ኢትዮጵያዊ  ምን ይመስላል? – ባይሳ ዋቅ-ወያ

የዛሬ ሃምሳ ዓመት ገደማ መሰለኝ የያኔው ወጣት የዩኒቬርሲቲ ተማሪው ኢብሳ ጉተማ “ኢትዮጵያዊው ማን ነው?” በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ አቅርቦ ለውጥ ፈላጊውን የዩኒቬርሲቲውን ማህበረሰብ ጥም ለማርካት የሞከረው። አብዛኛው የዩኒቨርሲቲው ተማሪ የፊውዳል ሥርዓቱ አገሪቷን ወደፊት እንዳትራመድ ጠፍንጎ የያዛት መሆኑን የተረዱና ሥርዓቱ ካልተለወጠ የሕዝቦቿ አብሮነት ውሎ አድሮ መሸረሸሩ አይቀሬ መሆኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማናበብ መላ ይመቱ ነበርና የዚህ ንቁ ተማሪ ግጥም ጊዜውን ጠብቆ የመጣ ነበር። በዚሁ ጊዜ ነበር ከተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች አንዱ የነበረው ዋለልኝ መኮንን የብሄር ጥያቄን አስመልክቶ ታሪካዊውን ጽሁፍ ያቀረበው። አንዳንዶች ያኔም ሆነ ዛሬ እነዚህን ጽሁፎችን አስመልክቶ ሁለቱን ንቁ የተማሪው ማህበረሰብ አባላትን አገሪቷን ለመበታተን ሆን ብለው ያቀረቧቸው አስመስለው ሲያወሩ ይታያሉ። በመጀመርያ ደረጃ የጽሁፉ አቅራቢዎች ወጣት በመሆናቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሸመነበትን ድርና ማግ በውል አልተረዱትም ተብለው ተተቹ። ገፋ ሲል ደግሞ የሆነ የውጭ አካል እጅ ቢኖርበት ነው እንጂ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ ከመሃላቸው አንደኛው ከሌላው የተሻለ ጥቅም ያገኘ ይመስል ከእኩዮች መካከል የትኛው ነው ኢትዮጵያዊው ብሎ መጠየቅ እብደት ነው ያሉም ነበሩ። የሚያሳዝነው ግን ዛሬም ተመሳሳይ አስተሳሰብ የሚያስተናግዱ ወገኖቻችን መኖራቸው ነው።

ይህንን አጭር ጽሁፍ ላካፍላችሁ ያነሳሳኝ አንድ ባለፈው ወር አዲስ አበባ ውስጥ ያጋጠመኝ ጉዳይ ነው። ታሪኩ ባጭሩ እንደዚህ ነው። የአገውን ሕዝብ 80ኛ ዓመት የፈረስ ጉግስ በዓል ላይ ተካፍለን ከበዓሉ በኋላ ከአዲስ አበባ የሄድን እንግዶች በሙሉ ባንድ ላይ በአይሮፕላን ተሳፍረን ቦሌ የአገር ውስጥ በረራ መናኸርያ አረፍን። ገና ወደ አዳራሹ ስንገባ አንዲት እንስት የኢሚግሬሽን ሠራተኛ እንደ ጄት ተስፈንጥራ መጣችና ከኛ ጋር በበዓሉ የክብር እንግዳ ሆኖ የነበረውንና ከፊቴ ተሰልፎ የነበረውን አኟክ ጓደኛችን ኦኬሎን “ፓስፖርት ፓስፖርት” እያለች ታጣድፈው ጀመር። ኦኬሎም ለነገሩ አዲስ አለመሆኑን በቁርጠኝነት ለማሳወቅ ይመስለኛል በዚያ በቁመቱ ልክ ገፍትሮአት ሲያልፍ አንዳች የሆነ በሕይወቴም አድርጌ የማላውቀው ነገር ከውስጤ ግንፍል ብሎ ሲወጣ ልጅቷን አንገቷን ጭምድድ አድርጌ ይዤ “ኢትዮጵያዊ ማለት ባንቺ ቤት እንደ አንቺ ቀላ ያለ መልክ፣ ሰልካካ አፍንጫና ሉጫ ጸጉር ያለው ብቻ ነው?” “እነ ኦኬሎን የመሳሰሉ ምኒልክ ጋምቤላን ሲያስገብር በቦታው የነበሩና በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እንዳሉ አታውቂም?” ብዬ ባልወለደ አንጀቴ ሳንቧረቅባት በቦታው ደርቃ ቀረች። ዛሬ አድገው ራሳቸውን ችለው በሚኖሩ ልጆቼ ላይ አንዲት ቀን እንኳ እጄን አሳርፌባቸው የማላውቅ ሰውዬ በቦሌ አይሮፕላን ጣቢያ በማላውቃት የኢሚግሬሽን ሠራተኛ እህታችን ላይ እጄን ማሳረፌ አሳፍሮኝ፣ መለስ ብዬ ረጋ ባለ መንፈስ ኦኬሎን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ማወቅ እንዳለባት አስረድቼ ወደ ሻንጣ መረከቢያ አመራሁ። (ስለሁኔታው የነበረውን ስሜት ሳላነጋግረውና ሳላስፈቅደው በእውነተኛ ስሙ ላለመጠቀም ብዬ ነው እንጂ፣ ኦኬሎ እውነተኛ ስሙ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ)።

ኦኬሎ ግን ዞር ብሎ ምን እንደተፈጠረ ለማየት አንዳችም ጥረት ሳያደርግ ቀጥ ብሎ ከግቢው ወጣ። ላለፉት አርባ አምስት ዓመታት የፈረንጅ አገር ኑሮዬ በጥቁረቴ ብቻ ተመሳሳይ ማንነትን ፈተና ውስጥ የሚከቱ ብዙ አጋጣሚዎችን ስላሳለፍኩ የኦኬሎን ውስጣዊ ስሜት ለመገመት አልከበደኝም። በቆዳ ቀለምና የፊት ገጽታ ብቻ ከሰው ሁሉ ለይተው የአንድን ግለሰብ ዜግነት ለማጣራት መሞከር ቆሽጥ ያሳርራል። ያበግናል። ከመቶ በላይ ከምንሆን ኢትዮጵያውያን ተሳፋሪዎች መካከል ኦኬሎ ብቻ በቆዳው ቀለምና ገጽታው ምክንያት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተለይቶ ፓስፖርት ሲጠየቅ እውነትም “ኢትዮጵያዊ ማነው?” የተባለው የኢብሳ ጉተማ ጽሁፍ ዛሬም ወቅታዊ መሆኑ ታየኝ። ግን ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? አንድ መቶ አምሳ ዓመት ሙሉ በአንዲት ኢትዮጵያ በምትባል አገር አብረን እየኖርን እንዴት ይቺ የኢሚግሬሽን ሠራተኛ ኦኬሎን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያንም አንዳሉ መረዳት አቃታት? በየሚዲያው እየወጣን “ለዘመናት ተጋብተን ተዋልደን የኖርን” እያልን ስንለፍፍ እንዴት ለዚህ ሁሉ ዓመታት ጨውና ውሃ ሳይሆን ዘይትና ውሃ ሆነን በአንዲት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ቻልን? የትኛውን የተፈጥሮ ሂደት ብናጣምም ነው ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ልክ ኦቦ ኢብሳ ከአምሳ ዓመት በፊት እንዳለው ዛሬም “ኢትዮጵያዊ ማነው?” ብለን ለመጠየቅ የተገደድነው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ ትንሣኤ! -nሲና  ዘ ሙሴ

እኔ ላለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በፈረንጅ አገር ያሳለፍኩት ከነጮች ተለይቼ ማንነቴን የማስረዳት ተደጋጋሚ ክስተቶች ትዝ ብለውኝ ልጅቷን ቆሌዋን ገፈፍኳት እንጂ ከኔ ኋላ ተሰልፈው የነበሩ ሰዎችማ ምን እንዳናደደኝ የገባቸውም አይመስለኝም። እንዲያውም በዚያች ጠባብ የኢሚግሬሽን መተላለፍያ ላይ ቆሜ መንገዱን ዘግቼባቸው “ለልጅቷ ትምህርት ስሠጥ” ምን የዞረበት ሩታሜ ነው ብለው በልባቸው እንደሚረግሙኝ ይሰማኝ ነበር። አዎ! ለዘመናት “የኢትዮጵያ ታሪክ” እያልን ስንማር የነበረው የኢትዮጵያን ግዛትና ዳር ድንበር እንጂ በዚያች ግዛት ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አልነበረምና ኩሩ ኢትዮጵያዊው ኦኬሎ በፈረንጅ አገር ሳይሆን ተወልዶ ባደገባት ባገሩ በወንዙ ፓስፖርት ሲጠየቅ አይቶ ዝም የሚል ኢትዮጵያዊ ራሱ ኢትዮጵያዊው ማን እንደሆን በውል የሚያውቅ አይመስለኝም።

ልጅቷን በግልፍተኝነት አጎሳቆልኳት እንጂ ጥፋቱ ከሷ ሳይሆን ከሥርዓቱ መሆኑ ተረስቶኝ አይደለም። በፊውዳሉ ሥርዓት ዘመን በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የኢትዮጵያውያን ምልክት ሆኖ ይቀርብ የነበረው ኢትዮጵያዊ ማንነት ከሞላ ጎደል የአማራ የኦሮሞና የትግራይ ሕዝብን ቋንቋ ባሕል አለባብስና አመጋገብ እንጂ የአኟኩንና የኑኤርን፣ የጉሙዝና ቤኒሻንጉልን፣ የወላይታና የዶርዜን፣ የሙርሲና የኮንሶን በአጠቃላይም የኒሎቲክና ኦሞቲክ ኢትዮጵያያንን ሕዝብ ያጠቃለለ አልነበረምና የወንድማችን ኦኬሎ ወላጆችና ዘመዶች ያኔ “ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች” እንጂ ኢትዮጵያውያን ተብለው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በመባል ከሚታወቁት ደገኞች (highlanders) እኩል እውቅና እንዳልነበራቸው ጠንቅቄ አውቅ ነበር። በኛው ዕድሜ እንዳየነው፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኒሎቲክና ኦሞቲክ ሕዝቦች በሕግ ፊት እንኳ እንደ አንድ ሙሉ ሰው ስለማይቆጠሩና ሥርዓቱ የኢትዮጵያን ልጆች በእኩልነት የማያስተናግድ በመሆኑ ነበር የማህበረሰባችንን ኢፍትሃዊ አሠራርን በመቃወም ያ ብሩህ ራዕይ የነበረው ዋለልኝ መኮንን በጊዜው “የብሄር ጥያቄ” የሚለውን ማኒፌስቶውን በአደባባይ ያቀረበው!

እኔን የሚያሳስበኝ ግን፣ እነዋለልኝና ኦቦ ኢብሳ ይህንን የኢትዮጵያዊነትን ጥያቄ ለሕዝብ ካቀረቡ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ዛሬም ልክ እንደ ያኔው ኦኬሎና ኦጁሉ በገዛ አገራቸው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተለይተው ፓስፖርት መጠየቃቸው ነው። ሌላው እንኳ ቢቀር የፊውዳሉ ሥርዓት ከተገረሰሰ ከአምሳ ዓመት በኋላና አሃዳዊው ሥርዓት ጠፍቶ የኢትዮጵያን ሕዝቦች እኩልነት ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ሥርዓት ከተመሠረተ ከሰላሳ ዓመት በኋላና “ብዝሃነታችን ውበታችን” እያልን በምንልፍፍበት አገር ቢያንስ ቢያንስ የኢሚግሬሽን ባላሥልጣኖቻችን እንዴት የእናት ኢትዮጵያ ሆድ ዥንጉርጉር መሆኑን ሳይረዱ ቀሩ? ኢትዮጵያም የዘጠኝ እኩል መብት ያላቸው የፌዴራል አባላት አገር ናት እየተባለ እንዴት ኦኬሎና ኦጅሉ ከባይሳና ጎዮቶም እኩል ኢትዮጵያዊ ሊሆኑ አልቻሉም? የኢሚግሬሽን እህታችን ዓይነቶች “ኢትዮጵያውያንም”  በዘጠኙ ክልላት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተለያየ መልክ እንዳላቸው እንዴት እስከዛሬ አልተረዱትም? ጋምቤላ የተባለ ክልል መኖሩ እየታወቀ ጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምን ዓይነት መልክ እንዳላቸው እንዴት ሳይገባን ቀረ? ለማወቅ ዕድል ከማጣት ነው ወይስ ለማወቅ ፍላጎት ከማነስ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለልጅ የሳቁለት፣ ለውሻ የሮጡለት፣ ለፖለቲከኛ ያጨበጨቡለት - ይገረም አለሙ

ሁኔታው እጅግ በጣም ያሳስባል። ብዙዎቻችን የጋምቤላ፣ የጉሙዝና ቤኒሻንጉል እንዲሁም “የደቡብ ሕዝቦች” በመባል የሚታወቁ ክልሎች የዘጠኙ የፌዴራል አባላት መሆናቸውን እንጂ በነዚህ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ወገኖቻችን ምን እንደሚመስሉ ለማወቅ ፍላጎቱ ያለን አይመስለኝም። አያድርስና ጠላት በምዕራብ በኩል ያገራችን አካል የሆነውን ጋምቤላን ቢያጠቃ ግን “አያቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው ያቆዩአት ምድራችንን አንዲት ስንዝር እንኳ አናሳነካም” ብለን እንዘምት ይሆናል። በጋምቤላ መሬት ላይ ከሚኖሩት ወገኖቻችን ይልቅ መሬቱ በራሱ የበለጠ ክብር ያለው ይመስለናልና! አያቶቻችንም ደማቸውን ያፈሰሱትና አጥንታቸውን የከሰከሱት በጋምቤላ ምድር ላይ ለሚኖሩት አኟኮችና ኑኤሮች ሳይሆን የጋምቤላን ምድር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለማካለል ነበርና! የሚገርመው ዛሬ ከተለያየ አቅጣጫ እየታየ ያለውን የማንነት ጥያቄ “ዘረኝነት” “ጎሰኝነት” እያልን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስናወግዘው፣ እውነተኛውን በቆዳ ቀለም ላይ ብቻ ተመሥርቶ ያገራችንን ሕዝብ ለዘመናት የከፋፈለንን ይህንን የዘር መድልዖ እንኳን መፍትሄን ልንፈልግለት ይቅርና፣ የችግሩን መኖር እንኳ ለማወቅ ጥረት የምናደርግ አይመስለኝም።

ኦኬሎ ከማንኛችንም በላይ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና ለሰው ልጅ መብት መከበር በመላው ዓለም የአሜሪካን ኮንግሬስን ጨምሮ እየዞረ አጥብቆ የሚሟገት ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሆኖ እያለ የኢሚግሬሽን ባላሥልጣኖቻችን ግን በአገሪቷ ውስጥ በሰላም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እኩል እንዳይዘዋወር መብት ሲነፍጉት ማየቱ እጅግ በጣም ያማል። ግን ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? አውቃለሁ አንዳንዶቻችሁ፣ “ዝም ብለህ ታካብዳለህ እንደምትሉኝ”። ስዊድናውያን ነጭ ጓደኞቼም በየጊዜው በቆዳዬ ቀለም ብቻ ከሌሎች ስዊድናዊያን ለይተው ፖሊሶች እንደሚያንገላቱኝ ስነግራቸው “ሊሆን አይችልም፣ ዝም ብለህ ታጋንናለህ” እንደሚሉኝ ነውና አልፈርድባችሁም። የሚያመው የተቆረጠው ቦታ ብቻ ነው ይላል ኦሮሞ ሲተርት። ኦኬሎን እንደዚያ ሲያመናጭቁት ሳይ በኔ ላይ ይደርስ የነበረውን እያመላከትኩ ነበርና ሌሎቻችሁ ተመሳሳይ መድልዖ ያልደረሰባችሁ ለኔ የሚሠማኝ ስሜት ባይሰማችሁ አይከፋኝም ለማለት ያህል ነው።

በኔ ግምት ይህን ዛሬ በኦኬሎና በሌሎች የኦሞቲክ እና ኒሎቲክ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን የመድልዖ ባሕል ለማስወገድ ከባድ አይመስለኝም። ይህ ሁሉ አሳፋሪ አቀራረብ በሕዝባችንና በተለይም በመንግሥት በኩል ቅንነትና ፍላጎቱ ቢኖር ኖሮ በቀላሉ ሊቀረፍ ይቻል ነበር ባይ ነኝ። በየኤርፖርቱ ባሉ የኢሚግሬሽን ቢሮዎች፣ በጉምሩክ መሥርያ ቤት፣ በአየር መንገዱ ቲኬት መሸጫ ቢሮዎች፣ የአየር መንገዳችን የበረራ አስተናጋጆች፣ በባንክና በኢንሹራንስ መሥርያ ቤቶች፣ በትላልቅ ሆቴሎች እንዲሁም ትላልቅ የንግድ ተቋማት የኒሎቲክና ኦሚቲክ ወገኖቻችንን ቀጥረው “በፊተኛው ጠረጴዛ” (Front Desk) ላይ ቢያሰማሯቸው ኖሮ፣ ይህ ዓለም በሙሉ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያለውን የተሳሳተ እይታ ለማስተካከል ይቻል ነበር ባይ ነኝ። በፖስት ካርድ ላይ ብቻ ቱሪስቶችን ለመሳብ ከማሰብ የነዚህን የዘረኝነት ሰለባ የሆኑትን ወገኖቻችንን ፎቶ ከመለጠፍ ባሻገር፣ እነሱኑ ለዘመናዊ ትምሕርት አብቅቶ አስተምሮና አስመርቆ በመሃል አገር ካሉ ከሌሎች “ደገኞች” ኢትዮጵያውያን እኩል ማሰለፍ ይቻል ነበር። ይህንን ለሰዎች ለማስረዳት ስሞክር “እነሱ እኮ ስላልተማሩ ነው እንጂ በመንግሥት ተቋማት የስልጣን ወንበር ያልተሰጣቸው ሆን ተብለው የተረሱ አይደሉም” የሚል መልስ አገኛለሁ። የኔ መልስ ግን፣ አማራው ኦሮሞና ትግሬው፣ እንዲሁም ሃዲያና ከምባታው፣ ሲዳማና አገው የመማር ዕድል ሲያገኙ የነዚህ የኒሎቲክና ኦሞቲክ ወገኖቻችን አለመማር ራሱ የጭቆና ምልክት ነው ባይ ነኝ።

ወገኖቼ! እስቲ ላንዳፍታ ቆም ብለን ራሳችንን በኦኬሎ ቦታ አድርገን እናስብ። የኢትዮጵያን ግዛትን ዳር ድንበር እንዳትነካብን የምንቆረቆርላትን ያህል በዚያች ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ወገኖቻችንም በማንኛውም መስፈርት ከሌላው ደገኛ ኢትዮጵያዊ እኩል እንዲታዩ ካልተሟገትንና እኩልነታችን በተግባር እንዲተረጎም ካላደረግን ፍቅራችን ለኢትዮጵያ እንጂ ለኢትዮጵያውያን ያልሆነ  የውሸት ፍቅር ነው ማለት ነው። ኢትዮጵያን ግን ኢትዮጵያ የሚያሰኛት ግዑዙ መሬት ሳይሆን በውስጧ የሚኖሩ ሕያው ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያዊ መባል ደግሞ በሕግ ብቻ በተደነገገው እይታ ሳይሆን በተግባር ሁሉም እኩል ኢትዮጵያዊ ሲሆን ብቻ ነው። አለበለዚያ ዛሬ በቦሌ አየር ማረፊያ ያገር ውስጥ በረራ መዳረሻ ውስጥ እንደ ውጭ ዜጋ ተቆጥሮ ፓስፖርት የሚጠየቀው ኦኬሎ ነገም ልጆቹ ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥማቸው ከላይ የጠቀስኳቸው አንዳንድ እርምጃዎች ካልተወሰዱ፣ ዛሬ ኦኬሎ ስለ ቁንጅናዋ በየዓለም ዳርቻው የሚሰብካትን ታላቋን ኢትዮጵያን ነገ ደግሞ “ይቺ ለአያቴም ላባቴም ያልሆነች ኢትዮጵያ ለኔም አትበጅም” ብሎ የሚነሳ ትውልድ ሊፈጠር ይችላልና በጥብቅ እናስብበት!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታማኝ እና ቴዲ ትላንት ምሽት (ከክንፉ አሰፋ) ጋዜጠኛ

አውቃለሁ አንዳንድ አንባቢዎች ያው የተለመደውን የተሳሳተ ትርክት ይዘው “እኛ እኮ ለዘመናት አብረን ተከባብረን የኖርን ነን፣ ዛሬ ጽንፈኞች ገብተው አተራመሱን እንጂ  ወዘተ” ብለው ይህንን የኔን መቆርቆር ለማጥላላት እንደሚሞክሩ። አንድ ትልቁ ያገራችን ሕዝቦች በተለይም የኤሊቱ በሽታ፣ አንድ ሕዝብ ወይም ቡድን በሆነ ምክንያት እኩልነት አልተሰማኝም ብሎ ስሞታ ለማቅረብ ገና ሲንደረደር፣ “ለዘመናት ተጋብተን ተዋልደን ተከባብረን የኖርን” በሚል ባዶ አባባል አደባብሶ ለማለፍ መሞከር መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል አለማወቃቸው ነው። የተጋባውና የተዋለደው ባብዛኛው የአማራ የኦሮሞና የትግሬ ሕዝብ ብቻ ነው። ኒሎቲኩና ኩሺቲክ ሕዝቦቻችን ግን ከአማራው ከኦሮሞውና ከትግሬው ጋር ሲጋቡና ሲዋለዱ አልነበረም፣ ዛሬም አይጋቡም አይዋለዱም። እንደ ውሃና ዘይት ግን ሳይዋሃዱ አብረው ጎን ለጎን ግን እየኖሩ ነው። እውነቱ ይኸው ነው። መጋባቱና ወዋለዱ ይቅርና አብሮ በመንግሥት ተቋማት በእኩልነት የመሥራት ዕድሉን እንኳ አላገኙም።

ከስንት ሚሊዮን የኒሎቲክና የኩሺቲክ ሕዝቦች መካከል ኢሚግሬሽን ኦፊሴር ወይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የሚሆን ሰው የጠፋ ይመስል ኢትዮጵያ ማለት በአየር መንገዱና በተለያዩ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ የምናያቸው የሓበሻ ልብስ የለበሱ ቆነጃጅቶችን ብቻ አድርጎ በማቅረብ የዓለምን ሕዝብ ማሳሳቱን እናቁም። ኢትዮጵያ ሌላ ገጽታ ያላቸውም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆችም አሏትና!  እነዚህን ልጆቿንም “ከደገኞቹ” እኩል ወደ መድረክ እናምጣቸውና እውነተኛውን የኢትዮጵያዊነትን ቡራቡሬ ገጽታ መጀመርያ ለራሳችን ከዚያ ደግሞ ለመላው የዓለም ሕዝብ እናሳውቅ! ይህ ደግሞ ተግባራዊ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ ሚና መጫወት ያለበት መንግሥት ቢሆንም፣ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በፈረቃ አገሪቷን ሲገዙ የነበሩና ዛሬም የችግሩ አካል የሆኑት ሶሶቱ ትላልቅ የኩሽ ሕዝቦችም የዚያኑ ያህል ኃላፊነት አለባቸው። በቆዳ ቀለም ላይ የተመሠረተ መድልዖ በሌሎችም ብዙ አገሮችም ሲከሰት የነበረ ስለሆነ፣ እነዚህ አገራት ለችግሩ እንዴት መፍትሄ እንዳገኙ ተሞክሮአቸውን በመዋስ ይህንን ለዘላለም የተጣበቀብንን እውነተኛውን የዘረኝነት ነቀርሳ ለዘላለሙ እንገላገለው።

ሁሉንም ልጆቿን፣ ባይሳና ኦኬሎን አደፍርስና ክብሮምን ኤርሳሞና ዴሌቦን በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በቅንነት የምናስብ ከሆነ ከሁሉ አስቀድመን የችግሮቻችንን ቅደም ተከተል በውል እንወቅና ቅድሚያ ሊሠጠው ለሚገባ አገራዊ ጉዳይ አስፈላጊውን ቅድሚያ እንስጥ። በእኩልነት የማይተያዩትን የኢትዮጵያን ልጆች ይዞ አንዲት ኢትዮጵያን እንገነባለን ብሎ መለፈፍ ራስን ማታለል ነው። ትርፉም ድካም ብቻ ይሆናል። ባይሳ ሰተት ብሎ ሲገባ ኦጁሉም ፓስፖርት ሳይጠየቅ የሚገባባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት በቅንነት እንነሳ።

