ህወሓት የፈጠረችው ዘረኛ ስርአት እና የአሀዳዊነት እውነተኛ ግጽታ – መንግስቱ ሞሴ

ዳላስ

የዘንድሮ ጽንፈኛ የዘር ድርጅቶች ፌደራል ሀገራዊ አወቃቀርን እንደመስፈርት በመውሰድ (ፌደራሊስት እና አሃዳዊ) የሚሉ ልዩነት ፈጥረዋል። ህወሓት እና የኦሮሞ ጽንፈኞች አሃዳዊ የምትል ቃልን መለኮታዊ ውግዘት እና ሰይጣናዊ ገጽታ ሰጥተው ልዩ እና ጭራቅ ስርአት አድርገው ለአልተማረ እና በለብለብ ፖለቲካ ለሚከንፍ ዜጋ እያቀረቡለት ነው። ግን አሀዳዊ ሆኖ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርአት መኖሩን፣ ፌደራላዊ ሆኖ አንባገነን እና ጨቋኝ ስርአት እንዳለ ሊያሳዩ አቅሙም ፍላጎቱም አይታይባቸውም። ለነገሩ 27 አመታት ኢትዮጵያን በዘር ጨቁና የገዛችው ህወሓት በእጅጉ የከፋ ዘረኛ ስርአት እንዳስተናገደች እነበቀለ ገርባ ባይናገሩት ዜጎች በደማቸው ተምረውበታል እናም ያ የወያኔ አስተዳደር ፌደራላዊ ከሆነ ምንም አይነት ስም ይልበስ ከህወሓት ዘመን የማይሻል የለም የሚያስብልጭራቅ መንግስታዊ አስተዳደር አስተናግደናል ህገመንግስቱ ዕስካልተቀየረ እና ዘረኝነት እና የዘር ክልል ከዘር የፖለቲካ ድርጅት ጋር ካልጠፋ የዜጎች ችግር እና ሀገራዊ የሀገራዊ አንድነት ችግርም ቀጣይ ነው። ሕዝብንም ለማደናገር የሕዝብ መብቶች በዚህ Concept ዙሪያ ብቻ የሚፈቱ ናቸው የሚያሰኝ አስተሳሰብ በሕዝብ ልቦና እንዲሰርጽ የተደረገ አደገኛ ፕሮፖጋንዳ ነው።

ሁለተኛው አስተሳሰብ አገራዊ አንድነትን፣ የሕዝብ እኩልነትን፣ የመጻፍ የመናገር መብትን ለጋሽ የሆነ ስርአተ መንግስት ይኑር ሲባል ፌደራላዊ ማለት እንዳልሆነ ግን ብዙወች በጽንፉ ጎራ ያሉት ልሂቃን አይገባቸውም ትቂቶቹ ደግሞ ያደናቁሩናል እናም ፌደራሊስት መሆን ለነሱ ፍጹምነት ሲሆን አሀዳውዊነት ደግሞ ጨፍላቂነት ነው ብለው አስትሳሰቡን ለህዝብ አስተምረዋል። ባጭሩ እነዚህ ሀይሎች ብዙወቹ ሳያውቁ የሚያስተጋቡ ሲሆን። ትቂቶች ኤሊቶች ግን አውቀው የሀገሪቱን አገራዊ እና የሕዝብ አንድነት ማየት ስለማይፈልጉ ለስርአተ መንግስት ታፔላ መለጠፋቸው ነው።

ባጭሩ እንዲህ እንጀምረው፦ ዴሞክራሲ እና ፌደራሊዝም በአንድ ሊሰሩም ተነጣጥለው ሊያገለግሉም ይችላሉ። ፌደራሊዝም በስርአተ መንግስት የተዋወቀው የአዲሱ አለም (አሜሪካ) ከተፈጠረች በኋላ ነው። አሜሪካ ስትፈጠር እና እንደሀገር 1776 ስትቆም ደግሞ እራሱን የቻለ ከሌሎች ሀገራት የሚለዩት ሁኔታወች ነበሯት። The newly formed congress of the United States of America on September 9, 1776 declared the name of the new nation to be the United States that was created from a cluster of colonies. አሁን የ 51 ግዛቶች ባለቤት የሆነችው አሜሪካ አፈጣጠሯ ግን በ13 ግዛቶች ብቻ ነበር። ሌሎቹ ግዛቶች ወደተባበሩት 13 የአሜሪካ ግዛቶች በተለያየ ግዜ የተጨመሩ ናቸው። ለምሳሌ ይህን መጣጥፍ አቅራቢ የሚኖርበት እና አሁን በተባበሩት አሜሪካ ግዛቶች ትልቁ የሆነው ግዛት ቴክሳስ ወደ Union የተጨመረው 1845 ነው። ይህ ማለት United Sates of America ከተመሰረተች እና ህገመንግስቷን ካጸደቀች 69 አመታት በኋላ መሆኑ ነው። ሌሎችም እንዲሁ እናም ፌደራል ማለትም ላላ ያለ የግዛቶች አንድነት ያስፈለገበትም ከዚህ እራሳቸውን ችለው የቆዩ ሀገራት በተለያየ ግዜ በመጨመር እና የራሳቸው የሆነ አሰራር የውስጥ ህግ እና ደንብም ይዘው ስለገቡ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሎም አዲስ ፌደራላዊ አወቃቀርም ለመስራት ያስፈለገበት ይህ ምክንያት ሆኖ ነው። ይህ መጣጥፍ ፌደራሊዝም እንዴት መጣ ኋላስ ሌሎች እንዴት ተጠቀሙበት የሚል ጥልቅ ትንታኔ ለመስጠት የታሰበ አይደለም ግን ለግንዛቤ እና ምሳሌ ለማቅረብ ያክል መሆኑ እንዲታወቅ ያስፈልጋል።

የአሜሪካም ሆነ ሌሎች ፌደራል ሀገራት ዴሞክራሲያዊ የሆነ ህገመንግስት በማውጣት ፌደራሊዝምን እንዲሰራ ያደረጉ እዳሉ ሁሉ፤ ፌደራሊዝም ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርአት ካልተጨመረበት የሕዝብ ጭቆናን እና በደልን የሚያስቀር አለመሆኑ ልንገነዘብ ይገባል።

 

ኢትዮጵያ ዘረኛ ድርጅቶች የዘር ክልል እና ፌደራላዊነት

 

ህወሓት/ኦነግ እና ሌሎች በዘር ተሰይመው የተደራጁ ሁሉ የባንቱስታን ወይንም ህወሓት ለቅኝ አገዛዝነት እንዲመቻት የፈጠረቻቸውን ክልሎች ፌደራል ናቸው መብት እና ስርአት ተከብሮልናል እና በትግል ያገኘነውን አናስነጥቅም የሚል ቧልት ይዘውል። እውነታው ግን በህወሓትም ሆነ ኦነግ የተከለሉ የዘር ክልሎች ዴሞክራሲን፣ ነጻነትን እኩልነትን እና ሀገራዊ ሉአላዊነትን ሳይሆን የሰጡን። የአንድ ሀገር ልጆች በባ’እድ አይን መተያየትን፣ መጠራጠር እና አለመተማመንን እኔ እና አንተ የሚል አስተሳሰብን ከሁሉም በላይ በየትኛውም ሀገር የሌለ በክልል ውስጥ የሚኖሩ የሌላ ክልል ወገኖችን ሀገራችሁ አይደለም ውጡ በሚል መገዳደልን። ሰው በሀገሩ ውስጥ ከአንድ ክልል ወደሌላ ከሄደ ባእድነት እንጅ ዜግነት የማይሰማው መሆንን ነው የሰጡን። ኢትዮጵያ እንደሀገር ትቀጥል ከተባለ ይህን አስተሳሰብ እና ስርአተ አስተዳደር በሉት ማስወገድ እና ዜጋ በየትም ሄዶ ሊኖርበት የሚችልበትን ሀገሬ ብሎ ሊሰራ፣ ሀብት ሊያገኝ፣ ትዳር መስርቶ ልጅ ወልዶ ሊያሳድግ የሚያስችለውን ከሁሉም የአንድ ሰው ድምጽ በሙሉ ነጻነት የሚከበርበት። የትም ሄዶ ይሆነኛል የሚለውን መሪውን ሊመርጥ እና እሱም ልመራ እችላለሁ በሚል ሊመረጥ የሚችልበት። መሪየ ብሎ ሀገሬ ብሎ ያለሰቀቀን በነጻነት የሚኖርበት ሀገር መሆን መቻል ይኖርበታል። አሁን በሀገራችን ያለው የክልል አወቃቀር አግላይ፣ ዘረኛ፣ ለዜጎች እኩል መብት የማይሰጥ በመሆኑ በቀጣ እርምት ካልተደረገለት እና ህገመንግስት የተባለው የህወሓት የፖለቲካ ፕሮግራም ካልተወገደ ሀገር ጨርሶ የሚያፈርስ ስለሆነ የስርአት ለውጥ የግድ የሚሆንበት ሁኔታ ነው ያለው።

 

ኢትዮጵያን ሀቀኛ እና ፌደራላዊ ማድረግ ይቻላል። በየትም የሚኖር ዜጋ በአፍ መፍቻ ቋንቋው ሊማር ስራ ሲሰራ ፍርድ ሄዶ ፍትህን ሊያገኝ በስማበለው ሳይሆን ምንም ያህል ቁጥሩ ያነሰ ቢሆን  ቋንቋው ባህል እና ወጉ ሊከበር ይገባል። ይህ ሊሆን የሚችለው በዘር ስለተከለለ ሳይሆን መብቱ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሀዊ በሆነ ስርአተ መንግስት እና ህገመንግስት ሲኖረው ብቻ ነው። አሁን ያለው ህገመንግስትም ሆነ ክልላዊ አወቃቀር ሀገራዊ አንድነትን መጋፋት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደሀገር እንዳትቀጥል የሚያደርግም በመሆኑ ነው። ያ ብቻ አይደለም ይህ ስርአት እና ክልላዊ አወቃቀር አዱ ለሌላው ጠላት ተወዳዳሪ ተፈታታኝ እንጅ የአንድ ሀገር ልጆች የሚያደርግን ስነልቦናዊነት አሟጦ የወሰደ የወያኔ ጠላታዊ አወቃቀር ነው። ከሁሉም የሚገርመኝ ትልቁ የኦሮሞን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶች ኢትዮጵያን ጠል የሆነችውን የሚጢጢዋን ወያኔ የፖለቲካ ፕሮግራም የሙጥኝ ብለው ሲይዙት እና አንድነትን ናፋቂ ደግ አሳቢ ዜጎችን ነፍጠኖች (የአማራ ልሂቅ ተስፋፊ አስተሳሰብ) ብለው ሲፈጸሙ ማየት ነው። ይህ አወቃቀር ትንሽ የሕዝብ ቁጥር ላላቸው ብሔረሰቦች የማይጠቅመውን ያህል በእጅጉ ወይንም በበለጠ ትልቅ ነን የሚሉትን ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን ብሄረሰቦች በከባዱ ይጎዳል። እያየን ያለነው ሁሉም ብሄረሰባት እየተነሱ እኔ ክልል መሆን አለብኝ ቢሉ አይሆንም ልንል እንዴት ይቻላል? እናም የእራስ ምታቱ ከአናሳወች ይልቅ ትልቁን ሀገራዊ አንድነት የመፍጠር ሀላፊነቱ የሚወድቅባቸው ሰፋፊ ብሄረሰቦችን ፈተና ላይ የሚያስቀምጥ ጎጅ አስተሳሰብ ነው።

አሀዳዊነት እና ዴሞክራሲ

ከላይ በስም ፌደራል ግን በተግባር የፍጅት ስርአት የሆነውን ለማሳየት ያክል ምሳሌወች አቅርቤአለሁ። ይህ ስርአተ አስተዳደር ደጎሞ በህወሓት እና መሰል ጽንፍ እና ዘረኛ ድርጅቶች ሰይጣናዊ፣ ጨፍላቂ፣ መብትን እረጋጭ አድርገው በመሳል ዜጋን የሚያስፈራሩበትን መንግስታዊ ስርአት ለማሳየት እሞክራለሁ።

አሀዳዊነት ሲነሳ ታላቋን ብሪታንያ (Great Britain, or United Kingdom, or England) እየተባለች የምትጠራዉን እና የመጀመሪያው የአለማችን ዴሞክራሲያዊ ህገመንግስት (Magna Carta) ፈጣሪ የሆነችው እንግሊዝን ያስታውሰናል። እንግሊዝ ዴሞክራሲያዊም ናት። መሪወቿን በምርጫ ትሰይማለች እንጅ ጨፍላቂ ጉልበተኞች የሚፈራረቁባት አይደለችም። ወይንም ታላቋን ብሪታንያ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ያደረጉ በውስጧ ያሉ ብሔረሰቦች ተነስተው እንገንጠል ብለው የሚዘምሩባት አይደሉም። በሰሜን አየርላንድ የነበረውን ንቅናቄም በዴሞክራሲያዊ ፍትሀዊ እና ሰላማዊ በሆነ ስልት ፈታች እንጅ ጦር ሰብቃ አልጨፈለቀችም። ባጭሩ አሃዳዊ ብትሆንም ግን የተለያዩ ሕዝቦች ያሉባትም አንድ አይነት ባህል፣ ወግ እና ስነልቦና ያለው ዜጋ ብቻ ሳይሆን ብዝሀነትን የምታካትት አሃዳዊ ሀገር ናት። እንግሊዝን እንግሊዝ ያደረጉ እና እኩል ወሳኝ ሀገር እስኪመስሉ እንደነ ስኮትላንድ አይነት አስተዳደሮች (ትላልቅ ብሄረሰቦች) ያሏት ለማሳየትም ዌልስ፣ ስኮትላንድ፣ ሰሜን አየርላንድ እና ሌሎችም ለግንዛቤ ሊጠቀሱ ይገባል። አሃዳዊነቷ ግን ለነዚህ ሕዝቦች እረግጦ አልገዛም ወይንም አንዱ ከሌላው በልጦ ወይንም አንሶ ጥላቻን አልፈጠረም። ዴሞክራሲያዊ የሆነ አስተዳደራዊ መዋቅር፣ የዜጎች ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ አኗኗርን አላሳጣም። እንደ እኛዋ ኢትዮጵያችን ውስጥ እየተደረገ እንዳለው አንድ ሰው ዌልስ ስለሆንህ ወይንም እስኮቲሽ ነህ ተብሎ እዚህ አትኖርም አላስባለም ወዘተ። ሌሎችም አሀዳዊ የሆኑ ግን ሕዝቦቻቸው በፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚኖሩ ማንሳት ይቻላል። ጃፓን ከአሜሪካ ቀጥላ ታላቅ የኤኮኖሚ እና ማህበራዊ እድገት ያላት ሀገር ናት ግን አሀዳዊ ስርአተ መንግስት ናት። ፈረንሳይ ሌላዋ ዴሞክራሲያዊ እና አሃዳዊ ሀገር ናት ግን ሕዝቦች በሰላም እና በፍትሀዊ አስተዳደር ይኖራሉ። ቋንቋን በተመለከተ ፍራንስ ጀርመኖች አሉ ግን ፈረንሳይኛ ቋንቋቸውም ነው። ጣሊያኖች አሉ ግን ፈረንሳይኛ ቋንቋቸምው ነው። ከ 20፡ኛው አጋማሽ በኋላ አረበኛ ተናጋሪ ዜጎች ቁጥር መጨመሩ ይነገራል ግን ፈረንሳይን ከአሀዳዊነት አልቀየራትም። እናም በሀገራችን እና በዘረኛ ድርጅቶች እና ያዋቀሩት ከፋፋይ ስርአት እንዳይፈርስ  የሀገር አንድነት በአጀንዳነት ያስቀመጡ እና ለሀገር አንድነት እና ሉአላዊነት የሚታገሉ ድርጅቶችንም ሆነ ግለሰቦችን ለማሸማቀቅ በይበልጥም አሃዳዊነት ጨቋኝነት ነው ብለው ያሳዩበትን መንገድ ማፍረስ እና እውነታውን ማሳየት ይገባል። የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ በዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ያምናል።፡በእርግጥም እውነተኛ የፌደራል ስርአት ከሚመኙት ውስጥ ነው። ይህ የጠሀፊው እምነት ግን አሃዳዊነት ሁልግዜ ጨቋኝነት ነው የሚለውን አይጋራም። ወይንም የስመ ፌደራሊዝም መለያየትን መራራቅን እና በይበልጥም ዘረኝነትን ሲወልድ በሀገራችን የተከሰተው የእውሸት ፌደራላዊነት በተግባርም ዘረኛ ክልልተኝነት ሆኖ መገኘቱ ልናስመርበት እና ልንታገለው የሚገባ አስተሳሰብ ነው።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.