ከምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

 በኢትዮጵያና ኢትጵያዊነት ላይ ምክክር ፓርቲ ለድርድር የማይቀርብ እንደመሆኑ መጠን በተመሳሳይ አዲስ አበባ ከዜጎቿም አልፎ የአለም ሕዝብን የሚወክላቸው ኢምባሲዎች የሚገኙባት ከተማ እና የአፍሪካ ሕብረት መዲና እንደመሆንዋ መጠን የሁሉንም ትኩረት የምትስብ ከተማ ነች፡፡

    አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተወለዱ እና ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡባት ዜጎች የሚኖሩባት ከተማ መሆኗ እየታወቀ ገዢው ፓርቲ አሁን አሁን ይህን እውነታ ባላየና ባልሰማ የአዲስ አበባን ዲሞግራፊን ለመቀየር የሚደረገውን እንቅስቃሴና ተዛማች ችግሮች እንዲቀረፉ ከዚህ በታች የተጠቀሰውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

  1. በአዲስ አበባ ከተማ ማንነት ላይ የገዢው ፓርቲ አንዳንድ አመራር አባላት የከተማዋን ዲሞግራፊ እንቀይራለን በሚል የሰጡት ሀሳብ በመንግስት ላይ ፓርቲያችን ምክክርና የከተማው ነዋሪ ጥርጣሬ አድሮበታል ፡፡ ጉዳዩ የመንግስት አቋም ካልሆነ መንግስት በግልጽ ወጥቶ ማስተባበያ እንዲሰጥ ምክክር ፓርቲ አበክሮ ይጠይቃል፡፡

  2. በ1997 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ የአዲስ አበባ ወጣቶች ገዢውን ፓርቲ ባለመምረጣቸው የህወሀት ኢህአዴግ መንግስት የከተማዋ ወጣቶች ላይ የብቀላ እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለከተማዋ ወጣቶች የተመደበው ተዘዋዋሪ በጀት በትክክል የከተማዋ ወጣቶች ያላገኙበት እና በጀቱ የከተማዋ ነዋሪ ላልሆኑና ለአንድ ብሔር ሰዎች የተከፋፈለ መሆኑንና ተዘዋዋሪ በጀቱን የወሰዱ አብዛኛው ገንዘብ አለመመለሱን ከዳሰሳ ጥናታችን መረዳት ችለናል፡፡ ተዘዋዋሪ በጀቱ የሀገር ሀብት ስለሆነ በሕግ አግባብ ተመላሽ እንዲሆን፣ አሁንም ለወጣቶች ተብሎ የተመደበው በጀት በትክክል ለከተማዋ ወጣቶች እንዲደርስ ምክክር ፓርቲ አጥብቆ ያሳስባል፡፡

  3. በከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ዜጎች ተቸግረው የቤት ችግራቸውን መፍትሔ እናገኛለን በማለት ለኮንዶሚኒየም ቤት ለመገንባት ከጉሮሮዓቸው ቀንሰው ያዋጡትን እና የተገነባውን ቤት በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ለተለያዩ ሰዎች መሰጠቱ ኢ-ፍትሀዊ በመሆኑ አስተዳደሩ ከድርጊቱ ተቆጥቦ ለቤት ችግረኞች ቤቱን እንዲያስከብር እንጠይቃለን፡፡

  4. የእርሻ መሬታቸውን ለቤት ግንባታ የሰጡ ገበሬዎች ለመሬቱ ግምት በቂ ነው የማይባል ክፍያ እንደተከፈላቸው እናምናለን፣ይሁንና በአዲስ አበባ ዙሪያ የተገነቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለገበሬው በቂ ክፍያ ስላልተከፈለ ከፊሉን ቤት ለገበሬ ልጆች መሰጠቱ ተገቢ አይደለም ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ከገበሬው የተወሰደው መሬት የእርሻ መሬት በመሆኑ ማካካሻ መሰጠትም ካለበት ተመሳሳይ የእርሻ መሬት መሆን ሲገባው የከተማዋ ነዋሪዎች ለረጅም ዓመታት ለቤት ግንባታ አዋጥተው ከችግር ወጣን ብለው ሲጠባበቁ በፖለቲካ ውሳኔ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በማለም የተገነቡትን ቤት ለቤት ልማቱ ላልቆጠቡ ሰዎች ማደል ለአዲስ አበባ ሕዝብ የሚቆረቆርለት የከተማ አስተዳደር የሌላት መሆኑን ያመላክታል ፡፡ድርጊቱንም ምክክር ፓርቲ ያወግዛል፡፡

  5. አዲስ አበባ በከተማዋ አስተዳደር የተመረጠ የራሷ ከንቲባ ኖሯት አያውቅም ፡፡ በዚህም ምክንያት በፖለቲካ ውሳኔ የሚሾመው አመራር የከተማዋ ነዋሪ ችግሮችን ሲፈታ አይታይም፡፡ በመሆኑም 6ኛው አገራዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ አዲስ አበባን ማስተዳደር ያለበት የአዲስ አበባ ተወላጅ የሆነና ስለ ከተማዋ ችግር የሚያውቅ መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በመሆኑም መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

  6. 20/80 እና 40/60 የኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ ዜጎች ተቸግረው የቆጠቡትን ገንዘባቸውን የእድሉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መንግስት ለማንም ያደለው ሳያንስ 20/80 እና 40/60 የተመዘገቡ የከተማዋ ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅታችሁ መንግስት ቦታ አቅርቦ ደሀና አቅም ያለው ሳይለይ  በጋራ ትገነባላችሁ መባሉ ተገቢ ነው ብለን አናምንም፡፡ መንግስት አቅም ለሌላቸው ዜጎች እንደ ቀድሞው መንግስት ገንብቶ በረጅም ጊዜ ክፍያ ለዜጎች እንዲያስረክብ እንጠይቃለን፡፡

  7. የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ገለፁ የተባለው ጉዳይ የመንግስት አቋም ካልሆነ መንግስትን አይወክልም በሚል ማስተባበያ እስካልሰጠ ድረስ የመንግስት አቋም አይደለም ለማለት እንቸገራለን፡፡ በመሆኑም መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡

  8. አጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪ ዝም ማለት የታመቀና ነገ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆነ እንቅስቃሴ ሊፈጥር ይችላል ብለን ስለሰጋን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አበክረን እናሳስባለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስሜቱ ይቁምና እስቲ አማራጮችን በእርጋታ እንመልከት - ግርማ ካሳ

                                     ነሀሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም

                                        የምክክር ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share