March 14, 2020
20 mins read

“ህይወት አጭር ጣፋጪ ና በሥቃይ የተሞላች ናት።” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

የፅሑፍ  መንደርደሪያዎች
 የፅሑፉ መንደርደሪያዎች ከመፅሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ጥቅስ  እና “ህይወት” ና “የማይጠገነው ብልሽት “የተሰኙ ግጥሞቼ ናቸው።መልካም ንባብ።
 3. አንድ ድርሻ ሁሉን እንዲያገኝ ከፀሐይ በታች በተደረገው ሁሉ ይህ ነገር ክፉ ነው፤ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ ክፋትን ትሞላለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ነው፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ።
 4. ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው።
 5. ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም።
(መክበበ 9፤3-5)
1-ህይወት
የሰው ህይወት ተአምር ነች
በሁለት የተቃራኒ “አካል” የተፈጠረች
በመሐፀን አድጋ፣በምጥ የተበሰረች።
የሰው ህይወት ተአምር ነች
በጡት እና በጡጦ፣በአንቀልባ ያደገች።
በመሬት፣በመደብ፣በአልጋ ላይ ዳክራ
ተንፏቃ ና ድሃ ፣   ታግላ ተውተርትራ
ወድቃ እየተነሳች በዳዴ– የቆመች።
ቀስ በቀስ ተራምዳ–መሮጥ የጀመረች።
በጮርቃነቷ በፍላሎት ምርቃና ሰማይ የረገጠች
በሽምግልና ቅዝቅዛ ፣ ትዝታና የሞቀች።
የሰው ህይወት ተአምር ነች
ጅማሬዋን ና ፍፃሜዋን የደበቀች።
…ተጀምራ እሥከምትጨረሥ
… እንደወንዝ የምትፈሥ።
የካቲት 30/2012 ዓ/ም
      2 . የማይጠገነው ብልሽት
የሰው ልብ ልክ እንደሰዓት ቆጣሪ
ትር፣ትርዋ  ይምሰል እንጂ ለዘላለም ኗሪ
ድንገት ይቋረጣል ልብ ምቷ
እንደ ሰዓት አይጠገንም ብልሽቷ።
መጋቢት 5/2012 ዓ/ም
   የሰው ልጅ ህይወት ዘወትር ከሞት ጋር እየታገለች ላለመሞትም እየተፍጨረጨረች ፣በተጋድሎ የምትሰነበት  ናት።የእያንዳንዳችን “ነፍስ” እኛ “ህይወት” የምንላት፣በወጣ ውረድ እየተዋከበች በአያሌ ገጠመኞች ታጅባ፣ በየዕለቱ፣ከአንዱ የህይወት ጥግ፣ ወደሌላው፣ “ከአንዱ የህይወት ጫፍ ወደ ሌላኛው፣ወዘተ። በኑሮ አሥገዳጅነት፣ እየባዘነች እሥከሞት የምትጣምን ናት።
    የእያንዳንዳችን ህይወት፣በማያቋርጠው የህይወት  ሽክርክሪት ፣በነጋ በጠባ፣ ከአንዱ ጋር በፍቅር፣ከሌላው ጋር ደግሞ በጥላቻ ከወዲያ ወዲህ፣ከወዲህ ወዲያ ትንገላታለች።ትላጋለች። ትወድቃለች።ትነሳለች።…ወድዳም ሆነ ተገዳ  እየተሞዳሞደችም ሆነ እየተጀነነች ከሁሉም ሰው ጋር፣ከአምሳያዋ ጋር ፣ከቢጤዋ ጋር ደግሞ ተጣብቃ  ጉዞዎን እሥከህልፈት ትቀጥላለች ።
ከቶ አይቀርም ሞቱ
ምንም ቢታክቱ
ምን ቢሰነብቱ
…………….
ከቶ አይቀርም ሞቱ…
     “ሰው ‘ተወለደ’ ሲባል ‘ሞተ’ ማለት ነው፣ እያሉ አንድ ካህን ሀዘንተኛውን ሲያፅናኑ የሰማሁት  በወጣትነቴ መተማ ኩመር ሰፈራ ጣቢያ በጤና ረዳትነት በእርዳታ ማሥተባበሪያ አማካኝነት የክሊኒኩ ብቸኛ ኃኪም ሆኜ ተቀጥሬ ሥሠራ፣ከሰፋሪው ወገኔ አንዱ አርፎ ቀብሩ ላይ ተገኝቼ እንደነበር ትዝ ይለኛል።
 እውነት ነው፣ሞት እና ህይወት የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው።ሥትወለድ ሞትም አብሮህ ተወልዷል።ይህንን ከተረዳህ ሞት እንግዳ አይሆንብህም።
   ሞት  አብሮን ያለ እና በተለያየ መንገድ እንደሚወስደን እርግጠኛ ብንሆንም ከመቀባር በለይ ለሚውለው ሥማችን ብዙዎቻችን አንጨነቅም። በትውልድ እየተዘከረ ለዘላለም በበጎ ለሚያሥጠራን ሥም አንጨነቅም።
   አብሶ ተምረናል የምንል፣ወረቀት ብቻ የምናመልክ ሆነን የተገኘን ግብዞች፣ሀገርን እና ዜጎችን በሚጠቅም ድርጊት ላይ ሥንሳተፍ ሳይሆን፣ጮማ እየቆረጥን፣ውሥኪ እየጠጣን፣ ባሥ ሲልም ጫት እየቃምንና ሺሻ እያጤሥን ፣ ደሃውን ህዝብ በጥፋት መንገድ  ላይ ለማሠለፍ ሌት ተቀን ሥናሴር ነው የምንሥተዋለው።
  እኛ የፍቅር ገዳዮች እና የጥላቻ አንጋሾች ብንሆንም፣የህዝብ ህይወት ግን ህይወት በምትጎዝበት  በዘመኑ የዓለም ወንዝ እንጂ  እኛ መቶ ፖለቲከኞች በቀደድነው ቦይ ውስጥ ከቶም አትጎዝም።የህይወት ጥሬ እውነት ይህ ነው። እውነትን እንረዳ።…
  እውነት በየቀኑ  እንደምታሳየን ከሆነ፣   በህይወት  ወንዝ ፍሰት ውስጥ ፍቅርን ገዳይ የሆነው፣ ጥላቻ ፣ለሰከንድ ሳያቋርጥ  ከፍቅር ጋር ተደምሮ  ይጓዛሉ። ይህም የተቃራኒ ዘወትሯዊ  ገጥምጥሞሽ፣በሰው ላይ ፣ያልተቋረጠ ሥቃይና ደሥታን  ያሥከትላል  ። ህይወት ያለሥቃይ ትርጉመ ቢሥ ናትና ፣ሰው ልጅ፣ ይህንን፣በደሥታ የታጀበ ህመም ጥርሱን ነክሶ ይቋቋመዋል። “ላይችል አይሰጥም ።” እያለ።
   “ላይችል አይሰጥም።” እያልን በህይወት ሥንኖር በፍቅሯ ውስጥ በየዕለቱ የሚገጥመንን ሥቃይ እንቋቋመዋለን። ደግሞም ህይወት ተቃራኒ ገጠመኞችን ባታሥተናግድ ኖሮ እንደምትሰለቸን እናውቃለን።ለዚህም ነው  ህይወት ሰው እንዳይሰለቻት  ብላ፣ ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን በጣምራ  ይዛ  ሁሌም የምትጓዘው።
    በሰው የዕለት፣ተዕለት ኑሮ ውስጥ ፣ለማይክሮ ሰከንድ፣ ያለማቋረጥ ፣ህይወት እና ሞት፣ጥላቻና ፍቅር፣ደስታ ና ሐዘን፣ሣቅና እንባ፣ ወዘተ – አብረው ይጓዛሉ።ህይወት ቁጥር ሠፍር በሌላቸው ተቃርኖዎች የተሞላች ነች። በእነዚህ ቁጥር ሥፍር በሌላቸው ተቃርኖዎች ውስጥ ሰው ልጅ እየዳከረ፣በፅናት የሚጣምነው  ተሥፋን ገንዘቡ አድርጎ ነው።
    ሰው ልጅ ከምግብ ፣ከድሎት፣እና ከምቿት ባሻገር  ተሥፋን ገንዘቡ በማድረግ ባይኖር ኖሮ  ህይወት በራሷ ታሥጠላው ነበር።ይሁን እንጂ “መከራም ሆነ ሥቃይ ያልፋል ።የደሥታና የፈንጠዝያ ሰዓታትም ነገ ይመጣሉ።” ብሎ በተሥፋ በመጠባበቅ ኑሮውን በነገ ብሩህነት ላይ እንጂ በዛሬ ጨለማ  ላይ  ባለማድረጉ   መኖሩን እየወደደ ይኖራል ።
      ሰው ልጅ፣ በዚች ዓለም ሲኖር ተቃራኒ  የሆኑ፣ የህይወት አሥደሳች እና አሳዛኝ  የሠርክ ገጠመኞች እየተፈራረቁበት  በተሥፋ ተሞልቶ  እስከጊዜው ኑሮውን ይገፋል ።ወንድ ብቻውን ይኖር ዘንድ አይገባውምና ተሥፋውን የበለጠ እውን ለማድረግም ከሴት ጋር ይጣመራል።ተቃራኒውን ይወዳጃል።ተቃራኒውን አፍቅሮ ያገባል።
    የተቃራኒ ፍቅር፣ በሴት እና በወንድ ይጀምራል ።በህየወት እና በሞት ይደመደማል። ትወለዳለህ ፣ጥቂት ወይም ብዙ ትኖራለህ።ደግሞም ትሞታለህ።
  ሰው ልጅ፣  ከሞት በፊት በህይወት ሲኖር  በሚመርጠው  መንገድ ወይም በመወለድ  ዕጣ ፈንታ ፣ ሀብት ና ድህነት ያጋጥመዋል።
    ሁላችሁም፣ ፈፅሞ  የማትፈልጉት ፣የምትጠሉት  የህይወት  አጋጣሚም ድንገት ይደርስባችኋል። ሳትዘጋጁ።ድንገት።በመንገድ ላይ፣በሥራ ላይ፣ ወይም በቤት ውስጥ ሆናችሁ። ወይም… ።
   እውነቱ ልክ እንደመወለዳችሁ ነው።ሁሉም ነገር በመወ ለድ ይጀመርና በሞት ይደመደማል።የእያንዳንዳችሁ ህይወ ት በሞት ከመደምደሙ በፊት፣በተቃራኒ መንገድ እየተጓዛ ችሁ ኑሮን ትገፋላችሁ።ኃይማኖተኛም ሁኑ ኢ -አማንያን ለተቃራኒ ህጎች መገዛታችሁ አይቀርም።
    ሰው በገዛ ሥጋው አሠገዳጅነት  ፅድቅና  ሐጥያትን በየዕለቱ ይፈፅማል።  ሁለችንም  ተቃራኒ አጋጣሚ በየቀኑ ያጋጥመናል።የእያንዳንዳችን ህይወት በተቃራኒዎች ተሞል ቷል ። እንደምታውቁት  ለህይወት እንኳን ሞት አለለት። ሞትን  ማንም አጥንት መቆርጠም የጀመረ ባይፈልገውም ቅሉ ‘አያ ሞት እንግዳ ‘ ሳያሥበው ከች ብሎ ይወሥደዋል።
  የማትፈልጉት ሞት እንኳ ህይወትን የሙጥኝ ሥላላቸሁ አይቀርላችሁም።ምንም ብትጠነቀቁ እና  ባለኝ ሚሊዮን ብሮች ፣ታክሜ እድናለሁ በማለት ፣በሃብታችሁ ብትተማ መኑም ሞት የጀግኖች ጀግና ነውና ከዶክተሮች እጅ መንጭቆ ወደ መቃብር ይወሥዳችኋል።እዛም ከደሃ  እኩል ትሆናላችሁ።የመቃብራችሁሐውልት በወርቅ ቢለሠን ለእናንተ ምን ይፈይድላችኋል ?  ምንም።
  ምንም አይፈይድላችሁም። ምንም እነኳን በህይወት ሳላችሁ ገንፎ አላማጭ እና ሙቅ አኛኪ  የነበራችሁ  ብትሆኑ፤ምንም እንኳን ዝና እና ሥልጣን ያላችሁ ፣የተማራችሁና የተመራመራችሁ ዓለም ሁሉ የሚያዠረግድላችሁ የነበራችሁ ብትሆኑ፤ይኽ ታሳቢ ተደርጎ  መቃብራችሁ ጋ ጥበቃ ቢመደብ፣ በአካል፣በሥጋ ሥለሌላችሁ፣ ዓለም ዞር በሎ የእናንተን ኃውልት፣በክብርና በመሽቆጥቆጥ  አያይም።  በህይወት ሥትኖሩ ብቻ ነው … አዳሜ እና ሄዋኔ ጭራውን የሚቆላላችሁ።…
   ሰዎች ሆይ አትሳቱ። ሰው በህመም ብቻም አይሞትም።  ተራራ የሚያክል ገንዘብ ቢኖረውም ከሞት አያሥጥለውም ።ጤናዬ  አስተማማኝ ነው ባለበት ቅስፈት እንኳ ድንገት በአደጋ ወይም ከግሉ  ዶክተር ቁጥጥር በሆነ ህመም ይሞታል። ያ የቻይና ዶክተር እንደመጥመቁ ዮሐንሥ ሥለ ኮሮና ቫይረሥ አሥጠንቅቆ ፣ህመምተኛን ሲረዳ እሱም ተይዞ ራሱን ማዳን ሳይችል ቀርቶ ክልትው ማለቱን አትዘንጉ ።  ሁሉም ሰው ከተወለደበት ቀን ጀምሮ በዚች ምድር ላይ የሞት ሰልፍ መሰለፉንም ተረዱ።
   እናም ለአፍታ እንኳን የሞት ሰልፍ መሰለፋችሁን እና ህይወት እና ሞትም ከጎናችሁ ሳይለዩ ለመቃብር አብቅተኋችሁ  እንደሚለዩአችሁ ተገንዘቡ።
   ለማንኛውም በጎ ነገር   ተቃራኒ እንዳለውም እውቁ ።በእግዚአብሔር ላይ እንኳን ሤይጣን በተቃራኒነት ተሰልፏል። …
  እናም ሁሉም ክስተት በተቃራኒነት ወይም መሣ ለመሣ ሥለሚጎዝ፣ ዛሬ ጤነኛ ብትሆኑ ነገ ታማሚ ናችሁ።በሽታ አይደርስብንም ብላችሁ በጥንቃቂያችሁ ብትኮፈሱ በማይጠነቀቀው ሌላ ሰው አማካኝነት በሽታ ይደርስባችኋል። በሽታ ብቻ አይደለም ባልተጠነቀቀ ሹፌር ለህልፈት ልትበቁ ትችላላችሁ። አትገበዙ፣ በዚች ደቂቃ ደሥተኛ ብትሆኑም ከዚች ደቂቃ በኋላ በሚመጡት ደቂቃዎች፣ደሥታችሁን የሚያሣጣችሁ አንዳች ሊከሰት ይችላል። …
   ሰዎች ሆይ፣በግብዝነት ላለመታመማችሁ  ሆነ ላለሞታችሁ፣ በእርግጠኝነት ለመናገር አትሞክሩ።ከዚህ እውነት የተነሳ እኔ ከእርሱ የበለጠ ኑሮ እኖራለሁ ብሎ የሚያሥብ ካለ ፣ይህንን እውነት ያልተረዳ ጅል ነው።
    እናም ” እኔ   የተሻልኩ ነኝ ።” ብላችሁ ደካማ ለሆነ ወንድማችሁ  በግብዝነት  ምክር  ሥትሰጡ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።  አንዳንድ ምክር ለተቀባዩ የቡጢ ያህል የሚያመው በግብዝነት የተሞላ ሢሆን ነው ና  አፋችሁ እንዳመጣላችሁ አትናገሩ።(ይህ ጅል ፖለቲከኞችን ና ከከፈሏቸው ለሤጣንም ለማገልገል ዝግጁ የሆኑትን የፖለቲከኞቹን ኮንደሞች ይመለከታል።)
  ለሰው ምክር ሥትሰጡ እግር እንዳለው በማሳየት ወደ ግፍ መንገድ፣ወደሞት መንገድ፣ወደሥካር መንገድ ፣ወደ ዝሙት መንገድ፣ወደ ሁከት፣ሀሜት እና ምቀኝነት ሠፈር  እንዳይሄድበት ፣አማራጫ እንዳለ አሳዩት   እንጂ ፣ እግሩን በእናንተ እግር ተክቶ እንዲጎዝ አትወትውቱት።
     ምክር ለሰው ሥትለግሱ፣ ዓይን እንዳለው፣ፈጣሪው በፈጠረለትም ዓይን፣ክፉን እና በጎውን በማየት እንዲማርበት፣ማለትም ሰውን ማየት ብቻ ሣይሆን በአትኩሮት፣ በማሥተዋል ፣በጥልቀት የሚያየውን ሰው ኑሮ  እንዲዳሥሥ  አሣሥቡት እንጂ የእናንተን አይን ተውሶ እንዲያይ በበዛ ንዝንዝ አትጣሩ።…
   ምክር ሥትለግሱ ፣ “ሰው እስከሆንክ ድረስ እንደእኔ በህሊና ነገሮችን መርምረህ ክፉና በጎውን መርጠህ ለምን በጎ፣በጎውን ብቻ አታደርግም ? “እያላችሁ ከመጨቅጨቅ  እና በእናንተ ህሊና እንዲጠቀም ከመወትወት ይልቅ፣ መጥፎ ድርጊትን በመፈፀም ያጣኸውን የህሊና ሰላም  እና መልካም በመሥራት ያገኘኸውን የህሊና እርካታ እና ጤና አመዛዝነህ የተሻለውን መምረጥ የአንተ  ፋንታ ነው፣ብላችሁ ምርጫውን ለሱ ተውለት።ዛሬ ያላችሁት ባይገባው ነገ በራሱ ጊዜ ይገባዋልና !!
  ሰዎች ሆይ ተደጋግፈን ፣ተረዳድተን፣ተሳስበን፣ተዋደን እና ተፋቅረን ይህቺን አጭር እና በሥቃይ የተሞላች ህይወታችንን በቁጭት ተሞልታ ወደመቃብር እንዳትወርድ ለማድረግ እንደምንችል ብናሥብ መልካም ነው።
   ለሁላችንም የሚበጀን በፍቅር አንቀልባ መታዘል ነው። ይህቺን አጭር ሆና በሥቃይ የተሞላች ህይወታችንን ፍቅር አዝሎ እሹሩሩ የማይላት ከሆነ ፣ የመኖር ትርጉሙ ይጠፋናል።…

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop