የግብጽ ምሁራን ግድቡ አደጋ ይፈርሳል ይሉናል፡፡ በእኛስ ምን እየሠራን ነው? – ሰርፀ ደስታ

የዚህ የግድብ ጉዳይ ማዘናጊያ ነገር እንዳይኖርበት አሰጋለሁ፡፡ በግብፆቹ በኩል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ በእኛ በኩል ምን እየተሰራ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ሆኖም ከመጀመሪያው ከናይል ቤዚን አገራት ወጥቶ ጉዳዩ ወደ አሜሪካ ሸምጋይነት የሄደበት ሁኔታና ቀጥሎም የሆነው ነገር በኢትዮጵያ በኩል የማያስደስት ነገር ይሰማኛል፡፡ አብዛኛው ሰው በሚዲያና በማሕበራዊ ድረገጾች ብዙ ብሎበታል፡፡ እኔ ይሄን ጉዳይ አንድ ነገር ቢሆን አሁን ኢትዮጵያን ወክለው ከሚደራደሩት አይወርድም፡፡ ለግብጽ ምንም አይነት ክፍተት መሰጠት አልነበረበትም፡፡ ከእኛ ተደራዳሪዎች ይልቅ የሱዳኖች አቋም ለኢትዮጵያ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳበረከተ ይሰማኛል፡፡ ሱዳኖች ከግብጽ ጋር ላለመወገን ግልጽ ያለ አቋም ነው የያዙት፡፡ ሆኖም በፊት በናይል ተፋሰስ አገራት የተያዘው አይነትን አቋም የመሰለ አስተማማኝ ነገር አልነበረም፡፡ የተፋሰስ አገራቱ ለግብጽ ግልጽ የሆነ የማስጠንቀቂያ የሚመስል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ የዩጋንዳው ፕሬዚደንት ሞሲቬኒ ግብጽ ድርድሯን ከውሃው ባለቤቶች ጋር ማድረጉን ትታ በሌሎች ተጽኖ ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን የምታደርገውን ሴራ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡ የሁሉም የተፋሰሱ አገራት አቋም ተመሳሳይ ነበር፡፡ ግብጽም አደብ ገዝታ ነበር፡፡

አሁን ግብጽ ከአፍሪካውያን የተፋሰስ አገራት ጋር ሳይሆን ዓረብንና አውሮፓን ከኋላ አድርጋ በአሜሪካ አደራዳሪነት (ፍርድ ሰጭነት) ዘመቻዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ ምሁራኖቿ የጥናት ውጤት የሚሉትን ሌሎችን ለማሳመን እያቀረቡ ነው፡፡ በአጠናቀቅንው ወር ሽፕሪንገል በተባለ አሳታሚ የግብጽ ምሁራኖች ባሳተሙት መጽሀፍ በግልጽ የአባይ ግድብ ሥራ እንዳይጀምር እነሱ ከፍተኛ ያሉትን የደህንነት ዓደጋ የጥናታችን ውጤት ባሉት በዚሁ መጽሀፍ ለዓለም እየተናገሩ ነው፡፡ በግልጽ የሚከተለወን ድምዳሜ ሰጥተዋል

Finally, safety surveys on dams have shown that the Ethiopian GERD Dam’s safety factor is only 1.5 degrees from 9 degrees. It is more probable that the GERD Dam will collapse. Experts said the dam was created to collapse. The safety of the dam is very low.”  ከሞላ ጎደል ሲተረጎም፡-  “በመጨረሻ የግድቡ የደህንነት ቅኝት ከሚጠበቅበት 9 የደህንነት ደረጃ  1.5ቱን ብቻ የሚያሟላ ነው፡፡ ግድቡ ሊፈርስ የሚችልበት አድል ከፍተኛ ነው፡፡ ግድቡ የተሠራው እንዲፈረስ ሆኖ እንደሆነ ባለሙያዎች (ሌሎች)ም ተናግረዋል፡፡ የግድቡ የደህንነት ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡”

ይሄ እንግዲህ የግብፅ ምሁራኖች የጥናታችን ድምዳሜ ብለው በታዋቂው የጥናት ውጤቶችን አሳታሚ የሽፕሪንግለር ባሳተሙት ከ 600 ገጽ በላይ በሆነው መጽሀፍ የግድቡን አስመልክቶ በስፋት በጻፉበት ምዕራፍ የሰጡት የጥናት ውጤት ድምዳሜ  ነው፡፡ የዚህን ምዕራፍ ከዚህ ጽሁፍ ጋር አያይዤ ልኬያለሁ፡፡ ሁሉም ማንበብ የሚችል ቢያንስ ቅንጭብ ሀሳቡን ያንብበው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ግድቡ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክነያ አደጋ እንደሚያሰጋው ሊያሳዩ ሞክረዋል፡፡ ሆኖም የጽሁፉን ዋና በደንብ ስታነቡትና ውጤት ብለው የሳዩት በራሱ የግድቡ አካባቢ በአስተማማኝ ሁኔታ የመሬት መንቀጥቀጥ እንደማያሰጋው ያሳያል፡፡ ምን እለባት ሳያስተውሉት ያሰቀመጡት ይሁን ወይም ለማደናገር ባይገባኝም በዋናው ጽፈሁፍ ምስል 17፡23 ላይ እንምታዩት የግድቡ አካባቢ ከመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ነጻ በሚባል መልኩ እንደሆነ በግልጽ ይታያል፡፡ ይሄ አይነት ነገር ለማደናገር እንጂ ተሳስተው አይመስለኝም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን በእኛ በኩል ምን እየተሰራ ነው? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ በባለሙያዎች የተጠና ምን መረጃስ አለ፡፡ በግብጽ በኩል ከዚህ ሌላም በቅረቡ የወጡ ጥናቶች ያሉ ይመስለኛል፡፡ ቀጥሎ ገለልተኛ ያጥናው ሊባል ይችላል፡፡ ገለልተኛ የሚባል ነገር የለም፡፡ ገለልተኛ የሚባለውን ግብጽ በራሷም ይሁን አሁን ደጅ እየጠናች ባለቻቸው አገሮች ድጋፍ ጥናቱን እንደምታዛባ ለማሰብ ብዙም አያዳግትም፡፡ በእኛ በኩል በቂና አስተማማኝ የሆነ ጥርት ያለ ጥናት እነሱ በሚያሳትሙበት አሳታሚዎች ማውጣት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ግድቡን በተያዘለት ጊዜ መሙላት መጀመር ሌላው የቁርጠኝነት ምልክት ነው፡፡ ግን ለዛ ምን ዝግጅት እየተደረገ ነው? አሁን ኮረና መጥቶ ነገሮችን ሁሉ አቅጣጫ አስቀይሯል፡፡ ሆኖም የሙሌቱ መዘግየት እንኳን ቢኖር ከሁለት ሶሰት ወር ባነሰ መሆን አለበት፡፡ ከዛ ደግሞ ምርጫ በሚል ሌላ ትኩረት መሳቢያ ይመጣል፡፡ ከምርጫ በኋላ ደግሞ ሀሳብ ሁሉ ሊቀይሩ የሚችሉ ሰዎች የግድቡን ነገር እየተከታተሉት ላለመሆናቸውም ማረጋገጫ የለንም፡፡ ሁሌም እንደምናውቀው ምርጫ ሲመጣ ለሕዝብ ዋና ነን የሚሉት ከምርጫ ማግስት ምን እንደሚሆኑ እናውቃለን፡፡ ያ የድሮው ቁማር ተቀይሯል ብሎ የሚያምን ካለ እየተሳሳተ እንዳይሆን፡፡ በእርግጥም የምርጫን ውጥት ተከትሎ የሚመጣውም የተለመደ ሁከት ሌላ ስጋት ነው፡፡ በቅን ከታሰበበት ግን ይሄን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ እቅድ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የአባይ ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያም አልፎ የብዙ አፍሪካውያን ጉዳይ ነው፡፡ ቀኝ ገዥዎች በማን አለብኝነት በሌሎች ሀብት የወሰኑበት እስከዛሬም ያለቀቀው የቀኝ ገዥዎች ቀንበር ለመስበር ልዩ ምልክትም ነው፡፡ ዛሬም የአገራት ድንበሮቻችን ሳይቀሩ ቀኝ ቀዥ ሆነው በመጡ የተወሰነልን መሆኑን በደንብ አስተውሉ፡፡ በዚሁ በአባይ ግድብ ጉዳይ ጀርመን የግድቡን ዋጋ ግብጽ እንድትከፍል እርዳታ እንስጣት ማለቷን አስታውሱ፡፡ የሚገርመው ለኢትዮጵያ እንስጥ እንኳን አደለም ያለችው ለግብጽ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላት ግብጽ ደግሞ ለእኛ ልትሰጠን ነው፡፡ እንግዲህ ዲፖሎማት ነን የሚሉት የኢትዮጵያዎቹ ይሄን የሚያህል ዘረኝነት የታከለበት አስተያየት ሲሰጥ ማብራሪያ መጠየቅ አለመጠየቃቸው አላውቅም፡፡ ቢጠይቁ ይሰማ ነበር፡፡ እንግዲህ ግብጽ ያለምክነያት አደለም አፍሪካውያንን ገሸሽ አድርጋ እንዲህ በሌሎች ደጀንነት እየተመካች ያለቸው፡፡ ይሄን ደግሞ ለማሳየት እንኳን ሌሎች ታክለውበት ኢትዮጵያ በቂ ነበረች፡፡ ሆኖም አሁን በያዙት የቋም ልስላሴ በኋላ ምን አስበው እንደሆነ አላውቅም፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

1 Comment

  1. አቶ ሰርጸ ደስታ መቸም ጦር ከአስፈታው ወሬ ያስፈታው ይብሳል ይላል የሀገራችን ብሂል።ግብፅ የእግር እሳት የሆነባት የግድቡ ግንባታ እውን እየሆነ ሲመጣ እበለጣለሁ ስጋት እና ሁሌም የእኛን እድገት ስለማትመኝ እንጂ የግድቡ ደህንነት ስጋት አደለም በመሆኑም እውነትን አጠልሽት የምትሄድበት ፕሮፓጋንዳ የእኛን ሀይል ለመበታተን የተለያዩ ምክንያት በመፍጠር መዞርዋ ግልጽ ነው ።ያሉት factory of safety 1.5 ቢሆን እንኳን መለየት የሚያቅታቸው ባለ ሙያተኞች የሌላት ሀገርም አደለችም ሀገራችን ። factory of safety 9 ያሉት ግን factor of ignorance እንዳይሆን ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.