አንድ ሱስ አለብኝ (ዘ-ጌርሣም)

አለብኝ አንድ ሱስ የሚያስለፈልፈኝ
ኢትዮጵያ እናት ሀገር እያለ እሚያስጮኸኝ

አውሊያ እንዳለበት ሰው
ተይዞ በመተት እንደ ተቀየደው
እየደጋገመ የሚያስለፈልፈኝ
መሳቂያ እስከምሆን በቀን የሚያስጮኸኝ
ተኝቸ ከእንቅልፌ የሚቀሰቅሰኝ
የምግብ ፍላጎት የሚከለክለኝ
አንድ ነገር አለ ሰላም የሚነሳኝ
እኔም አውቀዋለሁ
ተገንዝቤዋለሁ

አለብኝ አንድ ሱስ የሚያስለፈልፈኝ
ኢትዮጵያ እናት ሀገር እያለ እሚያስጮኸኝ

ሐኪም በመድኃኒት
ጠንቋይ ባለው መተት
የሃይማኖት መሪ በሚያደርሰው ፀሎት
ዳኛ ህግ ጠቅሶ በሚሰጠው መብት
ሊያክመኝ
ሊያሞኘኝ
ቀርቶ ሊያሳምነኝ
በህግ ሊዳኘኝ
ጭራሽ የማይቻል
ይሁን እንኳን ቢባል
ገና በልጅነት
በፀዳው ወረቀት
ሁሉን በሚቀበል
ነገር ሳይቀላቅል
ከፍቅር በስተቀር
ክፋት ሳይሸነቁር
ይሉኝታን እምነቱ
ቅንነት ኩራቱ
ሀገር ማለት እናት
ወኔ የአባት ዕትብት
የሕዝብ አንድነት
አብሮ ኑሮ መሞት
በጋራ መደሰት
ልዩነት አብሮነት
የአንድነት መሠረት
ብሎ የሚያስጮኸኝ
አንድ ሱስ አለብኝ
ብዬ የሰየምኩት የሕዝብ መድኃኒት
ፍቱን የተባለ የፍቅር ክትባት

አለብኝ አንድ ሱስ የሚያስለፈልፈኝ
ኢትዮጵያ እናት ሀገር እያለ እሚያስጮኸኝ

ሰው ገና አልገባውም
ቆይቶ ቢቆጨውም
ምንም ይዘግይ እንጅ ኋላ ላይ ይደርሳል
አዋቂ ለመባል ካለፈ ይቀላል
ከሱስ ለመላቀቅ
ከውድቀት ለመራቅ
ከፀፀት ለመዳን
መወጣት የድርሻን
ይሆናል ማርከሻ
ወይም መቀነሻ
እኔ ምን ቸገረኝ
ሰው ያለኝን ቢለኝ
ጭራሽ ሊያብስብኝ
ከሱስ ላያድነኝ
ወደዱም
ጠሉትም

አለብኝ አንድ ሱስ የሚያስለፈልፈኝ
ኢትዮጵያ እናት ሀገር እያለ እሚያስጮኸኝ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ባለታላቅ ታሪክ ነኝ ኢትዮጵያዊ - እስፋው ረጋሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share