ኮሚሽን+ ሙሥና =ያልተገባ ብልፅግና መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

” ኮሚሽን ካገኛችሁ ንፉ ! ”  ትላንት በአደባባይ ይባል ነበር። ዛሬም ይህ ሙሥናን የሚያበረታታ በባለሥልጣናት ይሁንታ የተቸረው አገር ገዳይ ረቂቅ ምዝበራ የለም ፡፡ ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመሥለኝም። ምክንያቱም የበዙ መረጃዎች ህዝቡ ውሥጥ አሉና !

የለመረጃ መፃፍ አያፀድቅም። ህዝቡ ውሥጥ ያለውን መረጃ ጠቅሶ የሚመለከተው የመንግሥተ ተቋም መፍትሄውን እንዲሻ ማድረግ ግን እንደሚያፀድቅ ከተገነዘብኩ ሰነበትኩ። ያለማሥረጃ መፃፍ በጥልቅ አንባቢ ከዱላ በባሰ ሂስ እንደሚያሥቀጠቅጥም ካወቅሁ ዘመናት ተቆጥረዋል። እናም የማውቀውን ምድር ላይ ያለውን የአገሬን እውነተኛ ችግር በመረጃ ላይ ተመሥርቼ እየፃፍኩ ነው። ለኃይማኖተኛው ወገኔ ትልቅ ክብር አለኝ። ደግሞም ባክኖ የማይቀረው እርግማኑንን እፈራለሁ።

የዚህ ኩሩና ፍቅር የሆነ ህዝብ፣ እርግማንም ሆነ ምርቃት ቶሎ ይደርሳል። በሐሰተኛ መረጃ ሠላሙን ማደፍረስ የማልፈልገው ለዚሀ ነው። እንደሁል ጊዜው ዛሬም ሰው መሆንን መካድ በመሥተማር ጎሳዊ አመለካከት እንዲኖረን ባደረጉት ባንዶች እና በአጫፋሪዎቻቸው ላይ እርግማኑ ሲደርሥ አይቻለሁና በግብዝ አሥተሳሰብ የተቃኘ ፅሑፍ አልፅፍም።

ከዚህ ኃይማኖተኛ ህዝብ ጋር በሐሰተኛ መረጃ ሰበብ መቀያየም ሥለሌለብኝ፣ የሚያውቀውን ወይም የልቡን እውነት ነው ዘወትር የምፅፍለት። ከዚህ እውነትን ያዘለ ፅሑፍ ተነሥቶ የአገሬ መንግሥት፣ በደሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሚደርሥበት ህዝብ መላ እንዲያበጅለትና ያልዘገየ መፍትሄ እንዲሰጠው ዘወትር መቆሥቆሴን ሥለሚገነዘብ በፅሑፎቼ ደሥተኛ ነኝ። (ሰው ሥለ አገሩ ህይወቱን ይሰጥ የለ እንዴ?)።

እናም ዛሬ ህዝብ ሥለሚያውቀው መንግሥት እብዛም ሥለላጨከነበት ግልፅ ዘረፋና ሌብነት ሥለ አገር አቆርቋዡ ” ኮሚሽን “እፅፋለሁ። ኮሚሽን ሌብነትንና ዘረፋ ፣ ለፅድቅ የማይበቃ ህዝብን አደናጋሪ ሥም ነው።

በዚች አገር ዛሬና አሁን በአደናጋሪው ሥም የመንግሥት እና የህዝብ ሀብት ያለ ሃይ ባይ ቢመዘበርም ቅሉ፣”  ኮሚሽን ካገኛችሁ ንፉ ” በማለት ለዘረፋ የሚገፋፋ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዳለ ግን አልሰማሁም። ወይም መረጃ የለኝም። እንደ ብዙዎቹ ተራ ሟቾች የማውቀው አንድ ነገር ቢኖር፣ የአደባባይ ይሁንታ ባያገኝም ዛሬም ያለከልካይ ኮሚሽን ይነፋል። በኮሚሽን ቤትና ንብረት በአጭርና በረዢም ግዜ ለማፍራት ይቻላል። የሙሥናው በር ዛሬም ክፍት ነው። የሥርቆት በሩ አልታሸገም። በኮሚሽንም የቅንጡ መኪና ባለቤት ለመሆን የሚያሥችለው መንገድም እንደተበረገደ ነው። (እሥከ ጋዜጠኞቻችን አክቲቪስቶቻችን ደረስ)

ይህ ግለሰብን አበልፃጊ አገር አውዳሚ የኮሚሽን መንገድ፣ ትላንት ወያኔ / ኢህአዴግ በነፍጥ ኃይል ምኒልክ ቤተመንግሥት ከገባ በኋላ የተደላደለ ነው። ይህ መንገድም አገር አውዳሚ የብልጣብልጦች ተግባርን የሚያሠልጥ ነው። ሌብነትን በኮሚሽን ሥም ማሽሞንሞን የብልጣ ብልጦች አሳቻ መንገድ መሆኑ መታወቅ አለበት ።ይህ አሳቻ መንገድ በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ ተወድሶ በአደባባይ ” ከሚሽን ካገኛችሁ ንፉ። “ተብለው የአምራች ፋብሪካዎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ በዘመነ ወያኔ/ኢህአዴግ ይሁንታ ተችሯቸው እንደነበር በ1988 ዓ/ም አንድ የሥራ ባልደረባዬ አጫውቶኛል።

በ1988  ዓ/ም አ/አ በአንድ ፋብሪካ ውሥጥ በሙያዬ ተቀጥሬ ሥሰራ አንድ በመንግሥት ልማት ድርጅት ሥብሰባ ላይ የተሳተፈ    (በቅርብ ወደ እኛ ፋብሪካ ከመቀጠሩ በፊት በሌላ ፋብሪካ ሰራተኛውን ወክሎ የቦርድ አባል የነበረ ) አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊን በሥም ጠቅሶ “ይገርምሃል አቶ እገሌ የመንግሥት የልማት ድርጅቶቾ ከፍተኛ ባለሥልጣን … የፋብራካ ሥራ አሥኪያጆችና ቦርዶችን ሰብሥቦን ምን እንዳለን ታቃለህ ? ” ከፍብሪካው ሂሳብ ወይም ካዝና ላይ አትሰረቁ እንጂ ኮሚሽን ካገኛችሁ ንፉ !! ” አለን። ” እውነቴን ነው የምልህ። ቃል በቃል “ኮሚሽን ካገኛችሁ ንፉ! ” ነው ያለን። ” በማለት አጫውቶኝ ነበር። ዛሬ በድፍረትና በማን አለብኝነት፣ በግልፅ በአደባባይ፣ምሥክር ባለበት ” ኮሚሺን ንፉ !”  የሚል ባለሥልጣን ባይኖርም ኮምሽን  ” በተዋረድ”  አይነፋም አንልም።

ለመሆኑ ኮሚሽን ምንድ ነው? ኮሚሽን ከእንግሊዘኛ የተወሰደ በአማርኛ አቻ ትርጉም ያልተሰጠው ቃል ነው። ብዙ ትርጉሞች እንዳሉት የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ይገልፃል።

ኮሚሽን አሥቀድሞ በተገባ ሥምምነት መሠረት የሚከፈል የአገልግሎት ዋጋ ነው። በዘመናዊው ዓለም የህግ መአቀፍ ተዘጋጅቶለት እንድተቋም ወይም ድርጅት ሠራተኞች ቀጥሮ ለሌላው ተቋም፣ ድርጅት ወይም ግለሰብ ለሚሰጠው አገልግሎት በህግ የተፈቀደለትን የአገልግሎት ክፍያ ወይም ኮሚሽን ይቀበላል። …ይህ አንድትርጉሙ ነው። ኮሚሽን ሌሎች ትርጉሞችም አሉት። አንድ የተወሰነ ተግባርን እንዲያከናውን በህግ ሥልጣን የተሰጠው ተቋምም ኮሚሽን ይባላል። የሥደተኛ፣ የጉምሩክ፣ የፖሊሥ ወዘተ። ኮሚሽንን ይጠቅሷል።

ለፅሑፊ የመረጥኩት የመጀመሪያውን የኮሚሽን ትርጉም ነው። ይህ የኮሚሽን ትርጉም ግን በእኛ አገር ትክክለኛውን ትርጓሜ የያዘ አይደለም። በእርግጥ በህግ የተቋቋሙ በህጋዊ ውል መሠረት አገልግሎታቸው ተለክቶ ኮሚሽን የሚከፈላቸው ተቋማትና ግለሰቦች አሉ። ከዚህ በተቃራኒው በሆነ መንገድ ደግሞ ህግ ከለላ አድርገው የሚዘርፉ አሉ።

ለምሳሌ በመንግሥት የፋይናሥ አገልግሎት፣ ኦዲተሮች ሽፋን ጭምር እየታገዙ የሚከናወኑ ህጋዊነትን የተላበሱ ዘረፋዎችና ሥርቆቶችን መጥቀሥ እውነቱን ያሥረዳል።

በእቃ ግዢ የተሰማሩ ከላይ እሥከታች የተሰማሩ የመንግሥት ሰራተኞች ከጨረታ ኮሚቴዎች ጋር ግን ባር በመፍጠር፣ በከፍተኛ አመራሩ በመደገፍ የራሳቸውን ኪስ የሚያሥከብር ያልተገባ ግዢ እንዲፈፀም ያደርጋሉ። በዚች አገር ዝቅተኛውን  የመንግስት መ/ቤት ኃላፊ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛውንም ኃላፊ የሚያካትት በኮምሽን ሥም ከፍተኛ ምዝበራ እየተፈፀመ ዘመናት እንደባጁ እናውቃለን።    ( ህግን ያጣመመ በሐሰት የተሞላ የትኛውም የመንግሥት መሥራቤቶች ሊጎዳ የሚችል ህጋዊ መሠል ሆኖም ህገ ወጥ የኮሚሽን አከፋፈል ተግባር በዚች ደሃ አገር በግልፅ በአደባባይ እየተከናወነ ብዙዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የግዢ እና የንብረት ክፍል ሠራተኞች ባለ ቪላ ቤት፣ባለመኪና እና የልዩ ልዩ የንግድ ድርጅቶች ባለቤቶች ብቻ ሳይሆኑ በብዙ ባንኮች ባለአክስዮን እንደሆኑ ህዝብ ያውቃል።)

በዚች ደሃ አገር፣ በዚች ብዙሃኑ በቀን አንዴ በሚበላባት አገር ከሚጢጢዋ ሙሥና እሥከ ትልቁ ሙሥና ላለፉት 27 ዓመታት ተንሰራፍቶ ግለሰቦች በመሬት ዘረፋ፣ በድለለና በኮሚሽን ከብረውባት እንደነበር የታወቃል።

ሚጢጢዋ ሙሥና ታች ባሉት ዝቅተኛ ደሞዝ ባላቸው እቃ ግዢዎች አማካኝነት የሚከናወን ነው። የ100 ብሯን ጥራት ያላትን እቃ በተመሳሳይ የማይረባ እቃ ቀይሮ በ70 ብር በመግዛት በትንሹ  20 ብር ከአንድ ዕቃ ኮሚሽን ማግኘት ነው። እርግጥ ነው፣ጥራት ባላቸው እቃዎችም ላይ ኮሚሽን ይገኛል። የተጋነነ ባይሆንም። እንግዲህ በተመሳሳይ እቃዎች እና ብዛታቸው ልክ ፣አንድ በገዢ ላይ የተሠማራ የመንግሥት ሠራተኛ ” ሥንትና ሥንት ኮሚሽን እንደሚነፋ ” አሥቡ? ይህንን ብቻ አይደለም ማሰብ ያለባችሁ፣ጥራት በሌለው እቃ ግዢ ሰበብ በሚያጋጥም ብልሽት ተጨማሪ ወጪ ለማውጣት እያንዳንዱ የመንግሥት መሥራቤት እና የመንግሥት ፋብሪካ እንደሚገደድም አሥቡ።

በሚጢጢ ሙሥና  (pity corruption )  ባልተገባ ኮሚሽን ወይም ሲቪል ሰርቪሱን እና የመንግሥት የልማት ተቋማትን በመጉዳት በጥቂት ዓመታት ውሥጥ የራሳቸውን ንብረት ያካበቱ፣   በለቤትና ባለመኪና የሆኑ ጥቂት አይደሉም።…

በዚህ ጉዳይ ላይ ከአንዲት የመሥራ ቤት ባልደረባዬ ጋር ሥንወያይ ” በደሞዜ ብቻ ሥለምሰራ ይኸው ጅምር  105 ቤቴን እንደነገሩ መጨረሥ አቅቶኝ ላለፉት አሥር አመታት እየተፍጨረጨርኩ ነው። ” ያለችኝን በአሥር ዓመት ባለ ቪላ ቤት እና ባለመኪና ከሆኑት፣ የኮሚሽን ተጠቃሚ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በማወዳደር በደሞዝ ብቻ ቤት መሥራት እንደማይቻል ተገንዝቤለሁ።…

ትልቁ ሙሥና (Grand  corruption ) ከትንሾ (pity corruption ) የሚለየው፣በሥርቆት ለመክበር ዓመታትን የማይጠይቅ፣ በቀናት ውሥጥ ሚሊዮነር የሚያደርግ በመሆኑ ነው።

ይህ ሙሥና የአገርን እድገት በእጅጉ የሚያቀጭጭ ነው። አገር እና ህዝብ በድህነት እንዲዘልቁ የሚያደርግም ነው። ይህ ሙሥና በከፍተኛው የሥልጣን አካል የሚፈፀም ምዝበራ ነው።ምዝበራውም በአገር ውሥጥ ከባንክ ጋር ሲገናኝ በውጪ አገር ደግሞ ከውጪ ምንዛሬ እና ከውጪ ኩባንያዎች ጋር ይገናኛል።

ከባንክ ጋር የተገናኘውን፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኢንቨሥትመንት ሥም የተዘረፈውን ብር እና ከኢትዮጵያ  ንግድ ባንክ በብድር ሥም የተፈፀመውን አያሌ ሙሥና ለመርመሪ ጋዜጠኞች እተወዋለሁ።…

ከሁሉ የሚያሳዝነው የአገር ውሥጥ ፋብሪካዎች በኮሚሽን ሰበብበ አገር ውሥጥ ጥሬ እቃ እንዳይጠቀሙ መደረጋቸው ነው። ፋብሪካዎቹ በአገር ውሥጥ ጥሬ እቃ እንዳይጠቀሙ ጉዳዩ በዋነኝነት የሚመለከታቸው የመንግሥት ሹማምንቶች በመንደር እና በሰፈር ጉልበተኞች ሲያላክኩ ይገርመኛል። ዋነኛው ሰበብ ኮሚሽን ነው። የኮሚሽንን ረብጣ ዶላር ለማግኘት በየመንደሩ ላሉት ጉልቤዎች ጥቂት ከዶላሩ ቆንጥሮ መክፈል ትላንት ያሥፈልግ ነበረ። ዛሬሥ ፣የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግሥት ቆርጦ ተነሥቶ እንደሻኪሶ የቧንቧ ውሃ መአድን ማውጫዎች በህግ አግባብ ሥራቸውን ለምን አይሰሩም ?ለምንድነው አገሪቱ በሌላት የውጪ ምንዛሬ አገር ውሥጥ ያለ ጥሬ እቃ ከውጪ እንድትገዛ የምትገደደው ?…ዛሬም “ኮምሽን ካገኛችሁ ንፉ ! “የሚል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን አለን??? (ይህንን ለምሳሌ ነው ያቀረብኩት፡፡እውነትቱን ሥለማውቅ)

እንዲህ ዓይነቱ አገር አውዳሚ እና በቀን አንዴ ለመብለት በሚያዳግተው ወገኑ ላይ የሚያላግጥ ዝርፊያና ሌብነትን የሚያበረታታ ባለሥልጣን ዛሬም ካለ፣ይህቺ አገር መቸውንም መበልፀግ አትችልም። ምክንያቱም እነዚህ ከሆድ የዘለለ ራእይ የሌላቸው ግለሰቦች ህዝብና መንግሥት በጥርጣሬ እንዲተያዩ ከማድረጋቸውም በላይ ተሥፋ አሥቆራጭ ሀሜቶችን እንዲስፋፋ ሥለሚያደርጉ ሁሌም ከግጭት አዙሪት ውሥጥ ለመውጣት ያዳግተናል።

ህዝብና መንግሥት ያለመጠራጠር፣ያለብዙ ሀሜትና ምሬት ለአገር እድገትና ብልፅግና እንዲሰሩ ” በኮምሽን” ሥም በተጨባጭ የሚፈፀሙ፣ ዘወትር በተለያዩ የመንግሥት መሥርያቤቶች የሚሥተዋሉ ግለሰባዊ ምዝበራዎች መገታት አለባቸው። ይህን ማንንም የማይጎዳ የሚመሥል ሆኖም እጅግ አገርን የሚጎዳ እና ግለሰቦችን የሚያበለፀግ እሥከዛሬ ያልተነቃበት “ምሥጢራዊ የሌብነት መንገድ ” ዛሬ፣ነገ ሳይባል የሚወገድበት መንገድ መበጀት አለበት። ትክክለኛውን ግልፅ የሆነ እና ተጠያቂነት ያለው በጥብቅ ቁጥጥርና ተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ አሠራርም መዘርጋት ይኖርበታል። ተቆጣጣሪ ተቋም ይህ የለውጥ መንግሥት ሊፈጥርና የተንሰራፋውን የሌብነቱን ሠንሠለት በአሥቸኳይ መቁረጥ ካልቻለ የምንፈልገውና፣ የምንደክምለትና ሌት ተቀን የምንጥርለት ብልፅግና ተረት ተረት ሆኖ ነው የሚቀረው።ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውሥጥ “ኮሚሽን ሌላው ሽቀባ ነውና” መንግሥት በአገር ሥም ሌባ ግለሰቦችን እያበለፀገ እንዳለ በቅጡ መገንዘብ ይኖርበታል።

እርግጥ ነው፣ ይህንን እውነት መንግሥት አልተገነዘበውም ለማለት አይቻልም። በቅጡ ያልኩትም ለዚህ ነው።ለዚች አገር ችግር በህግ አግባብ ትክክለኛ መፍትሄ ለመሥጠት ሌት ተቀን የሚባዝኑ፣ የሚጥሩና ከልባቸው የሚደክሙ ጥቂት በመሆናቸው የዝኽችን አገር ችግር በአጭር ጊዜ መፍታት እንዳልተቻለ አውቀለሁ።ይሁን እንጂ በልዩ፣ልዩ ወቅታዊ ችግሮች ቢዘገይም ዛሬ ለውጡ ወደ ትክክለኛው የብልፅግና መንገድ እየገባ እንደሆነም እረዳለሁ። እኔንን የሚያሳስበኝ ግን የሚሰራ ሰውን በመቀፍና ዛሬም ” የዚች አገር ሠላም ከተረጋገጠ፣ሰላም በምድሯ ከሰፈነ የእኛ ምዝበራ ያከትማል። በሌብነት ያከማቸነውም ሀብት ለውርስ ይጋለጣል። የአገሪቱ ሀብቱ የዜጎች ሁሉ ይሆናል። እና በውሸት፣ በሥም ማጥፋት፣ በሽፍትነት፣ መንገድ በመዝጋትና በማዘጋት፣በሁከት፣በሐሰተኛ ወሬ ይህንን ህዝብ በመበጥበጥ መንግሥት አቅመ ቢሥ እንደሆነ በማሳየት ሌላ የእኛን ጥቅም አሥቀጣይ መንግሥት እንዲፈጠር እናደርጋለን። ” በማለት ውሥጥ ለውሥጥ ከቀኝም ከግራ አገር እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ መኖራቸው ነው፡፡…ለአገሬ ጠ/ሚ እና አብረዋቸው በሃቅ ለተሰለፉ ጓዶቻቸው አድናቆቴ ከፍተኛ ቢሆንም ያለባቸውን የግራ እና ቀኝ ጫና ተቋቁመው የህግ የበላይነትን ለማሥከበር በብርቱ ካልጣሩና ዋንኛ ሰንኮፎቹን በህግ አግባብ ካላሶገዱ እና በመላው ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲኖርና ሰላም እንዲሰፍን ካላደረጉ በሥተቀ ርህዝቡ የሚሻውን ብልፅግና እውን ለማድረግ አይችሉም።

የህግ የበላይነት ሰፊ ትርጉም  አለው።በኮሚሽን ሰበብ መመዝበር በራሱ ህግ መጣሥ ነው። ህግን የበታች ማድረግ ነው። በአንድ የመንግሥት ተቋም ውሥጥ እያገለገለ ሥለራሱ ኮሚሽን የሚደራደር ህገ ወጥ ነው። ሌባ ነው። ይህ ግለሰብ እላይ ይኑር እታች፣ዝቅተኛ ሹመኛም ይሁን ከፍተኛ የሚያገለግለውን የመንግሥት ተቋም በኃቅና በደሞዙ ብቻ ማገልገል ይጠበቅበታል።

ዛሬ ና አሁን ግን ያለመታደል ሆኖ፣ ለተቀጠሩበት ተቋም ሳይሆን ለኮሚሽናቸው ቀጣይነት ዘወትር የሚጥሩ እና በመንግሥት ውሥጥ ሆነው እንደነቀዝና ምሥጥ መንግሥትን የሚቦረቡሩ እንዳሉ እንገነዘባለን። በዚህ አይነት በግልፅ ባልተነገረ በተግባር ግን ኮሚሽን በሚነፋበት አገር ውሥጥ እየኖርን እንዴት ነው ፣ዜጎች በእኩል ደረጃ መበልፀግ የሚችሉት???

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.