ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ለፓርቲ አመራሮች ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ

አዲስ አበባ፡- ዴሞክራሲን ከህግ የበላይነትና ከመደማመጥ ውጪ ሊመጣ ስለማይችል ፓርቲዎች በተቻለ መጠን ብንከባባር፣ ብንቻቻል፣ ብንደማመጥና የሰውን ሃሳብ ብናከብር ችግሮቻችንን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንፈታለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ በወቅታዊ የአገራዊ ጉዳዮችና በቀጣይ የውይይት አቅጣጫዎች ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ፤ዴሞክራሲን ከህግ የበላይነትና መደማማጥ ውጪ ልናመጣው ስለማንችል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጥላቻን ፖለቲካና ትርክትን፤ በሃሳብ የበላይነት ያልተንተራሰ ፖለቲካን እና ጭፍን ዋልታ ረገጥነትን በመተው በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት አለብን ብለዋል፡፡

ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ ሰላምና የህዝብ ሉዓላዊነት ለድርድር ማቅረብ የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ምንም ይሁን ማን ሰላም ካደፈረሰ ይጠየቅ ብንል፤ የሴራ ፖለቲካ ብንተው፣ ችግሮች ካሉ በውይይት መፍታት ቢቻል በኢትዮጵያ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

እስከአሁን በአገሪቱ ግጭትን የሚያቀናብሩ ሰዎች እንኳን እነሱ ቀርቶ ወንድሞቻቸው ቆስለው፣ ልጆቻቸው ታስረው እንደማያውቁ ገልጸው፤ የድሃውን ልጅ ማባለት መብት እነሱ ግን ሲነኩ ስህተት የሚሆንበት አካሄድ እንደማያዋጣም አስገዝበዋል።

አገር እያፈረሱና ህዝብን ከህዝብ እያባሉ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር አይሠራም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነ ፕሌ፣ እነ ማራዶና እነ ከሜሲ ስለሆንኩ ኳሷን በእጄም ባስገባ ማኖ አይባልም።ማኖ የሚባለው ለመንደር ተጫዋች ብቻ ነው የሚል ፖለቲካ አይሠራም፤ ህጉ ሁሉንም እኩል የሚዳኝ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ሃሳባችንን ሸጠን በምርጫ ማሸነፍ ነው የምንፈልገው ከሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየትና ለመደጋገፍ፣ ችግሮችም ካሉ ለመፍታት ፍላጎት እንዳለው አመልክተው፣ በአንጻሩ ሲመቻቸው ሰላማዊ መንገድን ሲያሻቸው ሁከትን የሚከተሉ ፓርቲዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። በሰላማዊ መድረኩ ቢሳተፉ አዋጪ እንደሚሆንም መክረዋል።

በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየተገደለና ሀብቱ እየጠፋ ያለው በዋናነት እንታገልለታለን በሚሉት ህዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ህዝቡን እያስገደልን ስለፖለቲካ ከምናወራ ቢያንስ በሃሳብ እየተከራከርን ሰው ሳይሞት፣ ንብረት ሳይወድም ሃሳባችሁን ሸጣችሁ ብትመረጡ መልካም ነው፤ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ ወንጀል ከሠራ እንደ ቀደመው ጨለማ ቤት አናስርም፣ ጥፍር አንነቅልም፣ እግር አንቆርጥም ግን በህግ ተጠያቂነት ከመሆን አያመልጥም ብለዋል። ካለአግባብ የታሰሩ ሰዎች ካሉ በህግ ስርዓቱ አግባብ እንደሚታይ ገልጸው፣ የህግ የበላይነት ካልተከበረ ግን ዴሞክራሲን ማምጣት አስቸጋሪ እንደሚሆን አብራርተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና ተወካዮች በበኩላቸው በአገራችን ውስጥ እንደፈለግን ወጥተን መግባት የምንችለው ሰላም ሲኖር መሆኑን ገልጸው፤ ከአገር ውስጥም ሆነ ውጭ የሚሸረብ ሴራ ካለ በጋራ ሆነን እናከሽፋለን፤ እንታገላለን ብለዋል፡፡

እንደ ፓርቲዎቹ ገለጻ፤ በሁከት፣ በብጥብጥና ግጭት ዴሞክራሲዊ ስርዓት መፍጠር አይቻልም።ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላም ጉዳይ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራትና መዘመር አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

መንግሥት በበኩሉ በውስጡ የተሰገሰጉ ጽንፈኛ አመራሮች ሀይ ቢላቸው፤ የህግ የበላይነትን ማስከበርና የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ላይ በትኩረት እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ለፓርቲ አመራሮች ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽም፣ ፓርቲዎች በተቋም ግንባታ፣ ህጋዊ ያልሆኑ አሠራሮች በማስተካከልና ወንጀል በማጋለጥ ከመንግሥት ጋር ተባብረው ከሠሩና መረጃ በመስጠት ካገዙ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ሁሉ ፈር እየያዙ ይሄዳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ በአገሪቱ በተከሰተው የጸጥታ ችግር በተያያዘ የተጠረጠሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራርና አባላት ብቻ የታሰሩ አለመሆናቸውን አውስተው በሁከቱ የተጠረጠሩ በርካታ የብልጽግና ፓርቲ አባላትና አመራሮች ጭምር መታሰራቸውን ጠቁመዋል፡፡

“ሃሳብ አይደለም ሰው ታርዶና ንብረት ወድሞ እያየን ነው፤ ይህን የሚያደረገው በብልጽግና ፓርቲና በእናንተ ፓርቲ ውስጥ የተሰገሰገ ሌባ ነው።የእኛንም ሆነ የእናንተን ታርጋ አይነካ ካልን በኢትዮጵያ የምንመኘውን ሰላም እንዴት ልናመጣ እንችላለን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

“እኔ ጋር ሽማግሌ አደራጅቶ በመላክ ጉዳዩን ለመፍታት የምታስቡ ሰዎች ቅንነታችሁን ባደንቅም ተጠርጠረው በህግ ቁጥጥር ስር ያሉትን ሰዎች የህግ ስርዓቱ ነፃ ወይም ፍርደኛ ያደርጋቸዋል እንጂ እኔ እስራቸውን በአንድ ቀን መጨመርም ሆነ መቀነስም አልችልም ብለዋል፡፡

በህግ ቁጥጥር ስር ያሉትን ሰዎች ሰብዓዊ መብት ከማክበርና ከአያያዝ ጋር ለሚነሱ ጥያቄዎች መንግሥት የአገሪቷ አቅም በፈቀደ መጠን እስር ቤቱ ንጹሕ እንዲሆንና የሚያስፈልጋቸው እንዲሟላ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ከአማራ ወይም ከኤርትራ አልያም  ከፌዴራል መንግሥት ግጭት እንዲያነሳ በጣም የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ እንዲሁ ከምንሸነፍ በጉልበት ተመታን በሚል መጨረሻችን ይደምደም በሚል ሃሳብ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ አመልክተዋል። የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር ውጊያ የመክፈት ፍላጎት የለውምም ብለዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ የጥይት ድምፅ መስማት ይበቃዋል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለትግራይ ህዝብ ክብርና ለዚህ እምነት ሲባል በርካታ ችግሮች ሲያጋጥሙ በዝምታ ሲታለፉ እንደቆዩ አውስተዋል።

ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸው፣ ቋንቋቸውና ማንነታቸው ተከብሮ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነው የምንሠራው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ስም መጥራት የማይፈልጉ አካላት እነሱ ይጠፋሉ እንጂ እሷ ትቀጥላለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ በብሄራዊ መግባባት፣ በማንነትና ወሰን ጉዳዮች፣ በተቋማት ግንባታና ሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች ለመወያየትም ተስማምተዋል።የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን)፣ የብልጸግና ፓርቲ፤ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ እና ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ፤ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ ላይ የመነሻ መወያያ ጹሑፍ እንዲያቀርቡ ተመርጠዋል፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2012

ጌትነት ምህረቴ

2 Comments

  1. በንፁሀን ዜጎች ላይ የተፈፀመው ጄኖሳይድ /በዘር በሀይማኖት ላይ ያተኮረ ጭፍጨፋ ጠ ሚኒሰቴሩ አደባብሶ ለማለፍ የሚያደርገው መንፈራገጥ ከየትም አያደርስም። ወንጀሉ በሚገባ ስሙ ተጠርቶ የሚሰፈልገው ህጌዊ ርምጃ መወሰድ አለበት።

  2. ዛሬ በኢትዮጵያ አምላክ ቸርነት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነው ዶ/ር አብይ አሁንም መልካሙን መንገድ እግዚአብሔር ያሳየው፣ እንደ ስግብግብ ስልጣን ፈላጊ የብልፅግናና የተቃዋሚ ፓርቲ ሌቦች ፍላጎት ቢሆንማ ይሄኔ እርስ በርስ ቱላልቀን ነበር።
    * አብይ በርታ፣ የኢትዮጵያ ን ዋነኛ ጠላቶች ወያኔና፣ኦነግን ከኦሮሞና የትግራይ ህዝብ ነጥለህ ምታ።
    *ዘረኛ አስተዳደርና አከላለል ከሀገራችን ከኢትዮጵያ ይጥፋ!
    *ሕገ መንግስቱ መልካም ነገሩ ተጠብቆ የኢትዮጵያን ህዝብ እንድነትና እኩልነት ባስጠበቀ መልኩ፣ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ውይይትና ይሁንታ ፣ይሻሻል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.