የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ ይባላል – አሁን ይላል

November 26, 2020
16 mins read

የነቢያት እጣም ተመሳሳይ ነው። ሕዝቡን ቀድመው ጥፋት እንዳይመጣበት ሲያስጠነቅቁት፣ ሲጮኹለትና ሲያለቅሱለት ይቆያሉ፣ በእንቢታው ወይም በግዴለሽነቱ ጸንቶ ጥፋት ሲያገኘው ደግሞ እኔስ ነግሬ ነበር እያሉ አብረውት ያለቅሳሉ። ጋዜጠኞች የሆኑ የሥርዓቱን ባሕርይ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ መረጃን እግር በእግር እያወጡ እኛ ሁላችን ኮንፊውዝድና ኮንቪንስንድ ሆነን ለውጥ አለ በሚለው ስካር ተጠልፈን ባለንበት አደጋ እንደተደቀነብን ቢነግሩን፣ ቢያስጠነቅቁን አልሰማ ብለን በታሪካችን ደርሶብን የማያውቅ ውርደት ደረሰብን።

የሰሜን እዝ የሀገሪቱን መከላከያ 70 % የሰው ኃይልና የመካናይዝድ አቅም እንደያዘ በ1 ሌሊት ተደመሰሰ። ይህንን ሊያስቆም የሚችል መረጃ፣ ከ9 ወራት በፊት ኢትዮ 360ዎች አቅርበው ነበር። መንግሥት በመረጃው ምንም ባለመጠቀሙ ጉዳቱን በከፊል እንኳን መታደግ ሳይቻል ቀርቷል። እንዲህ ያለው ተቋም ለወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት፣ እንዲህ ያሉት ውስጥ አወቅ ጋዜጠኛና ተንታኞችም ሊመሰገኑ እና ሊበረታቱ የሚገባቸው ናቸው። እርግጥ ከሰው ኃይል እና ከባጀት እጥረት እለት እለት ፕሮግራም ከማዘጋጀትም ጫና፣ በሚጠበቀው ደረጃ ሊሠሯቸው ያልቻሏቸው ሥራዎች እንዳሉ ግልጽ ነው። ጸሐፊው እንደጠቆሙትም ከነሱ በችሎታ የላቁ ኤክስፐርቶችን በየጊዜው ቢያቀርቡ የተሻለ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ። ከወጣትነታቸውም አኳያ ጠለቅ ያለ የኢትዮጵያ ታሪክና መልክዐ ምድራዊ እውቀት የላቸውም። በሕወሃት ዘመን በጥቅላላ የኢትዮጵያ ተቋማት ላይ በተደረገው ጥቃት ውስጥ የጎረመሱና የጎለመሱ እንደመሆናቸው በአንጻራዊነት በሚያስደንቅ ደረጃ ከትውልዱ ግንባር ቀደም ናቸው ለማለት ግን ይቻላል። ብዙ ሰው ከሚያደርገው ሥህተትም የሚድኑበትን መንገድ ከሕወሃት ጋር መሥራታቸው እድል ሰጥቷቸዋል።
ራሴን ጨምሮ አብዛኞቻችን የሕወሃት ተቃዋሚዎች ለድርጅቱ ካለን ወደር የለሽ ጥላቻ እንኳን የድርጅቱን የተለያዩ ሰነዶች ልንመረምር፣ ውስጣዊ አሰራሩን ልናጠና ይቅርና የአመራሩን ስሞች ለማወቅ እንኳን የማንፈልግ፣ ባጠቃላይ ሕወሃት ሲባል የሚያጥወለውለን እና የሚያቅለሸልሸን ስለ ሕወሃት ጠላት መሆኗን ከማወቅ በስተቀር ሌላ ነገር ለማወቅ የማንፈልግ ነን። ይሄ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል በሀገራችን ላይ። ሕወሃትም በሥልጣን እንድትቆይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ባጭሩ እነ ኤርምያስ ውስጥ አወቅ መሆናቸው ለጸረ ሕወሃት ትግሉ በረከት እንጂ እርግማን አይደለም። ሕወሃት ማለት ግን መቀሌ ፕላኔት ሆቴል ወይም አንድ ቤተክርስትያን ውስጥ ቆሞ የሚያጣጥረው የነስብሃት ነጋ ቡድን ብቻ አይደለም። ሕወሃት እንደ ራዕየ ዮሐንሱ አውሬ ብዙ ጭንቅላቶች ያሉት ብዙ ድራጎኖች ፈልፍሎ ያሳደገ ሲዖላዊ ድራጎን ነውና የሕወሃትን መሠረታዊ የሀገር ከፋፋይ አስተሳሰብ እና መዋቅራዊ ጥፋት ሳይዘናጉ ጎን ለጎን መፋለም የግዴታ ነው።

በዳቦ ስማቸው ራሳቸውን ዓለማቀፍ ሕብረተሰብ ለሚሉት ምእራባውያን ስለ ሕወሃት ለማስረዳት ትንፋሽ መጨረስ ለቀባሪው አረዱት የሆነ ተግባር ነው። አሰልጥነው፣ አስታጥቀው በብቸኝነት ኢትዮጵያ ላይ የአፓርታይድ ሥርዓት ዘርግቶ የሩዋንዳን ድንኳን እንዲዘረጋ ዘርፎ እንዲያዛርፋቸው የጎለቱብንን ሕወሃትን መጨረሻም የተፈጠረበትን ሥራ ከግብ ሲያደርስ በተረኛ አሻንጉሊት የተኩትን ሕወሃትን ነው ለነሱው የምናሳጣው? አሁን ባእዳን በጋራ ከሕወሃት ጋር ሆነው ከዘረፉት ሃብት ውስጥ ለሕወሃት የደረሰውን ድርሻ ከሕወሃት የሚያስተፉበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። በሁሉም የአፍሪካ አሻንጉሊት አስተዳደሮች የሚደረገው ይኸው ነው። ኃያላን በመፈንቅለ መንግሥት ወይም በሌላ ዘዴ አሻንጉሊታቸውን ይጎልቱብሃል። በአሻንጉሊታቸው አማካኝነት ከእርሱው ጋር ተካፍለው ሀገርህን ይዘርፋሉ። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ አሻንጉሊታቸው የሚሰራውን ወንጀል ይሸፋፍኑለታል። ከዚያ ሕዝቡ የአሻንጉሊታቸው ግፍ ሲመረው የገዛ ወንጀሉን አጋልጠው፣ የርሱን ድርሻ ምርኮና ዝርፊያም ቀምተው ሌላ አሻንጉሊት ይተኩበታል። ስለዚህ አሻንጉሊቱን መጀመሪያውኑ ለጎለቱት ጌቶቹ ስለክፋቱ በማስረዳት ትንፋሽ ከመጨረስ ጭቁኑ ሕዝብ ሌላ የራሱ መሪ እንጂ ሌላ አሻንጉሊት እንዳይጎለትበት ያለችውን ጉልበት ቆጥቦ መጠቀም ይገባዋል። ለኛ ሀገር — በግልጽ ለመገጋገር — የኪሲንጀርን መመሪያ ተጠቅመው የትግሬ ተረኛ፣ የኦሮሞ ተረኛ፣ የአማራ ተረኛ እየለዋወጡ የምንገነባውን መሠረተ ልማት፣እና የሰው ኃይል በፈረቃ እያወደሙ በቁርቆዛ አዙሪት ሊያኖሩን ካሰቡበት ወጥመድ የምንወጣበትን ማሰብ ነው የሚበጀን።

1953 ግርግር // ለልማት በግንባር ቀደም የተሰለፉት እነ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ እነ ራስ አበበ አረጋይ ተረሸኑ

1967 አብዮት // የሀገሪቷ ግንባር ቀደም ምሁራንና ባለሥልጣናት 60 ዎቹ ተረሸኑ
1969 አብዮት // አንድ ትውልድ ፊደል የቆጠረ ፣ ግንባር ቀደም የነበረ ተጨፈጨፈ
1981 መፈንቅለ መንግሥት // እንዲከሽፍ በተወጠነ መፈንቅለ መንግሥት 200 የሃገሪቱ የበላይ የጦር አዛዦች ተገደሉ፣ ታሠሩ

1983 የደርግ ውድቀት // የኢትዮጵያ ሠራዊት ፈረሰ፣ ተበተነ
1984 የወያኔ ንግሥና // 42 የዮኒቨርሲቲ ምሁራን ተባረሩ። ከኢትዮጵያ መሥሪያ ቤቶች ነባር ባለሙያዎች ተፈናቀሉ

2013 የወያኔ ግብአተ መሬት // በመከላከያ ውስጥ በተለያየ እርከን የሚገኙ የሰሜን እዝ ወታደሮች ተረሸኑ። በዚህ ድርጅት አቀፍ ክህደት መንስኤ ብዙ የወያኔ ጄኔራሎችና ሌሎች መኮንኖች ይታሰራሉ፣ ከሥራ ይባረራሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ። የሀገሪቱ የመካናይዝድ አቅም በራሷ አየር ኃይል ተደመሰሰ።

ነገስ? ነገ ደግሞ ዛሬ በኮንሶ፣ በጉሊሶ፣ በሻምቡ፣ በሻሸመኔ፣ በመተከል፣ በከማሺ፣ በከሚሴ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በሐረርጌ የዘር ጭፍጨፋ የሚያካሂዱ ባለሥልጣናት ከሥራ ይወገዳሉ፣ ለፍርድ ይቀርባሉ።

ከዚህ ትውልድን በሀገሪቷ አንጡራ ሃብት ለሥልጣን እያበቁ፣ መልሶ ደግሞ እያወረዱ ድባቅ ከመምታት አዙሪት የምንወጣበትን ማሰብ ይገባናል። ወያኔ ኤክስፓየሪ ዴቷ ካለፈ የከረመች ስለሆነች በወደቀች ወያኔ ላይ ብቻ እናተኩር ብለን ሌላ ከወያኔ የረቀቀ፣ የገዘፈ፣ የከፋ፣ ጥፋት ቀንድ እንዲያወጣብን መዘናጋት ፈጽሞ አይመከርም።

ፈረንጆቹ እኛ ስለወደድነውና ስለጠላነው አይደለም አሻንጉሊት የሚመርጡልን። ከራሳቸው ጥቅም አኳያ እንጂ። ለማስረጃው እንደሆነ አስረጂ አያስፈልጋቸውም። በመቶ ምናምን ኤምባሲ፣ እና የእርዳታ ድርጅት ስም ዝርዝር ዕለታዊ ዘገባ የሚደርሳቸው በመሆኑ። ትንፋሻችንን የምር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ለመረባረብ እናውለው። ለዚህ ደግሞ ገንቢ ተቃውሞ የሚያደርጉ እንደ ኢትዮ 360 ሚድያ ያሉትን ልናጠናክር ይገባናል። ከአርባ አምስት አመት በላይ በመንግሥት ሚዲያ ብቻ እንድንደነቁር ተደርገን በገዛ ሀገራችን ጉዳይ እጅግ የጫጨ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ እንድንሆን የተፈረደብን አይበቃም? ግዴለም ዲሞክራሲን ባይፈቅዱልንም እንለማመደው።

በነገሬ ላይ እነ ሃብታሙና እነ ኤርምያስ እኮ እጅግ ድንጉጥና እንደልባቸው እንኳን ለመናገር የማይደፍሩ ናቸው። ዘመድኩን በቀለን በሚድያቸው ያቀረቡት ቀን ፊታቸው ላይ ይነበብ የነበረው ምነው የርሱን ነጻነት ላንድ ቀን እንኳን ብታደለው የሚል የመጓጓትና የመቅናት ስሜትና ወዲያውም የመተንፈስ ስሜት ነበር። እንግዲህ እንዲህ ያሉትን ትሁቶችና ድንጉጦች ልንፈራ አይገባም። ማሸማቀቅም የለብንም። ግዴለም ሕወሃት በተጠራችበት ስም አንጥራቸው። ምንም ዶ/ር ዐቢይ ሕወሃትን አሸባሪ እንዳትባልበት ተጨንቆና ተሳቅቆላት ጁንታ የሚል በሕግ የማይጎዳት ስም ቢያወጣላትም። ሆኖም ይህ ቅጽል ወያኔን ባይጎዳትም እርሷን የመሰለች ወንጀለኛና ሀገር አፍራሽ ሰይጣናዊ ድርጅት የተጠራችበት እንደመሆኑ ቅጽሉን ሌሎች ላይ መጠቀሙ ለማይገባ ውግዘትና ጥቃት የሚያጋልጥ ይሆናል።

ሥራቸውን እየተቹና እያረሙ፣ እያመሰገኑና እየኮተኮቱ፣ እየነቀፉና እየደገፉ፣ ለሀገር መድኅን የሚድያ ተቋም እንዲሆኑ ማበረታት ይቀጥል።

(ከዚህ በላይ ያለውን እጅግ ጠቃሚ አስተያየት ያገኘሁት ከዘሀበሻ ድረገጽ ነው፡፡ አንድ መጣጥፍ አንብቤ ስጨርስ በሥሩ ከነበሩት ሁለት የአንባብያን አስተያየቶች መካከል ይህኛው በዚያ መጣጥፍ ሥር ብቻ ተወስኖ መቅረት እንደሌለበትና በሌሎችም ድረገፆች ራሱን ችሎ በመውጣት ቢነበብ መልካም እንደሆነ አመንኩ፡፡ ብዙ በሳል አስተያየቶች በዚህ መልክ እንደዋዛ በአንድ መጣጥፍ ሥር ብቻ ተነበውም ይሁን ሳይነበቡ በቀላሉ ታይተው ይታለፋሉ፡፡ እንደዚያ ባይሆን ጥሩ ነው፡፡ … ምንም ዓይነት አርትዖት አላደረግሁም፡፡ ጥሩ መማማሪያ ነው ብዬ አምናለሁና ኢትዮ360ዎችም ቢመለከቱትና ግንዛቤ ቢሸምቱበት ይበልጥ ያሳድጋቸዋል፡፡ መሰዳደብና መወነጃጀል እንጂ መጥፎው ሃሳብን በሃሳብና በአመክንዮ መሞገት ክፋት የለውም፡፡ እንዲህ ስናደርግ ደግሞ በተቻለን መጠን ግለሰብንና ሃሳብን ማሳከር የለብንም፡፡ በምንተቻች ጊዜ መነሻችን እውነት እንጂ ጥላቻና በቀል ሊሆንም አይገባም፡፡ በፈረንጅኛው ብሂል “ሕጻኑ የታጠበበትን ውኃ ከነሕጻኑ መድፋት” ያለውን ጉዳትም ልብ ማለት አለብን፡፡ አለቃ ገ/ሃናም “ለቦና ጥጃ ‹ውስ!› ምን አነሰው” ያሉት ወደው አልነበረም፡፡  ለማንኛውም የጽሑፉ ርዕስ – “የኢትዮ360 ጁንታ! ሚድያ – የፖለቲካ ፓርቲ ወይስ የነፃ ሚድያ?” ጸሐፊው ደጀኔ አያኖ፤ እኔ ደግሞ ይ.በ.)

አሁን ይላል

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የትህነግ ጽንፈኛ ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ጥቃት ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበት ነው።” የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ የሰራዊት አባላት የትዳር

Next Story

በማይካድራ ንጹሀን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ድርጊት እጅግ ማዘናቸውን የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

Latest from Blog

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት ዕለት መሆኑን ያ ለሁለት አሰርተ ዓመታት ከፍተኛ ዕልቂት እና ደም መፋሰስ የነበረበት ጦርነት አዲስ አበባ በደም

አቢይ አህመድ ታላቁን አሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ማታለል ይችላል ወይ? የአሜሪካ “ብሄራዊ ጥቅምስ ኢትዮጵያ ውስጥ“ እንዴት ይጠበቃል? የአሜሪካ እሴቶችስ(Values) ምንድን ናቸው?

ለመሳይ መኮንና ለተጋባዡ የቀድሞ “ከፍተኛ  ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት” በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን የስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ለሚስራው ኢትዮጵያዊ ሰው የተሰጠ ምላሽ!   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ግንቦት 19፣ 2016(ግንቦት 27፣ 2024) መሳይ መኮንን በአ.አ በ17.05.2024 ዓ.ም አንድ እሱ  የቀድሞው “ከፍተኛ የኢትዮጵያ

ጎንደር ሞርታሩን እስከ ጄነራሉ ተማረከ | ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | ብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን

ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | “ፋኖ ከተማውን ቢቆ-ጣ-ጠር ይሻላል” ከንቲባው |“አብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ኮ/ሉ |“በድ-ሮን እንመ-ታችኋለን እጅ እንዳትሰጡ” ጄ/ሉ
Go toTop