ዋይ ለልስ – አማራ (ጲላጦስ – ከባህር ዳር)

በዕለተ ሰንበት ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዛሬም የአማራ ሕዝብ ማቅ እንዲለብስ፣ ሐዘን እንዲቀመጥ፣… አስገድዷል፡፡ ሰዎች ፈልገውት፣ መርጠውት ባልተወለዱበት ብሔራቸው፣ እንደማንነት ከሌሎች ጋር አዋድዶና አከባብሮ የሚያኖር እሴትና ክብር ያለው ማንነታቸው መሆኑ መከበሩ ቢቀር በማንነታቸው እየተለዩ በገዛ ሃገራቸው ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል መገደላቸው እየቀጠለ መገኘቱ ሀገራችን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሷን ከማመላካቱም በላይ የአገሪቱ ሆነ የክልሉ መንግስት አቅም ቢስነቱን ያሳብቃል፡፡

መስቀል አደባባይ ላይ ቦንብ ቢወረወር፣ ሻሸመኔ ላይ ጭፍጨፋ ቢፈጸም፣ ምዕራብ አርሲ ላይ ክርስቲያኖች ቢታረዱ፣ መተከል ላይ ሦስት ዙር ጭፍጨፋ ቢደረግ፣ ጉራፈርዳ ላይ ሙስሊም አማራዎች በጅምላ ቢያልቁ ህውሓትና ኦነግ ጥቃቱን እንዳደረሱት ትነግሩናላችሁ፡፡ ቆይ እኔ እምለው መንግሥት የሚመራውና መከላከያ ሰራዊቱ የሚጠብቀው የአገራችን ክፍል የትኛው ይሆን?

በአገሪቱ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል፤ እየተፈፀመም ይገኛል። የአረመኔዎች ቅንጅት ሕዝባችን በደም ጎርፍ እንዲታጠብ አድርጓል። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል።

መንግስትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራትና ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን እርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የሕዝቡን ደኅንነት ከመጠበቅ ይልቅ ሰርክ ምሽት በየሚዲያው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የአማራ ክልል መንግስት፣ የብልጽግና ፓርቲ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣… እገሌ መሌ እያሉ የነፍስ ይማር መልዕክትና መግለጫ ማቅረብ ሰልችቶናል፡፡

አይ የኛ ነገር። ኢትዮጵያዊ የተራበ ወገኑን ስብስቦ ሲያበላ እንጂ፣ ስብስቦ ሲገድል ታይቶ አይታወቅም። እንዴት ሰው በገዛ አገሩ ላይ ወጥቶ ለመግባትና ሠርቶ ለመኖር ዋስትና ያጣል?፣ እንዴት በራሱ ወንድም ይታረዳል?፣ እንዴት ሰው ፈልጎና መርጦ ባልተወለደውና በዘሩ ምክንያት የጅምላ ጭፍጨፋ ይደረግበታል? ረ ለመሆኑ እንዴት ብንከፋ ነው ባልኖርንበት ዘመን የኋሊት እየሄደን የምንጠፋፋው? ቆይ ግን መቼ ነው? ይሄ ነገር የሚያበቃው? ማነውስ ለሰው ልጅ የመኖር ዋስትና የሚሰጠው?  እስከመቼስ ነው? አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ፣ አንዱ ታራጅ ሌላው ግን አራጅ ሆኖ የሚቀጥለው? ተረኝነት ተራነት ነው፡፡

ገዳይ የሚወደሰው በደጋፊዎቹ ሰፈር ቢሆንም ለሟችም የሚታዘነው በወገኖቹ መንደር ነው፡፡ ሚስትህ ወለደች ወይ ተብሎ ሲጠየቅ ማንን ወንድ ብላ ብሎ እንደመለሰው አባወራ በአማራ ሕዝብ እየደረሰ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል በህውሓትና በኦነግ ከምናላክክ የክልሉ መንግስትና ብልጽግና ተብሎ የሚጠራው የእንከፎች መጠራቀሚያ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ  ኢ-ሰብአዊ ጭፈጨፋ በተፈጸመ በማግስቱ የወገኖቹ ዕልቂትን ወደ ጎን ትቶ በባህር ዳር ከተማ በክልሉ ም/ቤት አዳራሽ በመሰብሰብ የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አዘጋጅቶ አሸሸ ገዳሜ ሲል መዋሉ ለሰማ እጅግ ያማል፡፡ ይኸነው እንግዲህ አማራ ወክሎ ያለው መንግስትና ፓርቲ፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ሰበብ እፈለገ ሕዝቡ ሐዘኑና ቁጭቱን በቅጡ እንዳይገልጽ ከማፈኑ በላይ የአማራ ሕዝብ የአገራዊ ፖለቲካው ሽኩቻ ሁሉ ብቸኛና ቋሚ ቀብድ ማስያዥያ ሆኖ እንዲቀጥል ተገዷል፡፡ በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ለማውገዝ ልነሳ ቢልም አማራ ማዘን እንኳን አይችልም በሚል እርቃን በወጣ አምባገነንነት እንዲከለከል ተደርጓል፡፡ ድንቄም ዲሞክራሲ፡፡ አሁን የሕግ የበላይነት ቦታ አጥቷል። መንግስት ሕግ የማስከበርና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት አለመፈለጉና አለመቻሉ ተረጋግጧል።

ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ነገ የተሻለ ቀን ይሆናል በሚል ተስፋ ከደሃ ኑሮው ጋር የሚታገልን ህዝብ ሰለባ በማድረግ በንጹሃን ደም የፖለቲካ ሂሳብ ማወራረድ ምን የሚሉት ብልጽግና ነው? ህዝባችንስ እስከመቼ በተለያዩ የማንነት መገለጫዎቹ አሰቃቂና ተፈራራቂ ጥቃት እየደረሰበት የስቃይ ኑሮውን ይገፋል? የሞቱትን በየተራ እየቆጠርን እኛስ እንዴት ቆመናል፣ እየኖርን ነው እንላለን? ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ የሚጠቁበትና የሚገደሉበት የደም ፖለቲካ መቆሚያውስ መቼ ነው? ሃገር ማለት ህዝብ አይደለምን? ንጹሃን ደም እየገበሩ አገርስ እንዴት በሁለት እግሯ ልትቆም ትችላለች?

መንግስት የዜጎች በሰላም የመኖር ዋስትና ማስጠበቅ ካልቻለ፣ ለዚህ የሚረዳንን ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ላይ መድረስ ካልተቻለ ሃገራችን መውጫው ወደራቀ አደጋ መግባቷ አይቀሬ ነው። እንደሀገር ያለንን ቀጣይነት ማረጋገጥ የምንችለው ፖለቲካችን የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት ከምንም በፊት ቅድሚያ የሚሰጥበትን ከባቢ መፍጠር ስንችል ነው። የንጹሃን እልቂት በአስቸኳይ ሊያበቃ ይገባል። ንጹሀንን ዒላማ ያደረጉ የትኛውም የፖለቲካ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።

የአማራን ማህበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም አለበት፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብ ልስህን ውጣ፣ በአማራነትህ ዋይ ለልስ በል፡፡ የሚያስተዳድርህ መንግስት ሆነ የሚወክልህ ፓርቲ የለም፡፡ ራቁት ትውልድ ማለት አማራ ነው፡፡ ንቃ፣ ንቃ፣ ንቃ፡፡

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.