August 25, 2020
26 mins read

የፖለቲካ ማንነት በዛሬዋ ኢትዮጵያ – አንዱዓለም ተፈራ

ረቡዕ፡ ነሐሴ፤ ፮ ቀን ፳ ፻ ፲ ፪ ዓ ም

መግቢያ

የኮሮና ቫይረስ ኑሯችንን አስቸጋሪ ባደረገበት ወቅት፤ ስለኮቬድ 19 ሳያወሩ ወደሌላ መሄድ በጣም አስቸጋሪ ነው። አንባቢዎች እንዴት ሰነበታችሁ? ተስፋዬ፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጋችሁ እንደሆነ ነው። መቼም ሊቆች ለዚህ ተውሳክ ክትባት አግኝተው ትንፋሽ እስኪለግሱን፤ ጥንቃቄያችን ከፍ ማለት አለበት።

በሀገራችን ያለው የፖለቲካ ዕውነታ፤ የያንዳንዳችንን ማንነት በተደጋጋሚ እየጠየቀ ነው። በርግጥ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ብቅ ካለበት ዕለት ጀምሮ፤ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ የግል ኢትዮጵያዊነታችን ተሰርዞ፤ በተወለድንበት ክልል እና በምንናገረው ቋንቋ በኩል በመንጋ ተዳብለን፤ ኢትዮጵያዊነታችን ተተርጉሞልናል። ያን ሥርዓት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛውን መስዋዕት ከፍሎ፤ አንፈልግህም ብሎ፤ ተፍቶታል። ማንኛውም ሥርዓት እንዲወገድ የሚደረገው፤ በሥርዓቱ የፖለቲካ ፍልስፍና፣ በአስተዳደር መመሪያውና፣ ባከናወነው ተግባር ምክንያት ነው። ስለዚህ፤ ሥርዓቱ ሲወገድ፤ እኒህ የሥርዓቱ መሠረታዊ ወለል፣ ግድግዳና ጣራ የሆኑ አካላቱ፤ ይወገዳሉ። በኢትዮጵያ ያየነው ይህ አይደለም። በሥርዓቱ መወገድ ሂደት፤ እንዲወገድ የታገለው ሕዝብ፤ ከውጤቱ ባለቤትነት ተገልሎ፤ ጥቂት የሥርዓቱ አካል የነበሩ፤ ነገር ግን የተወሰነ ለውጥ የፈለጉ ሰዎች፤ የውጤቱ ባለቤት ሆኑ። በዚህ ሂደት፤ የሕዝቡና የሀገሪቱ ዕጣ፤ በኒህ የሥርዓቱ አካል በነበሩ ሰዎች እጅ ወደቀ። ይህ ሁኔታ፤ ተከትሎ ለመጣውና አሁንም ላለንበት ግልጽ ያልሆነ የፖለቲካ ሀቅ ዳርጎናል። በርግጥ ሀገራችን ያለ መንግሥት፤ አውላላ ሜዳ ላይ ትቀመጥ የሚል ሀገር ወዳድ የለም። ነገር ግን፤ መሠረታዊ የሆነው የለውጡ ግዴታ መምጣት መነሻ፤ አሁንም መልስ አለማግኘቱ፤ ወደ ፊት እንዳንሄድ ምክንያት ሆኗል። በዚህ ጽሑፍ፤ የለውጡ መሽከርከሪያ የሆነው፤ የፖለቲካ ማንነት በዛሬዋ ኢትዮጵያ፤ ተዳሷል። በዝርዝሩ፤ የፖለቲካ ማንነት ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ በመሥጠት፤ ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተነስተው፤ ከዚያ ሊከተል የሚችሉት ተመላክተውበታል።

የፖለቲካ ማንነት ምንድን ነው?

የአንድ ሀገር ተወላጅ፤ የዚያች ሀገር ዜጋ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በጋብቻ ወይንም ባጠቃላይ አቤቱታ አቅርቦ፤ መስፈርቶችን በማሟላትና ተቀባይነትን በማግኘት፤ የዚያችን ሀገር ዜግነት መያዝ ይቻላል። በአንጻሩ፤ ሀገሩን ለቆ ሌላ ቦታ በመሄድ፤ የሌላ ሀገር ዜግነትን መስፈርት አሟልቶ በመገኘት፤ የዚያችን ሀገር ዜግነት መውሰድ ይቻላል። አንድ ግለሰብ በሀገሩ የሚኖረው መብትና ግዴታ፤ ግለሰቡን በሀገሪቱ ውስጥ፤ በየትኛውም ቦታ፤ በሚካሄዱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባሕል ክንውኖች እንዲሳተፍ ይፈቅድለታል። ይህ የግለሰብ የፖለቲካ መብትን ያመላክታል። ግለሰቧ በፈቃደኝነትና በአመለካከቷ፤ የፖለቲካ ማንነት ትወርሳለች። የፖለቲካ ማንነት የሚወሰደው፤ ከግለሰብ የግል እምነትና ፍላጎት ተነስቶ ነው። በሀገሪቱ ባለው በአንዱ ክፍል መወለድ፣ ወይንም የአንደኛውን ክልል ቋንቋ መናገር፣ የትምህርት ደረጃ ወይንም ያካበቱት ሀብት፤ የፖለቲካ ማንነትን በመወሰን በኩል ፍጹም አያገባውም። ስለዚህ በአንድ ሀገር ውስጥ፤ ግለሰቦች ለሚያደርጉት የፖለቲካ ማንነት ምርጫ፤ የግል እምነታቸውና የፖለቲካ አስተሳሰባቸው እንጂ፤ ሌላ ወሳኝ የሆነ ጉዳይ የለም። በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለ አካልም፤ የአንድን ግለሰብ የፖለቲካ ማንነት ሊወስን አይችልም። እንግዲህ መነሻችን ይህ ነው።

የግል ወይንስ የቡድን ማንነት ምንድን ነው?

በሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ላይ፤ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ አለ። ይሄም የግለስብ ወይንም የቡድን/የመንጋ መብት! የሚለው መሟገቻ ሃሳብ ነው። ቀላሉ መልስ፤ አንድ ግለሰብ ሙሉ መብት ካለው፤ ከማንም ጋር መቧደንና የፈለገውን የፖለቲካ ቅኝት ማራመድ ከቻለ፤ የአንድ መንጋ አባል በመሆን የሚገኝ መብት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ፤ ትርጉም ያጣል። ነገር ግን፤ ያላወቀውን ዝምተኛው ብዙኅን አግበስብሶ በመንጋ አጉሮ ለመያዝ፤ “እኛ አንድ ቦታ ስለተወለድን፣ አንድ ቋንቋ ስለምንናገር፣ አንድ ሃይማኖት ስላለን፣ . . . ወ.ዘ.ተ. አንድ ነን! አመለካከታችንም አንድ ነው! የጋራ የሆነ ጉዳይ ስላለን፤ የጋራ የሆነ መፍትሔ አብረን እናቀርባለን!” የሚል ዘዴ ሰንቆ፤ ለሥልጣን አቋራጭ መንገድ የፈለገ ልሂቅ፤ መከራከሪያ ያቀርባል። ከላይ እንደሰፈረው፤ የፖለቲካ ማንነት የግል ውስኔ ነው። በሀገር ጉዳይ ላይ የሚኖር ተሳትፎ፤ በመጀመሪያ የሀገሩ ዜጋ ሆኖ መገኘት፤ ቀጥሎ ደግሞ በአስተሳሳብ ከሚስማሙት ጋር ሆኖ የፖለቲካ ድርጅት መስርቶ መታገል ነው።

ሃይማኖትና ሙያ በማንነት ዙሪያ

ከላይ አጠቃሎ በሚይዘው ትርጉም አኳያ፤ ሃይማኖትም ሆነ ሙያ፣ የተወለዱበት አካባቢም ሆነ የሚናገሩት ቋንቋ፤ የፖለቲካ ማንነትን በሚመለከት ቦታ የላቸውም። ነገር ግን፤ የተወለዱበትን አካባቢ በሚመለከት ጉዳይ፤ ሰዎች ተሰባስበው ጥቅም ለማስጠበቅ፤ የሲቪክ ማኅበራትን በማቋቋም፤ ባሰፈሩት ተልዕኮ አኳያ ማቀንቀን ይችላሉ። ይህ ግን የፖለቲካ ማንነት ሳይሆን፤ በፖለቲካ ሂደቱ፤ በአንድ የኅብረተሰብ ጉዳይ ላይ መረባረብንና፤ የዚያን ጉዳይ ማሰፈጸምን ያመለከታል። ከዚያ በተረፈ፤ የተያዘው ጉዳይ ግቡን ሲመታ፤ ስብስቡ ይፈርሳል። ይህ የሥልጣን መወጣጫ መሰላል አይደለም! የጉዳይ አቀንቃኝነት እንጂ፤ የፖለቲካ ማንነት አይደለምና!

እስኪ ለዚህ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ፤ በሀገራችን የሰፈረውን የአስተሳሰብ ልዩነትና ያለውን የፖለቲካ ሀቅ እንመርምር። በአንድ በኩል፤ ለውጥ ፈላጊው ወገን፤ ለውጡ የት አለ? እያለ እየጠየቀ ነው። በሌላ በኩል፤ “እኔ አሻግራችኋለሁ!” ያሉን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን እና ድርጅታቸው፤ እጅና እግራቸው በነበረው ሥርዓት ሕግና ደንብ፣ መመሪያና መንግሥታዊ መዋቅር ተተብትቦ፤ ወደፊትም እንዳይሄዱ፣ ወደ ኋላም እንዳይመለሱ ተቀፍድደው ተይዘዋል። ይህ ደግሞ በበኩሉ፤ አንድም ራሳቸው የፈለጉትን እንዳያራምዱ ሲያግታቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ የሚጠብቀውን ባለማግኘቱ፤ የለውጡ ወዳጅ ናቸው ወይስ ጠላት? የሚል ጥያቄ በላያቸው ላይ ጭኖባቸዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት፤ መንግሥት በመሆናቸው፤ መንግሥታዊ ክንውኖችን ማካሄድ የግድ አለባቸው። በአንጻሩ ደግሞና በሚያሳዝን ሁኔታ፤ ያለውን መንግሥት መተካት ቀርቶ፤ አቅም ያለውና እውነተኛ ደጋፊም ሆነ ተፎካካሪ ሆኖ የቆመ ሌላ ድርጅት ባለመኖሩ፤ ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ፤ በሥልጣን ላይ ባለው ክፍል ጫና ሊያሳድር የሚችል ኃይል አሁን የለም። ይህ ላለው መንግሥት እፎይታና ሰቆቃ ሆኗል። እፎይታ ያልኩት፤ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ፈልጎ እሱን አስጊ የሆነ አካል አለመኖሩ ነው። ሰቆቃ ያልኩት ደግሞ፤ የሚታይና የሚዳሰስ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አድራጊ ኃይል በሌለበት እውነታ፤ በሕዝቡ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የልብ ትርታ ሊገነዘቡ የሚችሉበት ማያ መነፅር ስለሚነፍጋቸው ነው። ባላሰቡት ሁኔታ ሊገነፍል የሚችል ሕዝባዊ መነሳሳት ስለሚያንዣብባቸው ነው።

ከመካከላችን “ተፎካካሪ ድርጅቶች አሉ!” ብሎ የሚያምን አይጠፋም። ችግር የለውም። ተፎካካሪ ማለት፤ በቦታው ላይ ያለውን ተክቶ፤ የተለየ ሃሳብ ይዞና የተሻለ አማራጭ አቅርቦ፤ ቦታውን መሙላት የሚችል ለመንግሥትነት ብቁ ሆኖ መገኘት ነው። አለበለዚያ፤ “የጠመጠመ ሁሉ ቄስ ነው!” ማለት ይሆናል። የተፎካካሪው ራዕይ ምንድን ነው? የተፎካካሪው የፖለቲካ ፍልስፍና ምንድን ነው? የተፎካካሪው የአስተዳደር መመሪያ ምንድን ነው? የተፎካካሪው ዐቅም ምንድን ነው? ይሄን ሁሉ አመዛዝኖ ነው፤ ተፎካካሪ አለ ማለት የሚቻለው። እንዲያው ስም ብቻ ይዞ፤ “ተፎካካሪ ነኝ!” የሚለውን ማግበስበሱ፤ የትም አያስኬድም። ያለው የብልፅግና መንግሥት፤ የነበረው ሥርዓት አካልና፤ አሁንም ያንኑ ሥርዓት አስቀጣይ ለመሆኑ፤ ጥያቄ የለም። ነገር ግን፤ በሌላው ወገን፤ ይህን ለመለወጥ የሚደረገው ዝግጅት የሚያሳፍርና የሚያሳዝም ነው። ብሶትን እያነሱ እየጣሉ በየቦታው ማላዘን ተፎካካሪነት አይደለም። አለመታደል ሆኖ፤ በኛ ሀገር ፖለቲካ፤ ዋና ማሽከርከሪያው፤ ጠዋትም ማታም በደልን ይዞ መወዛወዝ ነው። ይህ የትም አያደርስም። የሶስተኛው ዓለም አካልነታችንን አልክድም። ላስረዳ!

ሕዝቡ በተለያየ መንገድ በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ላይ ሲነሳ፤ የነበረው የፖለቲካ ሂደት አንገፍግፎት ነው። ያ የፖለቲካ ሂደት አሁንም እንደቀጠለ ነው። ሕገ መንግሥቱና የአስተዳደር መዋቅሩ እንዳለ ነው። የፖለቲካ ፍልስፍናው አልተለወጠም። ባጭሩ ጉልቻውም ያው! ድስቱም ያው! ነው። ካወቀበት፤ ለውጥ ፈላጊው ክፍል የራሱ አጀንዳ አለው። መጀመሪያ፤ ያለውን መንግሥት ጊዜያዊ አስፈላጊነት አምኖ መቀበል ነው። ይህ ማለት፤ ሀገራችን መንግሥት አልባ ሆና መቀመጥ እንደማትችል መረዳት ነው። ይህ ያለውን መንግሥት በጊዜያዊነት የመቀበልን ግዴታ ያሳያል። ቀጥሎ መለወጥ ያለባቸውን ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ይህ ማለት፤

አንደኛ፤ ሕዝቡ ያነሳው፤ አንድ ነን! አትከፋፍሉን! ላለው መልስ መሥጠት ነው።

ሁለተኛ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ! በየትኛም የሀገሬ የኢትዮጵያ ክፍል፤ መንቀሳቀስ፣ መቀመጥ፣ ሀብት ማፍራት፣ በማንኛውም የኅብረተሰቡ ክንውን የመሳተፍ መብት አለኝ! ያለውን የሚተገበርበትን ሂደት ማስቀመጥ ነው።

ሶስተኛ፤ በሀገሬ የትኛውም ክፍል መወለዴ፣ የትኛውንም ቋንቋ መናገሬ ወንጀል አይደለም! ያለውን ማክበር ነው።

ለነኝህ ሁሉ መሠረታቸው፤ የግለሰብ የተፈጥሮና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር ነው። ለተፈጸሙት በደሎች ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ ነው። የተደረጉ ስህተቶችን ማስተካከል ነው። ወደፊት ለምንሄድበት፤ ግልጽ ራዕይ ማስቀመጥና መንገድ ጠራጊ መሆን ነው።

ለዚህ ሁሉ ደግሞ መጀመሪያው፤ ሕገ-መንግሥቱን መቀየር ነው። አንዳንድ ሰዎች፤ ሕገ-መንግሥቱን ለመቀየር፤ መጀመሪያ ምርጫ መካሄድ አለበት ብለው ያምናሉ። ይህ ትክክል አይደለም። ስህተቱ ለውጡን ካለመረዳት ይመነጫል። ለውጡን ፈልጎ የተነሳው ሕዝብኮ፤ መሪውን ድርጅት ብቻ ሳይሆን፤ ይህ ድርጅት ያስቀመጠውን ሕገ-መንግሥትና የአገዛዝ ሂደት በሙሉ ነው፤ “አልፈልግህም!” ያለው። ታዲያ በምን ሂሳብ ነው፤ እንዲከሰት የምንፈልገውን ለውጥ፤ እንዲለወጥ በምንፈልገው ድርጅት መመዘኛ ሂሳብ የምናስቀምጠው! ትክክለኛ ለውጥ የሚመዘነው፤ ለውጡን በሚፈልገው ሕዝብ ግንዛቤ እንጂ፤ እንዲለወጥ በተፈለገው ድርጅት ሚዛን አይደለም። ምርጫ መካሄዱ ለውጥ መምጣቱን አይወስንም፣ አይናገርም፣ አያረጋግጥም። ምርጫዎች በደርግም ሆነ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ተካሂደዋል። ይህ ትርጉም አልነበረውም። አሁንም ምርጫ መካሄዱ ምንም አይናገርም፤ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ከላይ እንዳስቀመጥኩት፤ ያለው መንግሥት ለጊዜው መቀጠል ያለበት፤ ምርጫ እንዲያካሂድ ወይንም ምርጫ እስኪያካሂድ አይደለም። ሀገር ያለ መንግሥት እንዳይሆን ነው። ይህ አካል በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ፤ መንግሥታዊ ተግባሮችን ማካሄድ አለበት። ለውጡን አሻጋሪ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። በዚህ ላይ ጥይቄ አይኖርም። ያለ አማራጭ ግን፤ ሽግግሩን ይህ አካል፤ ከሌሎች ጋር በመሆን ሊተገብረው ይገባል። ትናንት ሕወሓት፣ ቀጥሎ ኢሕአዴግ፣ ዛሬ ደግሞ ብልፅግና ብሎ ስሙን ስለጠራ፤ ለውጥ አደረገ ማለት አይደለም። በፓርቲያቸውና በሀገራችን መንግሥት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። በድጋሜ፤ በመንግሥትነት ብልፅግና ለጊዜው ይቀጥል ሲባል፤ ያለ ብልፅግና ኢትዮጵያ አትኖርም! በሚል ሂሳብ አይደለም። ወደ ጀመርኩት የፖለቲካ ማንነት ልመለስ።

የፖለቲካ ማንነትን ትርጉም ተለትሎ የሚመጣው ውጤት ምንድን ነው?

የፖለቲካ ማንነትን ከተረጎምን፤ በሀገር የፖለቲካ መድረክ ዙሪያ በሚደረጉ ክንውኖች ላይ፤ ግለሰቦች የሚያደርጉት ተሳትፎ፤ በዚህ ትርጉም መሠረት እንደሚከናወን ማመን አለብን። ለዚህ ነው፤ የፖለቲካ ማንነት ትርጉም ወሳኝ ሚና የሚጫወተው። ሥልጣን ጥመኛ ጥቂት ልሂቃን፤ ይሄን የፖለቲካ ማንነት ትርጉም በጉያቸው ይሸጉጡታል። ምክንያቱም፤ በጀርባው ያለውን የሥልጣን ፍለጋ ሩጫቸውን በድብቅ ያቀላጥፍላቸዋልና! ግለሰቦች በሀገራቸው ነፃ ሆነው፣ በፈለጉት መንገድ፣ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን በማያገል ሂደት፣ በአስተሳሰብ ከሚስማሟቸው ግለሰቦች ጋር፣ አብረው ሊያራምዷቸው የሚፈልጓቸውን አጀንዳዎች ነድፈው ቢሳተፉ፤ የሌሎችን አጀንዳ ሳይሆን፤ የራሳቸውን አጀንዳ ያራምዳሉ። በዚህ የግለሰብ ተሳትፏቸው፤ አንድም ሀገራዊ ግዴታቸውን ያሟላሉ፤ ሌላም የፈለጉት እንዲከሰት ጥረት ያደርጋሉ። ከግለሰብ ወጥቶ፤ አንተ የተወለድከው እዚህ ስለሆነ፤ ከኛ መንጋ ጋር ነው አሰላለፍህ! አንቺ ይሄን ቋንቋ ስለምትናገሪ፤ መግባት ያለብሽ እዚህ የኛ መንጋ ድርጅት ነው! የሚል ሩጫ፤ የሌሎችን አጀንዳ ማራመጃ ነው። ለዚህ ነው ሥልጣን ፈላጊ ልሂቃን የግለሰብ መብትን አንኳሰው የመንጋን መብት ቅድሚያ የሚሠጡት።

በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ክፍል የተቀመጠው፤ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ፣ የሚል የመንጋ የአስተዳደር ክፍፍልን ከነ ሕገ-መንግሥቱ ወርሶ ነው። ይህ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አጀንዳ ነው። ይሄን ተቀብሎ ልቀጥል ካለ፤ የሚልም ይመስለኛል፤ ከነበረው የሚለይበት አይታየኝም። በነገራችን ላይ፤ ብልፅግና አንድ ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሊሆን አይችልም። ላስረዳ፤ የየክልሉ የብልፅግና ፓርቲዎች፤ በመካከላቸው አንድ ሊያደርጋቸው የሚችል ገዥ ጉዳይ የላቸውም። የሚገናኙት በጥቅም ጉዳይ ነው! ለዚያውም የሀገሪቱን ባጀት በመከፋፈል ላይ! እናም ይህ የጥቅም ክፍፍል፤ ፉክክርን እንጂ የአንድ አካል አብሮነትን አያመላክትም። ይህ በመሆኑ፤ የሶማሌው የብልፅግና አባል ኦሮሚያ ውስጥ፣ የወላይታው የብልፅግና አባል ሲዳማ ውስጥ፣ አባል ሊሆንና ሊወዳደር አይችልም። እያንዳንዱ የብልፅግና ፓርቲ፤ ራሱን የቻለ ከመሆኑ ሌላ፤ ክልሉን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠርና ለራሱ ብቻ ማድረግ ነው ዋና ተግባሩ። እያንዳንዱ የብልፅግና ፓርቲና ክልሉ፤ የራሱ ቋንቋ፣ የራሱ የክልሉ ኃይል፣ ሙሉ መንግሥታዊ መዋቅር፣ የራሱ ሰንደቅ ዓላማ፣ የራሱ ፖሊስ፣ የራሱ የዜና አውታር፣ ባጠቃላይ ራሱን የቻለ መንግሥትነት አለው። የዚህ ሁሉ ድምር፤ ባንድ በኩል አምባገነንነት እንዲከተል ሲያመቻች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገራችንን እንድትቆራረስ የሚጋብዝ ነው። እናም የተያዘው መንገድ በቀላሉ፤ ውሃ ቢወግጡት እምቡጭ! ሲሆን፤ ሲከር ደግሞ ከነበረው የባሰ አደጋ ነው። ለውጡ ግቡን አልመታም ብቻ ሳይሆን፤ ለውጡ አልተጀመረም። ይልቁንም የከፋ የወደፊት አዘጋጅቶልናል። አማራጭ ማጣታችን ሌላው ጉዳይ ነው። ከብልፅግና ፓርቲ ሌላ ቢፈለግ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ነው ያሉት! የባሰ አታምጣ! ማለት የሚያዋጣ ዕቅድ አይደለም። ስጋቴ፤ “ሁኔታው አሳስቦኛል!”” በሚል ሂሳብ፤ አንድ መሪ፤ የአምባገነን አስተዳደር እንዲመሠርት እያመቻቸንለት ስለሆነ፤ ይህ መከተሉ ሀቅ እየሆነ መምጣቱ ነው። ረጋ ብላችሁ አስቡበት።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop