የማንነት እና ወሰን ማስከበር ነገር !!! – ማላጅ

በአገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎች ከሩብ ክፈለ ዘመን እና ከዚያ በላይ ከሚሆን ጊዜ ጀምሮ የድንበር እና ማንነት ጥያቄዎች በተለያየ መልኩ ሲጠየቁ ቢቆዩም አስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ወቅታዊ እና ህጋዊ መፍትሄም ሆነ ምላሽ ሳያገኙ በጥያቄነት በመኖራቸዉ ከዚህ ጋር ተየያዥ የሆኑ ችግሮች ተደጋግመዉ ሲስተዋሉ ይታያል ፡፡

ይህ ከሁለት አሰርተ ዓመታት አስቀድሞ በኢትዮጵያ የክልል እና የአካባቢ መስተዳደሮች አወቃቀር ከጅምሩ በችግር ተወልዶ በብዙ አለመግባባት እና ተግዳሮት ትብታብ የታነቀ ከመሆኑ በላይ የጉዳዩ ባለቤት የሆነዉ ህዝብ በግልጽ እና በቀጥታ ያልተሳተፈበት አደረጃጀት ስለመሆኑ ዛሬም ላይ ጥያቄዉ በጥያቄ እየተከተለ ሰሚ ያጣ ጮኸት ሆኖ አገሪቷን ለአላስፈላጊ የማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ቀዉስ እተያስከተለ ይገኛል ፡፡

በዚህ የማንነት እና ወሰን ጉዳይ አስመልክቶ በዜጎች ላይ ለረጅም ዓመታት እየደረሰ ያለዉ አለመረጋጋት፣ መፈናቀል እና ስደት፣ ድህነት እና ሞት በአገራዊ አንድነት እና አብሮነት ያሳደረዉ ተፅዕኖ የምርታማነት መቀነስ፣ የስራ አጥ ቁጥር መጨመር ፣ የምጣኔ ሀብት ድቀት እና በአገር ላይ ሠርቶ የመኖር ፍላጎትን በእጅጉ ሲፈታተን የነበር እና በገሀድ የታየ እና የሚታይ ነዉ ፡፡

ይህም በብሄራዊ ደረጃ የሚፈለገዉን እና የሚጠበቀዉን ሁለንተናዊ ዕድገት እና ብልጽግና ለማምጣት ትልቅ ደንቀራ እንደመሆኑ በድንበር እና በማንነት ጉዳይ ላይ የሚነሱ ብሶቶች እና ሮሮዎች በተለያየ ጊዜ ለሚመለከተዉ የመንግት አካል (የፌደሬሽን ምክር ቤት) የመቅረባቸዉ ጉዳይ የሚታወቅ ቢሆንም ለእነዚህ ጮኸቶች ሰሚ መኖሩ አጠያያቂ እንደሆነ ይገኛል ፡፡

በድንበር እና ማንነት ጉዳይ ምላሽ ማዘግየት በልዩ ዕይታ ወቅታዊ ዉሳኔ አለመኖር ወይም መዘግየት በአገር አንድነት እና ህዝቦች ጥቅም ላይ ሊያስከትል የሚችለዉን ዉጤት አገሪቷ ከነበረችበት እና አሁን ከምትገኝበት እዉነታ እና ወቅት ጋር በማስተሳሰር ተገቢዉን ትኩረት እና ጥረት ሊደረግ ቢችል እና ይህ ባይሆን ግን አገሪቷን እና ህዝቧን አስካሁን ለሚታዩት ተደጋጋሚ ችግሮች ከማጋለጡም በላይ በህዝብ አንድነት እና በአገር በሉዓላዊነት ላይ ለሚደረገዉ ብሄራዊ ጥረትም ሳንካ እንዳይሆን ሳይመሽ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያዉያን አንድነት-ለወያኔ ግብዐተ መሬት--ይገረም አለሙ

በተለይም በሰሜን ፣ በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የአገሪቱ የግዛት /አካባቢ ወሰን በየጊዜዉ እንደ ክፉ ደዌ በየጊዜዉ እያመረቀዘ እና እየመረዘ ያለዉ ችግር ከማንነት እና ከድንበር ወሰን ማስከበር ጥያቄ ጋር የሚነሳ እና ይህም ለግጭት እና መፈናቀል ፣ አለመረጋጋት እና ስደት(የአገር ዉስጥ /የዉጭ ) በአካባቢ ኗሪ ዜጎች ላይ ብቻ ሳይወሰን በአገሪቱ የህዝብ አስተዳደር ስርዓት/ፖለቲካ ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መስተጋብር ረገድ የሚያስከትለዉ አፍራሽ ሚና በቀላል ማይታይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት የአገራችን አካባቢዎች ለአብነት ለመጥቀስም ከአዲስ አበባ በአማካኝ 500. ኪ/ሜትር ረቀት ላይ የሚገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የግብርና ምርት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ የንግድ እና ገበያ ማዕከል አቅም ያላቸዉ የዞን መስተዳደሮች በተለይም ቤንች ማጅ እና ሸካ ዞን ባላቸዉ የተፈጥሮ ሃብት ክምችት ለብሄራዊ እና አካባቢ ህዝብ እና መንግስት ከሚኖራቸዉ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ ፣ የግብርና ምርት አቅም ፣ የተፈጥሮ ሀብት(የከርሰ ምድር እና ገጸ ምድር ) በተጨማሪ ያላቸዉ ተፈጥሯዊ መስህብ በተገቢዉ መንገድ በአስተማማኝ ሠላም እና ፀጥታ ቢሰራበት ለአገር ዉስጥ እና ዓለም ዓቀፍ ገበያ ሊዉል የሚችል ምርት ለማቅረብ የሚያስችል ሰፊ ዕድል ያለበት አካባቢ ነዉ ፡፡

ነገር ግን ስር በሰደደ እና እየቆየ በሚያገርሽ የድንበር እና የማንነት ጥያቄ ምክነያት አገሪቷም ሆነ የአካባቢ ኗሪ ህዝብ ከነዚህ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት እና የግብርና ምርት የሚፈለገዉን ያህል ተጠቃሚ ነበሩ ማለት አይቻለም ፡፡

በተለይም በሸካ ዞን መስተዳደር ስር የምትገኘዉ የየኪ ወረዳ መቀመጫ / ርዕሰ ከተማ የሆነችዉ ቴፒ በዉስጧ እና ዙሪያዋን የሚኖሩ ኢትዮጵያን እርስ በርስ ተግባብተዉ ፣ ተዛምደዉ እና በጋብቻ ተሳስረዉ መኖር ከጀመሩት ወይም ኢትዮጵያ እንደ አገር ከታወቅችበት እና ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ የሚቆጠር ታሪክ ያላቸዉ ህዝቦች ቢሆኑም በአገራችን የክልል አስተዳደር መዋቅር ስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ አስካሁን ጊዜ ድረስ በዚህ የክልል እና አካባቢ አደረጃጀት ጋር ቴይዞ በመጣ የማንነት እና ድንበር ወሰን ችግር እና ጥያቄ የተነሳ በከተማዋ እና አካባቢዋ በሠላም ወጥቶ ሠርቶ መኖርም ሆነ ዉሉ መግባት እና አዳር እንግዳ ነገር ከሆነ ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የንፁሓን ደም ይጮሃል! - በላይነህ አባተ

ይህች ነባር እና ደማቅ የግብርና ምርት እና ገበያ ማዕከል የሆነች ቴፒ ከተማ የአሁን መጠሪያዋን ከቀደመ እና ጥንታዊ ስሟ “ ታፓ ” እንዳገኘች ከአፈ ታረክ ከሰማንዉ እንገነዘባለን ፡፡

ይኸዉ ወደምት ስሟ “ታፓ ” በድሮ ዘመን በአካባቢ ነባር መስራች እና ኗሪ ከነበሩ የሸኮ ማዣንግር ጎሳ (ቋንቋ) ተናጋሪ ከነበሩ አባት መጠሪያ ስም ወይም ባላባት ነበር ይባላል ፡፡

ከረጅም ዘመናት ጀምሮ በከተማዋ የሚገኙ ኗሪዎቿ የብዙ ባህል እና ቋንቋ ባለቤቶች ናቸዉ ፡፡ በከተማዋ ኗሪዎች ከሚነገሩ ቋንቋወችም ሸኮ ፣ ማዣንግር፣ቤንች፣ አማርኛ ፣ ኦሮሞኛ ፣ሸክኛ ከብዙ ጥቂቶች ናቸዉ ፡፡

ሆኖም በተለይ በግዛት ፣ወሰን እና ማንነት መሰረት እና መነሻ ሰበብ በተለይም ከ 1988 .ዓ. ም. ጀምሮ አስካሁን ጊዜ ድረስ የግጭት እና የሞት ስጋት የማይለያት ከተማ ሆና መዝለቋ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ፣ ምቹ እና ከፍተኛ የንግድ ማእከልነት እና ሠፊ የገበያ መዳረሻነት አቅም በመጠቀም አገር እና ህዝብ መጠቀም የሚገባቸዉን ያህል ትሩፋት ማግኘት አልቻሉም ማለት ይቻላል ፡፡

አካባቢዉ በአገር አቀፍ ደረጃም ቢሆን ከፍተኛ እና ቀዳሚ በሚባል የልምላሜ ፣መጠነ ሠፊ የግብርና ምርት መገኛ፣ ትልቅ የገበያ ቦታ እንዲዉም “የኢትዮጵያ ታይዋን ” መሆን የሚያስችል የተፈጥሮ ሃብት እና መልካምድር አቀማመጥ ያላት የደቡብ ምዕራብ ኢትጵያ የአስራ ሶስት ወራት የፀሃይ ብርሃን እና አረንጓዴ ምድር (ጃኖ ለበስ ) የደቡብ ኢትዮጵያ ፈርጥ ከተማ ናት ፡፡

ነገር ግን ከላይ በተጠቀሱት የዞን መስተዳደሮች እና በየኪ ወረዳ አካባቢ ለረጅም ዓመታት እያሳለሱ የሚነሱ የድንበር እና የማንነት ጥያቄወች በሚመለከተዉ አካል በቂ እና ወቅታዊ ትኩረት ቢያገኙ አካባቢዉን ከተጨማሪ ጥፋት እና ሞት ለመታደግ በማስቻል ለልማት እና ዕድገት የላቀ ዕድል ያስገኛል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይቅርታ የማስጠየቅ ሱስ - ይሄይስ አእምሮ

በርግጥ ለዚህ አካባቢ ዘላቂ መፍትሄ ለማስፈን ከ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በክልል እና አገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ችግሩን ከስሩ በማጥራት ለመፍታት የተሄደበት መንገድ ግን ትክክለኛ እና የነገሩን ስረ መሰረት ያላገናዘበ እንደነበር ከ20 ዓመት በላይ መልክ እና ቅርጽ እየቀያየረ ፣በመጠን እና ዓይነት እየበዛ ስለመሆኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ዕዉነታወች በቂ ምልክቶች ሲሆኑ የቴፒ እና አካባቢዋ ትኩሳትም ለዓመታት እየዞረ የመጣ እነገር ግን ያለዉን ቅራኔ ለማስቀረት ከልብ እና ከአገራዊ አንድነት ስሜት መነሳት ካለ የሚታዩ ችግሮችን በአችር ጊዜ እና በቀላል ዋጋ መቅረፍ የሚቻል እንደሆነ ማናችንም የምንረዳዉ ሀቅ አለ ፡፡

በመዐረሻም የማንነት እና ድንበር ወሰን ጥያቄ ፡-

፩) ለህብረ ብሄራዊ አንድነት እና ለአገር ሉዓላዊነት የሚኖረዉ ፋይዳ ከፍተኛ አስከሆነ ድረስ ፣

፪) ለአገር እና ዜጎች የጋራ ዕድገት እና ብልፅግና አዎንታዊ ዉጤት አስካስገኘ ጊዜ ድረስ ፣

ሳይዉል ሳያድር የዕሳካሁኑ የዜጎች እና የአገሪቷ መጎሳቆል ቀርቶ እንኝህን መፃኢ የህዝብ እና አገር ሁለንተናዊ እንደምታዎች ከግምት በማስገባት እና በመመልከት የማንነት እና ወሰን ጉዳይ ወቅታዊ እና ተገቢ ምላሽ የመስጠት ትኩረት ቢሰጥበት አገሪቷን እና ህዝቧን ከዳግም ጉስቁልና እና ብክነት በመታደግ ለእድገት እና ስልጣኔ የሚደረገዉን አገራዊ ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና ተጨባጭ ለዉጥ ለማስፈን የዘመናችን አማራጭ የሌለዉ ብቸኛ እና ወቅታዊ አማራጭ እንደሆነ የሚያስማማ ነዉ ፡፡

“ምን ጊዜም እናት አገር ” !!!

ማላጅ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.