ፣አሜሪካ፣እንግሊዝ ፣ሩሲያ፣ቻይና፣ጀርመን ፣ አፍሪካን ለመበዝበዝ እንጂ ፣አፍሪካን ለማበልፀግ ጥንትም ሆነ ዛሬ ብርቱ ፍላጎት የላቸውም።
አሥቀድመው የፈጠሩትን ምንሽር ፣ዲሞትፈር፣ለበን ፣ኤም ዋን …ዛሬ አቅርቦ ማሳያ በተገጠመላቸው ፣እሥከ 1000ሜ ድረሥ ያለ ዒላማ ለመጉዳት እንዲችሉ ተደርገው በተፈበረኩ መሣሪያዎች ቀይረዋል።
እደሜ በዜግነታቸው ኮርተው ፣በአርበኝነት መንፈሥ የጦር መሣሪያ ለሚፈለስፉላቸው ኢንጂነሮቻቸው ይሁንና …።
እንዲህ አይነቱን የጦር መሣሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈለሰፈው ኢንግሊዛዊው እንጂነር ጆሴፍ ኋይትወርዝ በ1853 እኤአ እንደነበረ ያሥታውሷል።ዛሬ ይህንን ገዳይ መሣሪያ በፀረ ሰው፣ ና በፀረ ተሽከርካሪ በመሥራት እጅግ አዘምነውታል።
የጥፋቱንም የልማቱንም መሣሪያ በመፍጠር ብቻ ሳይሆን በገፍ በማምረት ፣በማከማቸትና የኃይላቸውን ከፍታ በሰማይ ላይም በሳተላይትና በድሮን በማሣየት ዓለምን የሚገዞት እነሱ እንደሆኑ በገደምዳሜ ይነግሩናል።
የአፍሪካ አገራትም በፈጠራ እንዳይበለፅጉ ፣ ምጥቁ ጭንቅላት ያላቸውን ልጆቻቸውን ከየአገሩ እያደኑ ወደ አገራቸው ይወሥዳሉ። አገራቱንም በልዩ ልዩ አሻጥር ውሥብሥብ የኢኮኖሚ እና የፖለታካ ችግር ውሥጥ እንዲዘፈቁ ያደርጋሉ።ለእነሱ ብዝበዛ በቅጡ የሚገዛ የአፍሪካ አገር መሪ ሺ ዓመት እንዲገዛ ድጋፍና ጥበቃ ያደርጉለታል።ህዝቡንም በእርዳታና በጊዚያዊ ጥቅም ይደልሉታል። ‘ ለአገሬ ብልፅግና ያለመሞዳሞድ በህግ አግባብ ከሁሉም አገራት ጋር በትበብር እሠራለሁ።በተወሰነ የጊሥልጣን ጊዜ አምናለሁ።ሺ ዓመት ለመግዛት አልፈልግም።አገሬን እንደእናንተ ዓይነት መንግሥት በማቋቋም የታፈረች፣የተከበረች እና የበለፀገች አገር ለማድረግ እጥራለሁ።የብዝበዛ በሩ ዝግ ነው። ‘ የሚል የአፍሪካ አገር መሪ በአገሩ ሠላም እንዳይኖር እዛና እዚህ በራሱ አገር ሰው መሠል አውሬዎች አማካኝነት ሠላማዊ ሰው እንዲያልቅ በማድረግ የዋሁ ህዝብ መንግሥትን ለመቃወም ግልብጥ ብሎ እንዲወጣ በማድረግ ከሥልጣኑ ፈንግለው ፣ የራሳቸውን አሻጉሊት መንግሥት ይፈጥራሉ።
አፍሪካውያን መሪዎች ተደላድለው የመሪ ወንበር ላይ እንዳይቀመጡ በማድረግ ፣ ባላቸው የኢኮኖሚ ኃይል ና ወታደራዊ ጡጫ ፣በረጅሙ እጃቸው መሪውን እነሱ በፈለጉት አቅጣጫ ያሽከረክሩታል ። በተዘዋዋሪ (በእጅ አዙር) ቅኝ ይገዙታል።

አፍሪካ ብቻ ሳትሆን መላው ጉልበት አልባ መንግሥት በእነዚህ ኃያላን የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች አሥተሳሰብ የተነሳ እና ኃይማኖትን የጥቅም ማግኛ ባደረጉት በበለፀጉት አገራት ሞራለ ቢሥ በሆነ በማፋጀት ሥልት ዛሬም በዓለም ላይ ሺዎች ይሞታሉ።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን በትንሹ 108 ሚሊዮን ሰዎች በዓለም ዙሪያ በተካሄዱ ጦርነቶች እንደሞቱ ይታመናል።በዓለም ታሪክ በጦርነት ሰበብ እሥከ ዛሬ የሞቱ ከ150ሚ እሥከ አንድ ቢሊዮን እንደሚጠጉ የገመታል። የሃያኛው ክ/ዘመን ግን የባሰ ነው። እኤአ ፋሺሥት ኢጣሊያ በመርዝ ጋዝ እና በቦንብ በትግራይ ምድር በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባትና እናቶቻችንን መጨረሱን አሥታውሱ።
ምእራባውያን ጦርነት ጠቀሜታ አለው ብለው ያምናሉ ። ጦርነት ባሎችን ስለሚያጠፋ የወሊድ ቁጥርን ይቀንሳል የሚል ምፃታዊ ንግግር አላቸው።እርግጥ ነው በ20ኛው ክ/ዘ የ20 ሚሊዮን ህዝብ ያለመመጣጠን ነበር። ከጋብቻና ከወሊድ አንፃር።
ዛሬ በዓለም ዙሪያ 21.3 ሚሊዮን በበቂ መጠን የሠለጠነ ወታደር አለ።ከዚህ ውሥጥ 2.4 ሚሊዮን ወታደር የቻይና ነው።ቻይና አንደኛ ናት በጦር ኃይሏ ብዛት።ሁለተኛ በጦር በዛት አሜሪካ ናት።1.4ሚሊዮን ጦር አላት።ሦሥተኛዋ ህንድ ናት 1.3 ሚሊዮን ሠራዊት አላት። አራተኛዋ ሰሜን ኮርያ ሥትሆን አንድ ሚሊዮን ተዋጊ ጦር አላት። ሩሲያ 900,000 የዘመነ ጦር የመከላከያ ኃይል አላት። በማደግ ላይ ካሉ አገራት ውሥጥ አሥራ አራቱ በከፍተኛ ደረጃ በሰው ኃይልና በመሣሪያ የተደራጀ ኃይል አላቸው። ከእነዚህ ውሥጥ ግብፅን ይጠቅሷል።
የዓለም አገራት ይህን ያህል በዘመናዊ መሣሪያ ፣በሰው ኃይል ተደራጅተው ድንበራቸውን በተጠንቀቅ ከመጠበቅ አልፈው የሌላውን ኃያል አገር እንቅሥቃሴ በሳተላይታቸው 24 ሰዓት ይከታተላሉ ።
እነዚህ የበለፀጉት አገራት ጦር መሣሪያዎችን ደግነው ሌላውን ባለፀጋ አገር የማከታተሉት የጦረነት ሱስ ወይም በደማቸው ውሥጥ የገዳይነት ዘረ መል ሥለለ ነውን? አይደለም። የሰው ልጅ ከአራዊት ኑሮ በቀሰመው ልምድ መደራጀትና በህበረት ና በከፍተኛ ኃይል ማጥቃት ለመከበር እንደሚረዳ ሥለተማረ ነው።አንበሳ ብቻውን በጫካ ውሥጥ ተከባሪ ሆኖ አይዘልቅም ።ከበዙት ዝርያዎቹ ጋር ከሆነ ግን ዘላለም የጫካው ንጉሥ ነው።በቃ። ከዚህ አንፃር ጥያቄህን ተመልከተው።ጫካውን እንደ ዓለማችን ውሰደውና። ”
“አቶ ኦደአት አበሻ አንተሥ ምን ትላለህ ?”
” ኧ ! በበኩሌ በሪሞት የመቆጣጠር ሥራውን አንበሶቹ ኃያላን መንግሥታት ነገም ይቀጥላሉ። ምክንያቱም የእጅ ጥምዘዛቸውን ከቶም መቀልበሥ አይቻልም። ለማደግ፣ለመበልፀግ የሚፍጨረጨሩ አገራትም ከብረት የጠነከረ የኢኮኖሚ ጡንቻቸውን በፍፁም መቋቋም አይችሉም። እናም አማራጫቸው እንብዛም የማይሰገበገቡትን ግን ደግሞ ከአገራቸው ዘላቃ ጥቅም አንፃር የታዳጊ አገራትን የማደግ ፍላጎት የሚያግዙትን የሙጥኝ ማለት ነው።
እርግጥ ነው ፣ የታዳጊ አገር ዜጎች 50 % ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚኖሩ ናቸው።የኢትዮጵያ ደግሞ እጅግ የከፋ ነው።ከ85% የማያንሰው ኑሮው ከእጅ ወደአፍ ነው።ኢትዮጵያ በዓለም ካሉ እጅግ ደሃ ከሆኑ አገራት የምትበልጠው ሥድሥት አገራትን ነው። ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎን ፣ሞዛምቢክን ፣ዩጋንዳን፣ካጃክሥታን ፣የመን እና ሄቲን ነው። ታንዛንያ ኪሪጊኪሥታን ሁዝቤኪሥታን፣ ደግሞ ከ10ሩ የመጨረሻዎቹ ደሃ አገራት ዝርዝር ውሥጥ በ8,9 ና አሥረኛ ደረጃ የተቀመጡ ናቸው።
በዚህ ሁኔታ ውሥጥ እያለህ ፣ ሀብታም አገራትን ማግለል አትችልም።የምትዘባነንበት ሁለንተናዊ አቅም የለህም።ድህነት በራሱ ደቁሶሃል። የህዝብህ መሠረታዊ ችግር ገና አልተፈታም።በቂ መንገድ የለህም።ንፁህ ውሃ ለህዝብህ ገና አላደረሥክም። ከዜጎችህ መካከል ብቁ የሚባል መጠለያ ያላቸው ጥቂቶች ናቸው። ዘመናዊ ኑሮን የሚያግዝ የኤሌትሪክ ሥርጭትህ ሃምሳ ፐርሰንት እንኳን ለህዝብ አልተዳረሰም። እርሻህ ኋላ ቀር ነው። የጤና ተቋሞችህ ለመላው ህዝብህ አልደረሱም ።አንተ በባለአምሥት ኮኮብ ሆቴል ሥለምትፈላሰስ በውስኪ ስለምትታጠብ ና አደግዳጊህ ሰለበዛ በአሳፋሪ ድህነት ውሥጥ የምትኖር አገር ዜጋ መሆንህን አትርሳ። የአውሮፖ አገራት ምሁራን መዘባበቻ ደሃ መሆንህን አትዘንጋ።
የአውሮፓ ና የአሜሪካ ምሁራን ዓለም አቀፍ ሙያዎችን ተምሮ የተመረቀን ሙያተኛ በቋንቋ ገድበህ በየክልሉ እንዲወሰን ማድረግህን አይደግፉልህም። ሙያ ቋንቋ ተኮር በማድረግ በቂ የእውቀት ሽግግር እንዳይኖር በማድረግ በክህሎት ደካማ የሆኑ ባለሙያዎች እንዲበዙና መላው ዜጋ እንዳይጠቀም አድርገሃልና። የሳይንሥ ሙያዎች በቋንቋ ተከልለው ቅጥርን የሚገድቡ አይደሉም። እንደወትድርና ሣይንሥ ብሔር፣ጎሤ፣ነገድ፣ቀለም ቋንቋ የለቸውም።…ግን ፖለቲከኞች ይህንን አይገነዘቡም። …
ፖለቲከኞቹ ይህንን ያልተገነዘቡት የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ያጠመዱላቸው ወጥመድ ውሥጥ አንገታቸውን ሥላሥገቡ ነው።የእኛ ፖለቲከኞች የአእምሮ ደሃ ናቸው።ዓለም ከምን ተነሥታ የት እንደደረሰች አያሥተውሉም።አንገታቸውን ይዘው የሚጎትቷቸው የበለፀጉት አገራት የፖለታካ ሤረኞችም የአገራቸውን የእድገት መንገድ አያሥተምሯቸውም። የሚያሥተምሯቸው በያዙት ቆዳን የማዋደድ መንገድ እንዲገፉ ነው። ዛሬ ያለአግባብ የሚበሉትን እንጀራ ለማሥቀጠል የሚችል ብቸኛ መንገድ ቆዳ ማዋደድ ብቻ እንደሆነ አሥረግጠው ይነግሯቸዋል።እናም በኢትዮጵያ የቋንቋ ትርጉም ከበለፀገው አገራቸው ከተሰጠው በተቃራኒ እንዲሆን ያበረታታሉ ።የራሳቸው ቋንቋ በአፍሪካ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሣለ በእኛ አገር አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይሆን ተሟጋች ፖለቲከኞች ይፈጥራሉ። በአማርኛ በጎንደር ዘዬ እየተናገረ አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይሆን የሚሞግት የጎሣ ፖለቲካ የመሠረተ የፖለቲካ ፖርቲ መሪ በኢትዮጵያ ብቻ ነው ያለው።
ይህ እውነት በብዙዎቹ በሳል ምሁራኖች ፣ሊቆችና ጎምቱ ፖለቲከኞች ገና ወያኔ/ኢህአዴግ ሥልጣን እንደያዘ ቢነገር እና በየመፀሔቱ ቢፃፍም ሰሚ ባለማግኘቱ ይኸው ለዛሬው ትርምሥ በቅተናል ።አሁንም በዚች አገር የሥያሜ ለውጥ እንጂ የተግባር ለውጥ ገና አልመጣም።’ጉልቻው ተቀየረ እንጂ ሾርባው ያው ነው። ‘ሳናውቀው እየጨረሰን ያለው የዘር፣የጎሤ፣የነገድ ና የቋንቋ ካንሰር በአማራም፣በኦሮሞም፣በትግሬም ጎሣ አለ።ይህ አገር አጥፊ የሆነ ፀረ ሠላም ፀረ ፍቅር ካንሰር በደቡብ የአገራችን ክፍልም እንዳይሥፋፋ እሠጋለሁ። ሥጋቴ እውን የማይሆነው እንደ ኃያላኑ አገራት መንግሥታት ሥለአገራችን ታላቅነት፣ክብር እና ሥለ “ዜጎች ብልፅግና” ማንኛውንም መሥዋትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ መንግሥት ሲኖረን ብቻ ነው።…”
” አቶ ኦደአት አበሻ እና አቶ ላሊበላ ዘ አክሱም ፣ ሥለነበረን ጊዜ በተመልካቾቼ ሥም አመሠግናለሁ።እግዜር ይሥጥልኝ።”
“እናመሠግናለን !!”

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop