የአባቶች ምክር – ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን

07/01/2020

የእስራኤል ጉባኤ ወደ ሮብዓም መጥተው “አባትህ ከባድ ቀንበር ጫነብን፣ አንተ ግን  አባትህ የጫነብንን ከባድ ቀንበር ብታቀልልን እንገዛልሃልን” አሉት፡፡የሮብዓም አማካሪ ሽማግሌዎችም  “ዛሬ አንተ ለዚህ ሕዝብ አገልጋይ ብትሆን፣ ብትገዛለትና ደስ የሚያሰኝ መልስ ብትሰጠው፣ይህ ሕዝብ ምን ጊዜም ያንተ አገልጋይ ይሆናል“አሉት።ሮብዓም ግን ከሽማግሌዎቹ ምክር ይልቅ የጓደኞቹን  ምክር ሰማ፣ “ከአባቴ ይልቅ አገዛዜን አከብድባችኋለሁ” በማለትም የሕዝብ ተወካዮችን አስፈራርቶ መለሰላቸው።በዚህም ድርጊቱ ሕዝቡን አስቆጥቶ፣ ከነገደ እስራኤል በአስሩ ላይ የንግሥና ሥልጣኑን አጣ።

ይህ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ነው።ይሁንና የሰው ልጆች ሁሉ ፍላጎት  ተመሣሣይ ነው። አገልጋይ የሆነና መብቱን አክብሮ፣ በእኩልነት የሚያስተዳድረውን መሪ ነው የሚፈልገው።ሕዝባችንም እንዲሁ ጥያቄዎቹን ሰምቶ የሚፈታና ጭቆናዎችን አስወግዶ፣ በሰላምና በእኩልነት አስተባብሮ ወደ ብልጽግና ጎዳና የሚመራውን ነው የሚፈልገው

ከዚሁ አንጻር የብሔርና የክልል ሥልጣን ጥያቄን ብንመለከት፣ ብሔር በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ሥርዓት፣ በብሔረስቦች ውህደት የሚደረስበት የማኅበረሰብ የድገት ደርጃ ነው።የአገራችን ኢኮኖሚ በፊውዳሊዝም በመቀጨጩ፣ የመገናኛ አውታረ መረብ ባለ መዘርጋቱ፣ ከሕዝባችን መካከል ወደ ብሔር እድገት ደረጃ የደረሰ አንድም የለም።

ይህንኑ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ በምሳሌነት ትግራይን ብንወስድ፣ ካፒታሊዝም ዳብሮ የቅኝ ግዛት መስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ፣ትግራይ በቅኝ ግዛትም ይሁን፣ በአስተዳደር በደል፣ ከማዕከላዊ የኢትዮጵያ መንግሥት ግዛት ተለይታ፣ የራሷ የሆነ መንግሥትና ግዛት ኖሯት አያውቅም። ስለዚህም ትግራይን ከተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት የሚለያት፣የራሷ ወሰን ስለሌላት የብሔር መለኪያን አታሟላም። እንዲሁም ትግራይ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ብሔረሰቦች፣የተለያየ እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች መኖሪያ ስለሆነች ብሔር የሚያሰኘውን መለኪያ አታሟላም።

ይሁንና ብሔር አለመሆን፣ በመብት ላይ ለውጥ የለውም፣ ብሔሮች ያሉአቸውን መብት ሁሉ ብሔረሰቦችም ይኖሯቸዋል።ነገር ግን የራስን እድል በራስ የመወሰንና እስከ መገንጠል የሚደርሰው መብት የሚረጋገጠው፣ከቅኝ ግዛት ነጻ ለሚወጡት መሆኑን ለማመልከት ነው እንጂ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕገ-መንግስቱን ለማሻሻል ለሚደረገው ሕዝባዊ ውይይት ይጠቅማሉ የምንላቸው ሐሳቦች (ከተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን)

በሌላውም በኩል በደቡብ ሕዝቦች ክልል የሚገኙ ዞኖች በክልል የመደራጀት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው። ዞኖች የክልል ጥያቄ እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸው፣ የሐረሪ አደረጃጀት ነው።ሐረሪ  የተለያዩ ሕዝቦች በጋራ የሚኖሩበት ከተማ መሆኗ እየታወቀ፣በክልል እርከን ተደራጅታለች። ስለዚህም ሌሎች ዞኖችም በክልል እርከን የመደራጀት ጥያቄ ማቅረባቸው ተገቢ ነው። የአማራና  የኦሮሚያ  ዞኖችም በክልል  እርከን መደራጀት ይሻሉ።በመሆኑም አንድ ወጥ የማስተካከያ እርጃ መውሰድ የሚገባው፣ የፌድራል መንግሥቱ ነው።

ሌላው ስህተት ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ ቋንቋ ስለ ተናገሩ የአንድ ብሔር አባል የሆኑ ይመስላቸዋል።ነገር ግን የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ አባል ለመሆን በአንድ አገር፣ በኩታ ገጠም፣ በኢኮኖሚ ተሳስሮ አብሮ መኖርን ይጠይቃል።

ለምሳሌ ያህልም አፋን ኦሮሞ የሚናገሩ ሰዎች ከአገራችን ውጪ፣ በኬኒያ፣በሱማሊያና በታንዛኒያ ይኖራሉ፣ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በኢኮኖሚ የሚያስተሳስራችው አንድም ነገር የለም፣ስለዚህም የኦሮሞ ብሔረሰብ አባል አይደሉም።

እንዲሁም አማርኛ የሚናገሩ ብዙዎች አሉ፣በኢኮኖሚ ከአማራ ክልል ጋር ካልተሳሰሩ በቀር፣ አማርኛ ቋንቋ መናገራቸው ብቻ የአማራ ብሔረሰብ አባል አያደርጋቸውም።

ይህን ያህል ስለ ብሔር ብሔረሰብ ከተመለከትን አሁን ደግሞ  በአገራችን የብሔር ጥያቄን ያወሳሰበውን ችግር  እንመለከታለን።    በአገራችን ሠራተኛው እንደ መደብ ጠንክሮ በመውጣት የመሪነትን ሚና ሊጫወት አልቻለም። ስለሆነም አገሪቱን ሲመራ የቆየው ምሁሩ፣ የብሔራዊ ከበርቴ ወገን ነው።ብሔራዊ ከበርቴው ደግሞ ለብሔሩ መወገኑ አይቀሬ ነው፣እንደ ጎበነ ዳጪ ብሔሩን የሸጠ ካልሆነ በቀር።ስለዚህም ተግባብተውና ተስማምተው ከኅብረተሰቡ መካከል ያለውን ቅራኔ ሊፈቱ አልቻሉም።

ሌላው የመስመር ልዩነት ነው።በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣን የጨበጠው  ኢሕአዴግ የሚከተለው  የአቢዮታዊ ዲሞክራሲ መስመርን ነበር።ይህ መስመር ደግሞ የአቢዮታዊ ፓርቲ አመራርን ይጠይቃል።ኢሕአዴግ ደግም በስም እንጂ በተግባሩ አቢዮታዊ ፓርቲ ባለመሆኑ ነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ አመራር ያጣው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የ‘ፍም እሳቶች’ እምቢ ባይነትና ጽናት የሚያኮራን ነው

ለዚህ ነው በአገራችን ማዕከላዊነት ላልቶ አንጃነት የበዛው። የሥልጣን ሽሚያ፣የመሬት ወረራ፣ ጉቦና ምዝበራ ተንሰራፍቶ፣  ሕዝባችን እርስ በርሱ እንዳይስማማ ያደረገው።

እንግዲህ አገር በጥላቻና በቅራኔ አትገነባም። ጥላቻ ዘርቶ ፍቅርን ያጨደ የለም።የሕዝቡን የልብ ትርታ ሳያደምጡ ሕዝቡን አሳምኖ ማስከተል አይቻልም።በመሆኑም ከሮብዓም ስህተት መማሩ ይገባል።

አሁኑ በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የከረረው   የመንግሥት ሥልጣን ጥያቄ ነው። እርሱ በድርድር ሊፈታ ይገባል።ሰሞኑን በአጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በሚመለከት፣ የጸጥታ ከፍሉ ቀድሞ መረጃ ደርሶታል፣ምንጩንም ያውቀዋል።የጸጥታው ክፍል ተግባሩን ባለመወጣቱ ነው፣የአጫሉ ደም የፈሰሰው።ታዲያ በዚህም ድርጊት ተበሳጭቶ በቁጣ የተነሳውን ሕዝብ ከማረጋጋት ፈንታ፣ መሪዎቹን በማሰር ሕዝቡን በይበልጥ ማበሳጨት ለምን አስፈለገ? ንቀት ካልሆነ በስተቀር።

ስለዚህም በፖለቲካ ጉዳይ የፖሊስ ጣልቃ ገብነት፣ቆመጥ፣ እስራትና ግድያ  የሕዝቡን ቁጣ ያባብሳል። ይልቅስ የህዝቡን ጥያቄ አክብሮ ለሐውልቱ ተስማሚ ስፍራ ቢዘጋጅ ቁጣን ያበርዳል፣ ለሰላም በር ይከፍታል።

በተረፈ፣ ሕዝብን ከሚያስቆጣ ደምንም ከሚያፋስስ  ተግባር በመራቅ፣ በትዕግሥት ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገር፣ ችግሩን በሰላም መፍታት ይገባል።የብሔር ብሔረሰብ ጉዳይ ከውስጥም ክውጭም መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም  ከመቼውም ይልቅ ዛሬ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአባገዳዎችና የአገር ሽምግሌዎች ፈጣን ትብብር ያስፈልጋል።የአባቶች ምክርና ተግሳጽም፣ በግብታዊነት በዜጎች መካከል ከሚከሰት ጥፋትና ከህሊና ጸጸትም ያድናል።

ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share