September 2, 2020
23 mins read

ወላፊንድ አሥተሳሰብ ካለን “እኛ ሰው ነን ።”ማለት ይከብደናል (መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ)

ግጥም እንደ መግቢያ

ይህ ግጥም ለሁለተኛ ጊዜ ፣ተሻሽሎ የተፃፈ ነው።ርእሱ ተቀይሯል።አንዳንድ ሥንኞች ላይም እርማት አድርጌባቸዋለሁ።ግጥሙ ፅሑፊን ያጠናክርልኛል ።

” ከጅብ ቆዳ የተሠራ ከበሮ…”

እኔ ሰው አይደለሁም፣ዕወቅ ” ትግራዊ” ነኝ!
እኔም” አማራ ነኝ።” ሰው ነህ አትበለኝ !
ለምን ሰው ትለኛለህ?”ኦሮሞ!” ብለህ ጥራኝ።
አቤት አልልህም፣”አንተ ሰው! “ስትለኝ።
እኔ ብሔረሰብ፣ጎሣና ክልልነኝ።
ወላይታ ጋሞ፣እኔ ሲዳማ ነኝ!
አገው፣ኩናማ ዕወቅ መዠንገር ነኝ።
የወል መጠሪያዬን ጎሣዬ ወስዶታል
በጎሣና በቋንቋ መጠራት ግዴታዬ ሆኗል።
……………………………………………….
ኦባማ፣ ኬኒያዊ ዘር ኖሮት አሜሪካንን ሲመራ
ትራፕ ከጀርመን ፈልሶ፣ ሲሆን እሱም አውራ
አንተ እበላ በይ ፖለቲከኛው፣ወደኋላ ተመልሰህ
ዘመነ መሳፋንት ውስጥ መክሊትህን ቀብረህ
“ሰው ከቶም አይደለሁም _ቋንቋ ነኝ “ትላለህ።
ለሆድህ ተገዝተህ
ቋንቋ፣ጎሣ እያልክ …
በዘውግ ፖለቲካ…
ህዝብን ታባላለህ…
…………………………………………
” መልኬን ቁመናዬን፣እርሳው ሰውነቴን
ከአለም ህዝብ ጋር፣ያለው አንድነቴን።
ወግድ! አጨቅጭቀኝ፣በቃ! እኔ አገውነኝ!
ጉራጌ ወላይታ፣አፋር ቅማት ነኝ!
ራያ፣አርማጮህ፣ቤንችና ማጂነኝ!
ቦዲ፣ሀመር፣ሸካ፣በርታ፣ሲዳማነኝ!”
እንዲል ፣
ቀዬው ድረስ ወርደህ ትቀሰቅሳለህ
በማህበራዊ ሚዲያ እሳት ትጭራለህ።
ይህ ብቻም አይደለም፣ያንተ ተንኮልህ
ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር አንድ ግንባር ፈጥረህ
በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ውስጥ ልዩነት አጉልተህ
በቆዳ ማዋደድ ፣በቋንቋ ፖለቲካ፣ሀገሬን አጥምቀህ
ሰው እርሥ በእርሥ እንዲባላ ዛሬም ታደርጋለህ።
ምሁራንን ሣይቀር ታመፃድቃለህ
“እኔ ሰው፣አይደለሁም የጠራው መንዜ ነኝ
የተጉለት የቡልጋ…እኔ የሸንኮራ ነኝ!
ከጎጃምም የደጀን… የደብረማርቆስ ነኝ።
ከጎንደርም ቀብራራው !ደብረ ታቦሬ ነኝ።
እውቅ ፈሪ ሁላ!እኔ አርማጮህ ነኝ።
እኔ ያባ ጃሌው…ዕወቅ የቋራ ነኝ !!
ዕወቅ ሰው ነኝ ባይ ሁላ፣
ከኦሮሞም ምርጥ ኦሮሞ እኔ ወለጋ ነኝ!
የነቀምቴ !የነጆ…የደምቢ ዶሎ ነኝ !!
መጠሪያዬ ሰው አይደለም፣እኔ አሩሲ ነኝ !!
በቆጂ፣ኢትያ፣ደግሞም ሮቤ ነኝ።
እኔ የባሌ ልጅ ፣ያውም የጊኒር ነኝ።
እኔ የሐረረጌ ፣የሀሮማያ ነኝ።”
እንዲል ታደርገለህ።
……………………………
እናም ዛሬም ትለኛለህ….
“ይበል ምን አገባህ፣ቆዳውን ያዋድ
እኔ ቢዝነስ ልሥራ ፣ ንግዴን ልነግድ
‘ሰው ነኝ።’ ባይ ሁላ ፣ በቃ አፍህን ዝጋ !!
በቋንቋ ፖለቲካዬ ላይ፣ አታምጣ አደጋ።
ከ27 ዓመት በፊት ለሥልጣን ስበቃ
ተገን አድርጌ ነው የቋንቋን ጠበቃ !!
እንደሥልጥኑ ዓለም ፣ በራሥ እሴት ብመካ
ይኑር ብል እንደተከበረ፣ ‘የሀገር ፊደል’ ሳይነካ
ልራመድ ብሞክር፣በምዕራቡ በራሥ የመኩራት ፖለቲካ
መቼ ይገኝ ነበረ ፣የቋንቋ ፖለቲከኛው ወሬውን እየከካ!
ቋንቋ ሥልጣን መሥሎት፣በግብዝነት እያስካካ!
መች ይኖር ነበር፣ተቧድኖ ፣ እየተላላሰ አዳሜ ሲያውካካ!
አልገብቶህ እንደሆን፣ውሥብሥብ ሤራ ነው የእኛ ቦጠሊቃ!!
የውሸት፣የቅጥፈት፣የሸውዳ …እና የነጠቃ
ሰርክ በጅብ ቆዳ የተሠራ ከበሮ ድለቃ
እያለ የሚጮኽ…
‘ብዝበዛህን አፋጥን፣ህዝብ ከእንቅልፉ ሳይነቃ።”

(ጥቅምት 14/2011 ዓ/ም)
ወደ ዋናው ርእሴ ገባሁ።
“እኛ ሰው ነን።” የሚል ሰው ሁሉ ፣የምድር ቆይታው በሥቃይ የተሞላ አይሆንም።እኛ ሰው ነን የሚል ሰው፣በእርግጠኝነት እርሱ ሰው እና ሰው ብቻ መሆኑን የተገነዘበ ነው። ሰው፣ከሰው የዘለለ ምንምነት የለውም። ሁላችንም በተፈጥሯችን አንድ ነን።እኛ ሰው ነን ።
እኛ ሰው ነን ። መልካችን የፈለገውን አይነት ይሁን የትኛውንም የመግባባቢያ ቋንቋ እንናገር፣እኛ ሰው እንጂ ፣ቀለማችን እና ቋንቋችን ሌላ ሥም አያሰጠንም።
እኛ ሰው ነን ።ሥንወለድ የወል ሥማችን ” ህፃን” የተባለ።
ህፃን ሆነን፣ወደዓለም ሥንመጣም ምንም ይዘን አልመጣንም።አርጅተን ወይም ጃጅተን እንኳን ብንሞት ራቁታችንን ነው ወደ መቃብር የምንገባው። እኛ ሰው ነን ሥንል ይህንን እውነት በመገንዘብ ነው።
ይህንን እውነት ሰው ሁሉ ያውቀዋል። ግና አያሥተውለውም።ሰውነቱን ፣ለምድር እንግዳ ሆኖ ኗሪነቱ አይገነዘብም። በራሳችን ምርጫ፣ወደንና ፈቅደን ወደ ዓለም እንዳልመጣን ሁሉ፣ከዓለም የምናገኘውም የተኮረጀ እና ለመሠንበት የሚረዳን ነው።ቋንቋም ቢሆን እየተግባባን ለመኖር እንጂ ሰውነታችንን የሚያሥክድ ወይም የሚቀይር አይደለም።
እኛ ሰዎች ነን ።ራቁታችንን ተወልደን ፣በጉልምሥናችን ብዙ ሀብት ብናፈራም፣ ምንም ይዘን ወደ መቃብር አንወርድም። ለትውልዳችን አውርሰን ማለፋችን ግን እርግጥ ነው።የተትረፈረፈው ሀብት እኛን ከሞት አያሥጥለንም።ደሥታና ሃሴትንም አያጎናፅፈንም።
በእውነቱ ይመሥለናል እንጂ የተትረፈረፈ ሀብት ና ንብረት ጤና፣ሠላም ና በበዛ ደሥታ የታጀበ ኑሯን እንድንኗር አያደርገንም። በተትረፈረፈ ሀብት ና በንብረት ብዛት በህይወት ለዘላለም የመቆየት ዋሥትና የለንም።እርግጥ ነው የተቀማጠለ ና የተዘባነነ አኗኗር ብርቅ ላይሆንብን ይችላል።በተላላፊ በሽታዎች የመጠቃት እድላችንም አነሥተኛ ይሆናል። በኮሮና ላለመያዝም ቤታችንን ዘግተን ለመቀመጥ የሚያሥችል አቅም ሊኖረን ይችላል ።ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እና ከአደጋዎች ግን አናመልጥም። ከስኳር፣ ከግፊት ፣ከኩላሊት፣ከጨጓራ፣ከልብ፣ከነርቭ፣ከካንሰር ወዘተ በሽታ። አናመልጥም።…
ከመሬት መንቀጥቀጥ፣ከመኪና አደጋ፣ከተለያዩ ትንታዎች ፣ከመውደቅ፣ከመሠበር ወዘተ።1 ፐርሰንት ለመጠበቅ አንችልም።
እንደ አለመታደል ሆኖ፣ ይህንን እውነት በቅጡ የሚገነዘቡ እና ህይወታቸውን በጥንቃቄ የሚመሩ ሰው መሆናቸውን የተገነዘቡ ጥቂቶች ናቸው።
አብዛኛው ሰው ነፍሥ ካወቀ በኋላ፣ ያለእረፍት በመስራት ክፉ ቀን በህይወት ዘመኑ ቶሎ አይከሰትም ብሎ የሚኖር የዋህ ፍጡር ነው። ሀይማኖቱኛውም በፀሎቱ ብርታት ፣ ዛሬ ና ነገው እንዳይደፈርስ በብርቱ እየተጋ በፈጣሪው ተማምኖ የሚኖር ነው።አህዛብ የተባለውም እንደሚኖርበት የዓለም ሥርዓት ዛሬን ጠንክሮ በመሥራት የነገ ኑሮውን ለማደላደል የሚጥር ምሥኪን ነው። በእርግጥ በየማለደው ለፀሎት፣ ፈጣሪ ፊት ከሚቆመው እና በሰው ሚዛን ፃድቅ ከሚባለው ኃይማኖተኛ በልጦ ከሞተ በኋላ ገነት ቢገባ ሊገርመን ይችላል ። …
ይህ እውነት ያሥገርማል።ከሰው አእምሮ በላይ ነውና።ሥለፈጣሪ ፍርድ አሰጣጥ በሰውኛ ህሊና ድምዳሜ ላይ መድረሥ እጅግ የሚከብድ ይመሥለኛል።ብዙዎች ሥለ ፈጣሪ ለማወቅ የሚጥሩ፣ሣይንቲሥቶች፣ምሁራንና ፈላሥፎች ፣ሥለፈጣሪ በቅጡ ሳይረዱ እሥከወዲያኛው ማሸለባቸውን ሥትገነዘቡ ፈጣሪያችን ከአእምሯችን በላይ መሆኑን ትገነዘባላችሁ።እኔ ሁሌም እንደምለው፣በዚህ ዓለም በህይወት እየተንጎማለሉ ያሉት የፈጣሪ፣ልዩ፣ልዩ ሸክላዎች ናቸው።ነገ አፈር የሚሆኑ የሚያማምሩ የእግዜር ሸክላዎች።
ይህንን እውነት ግን የማንቀበል ብዙዎች ነን።ባለፉት ዘመናትና በዚህ ዘመንም፣አያሌ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣አባትና እናቶቻችን ፣ሸክላነታቸውን ሣይገነዘቡ፣ በዝንጋታ ገመድ እየተጎተቱ ወደመቃብር ወርደዋል።ሸክላነታቸውን እንድናውቅ።ይሁን እንጂ እኛም ካልሞትን በሥተቀር አፈርነታችንን አንገነዘብም ? ግን፣ግን ሰው እንዴት ሞቶ አፈርነቱን ይገነዘባል?ወለፈንዴ ነገር ነው።
ሞተን አፈርነታችንን ከመገንዘብ ፣በህይወት ሣለን እውነቱን ብንረዳ እና ሞትን በጉያችን ይዘን እንደምንዞር ብንገነዘብ ፣የተሻለች ና ፍቅር የነገሰባት ዓለም ለመፍጠር ያሥችለናል።
በዓለም ፍቅር የጠፋው፣በዙው ሰው ነገ ሞት እርሱ ጋር መምጣቱን ባለመገንዘቡ ይመሥለኛል።የወንድሜ ሞት ይጠቅመኛል ብሎ ፣ቃዬል አቤልን እንደገደለው ፣በእኩይ ቅናት ና በጥላቻ ወንድምህን ብትገለው፣ያ የንፁህ ደም አሳዶ፣አሳብዶ ፣እንቅልፍ አሳጥቶ ወደ መቃብር እንደሚያወርድህ እወቅ።የጭካኔ ደርጊትህ ዘላላም ኗሪ አያደርግህም።
አብዛኛው የዓለም ሰው ፣ ሞትን በጉያው ይዞ እንደሚቀሳቀስ እና በሞት ሰልፍ ውስጥ እንዳለ የዘነጋ ነው።በህይወት ያለ፣ የዓለም ሰው ዘወትር የሚያሥበው “ሁሌም የሚሞተው በሬሣ ሣጥን ውስጥ ያለ ብቻ ነው።”ብሎ ነው።
ጥቂት ሃሳብያን ግን፣ “ሰወ ልጅ በሌላው ሞት ለማትረፍ መንቀዠቀዡን እሥካላቆመና ፣በቀቢፀ ተሥፋ፣በምቀኝነት፣በእኩይ ቅናት፣በቆዳ ማዋደድ፣ የፈጣሪን ሥልጣን በመቀማት(ኃይማኖት አክራሪነት ማለት በሁሉን ቻዩ ፈጣሪ ሥራ ጣልቃ መግባት ነው።) በጭፍን ጥላቻ፣በሥግብግብነት፣እነዚህን በመሣሠሉት ሁሉ ተነሳስቶ ወንድሙን መገደል አስካላቆመ ጊዜ ድረስ፣በዚች ዓለም ላይ ሰላም አይሰፍንም።ምድሪቷም ደም እየጠጣች ትኖራለች።”ይላሉ ።
ከዚህ መንደርደሪያ ሃሳብ ተነሥተን ኢትዮጵያዊያን ቆም ብለን እሥቲ ራሳችንን እንይ።
ተምረናል ተመራምረናል፣ደክተርና ፕሮፌሰር ተብለናል የምንል እውን እንደ አእምሯችን ከፍታ እናሥባለን?ወይሥ ህሊናችንን በንዋይ እና በበቀል ሸጠነዋል?
ሰሞኑን የሰማሁት ፣የምኒልክ ቴሌቪዢን ፕሮግራም(በመረጃ ቴሌቪዢን) ተራ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ነው የሆነብኝ።ግለሰቦቹ በተሻለ መንገድና አቀራረብ ፣በመንግሥት አሠራር ላይ ያላቸውን ቅሬታ ማቅረብ ይችሉ ነበር።ለምን ጎሰኝነትን የሚያራግብ፣ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽር ሃሳብ እንዳቀረቡ አይገባኝም።ትግራይን ለመገንጠል ያሰበው እጅግ በጣም ጥቂቱ የህወሓት አመራር ከፍሏቸው ይሆንን? እንዲህ አይነቱን የጥላቻ መርዝ የሚነዙት?የሚል ጥያቄም ህሊና ጭሮብኛል?
ለኢትዮጵያ የወደፊት እድገት፣ለህዝቧ ፍቅር ቢጨነቁ ኖሮ፣ጠቅለል ያለ እውነትነት ያለውን ሃሳብ በማቅረብ ፣በሽግግር ሂደቱ ላይ የራሳቸውን ጡብ ያኖሩ ነበር።
ለምሳሌ
“ሀገሪቱን የሚያሥተዳድረው መንግሥት ዛሬም በኢህአዴግ ቅኝት እየዘመረ ነው። እየተገበረው ያለ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማህበራዊ ተግባር ቀበሌ ሲደርስ እንደ ጥንቱ ነው።ዛሬም፣ለውጡ ዜጎችን ያሳተፈ አይደለም።የተደበላለቀ ፣የበዛ የጎሣ ሥብጥር የሚኖርበት ከተማ ፍትሃዊ አሥተዳደር ያሥፈልገዋል።እናም ብልፅግና ምን አሥቧል። ኗሪውን ባለቤት ያላደረገ ፣ለሰው ሳይሆን ለቋንቋ የሰገደ ሥርዓት፣ከሁቱና ቱትሲ በምን ይሻላል ? ይህንን ሁቱና ቱትሲነት እሥከወዲያኛው ለመገላገል ምን የተሻለ እቅድ አለው?እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልሥ እና የከተማ ብልፅግና የየአንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ብልፅግና ነው።ብሎ የማያምን ትውልድ ፈጥሮ ፣ከተማን ቢያበለፅግ ነገ ላለመውደሙ ምን ዋሥትና አለው?ዓለም የሰው ሁሉ መኖሪያ ናት ።ማንም በህጋዊ መንገድ ገብቶ የማንም ሀገር ዜጋ መሆን ይችላል ።እንኳንሥ በተወለደበት ሀገር ይቅርና…በማለት አግላዩን የ27 ዓመት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት እንዴት አድርጎ ነው፣በተጨባጩ እና በመላው ሰው ቅቡልነት ባለው ፣የፍትህ፣የእኩልነት፣የነፃነት ሥርዓት የሚቀይረው?እሥከመቼ ነውሥ የኢትዮጵያ ፖለታከኞች ለሥልጣናቸው ሲሉ ሰውነታቸውን ዘንግተው፣ቋንቋ ነን እያሉ አሸሼ ገዳዬ፣ስበር ተጋዳላይ፣ከኤ ነጨባ የሚሉት? …..
“ብልፅግና ፖርቲ ከሆነ የኢትዮጵያ ብልፅግና ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ ተብሎ በአሳታፊነት በአዲስ መልክ ይቋቋም እንጂ፣በአሮጊ አቁማዳ ውሥጥ ዛሬም መደበቅ አለበት ወይ?ከዚህ እውነት ተነሥተን ሥርዓቱን ሥናየው ዛሬም ያለው የዘውጌ ና የቋንቋ ቡድናዊ ፖለቲካ ሲሆን ጠቃሚነቱም ለጥቂት ሹመኞች እንጃ ለባለ ቋንቋዎቹ አይደለም ብለን መደምደም አንችልም ወይ?
“አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች ዋና ቋንቋቸው “ባዴ” ነው ፣ግን ከመበልፀግ አልገታቸውም።ኢትዮጵያን ያነቃት ከሶሻሊሥቱ ቡድናዊ መዋቅር ያለመውጣቷ ብቻ ሳይሆን ፣ወያኔ ኢህአዴግ ከሞሶሎኒ እና ከወቅቱ ቅኝ ገዢዎች ኮርጆ ከ1983 በኋላ የተከለባት፣የቋንቋ አሥተዳደር እና አንድ ለአምሥት ጠርናፊ ሥርዓት ነው። ይህ ከፋፋይ ሥርአት በተግባር መወገድ የለበትም ወይ? ፍትህ፣ነፃነት እና እኩልነት ዜጋ ለሆነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማምጣት የምንችለው፣በነገድ፣በጎሣ ና በቋንቋ ቡድን ፈጥረን በመተጋተግ ነው ወይ? ፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ና ሹመኞች በህግ ተጠያቂ መሆን የለባቸውም ወይ? አርነትሥ የሚያወጣቸው እውነተኛ የፍትህ ሥርዓት መሆን የለበትም ወይ?” በማለት ፣ምክንያታዊ የሆነ፣ሃሳብ ላይ በመወያየት “ለመጪው ትውልድ የምትበጅ፣አያሌ ተሥፋን ያጨቀች ኢትዮጵያን እንዴት እንፍጠር?” በማለት በቅን ልቦና ላይ የተመሠረተ ሃሳብ ማቅረብ ይችሉ ነበር።
እንደ እኔ እምነት፣ በልቶ…ተራ ሞት በመሞት ዓለምን በጊዜውም፣ያለግዜውም ከመሠናበት ይልቅ፣ከአድማስ ባሻገር የምትታይ፣ የበልፀገች፣የታፈረች እና የተከበረች ልዕለ ኃያል የሆነችውን ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ ፣ በንፁህ ልብ እና በሃቅ መሥራት ተራ ሟች ያልሆነው ሰው ምግባር ይመሥለኛል።…
እርግጥ ነው፣ተራ ሞቹ ሰው፣በጣም ግልፅ የሆነውን ፣በየቀኑ የሚመለከተውን፣የሚያስተውለውን፣ እና ተጨባጭ የሆነውን ሞት እንኳን ይዘነጋል።እናም ትላንት ሥህተት ነው፣ያላቸውን፣ትላንት ነውረኛ ያላቸውን ተግባራት ፣ “ዛሬ ጊዜው የኔ ነው ደሞ…ማን አለኝ ከልካይ ያሻኝን…” በማለት ነውር መሥራት ሊጀምር ይችላል ።ይህ ነውር ሥራ ግን ቢዘገይም ዋጋ ሳያሥከፍለው አይቀርም።እንዲህ ዓይነቱን ተደጋጋሚ የኋሊት ጉዞ ለማሥቀረት፣ በተቋማት የሚመራው ሰው ልጅ ከወላፊንድ አሥተሣሰብ ራሱን ማንፃት አለበት።
በጎ፣ቅን፣መልካም፣ እውነተኛ ና ለሁሉም ሰው ጠቃሚ የሆኑ ተግባራዊ ሃሳቦች በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውሥጥ እንዲያብቡ “እኛ ሰው ነን” ብሎ ከሰው በላይ የገዘፈውን ቋንቋ ከመግባቢያነት ውጪ ፋይዳ እንደሌለው ማሥተማርም ሰው መሆኑን ካመነ ዜጋ ሁሉ ይጠበቃል ።

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop