የታሪክ አዙሪት? (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

መንግሥቱ፣ መኢሶን፣ ኢህአፓ
ዐቢይ፣ ኢ. ዜ.ማ፣ ኢ. ዴ. ፓ?

የታሪክ ግጥም ይመስላል። 1969 እና 2012። የሰሞኑን በሁለት የተከፈለ የፖለቲካ ውዝግብ ሳጤን በ69 በጋዜጣና በጎዳና በኢህአፓና በመኢሶን መካከል ይካሄድ የነበረው ፍልሚያ ታወሰኝ። የዚያ ጊዜውን ሦስትዮሽ እና ያሁኑን ሦስትዮሽ በኅሊናዬ አሰብኳቸው።

መንግሥቱ፣ ሃይሌ ፊዳ እና ተስፋዬ ደበሳይ   V    ዐቢይ፣ ብርሃኑ ነጋ እና ልደቱ አያሌው

1969                            2012

መኢሶን ቤተመንግሥት ገብቶ ለውጡን በመደገፍ ሲንቀሳቀስ ኢህአፓ የዲክታተርሺፕ መንገድ ያለውን በመቃወም የሽግግር መንግሥት እየጠየቀ ጎዳና ላይ ነበር። ደርግ ደግሞ በቤተመንግሥት።

ኢዜማ ቤተመንግሥትን ተጠግቶ ለውጡን በመደገፍ ሲንቀሳቀስ ኢዴፓ/አብሮነት የሌጂቲሜሲን ማብቃት በማስገንዘብ የሽግግር መንግሥት እየጠየቀ “ጎዳና” ላይ ነው። ብልጽግና/ኢህአዴግ ደግሞ በቤተመንግሥት አለ።

በቅድሚያ የዚያን ጊዜው የኢህአፓ አቋም ትክክል ነበር ወይም መኢሶን ተሳስቶ ነበር ለማለት በግልባጩም ለመፈረጅ የቀረበ ንጽጽር ሳይሆን የኃይሎችን አሰላለፍ እና አጠላለፍ በታሪካዊ ማንጸሪያ ለማሳየት የቀረበ ምሳሌ ነው። የኢህአፓ አቋም ስሁትም ሆነ ትክክል በተቃውሞ ለቆመው ለኢህአፓ ይቅርና ሂሳዊ ድጋፍ ብሎ ቤተመንግሥት ለከረመው መኢሶንም ቢሆን የደርግ አንጀት ርህራሄ ሳያሳይ ቀረጣጥፎታል።

ይሄ ንጽጽር ብዙ እውነት የሚመስሉ ነገሮች ያሉት ቢሆንም የስልሳዎቹ ፍጸሜ የመበላላት ወይም የመበላት ስለነበር ዛሬ ለማሟረት የመጣ ሳይሆን ከታሪክ እንድንማር እና ያንን ስህተት እንዳንደግም ለማስገንዘብ ነው። በዚያን ዘመን አንድ እስረኛ መተባበር አቅቶን እኛ ተጠላልፈን በመጨረሻ ሁላችንም በአንድ ላይ በመንግሥቱ ኃይለማርያም እሥር ቤት ተገናኘን ብለው ነበር።

በወቅታችን ያሉት የፖለቲካ ኃይሎች እነዚህ ሦስቱ ብቻ ናቸው ለማለት ሳይሆን የሌሎቹም አሰላለፍ ቢሆን በግርድፉ በነዚህ መስመሮች ሊጠቃለል ይችላል ለማለት ነው። ሕወሃት ግን ያኔም ጫካ ነበር አሁንም “ጫካ” ነው። ይህም ሌላው ታሪካዊ ትምህርት የምንቀስምበት ትዝብት ነው። መንጌም ሌሎቹን ከበላ በኋላ የተበላው በሕወሃት ነበርና። ዛሬ ደግሞ ሕወሃት እንደ ራዕየ ዮሐንሱ አውሬ ብዙ ራስ አለው። አንዷን ራስ ብቻ እያዩ መሸወድ አደገኛ ፍጻሜ ላይ ይጥላል።

ያኔም እንዲህ ነበር በእርሳስ በጋዜጣ

ፍልሚያ ንትርኩ ባንዲት ሀገር እጣ

መብላት መበላላት ኋላ ላይ ሊመጣ

በዪንም ልትበላው ሕወሃት አድፍጣ።

ጎበዝ!

ያስተዋለው የለም የባሰውን ጣጣ!

እንዲህ ስንጫወት ቁማር በጨበጣ

ሀገር ማለቋ ነው በጓሮ ተሸጣ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.