“አደፍርስ ! ካልደፈረሰ አይጠራምና” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ብዙውን ጊዜ   ካላደፈረስህ በስተቀር እውነቱን አንገነዘብም።እናም መደፈርሥ ለተሸዋረረ እይታችን ታላቅ መፍትሄ ነው ።  ለምሳሌ በአንድ ውሃ ባቆረ ኩሬ ውሥጥ ጭቃ እንዳለ በአንዳች ነገር ካላደፈረሥከው አታውቅም።ውሃው ከላይ ተንሳፎ ነፅቶ ሲታይ ከሥሩ ጭቃ እንዳለ ትዘነጋለህ።እናም ጭቃ መኖሩን አውቆም ሆኖ ሳያውቅ የሚያሥገነዝብህ አደፍራሽ ሰው ያሥፈልግሃል።

በህይወት ሥትኖር በቀቀን ሆነህ ዘመንህ እንዳያከትም ፣የሌሎችን ሃሳብና ፍቃድን ፈፃሚ ብቻ እንዳትሆን ፣በኑሮ ውጣ ውረድ ውሥጥ የሉ ቀለማት ነጭና ጥቁር ብቻ ያለመሆናቸውን የሚያሳይህ አንተ ያላየኸውን አያሌ ቀለማት የሚያሥመለክትህ  አደፍራሽ ሰው የሥፈልግሃል።

ሥልቻ ይመሥል በሐሰት ትርክት ሲጠቀጥቁህ፣ ሁሌም በጥቁር ና ነጭ ትርክት ናላህን ሲያዞርህ የኖሩትን በሐሰት የከበሩትን ዘመነኞቹን  በቋንቋ ሸቃጭ ነጋዴዎች፣በቋንቋ ፖለቲካ የበለፀጉ ከበርቴዎችን ገበና የሚያጋልጠው አደፍራሽ ሰው ነው።

አድፍራሽ ሰው አንቂ ነው። “አደፍራሽ ካለ የጠራ ውሃ ለመጠጣት አይቻልም።” ማለት ሥንፍና ነው።ውሃ ከሥሩ ጭቃ እንዳለው ከተረዳህ ፣ ኩሬህን በወጉ ማጠር እና በጥንቃቄ መጠቀም ያንተ ፋንታ ነው።ደሞም ኩሬህን ለማደፍረሥ የሚያበቃው ሰው ብቻ እንዳለሆነም አትዘንጋ።

የዛሬውን ፅሑፊን ርእሥ “አደፍርስ”ያልኩት የውድ ፣ድንቅና ብርቅ ኢትዮጵያዊውን ደራሲ የዳኛቸውን ወርቁን የልቦለድ መፅሐፍ ” አደፍርስን ” ተውሼ ነው።

 

የየቸከበርከው( የተከበርሺው)  አንባቢ ሆይ  አደፍርስ በተሠኘው የዳኛቸው ወርቁ መፀሐፍ የአደፍራሹን የአደፍርሥን ሃሳብ ከመፀሐፉ መረዳት መልካም ነው።አደፍርሥ በወቅቱ የነበረውን መንግሥት አወቃቀር ፣ የአምልኮ ሥርዓታችንን፣ጥንቆላን፣ሞርትን፣የደብተራ ሥራን፣ያለምርምር የተቀበልናቸውን ተረትና ምሳሌዎችን ወዘተ ።ይቃወማል።በመፀሐፉ በገፅ 153 እና 154  “በሮም ሥትኖር እንደሮማውያን ሁን ።”  የሚባለውን ተረትና ምሳሌን ያለመቀበሉን የገለፀበትን መንገድ ብቻ ተመልክተን አደፍርሥ እውነትም አደፍርሥ ነው።ብለን ለመመሥከር እንችላለን።

“እንሆ በረከት”

” እኮ እርስዎኮ  የሚሉት አሁን በአጭሩ -ሮም ስትሄዱ እንደሮማውያን ሁኑ።- በእግር መሄዳቸውን ትተው በእጅ ሲድሁ ብታገኟቸው አናንተም በእጅ ዳሁ።-ቁንጣን እሥኪይዛችሁ በልታችሁ፣ በመንገድ ሥንትሸራሸሩ፣…የአጋጣሚ ነገር አንድ ምሥኪን ደሃ ረሐብ ይዞት ሢፈራገጥ  እንደእናንተው በዛ በኩል የምታልፍ አንዲት ሴት ቁረሽ እንጀራ ስትሰጠው  ብታዩና…ቢጎርሰው ከሞት እንዲድን ብታዎቁም :-ከእጁ መንጭቃችሁ ራሳችሁ ጉረሱትና ብትፈልጉ መልሳችሁ አሶጡት አይደለም?… ሌላው ሃሳቦ ደግሞ  በባህላችን ውሥጥ መሠል ካልተገኘ ፣በሥተቀር አዲስ የስልጣኔ አካሄድ አሥፈላጊ አይደለም።–ቢያሥፈልግም ህዝቡ ሥለማይቀበለው መግባት የለበትም…በግድ መግባት አለበት ብትሉም እንደ ፍሊጶ መውደቂያ ታጣላችሁ አይደለም…?”

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቢያንስ የወደፊቱ መልካም ይሁን! - አቤክስ ዳኛቸው 

በነገራችን ላይ፣ፍሊጶ የማርትሬዛ ልጅ ነው።እናቱ ኦስትርያን ለ99 ዓመት ከገዛች በኋላ በእግሯ ተተክቶ የነገሠ።ይህ ንጉሥ ንቃት ያላቸውን አሥተዳዳሪዎች ና ከበርቴዎች  ለግብር ጠርቷቸው በቤተመንግሥቱ እሥረኛ ሆነው እንዲቀመጡ በማድረግ ደሃው ህዝብ ራሱን እንዲያሥተዳድር ፈቀደ።ይሁን እንጂ ህዝቡ የሚፈልገው ነፃነት፣እኩልነት፣ወንድማማችነት ሊሰፍንለት አልቻለም።እንደውም በህግ አግባብ ማሥተዳደር በማይችሉ ፍዳውን ማየት ጀመረ።እናም ከታሠሩት ውሥጥ ሁለት በንቃተ ህሊና የበለፀጉትን  ጥበበኛ ሰዎች   በማሥፈታት የኦስትሪያ ህዝብ  በተደራጀ መንገድ ታግሎ ንጉሥ ፍሊጶን ከዙፋኑ እንዳወረደው ታሪክ ይነግረናል።

ወደእርሳችን እንመለስ።አንድን ነገር ከሥር መሠረቱ ለመረዳት  ነገሩን ማደፍረስ ይጠበቅብናል።ዳቦ ዳቦ ከመባሉ በፊት ምን ነበር?እንጀራሥ? ይህን ሥንጠይቅ ለመልሱ ወደ ገበሬውና እርሻው እንዘልቃለን።ዘልቀንም ሥናበቃ ትንንሾቹ የሥንዴ ና የጤፍ ቅንጣቶች በምድር ላይ በዘሪው ተዘርተው እጅግ እንደበዙ እናሥተውላለን።

ይህ ግንዛቤን እጅግ አደፍርሰን የሰው ማንነትን ሥንፈትሽ ሰው ቅንጣት የወንድ ሥፐርም ና የሴት ሚጢጢ እንቁላል ውህድ መሆኑን እንረዳለን።የማንነት ጩኸታችንም እዚህ ላይ ያከትማል።ምክንያቱም ሌሎች የባህል ማንነቶች በማህበራዊው ኑሯችን በየጊዜው የተፈጠሩ ናቸው።አብዛኛው የፖለቲካ እምነታችንም ከገል ጥቅም የሚመነጭ ነው።

ከግል ጥቅም የሚመነጨው የፖለቲካ እምነት በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ ፈጥሯል። ዛሬ በኢትዮጵያ ግዛት በትግራይ በህወሓት ሥም የሚነግደው ያለልፋት፣ያለጥረት ና ያለግረት በምላሥ ጉልበት ብቻ፣ በደሃ ደም ፣ ከተራ ህዝብነት ወደከበርቴነት የተሸጋገረው  የእብድ ሥብሥብ ፤በተለመደ የማባለት መንገዲ ቀጥሎ፣ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ክፍፍል  በመከላከያ ውሥጥ በመፍጠር ፣ጦሩን እርሥ በእርሥ ለማባላት ያልተሳካ ሙከራ አድርጓል።ያውም እንደ ጨው ለተበተነው ትግራዊ ደንታ ቢሥ በመሆን።

የትግራይ ተወላጁ እንደ ማንኛውም ዜጋ በዜግነቱ ከርቶ ፣ እንደ ጨው ተበትኖ በኢትዮጵያ ግዛት ሁሉ ተበትኖ ተጋብቶ፣ተዋልዶ፣ሀብትና ንብረት አፍርቶ የሚኖር ነው።ይህንን በሚሊዮን የሚቆጠር ትግራዊ ከመጤፍ ባለመቁጠር ለጊዜያዊ ጥቅሙ ሲል ይህ እብድ ቡድን በትላንት እኩይ ድርጊቱ ሳይፀፀት ዛሬም ዘረኝነቱን በንዳ ና የፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ተላላኪነቱን አሥመሥክሯል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ነፍሴ ቸኩላለች !!

ይህንን አጥፊ ዓላማውን እምንረዳው፣ነገሮችን አዳፍርሰን የያንዳንዱን የህወሓት ቱባ ባለሥልጣን ቤተሠብ አኗኗር ሥንፈትሽ ብቻ ነው።እነዚህ ሰዎች ሀብትና ንብረታቸው ብቻ ሳይሆን ቤተሠቦቻቸው በሀገር ውሥጥ የሉም።

ለመሆኑ የዋና ዋናዎቹ የህውሃት መሪዎች ልጆች በአገር ውሥጥ ካሉ እሥቲ አቤት ይበሉን። ሥንቶቻችን ይህንን እውነት እናውቃለን?

በአገር ውሥጥ የሚገኙትም የባለሥልጣናቱ  የኑሮ ሁኔታም ከአጠቃላይ የሀገሬው ኑሮ ጋር   ሥታሥተያዩት ሰማይና ምድር አይደለም ወይ?የዋሁ የትግራይ  የደሃ ልጅ  በርሃብ ላለሞት ብሎ ለአነዚህ ሰው መሆናቸውን ለረሱ ጭራቅ ና እብድ መሣፍንቶች ሲል  ከወንድሙ ጋር መጋደልሥ አለበትን??? በእውነቱ ይህ እኩይ ድርጊታቸው ህሊና ያለንን ዜጎች ሁሉ እጅግ አሳዝኖናል።

እጅግ የምናዝነው ይህንን እውነት ከደፈረሰ በኋላ በመገንዘብ ነው።   ችግሩን በቅጡ  የምንረዳው ሰላማችን ደፍርሶ ሥናየው ነው።እነዚህ በማሥመሠል የተካኑ ፣ በውሸት የበለፀጉ ህሊና ቢሥ ጥቂት ቡድኖች በዚች አገር  ከፋፋይ የአፓርታይድ  የቋንቋ ፖለቲካ ለመመሥረት በብርቱ የሚታገሉ መሆናቸውን አሥመሥክረዋል። አገር አፍራሽ እብድ ቡድን መሆኑንን ዛሬ በውል የተረዳነው ይመሥለኛል።ካልደፈረሰ አይጠራም የሚባለው ምሳሌያዊ አነጋገር እውነትም ዛሬ ግልፅ የሆነልን ይመሥለኛል።

ይህም ሆኖ ወዛቸው ችፍ ያለ የድምፀ ወያኔ ፕሮፖጋንዲሥቶች እነሱ ብቻ ብልጥ የሆኑ ይመሥል አይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ ይሉናል። እጅግ የሚያሳዝነው በርሃብ አለንጋ በሚገረፈው በትግራይ ህዝብ ላይ በጥጋብ ሲያጋሱበት ሥናሥተውል ነው ።ለመሆኑ  በ30 ዓመት አገዛዛቸው ለራሳቸው እንጂ   ለትግራይ  ህዝብ  ምን አደረጉለት ? ዛሬም እነሱ ሺ እያለቡ ሲጠጡ፣እርሱ በገል ለማግኘት እንኳን ብርቅ ሆኖበታል።

ይህንን እውነት ዛሬ ሲደፈርሥ እንደሚረዳ አምናለሁ።የእያንዳንዱ ሰው  ህሊና ማሰብ የሚጀምረው ሰላም ሲያጣ ነው።የሠላሙን መደፍረሥ መንስኤ ለመረዳት እና ያንን ፀረ ሠላም ኃይል አምርሮ የሚዋጋውም ያኔ ነው።ሲደፈርሥ ነው ፣አጥርቶ ማየት የሚችለው።ከዚህ ፅሑፍ ቀደም ሲል የፃፍኩትም የሚያሥተሣሥረን የመፍትሄ ሃሴብም የሚገባን ያኔ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ አንድነት ፈተናዎች - ከአበበ ከበደ

አዎ ዛሬ ደፍርሶል ።ኢትዮጵያ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ እንደሚያሥፈልጋት ይህ ቋንቋም በእያንዳንዱ ክልል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበናል።ብሔራዊነት የሚኖረው እንዲህ አይነቱን የሚያዋህደንን መንገድ በመከተል ነው…።

ዛሬ በህውሃት ሥም የሚነግደው ና የገንጣይ ሥም የያዘው ህሊና ቢስ ቡድን  ላካበተው ሀብት በመሥጋት ጦርነት ከፍቶ፣ የትግራይን ምሥኪን ህዝብ ከንቱ ና አላሥፈላጊ መሠዋትነት እያሥከፈለው ነው።ይህም እጅግ አሣፋሪ ጦርነትም  ዛሬ የትግራይን ሠላም አደፍርሶታል።ይህ የሠላም  ማደፍረሥ የኢትዮጵያን የፖለቲካ እውነታ የበለጠ አጥርቶ በማሣየት ፣ወደትክክለኛ መፍትሄ የሚወሥደንም ይመሥለኛል።

ይህ ጦርነት በኢትዮጵያኖች አሸናፊነት ይደመደማል። በኢትዮጵያም ወሥጥ ዛሬ የሚንፀባረቀው የብሔር ትምክህተኝነት ና የቋንቋ ፖለቲካም ያከትማል።

የብሔር ትምክህትኝነት አውዳሚ ነው።የቃሉ ትርጉምን እሥቲ እንመልከት።

የብሔር ትምክህተኝነት( National chauvinism )

ብሔርተኝነት የከረረ አቋም ይዞ የሚገኝበት ሁኔታ የብሔር ተምክህተኝነት ይባላል።የብሔር ትምክህተኝነት የአንድን ብሔር ጥቅም ከሁሉ በላይ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ሌሎቹን ብሔሮች በጥላቻና በበታችነት የሚያይና ለአሥከፊ ብዝብዛ ና ጭቆና የሚያዘጋጅና አንዳንዴም ጨርሶ ለመጨፍጨፍ የሚነሣሣ ነው።የብሔር ትምክህተኝነት አንዱ አዝማሚያ ዘረኝነት ነው።የብሔር ትምክተኝነት መደባዊ ምንጭ እንዳለው የሚያጠያይቅ አይደለም።ብሔሮችን በበላይና በበታች፣በገዢና በተገዢ የሚከፋፍል አመለካከት በመሆኑ፣ የከፋ ብዝበዛንና ጭቆናን ለመፈፀም የሚጠቅም ነው።

ከዚህ ትርጉም አንፀር ከድል በኋላ ከመንግሥት፣ከፖርቲዎች እና ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ የሚጠበቅ የበለጠ የሚያፋቅረን አንድ ወጥ የሆነ የሀገር ፍቅር መዝሙር ይፈጠራል ብዬ አሥባለሁ።

በተባበረ የፍቅር፣የአንድነት፣የመተሳሰብ፣የሠላም ናየይቅርታ መንፈሥም የምንመሠርተው  የኢትዮጵያ መንግሥትም በፍትህ፣በእኩልነት፣በህግ የበላይነት ላይ አተኩሮ የሚሠራ እና የሁሉም ዜጎች መንግሥት ይሆናል ብዬ አልማለሁ።በደፈረሰው ሁኔታ ውሥጥ የሚወለደው አዲሱ ና ጠንካራው የኢትዮጵያ መንግሥትም   ለጠላቶቻችንን ታላቅ መርዶ ይሆናል።…

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share