ማን ሆነና ጠብ አስተናባሪው! – አሁንገና ዓለማየሁ

የሰሞኑ ሕገመንግሥት ነክ ውይይት አንዴ ያነበብኩትን ተረት አስታወሰኝ። ካህኑ አንዱን ዘላን (በከብት እርባታ የሚተዳደር) ክርስትና ያስተምሩና ያጠምቁታል። ከተጠመቀ እለት በኋላ ግን ቤተክርስትያን አይተውት አያውቁም። ታድያ አንድ ቀን ወደ ቤቱ ይሄዱና ለክርስትያን እሁድ ማልዶ ማስቀደስ ተገቢ መሆኑን ነግረው ከእንግዲህ እንዳይቀር አደራ ብለውት ይመለሳሉ። አንድ እሁድ ቀን የቅዳሴ መግቢያው ሰዓት ደርሶባቸው ካህኑ እየተቻኮሉ ወደ ቤተክርስትያን ሲሄዱ ያ ዘላኑ ሰው አንዳች ጭራቅ እንዳባረረው በተቃራኒው አቅጣጫ እየሮጠ ይመጣል። ካህኑም
“ምነው ልጄ እሁድ እሁድ ሌላ ሌላ ሥራህን ትተህ ቤተክርስትያን እየሄድክ አስቀድስ ብዬህ! የት ነው በሌሊት የምትሯሯጠው? በል ና ከኔ ጋር ወደ ደብር እንሂድ!” ይሉታል።
“በፍጹም!በፍጹም! ከዚያ እኮ ነው የምመጣው። እንኳን እኔ ልሄድ ለሶም እጅግ አደገኛ ነው እንዳይሄዱ!” ይላቸዋል።
“ምነው ምን ተፈጠረ? ሰላም አይደለም እንዴ?”
“እንደመከሩኝ በሌሊት ሄጄ ማስቀደስ አለብኝ ብዬ ቤተክርስትያን ዘው ስል ካህናቱ ተጣልተው በዱላ ሊከታከቱ ሲገባበዙ ደረስኩ። ምናለፋዎ ድብልቅልቅ ብሏል።” ይላቸዋል።
“እንዴት? እንዴት? አለቃው የሉም እንዴ ይሄ ሁሉ ሲሆን? ጠቡ እንዲህ ሲጋጋል የት ሄደው ነው?” ይላሉ ካህኑ።
“አሉ እንጂ። ዋናው ጠብ አስተናባሪው ማን ሆኖ?” ይላቸዋል።
እንግዲህ ሌሊት ማሕሌት ሲቆሙ ካህናት መቋሚያ ይዘው አለቃው በመቋሚያ እየመሩ የሚደረገውን የአቋቋም ሥርዓት አይቶ ነው የተደባደቡ መስሎት ደንግጦ በመፈርጠጥ ላይ የነበረው።

አሁንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠብ ሲነታረኩ (እነዚህ የምራቸውን ነው)ሕገ መንግሥት የለም እንዴ ብሎ ለሚጠይቅ ዋናው የጠቡ አስተናባሪ ማን ሆኖ (ይህም የምር ነው) የሚል መልስ ተገቢ ነው። በቅኝ አገዛዝ ዘመን ያመለጣቸውን ኢትዮጵያን በቋንቋ እና በጎሳ ከፋፍሎ አዳክሞ የመግዛት ሕልም በኦነግ/ወያኔ አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ የመጫን ለባእዳን እድል የሰጣቸው ሕገመንግሥት ተብዬ ሰነድ የቅኝ ግዛት አፓርታይድን በኢትዮጵያ ላይ ማንበሪያ ሆኖ ያገለገለ ፍጹም ባዕድ የሆነ የባዕዳን መሣሪያ ነው።
አሁን ታድያ ሕገመንግሥቱ ቀውስ ውስጥ ገባ ይላሉ:: ቀውሱ ራሱ ማን ሆኖ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ - የአባይ ወንዝ ባለቤትነት ጉዳይ - ኪዳኔ ዓለማየሁ

ካስነሱት ያስነሳል
እስኪ ዝም በሉ!
ሟርተኞች በሙሉ!
መስከረም ሰላሣ ሕገመንግሥታችን ይሞታል ስትሉ
ረስታችኋል መሰል የበዓል ካህናት ዙሪያውን እንዳሉ።
ሳይሞት ያስነሱታል በተራው ነፍስ ዘርቶ ሲመልስ ውለታ
ያስነሳላቸው ዘንድ ሥልጣናቸው ሲሞት ዘመኑ አብቅታ።
እና ግድግዳው ላይ ቢታይም ጽሑፉ
ሕገመንግሥታችን /ይሞታል ብላችሁ/ ከንቱ አትለፍልፉ
ከትቢያ አንሥቶ /ባልጋ ያኖራቸው /ጠቅላላ ሳያልፉ።
ፊት እንዳነሳቸው/ ከድሜ አንስተው/ ያነሳሱበታል/ እያጨሱ እጣን
ቀን ድንገት ደርሶበት/ እዚም እዚያም ወዲያም/ የሚሞትን ሥልጣን።

አሁንገና ዓለማየሁ፡ ሚያዝያ 2012

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share