በቸር ይግጠመን።

 

ጄኔቫ፣ 23 ፌብሯሪ 2020 ዓ/ም

email:  wakwoya2016@gmail.com

 

8 Comments

  1. The passport or immigration worker acted in accordance with her duties. She had not acted to discriminate his fellow traveler (Okelo) because of his physical appearance and skin color. The apparently aggressive reaction of the writer was not warranted. It appears that he is also biased against fair skinned Ethiopians. Instead of judging, politicking and blaming the worker, he should have explained to her that she acted inappropriately. He himself could have a non-Oromo ancestry like many who have been assimilated and adopted the Oromo identity.

    • Don’t think that Amharas are a separate people. They are intermingled people from various Cushitic people of Northern Ethiopia. This means that they are from Oromo, Agaw, Beja, Saho, etc. The evidence is that the names of forefathers of people that consider themselves as Amhara have Oromo names. How did this Oromo names entered into Amharic speakers descendants? It is not by mere chance. It is by assimilation of the Oromo, agaw, beja, or others that the current Amharic speakers created. Amharic speakers cannot be free from Cushite as the dominant people living in north Eastern Africa staring from Napata, Merowe, etc were Cushite. Some evidence of Cushitic names in northern and central Ethiopia include Aksuma, Walduba,Addet, Merawi (merawa), Ganda wuha, Warra Lake, Adde Guddo, Ona, Korommi, etc, and most of the names in Wallo where Amharic speakers are dominant now. So the likelihood that Amharic speakers are standalone people without assimilation from other language speakers would be a fiasco. Through long time intermarriage and living together, Tegarus, Amharic speakers, etc share common ancestral heritage and culture from the Cushite who first used to live in that part of the country including the whole horn of Africa, lakes region and central Africa. Thinking this way, can help us to cement our long historical relations and discarding the false historical narratives of the Amhara ruler, clergies and creating consensus on our real history. Have a courage to come out of the box of dictatorial kings and clergies and make yourself ready for political discussion and consensus building to end the long unsettled issue of suppression and domination in this country.

  2. ዛሬም እኮ ልክ እንደአጼዎቹ ዘመን ኢትዮጵያ የአንድ ቋንቋ አንድ ባህል እና አንድ ሃይማኖት ሃገር ናት ብለው የሚያቀርቡ፣ ያንንም ለመፍጠር የሚኳትኑ መኖራቸውን አንርሳ! በምንልክ ዘመን የደነቆሩ እስከዛሬም አሉ!!

  3. Yes the “KEGNA” group is so selfish and barbaric and wants everything for itself. You find this group at Addis Ababa`s municipality office, Bole airport, and all kebele offices in Addis.

    Bayissa waaakoya is one of the prominent members of this barbaric group. I clearly know to whom you addressed this piece of writing. But the most hateful group towards people from Gambella and other border areas is your own barbaric “kegna” group. A typical example is how this group hates the great Ethiopian OBANG METO calling him names simply because he stands for Ethiopia and Ethiopians.

  4. Mr. “showoff”፣ ካሁን በፊት የተወሰኑ ፅሑፎችህን አንብቤ ሳበቃ፣ ደህና ሰው ነው የሚል አባባልን ይዤ ነበር::

    1. ዛሬ ግን ጊዜ አጠፋህብኝ፣ ስነስርአት አስከባሪዋ ወገናችን ሃሳብ ውስጥ ያለው ውጥንጥን፣ አዲስ አበባ የድራግ መተላለፍያ pivot point መሆኑን ታውቃለችና፣ “እነዚህ ደግሞ ከሌጎስ ወደ ቻይናና የመሳሰሉትን ማጓጓዛቸው እንዳይበቃቸው አሁንስ ደግሞ ሃገሬን ሊበክሉ ወደ አገውም ሁሉ ማዳረስ ጀመሩ እንዴ” እያለች ነው ያለችው፣ የሆነን ነገር ከሆነ ጉዳይ ጋራ በማያያዝ

    2. እኔን ለምሳሌ፣ ምንም እንኳን የማያጠራጥር የከወደ ግዛት ዓድዋ ምድረ ፅዮንነት መልክ እያለኝም፣ ግን ስንት ኤርትራዊ ነው መሰለህ፣ በግብፅ በኩል ስላለፈ እና የሆነን ነገር assimilate ስለሚያደርግ ብቻ፣ “ግብፅ ነዎት?” ብሎ የሚጠይቀኝ፣ ኩባ ነዎት፣ ሞሮኮ ነዎት የመን ነዎት ህንድ ነዎት ብሎ የሚጠይቀኝን ቁጥር የለሹን ሁሉንማ ጥፊ ሰንዝሬበት አይሆንም፣ የኔ ቀላሉ ለሁሉም መልስ፣ በተለይም እኔን በግብፅነት ለሚጠረጥረኝ የመረብ ሌላኛው ዳርቻ ልጅ፣ ደግሞ “ከአባይ ምንጭነቴ ልታስጥለኝ ነው እንዴ” ምንትሴ ብየ አልበሳጭበትም፣ ቀለል ያለውንና የመተባበር መልክም ያለውን፣ “የለም አባይን ከባህር መጥለቅያው አካባቢ ሳይሆን ከወደ ምንጩ አካባቢ ነኝ የምገናኘው” ብዬ ጠያቂዎችን ትብብር ባለው መልኩ መልስ ሰጥቶ መሄድን ነው የተመረጠው ልምዴ፣

    3. ፓስፖርት ጠያቂዋም ያሉዋት ልምዶች እንደ አስተዳደግዋ ነው፣ መጀመርያ አስተዳደግዋን ለውጠህ ከዚያን በኋላ እያወቀች ስህተት ስትሰራ ነው እንጂ፣ ሳታውቅ ላደረገችው ጥፋት ልጅቱን ማነቅህ፣ አንተን እንደ አልባ Pädagogik ያስወስደሃል፣ ከዚያም በላይ ራስህ በጥፋትህ ስላመንክ፣ ምስክር ሳይጠራ ያስከስስሃልና፣ ይሄ ሁሉ ከመድረሱ በፊት ስነስርአት አስከባሪዋን ከካሳ ጋራ ይቅርታ ጠይቃት፣

    4. ከአንተ ይልቅ ዝብ ብሎ ያለፈው ይሻላል፣ ግን እርሱም ቢሆን በተጠየቀው መሰረት ፓስፖርቱን አሳይቶ ሲያበቃ፣ አየሽ ኢትዮጵያ የሞዛይክ ሃገር ነች ብሎ ተባብሯትና ትምህርት ለግሷት ሊያልፍ ይችል ነበር፣

    5. ሁሉም ስነስርአት ለማስከበር የተመደበን ሰው እየገፈተና ጭራሹም በጉሮሮ እያነቃ ከተንቀሳቀማ አናርሺ ብቻ ሊሰፍን አይደለም እንዴ፣ አዲስ ብቻ ሳትሆን መላ ኢትዮጵያ (under hostage ካለው ትግራይ በስተቀር) ወደ አናርሺ እያዘገመች ነው የሚባለው ለካስ ዝም ብሎ አይደለም፣ ታድያ አንተም ተጨመርክበት!?

    6. የነ ዋለልኝ መኮንን አርቆ አስተዋነት አድናቆትህን ግን እኔም እጋራሀለሁኝ

  5. ኢብሳ ጉተማም ሆነ ዋለልኝ መኮንን ለሃገራችን ትተው ያለፉት መርዝ አሁን የሚታየውን ውጥንቅጥ አንደሚያስከትል ቢያውቁ ኖሮ አይጽፉም ነበር። እንደዚህ አገሩ በክልል ተዘግቶ የእኛና የናንተ በሚል የቅሚያና የማግልል ፖለቲካ ተብዮ ሊኖር መቻሉ ኣልታያቸውም። ስለዚህ ስማቸውን በከንቱ እያነሳን የፈለግነውን ለመጻፍ ባንጠቀምባቸው ደህና መሰለኝ።

    ባይሳ ዋቅ ወያ አኟክ ጓደኛዬ ኦኬሎ “ፓስፖርት” ተጠየቀ በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ይህ የእኛና የናንተ የሚል ፖለቲካ ጭንቅላቱ ላይ ስለወጣ ነው። ነገርየው ምክኛታዊነትን የሚያጠፋ፣ ስሜታዊ የሚያደርግና ወደሃይል ድርጊት የሚገፋፋ ነው። በረራዉ የሂገር ዉስጥ ቢሆንም የኢሚግሬሽን ሠራተኛዋ አጠራሪ ሁኔታ ካጋጠማት ዜግነት ምን ለመለየት “ፓስፖርት” የመጠየቅ ግዴታ አለባት። ኦኬሎ የዉጭ ዜጋ ከመሠለ “ፓስፖርት” መጠየቁ ክፋቱ አልታየኝም። ጉዳዩ የማንነት ፖለቲካ ሳይሆን የደህንነትና የሰላም ማስከበር ስራ ነው። ባይሳ ዋቅ ወያ ጉዳዩን ከዚሃ አንጻር አለማየቱ ምን ያህል የዘር ፖለቲካ ናላውን እንዳዞረው ያሳያል።

    ስራዋን በአግባቡ የምታከናውን ሠራተኛ በሥራ ቦታዋና ሰዓት አንገቷን ጭምዽድ አድርጎ መያዝ የወንጀል ስራ ስለሆነ ሊጠየቅበት ይገባል እላለሁ። ቅሬታ ከነበረዉ በጨዋ ደንብ ለሐላፊዎች አሣዉቆ መመሪያዉ እንዲታረም ሰራተኛችም በምትሀታዊ ሥልት የተጓቮችን ማንነት እንዲለዩ ሥልጠና እንዲያገኙ በረዳ ነበር። ፍላጎቱ ግን እንደመሠሎቹ ስሜን ያላቸዉን ከሌሎች ሕዝቦች ማጋጨት መሆኑን ከጽሁፋ መረዳት ይቻላል። የዉጭ ዜጎች እንደዚህ አይነት የሚያጋጭ ነገር ከመሸረብ ቢቆጠቡ ምንኛ በረዳ። ሃገሪቱ በራሷ ሂደት ትፈታዋለች። እንኳን እኛ ጀማሪዎቹ በእኩልነት የገፋትም ችግሩ አለባቸዉ። እና “ቶሽ”እላለሁ።

    ከሌላ አንጻር ሲታይ ሠራተኛዋ ኦኬሎን ዝም ብላ ብታሳልፈው ኖሮ ባይሳ ሃገራችን ተሻሽላለች፤ አኩልነት ሰፍኗል በሚል የሚጽፍ አይመስለኝም። በብሄር ፖለቲካ ናላው ዞሮ ባይሆን ኖሮ የሃምሳ ምናምን ዓመት ታሪክ ባልጻፍፈ ነበር። አንደማየው ክሆነ የብሄር ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ናላውን ያዞረው ግማሽ ምዕተ ዓመት የኖረበት የውጭ ሃገር የነጭና ጥቁር ፖለቲካ የፈጠረው ዘረኝነት ሰላባ መሆኑ ጭምር ይማስላል። አዚህም ላይ “የቄሳርን ለቄሳር” ቢያደርግ ይሻላል።

    በመጨረሻም ኦኬሎ ለምን ዝም ብሎ ሄደ የሚል ሃሳብ ሊነሳ ይችላል። ጉዳዩ አንዸሚመለከተው ሰው ቅሬታውን መግላጽ፣ ወደፊትም አንዲታርም የመጠየቅና ማስተካከያ አንዲድረግ ማሳሰብ መብቱ ነው። አሱ ግን በስተት አንጂ ሆን ተብሎ አለመሆኑን ተረድቶ ኣልፎታል። ድርጊቱ ሊያስመሰግነው የሚገባ ነው አላለሁ። እንደኔ ከሆነ ኦኬሎ የባይሳን አንቶ ፈንቶና ከፋፋይ ድርሰት ውድቅ አንደሚያደርገው አልጠራጠርም። በተለይም ለራሱ መናገር የማይችል ድንጋይ ራስ ኣስመስሎ በተቆርቋሪነት ክለላ ክፋፋይ ሙግት መግጠሙን ሲያይ ሰውየው ምን ነካው ማለቱ አይቀርም።

    የኢሚግሬሽን ሠራተኛዋ ባይሳን መክሰስ ብትፍልግ የራሱ ጽሁፍ መነሻ ማስረጃ ይሆናል። ለሌችም ትምህርት ስለሚሆን ሞክሪው በሏት። አነዚህ የውጭ ዜጎች ውጭ ሃገር የማይሞክሩትን ነገር አዚህ ሃገር አንዳሻቸው አያደረጉ ሃይ የሚላቸው መጥፋቱ ይገርማል።

    • ችግሩ የተፈጠረው ኢብሳ ጉተማ ወይም ዋለልኝ መኮንን ስለጻፉት ነው ልትለን ትፈልጋለህ?? አንድ ችግር ከመሰረቱ ከሌለ ስለተጻፈ ወይም ስለተወሳ ብቻ ይፈጠራል?? ካልተጻፈስ ችግሩ መፍትሄ አገኘ ማለት ነው?? ያለፈው ትውልድ “ለሃገራችን ትተው ያለፉት መርዝ” ብሎ መለፋደድ መህይምነት ነው!!

  6. በቦሌ ኢምግሬሽን ሠራተኛ አማካይነት ጓደኛቸው ኦኬሎ በአገሩ ላይ ፓስፖርት ለምን
    ተጠየቀ በሚል መነሻ ባይሣ ዋቅ ወያ ያወጡት ጽሁፍ በእውነትስ ለግለሰቡ ተቆርቁረው ሳሆን በትግራይ ሕዝብ ጉያ ተሸሸግው የአገር ጸጥታ ከሚነሳው ቡደን ጋር ስለሚሰራው የአረብ አገሮች ቅጠረኛና ኢትዮጵያን እንጠፋለን ብሎ በእንጊሊዝ አገር በይፋ የተናገረው ወዳጃቸው ጀዋር በአሁን ወቅት የኢትዮጵያዊነት ማረጋገጫ አምጣ ተብሎ ለምን ተጠየቀ ለሚለው ውስጠ-ወይራ አነጋገር እንጂ እውነትስ ለኦኬሎ ተቆርቁረው አይደለም፡፡ይህንን ያልኩበት ምክንያት ጸሐፊ ባይሣ ዋቅ ወያ ከአሁን በፊት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ “ከጅብ ጅማት…….. “ ብለው በ4/15/19 ባወጡት ጽሁፍ ስለጀዋርና እሱ ስለሚያስተዳድረው OMN ድርጅት በተመለከተ መልስ የሰጡትን ሰፊ ገለጻ ማንበቡ ጽሁፉቸው ከተንኮል የፀዳ ላለመሆኑ በቂ ማስረጃ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share