መሞት ካልቀረልን*
በኢህአዴግ ድግስ
ላልቀረልን ሞቱ
ባያንጓልለንስ ውንበዳው ቅጥፈቱ?
ቅጥፈትና ውሸት ግራ ቀኝ ከሚሻማን
ምናለ ብንሞት እውነት እየሰማን?
በዘረፉት ገንዘብ እየገዙ ካድሬ
ያም ያም ሲነዛ ያሰት ቅጥፈት ወሬ
ልብ ወለድ ዜናውን ጧት ማታ ሲረጨው
የጆሯችን ታምቡር እውነት ሳይጋጨው
የግራ ቀኙ ክፋት እድሜን እስኪቀጨው
ምን ነበር?
ሞት የአዳም ልጅ እጣ ላይቀር ለሁሉም ሰው
የሐሰት ማእበል ቀብሩን ባያለብሰው።
ከምር ያሳዝናል እድሜያችን ማለቁ
ያም ያም ሲዋሹ ያም ያም ሲሳለቁ።
*ሻዕቢያና ወያኔ በባድሜ ወንድማማቾችን ሲያፋጁ ከሰዉ እልቂት ያላነሰ ያቅለሸልሽ የነበረው ለከት የለሹ ውሸታቸው ነበር። ሁለቱም ሙልጭ ያሉ ወራዳ ውሸታሞች ስለሆኑ አንዱንም የሚያወሩትን ነገር ሆነ መረጃ ብለው የሚሰጡትን ማወናበጃ ለመቀበል ሕዝብ ለአመታት ተቸግሮ ቀርቷል። ሁለቱም የመንግሥት ሥልጣን ይዘው በኢትዮጵያ የ3 ሺ ዘመን ሀገረ መንግሥት ታሪክ ያልነበረ መንግሥታዊ ቅጥፈትን ተራ የእለት ተእለት ተግባራቸው አድርገዋል። ሌላ ቀርቶ እስከዛሬ በባድሜው ጉዳይ ኤርትራውያን ወያኔን ቀዳሚ ወራሪ ሲያደርጉ፣ የትግራይ ሰዎች ደግሞ ተንኳሽና ወራሪው ሻዕቢያ ነው ይላሉ። ድርጅቶቹ በጦርነቱ ወቅት እጅግ የሚያምታታና የቅጥፈት ዜናና መረጃ ከመልቀቃቸው የተነሳ ማናቸውም የሚሉትን ነገር ምኑንም ለማመን አይቻልም ነበር። ጦርነቱም ካለቀ በኋላ ቅጥፈታቸው ባሰባቸው እንጂ አልተሻላቸውም። ያ ዘመን በድጋሚ የተከሠተ በሚመስል ጅማሮ ሕወሃትና ብልጽግና የተባሉት የወንጀለኛው የኢህአዴግ ክፋዮች ካሁኑ ሕዝቡን የሚያምታቱ እርስ በእርስ የተጋጩ መረጃዎች መልቀቅ ጀምረዋል። ያንን አስከፊና አስጸያፊ ዘመን መልሰው ሊያመጡት ይመስላል። ለካስ ሰው ሲሞትም ትክክለኛውን፣ እውነተኛውን ነገር እየሰማ መሞት መታደል ነው?
እህአዴጎች እባካችሁ እውነት እየሰማን እንሙትላችሁ። የውሸት ውዥንብሩ ይቅር። መግደል፣ ማስገደል፣ ማጋደል፣ ማገዳደል በእናንተ መሞትም በእኛ አልተጀመሩም።