ዕንባም አያብሰው (ዘ-ጌርሣም)

ምን ያደርጋል ጆሮ ምን ያደርጋል እጅ
ሁሉን የሚመዝን አዕምሮ ነው እንጅ
እጅም ሥራ ይሥራ እግር ይራመድ
ስህተት ላይ ይጥላል ቁጭ ብሎ መፍረድ
ሲፈርዱ ለራስ ነው ነግ በኔ ላይ ብሎ
ግፉ እንዳያስጠይቅ ትዉልድ ተከትሎ

ቂም በቀል ይወገድ መዘዙ ብርቱ ነው
ግፍ በግፍ ሲመለስ እንባም አያብሰው
መታገስ ደግ ነው ለሁሉም ይጠቅማል
አጉል መበሻሸቅ መቀመቅ ይከታል

አንድ ጉዳይ አለ መስተዋል ያለበት
የራስን ሳያዩ መመኘት የሰው ሞት
አይበጅም ለትውልድ አያሻግርም ወንዝ
ከማስከተል ሌላ ውድቀትና መዘዝ

ተው በሉት ያነን ሰው
ተይ በሏት ያችን ሰው
ግፍ በግፍ ሲመለስ እንባም አያብሰው
ያባብሳልና ቁስሉን መቦጫጨር
አዲስ ታሪክ ይቅር ያልነበረ ነገር

አንድ ዕውነት አለ መቀበል ያቃተን
ወደድንም ጠላንም ሁላችንም ሟች ነን
አንድ ሞት ክብር ነው ሁሌም የማይቀረው
ከዚያ ከበለጠ ዕንባም አያብሰው
ሞቴን አሳምረው ተብሎ ይፀለያል
ዕንባ ከደረቀ አርፈናል ያሰኛል

ብዙ ሞቶች አሉ ስም የወጣላቸው
ከሁሉም የከፋው በስም የሞተ ነው
ከሙታንም በታች ብዙ ሞት የሞተው
ተረስቶ ይቀራል ዕንባ ሳይቸረው

ብለን እንፀልይ ሞቴን አሳምረው
ግፉን ካበዛነው ዕንባም አያብሰው

ተጨማሪ ያንብቡ:  መቃብር ብቻ ሆንሽ!! - ያሬድ መኩሪያ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share