መጋቢት 06፣ 2020
መግቢያ
የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር የብዙ መቶ ሺሆች ዐመታት ዕድሜ ቢያስቆጥርም ታሪክን መስራት የጀመረው ምናልባትም ከአስር ሺህ ዐመታት ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። በአንድ ቦታ ረግቶ መኖርና ከእርሻ ተግባር ጋር መለማመድ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። ዛሬ በአገር ደረጃ የሚጠሩና ወደ ህብረ-ብሄር የተሸጋገሩ አገሮችን ታሪክ አለፍ አለፍ አድርገን ካለብዙ ምርምር ስንመለከት የሁሉም አገሮች መነሻ ተመሳሳይነት አለው። ማንኛውም አገር ከስልጣኔ ጋር አልተወለደም። ማንኛውም ህዝብ ከላይ ወደ ታች በአንዳች ኃይል ስልጣኔዎች ከተዘጋጁ በኋላ በመወርወር የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር አልተደረገም። ዛሬ የምንጠቀምባቸው፣ የምንበላቸውና የምንጠጣቸው፣ የምንጓዝባቸውና የምንኖርባቸው ነገሮች በሙሉ የሰው ልጅ የረጅም ጊዜ የማሰብ ኃይል ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ሁሉ በአጠቃላይ አነጋገር ባህላዊ ለውጦች ናቸው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ከአንድ የአኗኗርና የአመራረት ስልት ወደ ሌላ ለመሸጋገር የሚያስችል ውስጣዊ ኃይል ወይም የማሰብ ኃይል ስላለው የግዴታ ህብረተሰብአዊ ለውጥን ያመጣል። በዚህም አማካይነት ተፈጥሮንና የሚኖርበትን አካባቢ ለመለወጥ ይችላል።
የማቴሪያል ሁኔታዎች ሲለወጡም ከሞላ ጎደል የሰው ልጅ አስተሳሰብም እንደሚለወጥ በኢምፔሪካል ደረጃ የተረጋገጠ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የማቴሪያል ሁኔታዎችም ተለውጠው በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ሊኖረው በፍጹም አይችልም። እንደቤተሰብ ሁኔታ፣ አስተዳደግና የትምህርት አቀሳሰም የየግለሰቦችም አመለካከትና ነገሮችን መገንዘብ እንደዚሁ ይለያያል። አንደኛው በሰፊውና በጥልቀት ነገሮችን ሲመለከትና ለመተንተን ሲሞክር፣ ሌላው ደግሞ ነገሮችን በጠባብ ይመለከታል። አንደኛው ሰብአዊና ማህበራዊ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ለራሱ የሚያስብና በራሱ ዓለም የሚሽከረከር ይሆናል። በአንድ ቤተሰብም ውስጥ ሆነ በአንድ አካባቢ ተወልደው የተለያዩ ሰዎች የተለያየ አመለካከት ለምን እንደሚኖራቸው ምክንያቱ እንደዚህ ነው ብሎ መናገር በፍጹም አይቻልም። በሌላ ወገን ግን ፈሩን እስካለቀቀና ወደ ግጭት እስካላመራ ድረስ የተለያየ አስተሳሰብ መኖሩ ክፋት የለውም። አንድ ዐይነት አስተሳሰብ በሰፈነበት አገር ውስጥ ህይወት እራሱ ይሰለቻል። አንድ ዐይነት አስተሳሰብ በሰፈነበትና ክርክር ባልተለመደበት አገር ዕድገት በፍጹም ሊኖር አይችልም። ቋንቋ፣ ሙዚቃ፣ ሰነ-ጹህፍ፣ አርኪቴክቸርና ሌሎች ለአንድ ህብረተሰብ የኑሮ ጣዕም የሚሰጡት ነገሮች በሙሉ መዳበር አይችሉም። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የአብዛኛው ሰው አስተሳሰብ ውስን ይሆናል። አንድን ነገር መረዳት ያቅተዋል። ተማርኩ የሚለውም የዚህ ዐይነቱ አንድ ወጥ አመለካከት ሰለባ በመሆን ተመሳሳይና አሰልቺ ነገሮችን በመደጋገም ታዳጊውን ትውልድ ያደነቁራል። ከመጀመሪያውኑ ጭንቅላቱ በማይረባ ነገር ስለሚወጠር ከሱ ለየት ያለ አስተሳሰብ ሲመጣ ይደነግጣል፤ አሳሳች አስተሳሰብ ነው ብሎ በመገመት መጠራጠር ይጀምራል። በመቀጠልም የሚሆን የማይሆን በማውራት በሰዎች ዘንድ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ያደርጋል።
የስልጣኔን ታሪክ ለተመራመረ፣ የእርሻን ተግባርንና የዕደ-ጥበብን ሙያ ያልተማሩ ሰዎች ቢያፈልቁትምና ቢያዳብሩትም፣ እነዚህ ሁሉ መልክ መያዝ የጀመሩትና ትላልቅ ስልጣኔዎች ሊፈልቁ የቻሉት የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉን በከፍተኛ ደረጃ መጠቀም ከጀመረ ወዲህ ነው። ይሁንና ትላልቅ ስልጣኔዎችን የገነቡ፣ ለሂሳብና ለሳይንስ ምርምር የመጀመሪያውን መሰረት የጣሉ አገሮች፣ የየራሳቸውን ፊደሎች የፈጠሩና የቋንቋም መሰረት እንዲሆን ያደረጉ፣ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ በተለያየ መልክ የሚገለጹ ባህሎችን ያዳበሩ አንዳንድ አገሮች በዚያው የስልጣኔ ፈለጋቸው ሊቀጥሉበትና ወደ ከፍተኛው ደረጃ ሊጓዙ በፍጹም አልቻሉም። ይህንን ጉዳይ ለመረዳት የአገራችንን የህብረተሰብ ታሪክ ማጤኑ እጅግ ጠቃሚ ነው። ስለሆነም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ቀድሞ ከነበሩበት ቦታ በመሻገር ለምን ወደ ሳይንስና ወደ ቴክኖሎጂ የሚገለጽ ማህበረሰብ ሊፈጥሩ አልቻሉም? ለምንድን ነው እዚያው በዚያው በመንደፋደፍ በድሮው ታሪካቸውና ስልጣኔያቸው እየተዝናኑ አሁንም ከድህነትና ከረሃብ ያልተላቀቁት? በተለይም ባለፉት አርባ ዐመታት ትላልቅ ጭንቅላቶች የሚፈጠሩባት አገር ከመሆን ይልቅ ለምን ትናንሽ ጭንቅላቶች የሚፈልቁባት ወይም የሚወለዱባት አገር ለመሆን በቃች? በዚህ ጽሁፍ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ በጣም አዳጋች ነው። የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ትናንሽና ትላልቅ ጭንቅላቶች በምን መልክ እንደሚገለጹ ማሳየት ነው። ምክንያቶቻቸውን ሳይሆን በተለይም በአገራችን ምድር በትናንሽ አስተሳሰብ የተያዙትን ሰዎች ባህርይና አጥፊ ድርጊታቸውን ለማሳየት ነው። በዚያው መጠንም ትናንሽ ጭንቅላቶች በበዙባቸው አገሮች ውስጥ አንድ ህዝብ ተረጋግቶ መኖር እንደማይችልና የዕድገት ወይም የስልጣኔ ባለቤትም ለመሆን እንደማይችል ለማሳየት ነው። ስለሆነም የጽሁፉ ዋና ዓላማ ትናንሽ ጭንቅላቶች እንዴት ከትላልቅ ጭንቅላቶች እንደሚለዩ ለማሳየት ነው። ከዚህም በማለፍ ትናንሽ ጭንቅላቶች በነገሱበት፣ በተለይም ደግሞ የፖለቲካ መድረኩን በሚቆጣጠሩበት አገር ውስጥ አንድ አገር ወደ ውዝግብና ወደ ጦርነት አውድማ ውስጥ እንደምትወድቅ መረዳት ይቻላል። የትናንሽ ጭንቅላቶችን አስተሳሰብና ድርጊት ለመረዳት በመጀመሪያ የትላልቅ ጭንቅላቶችን አስተሳሰብ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ትላልቅ ጭንቅላቶች በምን ይገለጻሉ!
ፍልስፍናና ሳይንስ፣ ግጥምና ድርሰት፣ የሚያማምሩ ትላልቅ ህንፃዎችና፣ እንዲሁም የተለያዩ ነገሮችን የሚገልጹ ስዕሎች ልዩ ስጦታ ያላቸው ሰዎች የማሰብ ኃይል ውጤቶች ናቸው። በታሪክ ውስጥ እንደተመዘገበው የመጀመሪያው የፍልስፍናና የሳይንስ አባት የሚባለው በግብጽ አገር እንደተፈጠረና ከሱ በኋላ ለተነሱ ጥበብን ለሚፈልጉ መሰረት ጥሎላቸው እንዳለፈ ታሪክ ያረጋግጣል። ይህ ታላቅ ሰው ሄርመስ ትሪስሚግስቶስ ወይም ቶት በመባል ይታወቃል። የአስትሮኖሚ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የሳይንስና የአልኬሚ አፍላቂ እንደነበረና ለስልጣኔ መሰረት እንደጣለ ይነገራል። በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ መጽሀፎች እንደጻፈ ሲነገር፣ ሌሎች ደግሞ እነዚህ ሁሉ መጽሀፎች በአንድ ሰው ዕድሜ ውስጥ ሊጻፉ እንደማይችሉ ይናገራሉ። ይሁንና በእርግጥ እንደተመዘገበው ፒይታጎራስ የሚባለው የግሪኩ ፈላስፋ ዕውቀቱን ከግብጽ ቀሳውስት እንደቀሰመ ይነገራል። ከዚያ በኋላ እንደሶሎንና ፕላቶ የመሳሰሉት ታላላቅ ገዢዎችና ፈላስፋዎች ግብጽ አገር ፍልስፍናንና ጥበብን እንደተማሩና ወደ ግሪክ ከተመለሱ በኋላ ከአገራችው ሁኔታ በመነሳት ፍልስፍናና ሳይንስን ማዳበርና ማስፋፋት እንደቻሉ በሴኔጋሉ ፈላስፋና የፊዚክስ ምሁር በአንታይ ድዮፕና፣ እንዲሁም በአይሁዲው ተመራማሪ በማርቲን በርናል መጽሀፍ ውስጥ ሰፍረዋል።
ጥያቄው እዚህ ላይ ፍልስፍናና ሳይንስ መቼ እንደተፈጠሩ ለማሳየት ሳይሆን፣ ከእነዚህ ዐይነት ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ እንዴት ሊፈልቁ ቻሉ የሚለውን ለማስፈር ብቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እንደፒታጎራስ፣ ሶክራተስ፣ ፕላቶንና አርስቲቶለስ… ወዘተ. የመሳሰሉት ታላላቅ ፈላሳፋዎችና የሳይንስ ሰዎች ምን ዐይነት ጭንቅላት ቢኖራቸው ኖሮ ነው ጭንቅላታቸውን ለፍልስፍናና ለሳይንስ ምርምር ብቻ ያዋሉት? እንዴትስ ሊገለጽላቸው ቻለ? ምን ዐይነት ኃይል ነበር ተፈጥሮና ኮስሞስን እንዲቃኙ ይገፋፋቸው የነበረው? በአንድ ወቅትስ እነዚህን የመሳሰሉ የፍልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች በመነሳት እንዴትስ አድርገው በአካባቢያቸው የነበረውን ሁኔታ ማዳረስ ቻሉ? ከዚያስ በኋላ ይህ ዐይነቱ ምሁራዊ ዕውቀት የዓለም ስልጣኔ መሰረት እንዴት ሊሆን ቻለ? የሰውንም ልጅ ህይወት ለማቃለል ምን አስጨነቃቸው? አዕምሮአቸው ለምን ወደ ጦርነትና ወደ ተንኮል በመሰመራት የሰው ልጅ ህይወት በሙሉ የስቃይ ኑሮ ብቻ እንዲሆን ለማድረግ አልበቁም? እንደነዚህ ዐይነት የመሳሰሉ ታላላቅ ጭንቅላቶች ያላቸው ሰዎች ባይፈጠሩ ኖሮ የሰው ልጅ ዕጣ ምን ይመስል ነበር? እነዚህና የኋላ ኋላ ብቅ ያሉትና ለህይወታቸው ሳይፈሩ የካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎችን ቀኖናዊ አስተሳሰብ ትክክል አለመሆኑን በማሳየት ትክክለኛውን የስልጣኔ ፈለግ ለሰው ልጅ ያሳዩትን የሳይንስና የፍልስፍና ሰዎችን የህይወት ታሪክ ስንመለከት በሰው ልጅ መሀከል የአስተሳሰብ ልዩነት እንዳለ እንገነዘባለን። ወይም ደግሞ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችን አንድ ልዩ ኃይል የሰውን ልጅ ከጥፋት እንዲያድኑ ልኳቸው ይሆን?
የጥንቱን የግሪኩን ስልጣኔ ፈለግ በመከተል በአውሮፓ ምድር ተፈጥሮን መቃኘትና ሳይንሳዊ ዕውቀትን ማፍለቅና ማዳበር የጀመሩትን እንደ ጋሊሌዮ፣ ኮፐርኒከስ፣ ኬፕለር፣ ኩዛኑስ፣ የኋላ ኋላ የተነሱትን እንደ ላይብኒዝ፣ ካንት፣ ሄገል፣ ጎተ፣ ሺለር፣ ሁለቱ ወንድማማቾች ሁምቦልድ ተብለው በመጠራት የሚታወቁት፣ የሂሳብና የሳይንስ ተመራማሪ የነበሩት ጋውስና ሪማን፣ እንዲሁም የአልበር አይነስታይንን… ወዘተ. ስራቸውን ስንመለከት አምላክ የሰውን ልጅ ከጥፋት አድኑ ብሏቸው የላካቸው ይመስላል። ከዚህም ባሻገር እነዚህና ሌሎች የእንግሊዝ ፈላስፋዎችንና የሊበራል አስተሳሰብንና ለህግ ተገዢ መሆን ወይም ህግን ማክበር (The Rule of Law) ለአንድ ህብረተሰብ ተቻችሎ መኖር አስፈላጊ ነው ብለው ያፈለቁትን ስራቸውን ስንመለከት እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ባይፈጠሩና ግለሰብአዊ ጥረት ባያደርጉ ኖሮ የሰው ልጅ ዕጣ ምን ይሆን ነበር? ባጭሩ እነዚህና ሌሎች የክላሲካል ሙዚቃና የስዕል ሰዎች ስራ የሚያረጋግጡት በደንብ የዳበረና ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ባህርይና ድርጊቱን የመመልከት ችሎታ ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው የሰውን ልጅ ከጥፋት ለማዳን የሚችሉት።
ይሁንና በእነዚህ የተለያዩ ምሁራን ዘንድ ዕውቀትንና ምንጩን በሚመለከት የተለያየ አመለካከት ቢኖርም በአጠቃላይ ሲታይ መንፈሳቸው ከተንኮል የጸዳ ነበር ማለት ይቻላል። በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለ የሚረዱ ናቸው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ሁኔታ መሀከል መተሳሰር እንዳለና አንደኛው በሌላው ላይ ተጽዕኖ ማድረግ እንደሚችል የተገነዘቡ ናቸው። ስለሆነም ዲስፖታዊና ጨቋኝ አገዛዝ በሰፈነበት አገር ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ዕይታ ሊዳብር እንደማይችል አጥብቀው የተረዱ ናቸው።
የአውሮፓን የህብረተሰብ አወቃቀር ታሪክ ስንመለከት ህብረተሰብአዊ ለውጥ ሊመጣ የቻለው ለፖለቲካ ዓላማ ብቻ በሚታገሉ ወይም ደግሞ በገዢ መደቦች ፈቃድ አይደለም። በየአገሮች ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የቻለው የአንድን ህብረተሰብ ዕድገት ከልዩ ልዩ አንፃር መመልከት የቻሉና ወደ ውስጥ ምርምር ባደረጉ ግለሰቦች አማካይነት ብቻ ነው። ዕደ-ጥበብ፣ ንግድ ሲዳብሩና ከተማዎች ሲገነቡ የተገለጸላቸው ግለሰቦችም ብቅ ማለት ቻሉ። እነዚህ ልዩ ልዩ ምሁራዊ ኃይሎች ሃሳባቸውን በማጣመርና ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ ከላይ ሆኖ ጭቆናን ያሰፈነውንና ዕውነተኛ ስልጣኔ እንዳይመጣ የሚፈልገውን ኃይል በምሁራዊ ኃይል መዋጋት ቻሉ። ስለሆነም ስልጣን ላይ ያሉ የገዢ መደቦችና የሚከተሏቸውንና በጥቅም የተሳሰሩ ኃይሎችን ጭፍን ርዕዮተ-ዓለማቸውን በሳይንስና በፍልስፍና መሳሪያ መዋጋት ቻሉ። ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያሉ ኃይሎች እራሳቸውም የሰው ልጆች ስለሆኑና፣ ከሌላው እንደማይበልጡ በማሳየት ሰፊው ህዝብ በራሱ ላይ እንዲተማመንና የማሰብ ኃይሉን እንዲያዳብር መንገዱን አሳዩት። ይህ ዐይነቱ እየሰፋና እየጠለቀ የመጣ ብሩህ አስተሳሰብ የንጉሳዊና የአሪስቶክራሲውን፣ እንዲሁም የፊዩዳሉንና የካቶሊክ ቄሶችን ጭፍን አስተሳሰብ ማንኮታኮት ጀመረ። ወደ ታች ሲወርድ ደግሞ ስራና ፈጠራ የሰው ልጅ ማንነት መግለጫዎች በመሆን የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ተደረገ። የሰው ጭንቅላት በስራና በፈጠራ ስራ ሲወጠር ተንኮልና ሌላውን ማጥቃት ቦታ እንዳይኖራቸው እየተደረገ መጣ። በጊዜው እየሰፋ የመጣው በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ የስራ-ክፍፍልና ንግድ መዳበር የሰው አስተሳሰብ በዚህ ዐይነቱ ዙሪያ ብቻ እንዲሽከረከር አስቻለው። በዚህ መልክ ትናንሽና ሌላውን የሚያጠቁ አስተሳሶቦች እየተወገዱ ለመምጣት ቻሉ። ይህም የሚያመለክተው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ፊዩዳላዊ አስተሳሰብና ጭፍን ሃይማኖት ወይም አመለካከት ሲንኮታኮቱ ብቻ እንደሆነ ከአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ መማር እንችላለን። በተለይም በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ አስተሳሰብ ሲዳብርና ወደ ውጭ ወጥቶ ክርክር ሲደረግበትና ሌላውን ማስተማር ሲቻል ብቻ በተንኮል የሚገለጹ ትናንሽ አስተሳሰቦች ይወገዳሉ። ፖለቲካም ተንኮልን መተብተቢያ፣ አንዱን የሚያቀርብ፣ ሌላውን የሚያርቅ መሳሪያ ከመሆንና እንደ ግል ሀብት ከመቆጠር ተላቆ ህዝባዊ ሀብት በመሆን ታሪክ የሚሰራበት ሳይንሳዊ መሳሪያ ለመሆን ይበቃል ማለት ነው። ፖለቲካ በግልጽ አስተሳሰብንና ዕምነትን ማራመጃ እንጂ አዋቂ ነኝ የሚለውን በጭፍን በመከተል አገር አጥፊ መሳሪያ መሆኑን ያበቃል ማለት ነው። ሶክራተስ „ተናገርና ማንነትህን ላውቅ እችላለሁ“ እንዳለው የአስተሳሰብ ሞኖፖል በሌለበት ቦታ እያንዳንዱ ሃሳቡን የመግለጽ መብት ስላለው በሚናገረው ወይም በሚያስተጋባው ማንነቱን ማወቅ ይቻላል። ስለሆነም ግልጽ የሆነ አመለካከት በሚዳበርበትና ሃሳብ በሚንሸራሸርበት ማህበረሰብ ውስጥ ተንኮልና አንዱ ሌላውን ማጥቃት ቦታ አይኖራቸውም ማለት ነው።
ይህ ማለት ግን የአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክና ዕድገት ከግጭትና ከጦርነት የተላቀቀ ነበር ማለት አይደለም። በየኢፖኩ የሚፈጠሩ አዳዲስ ሁኔታዎች የኃይል አሰላለፍ ለውጥን በማስከተል ጦርነትና ህብረተሰብአዊ ግጭቶች ልማዳዊ በመሆን ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ምክንያት ለመሆን ችለዋል። በተለይም የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን የተቀዳጁ ኃይሎች የተወሰነ አስተሳሰብን ወይም የጦርነት ርዕዮተ-ዓለምን በመከተል ከድንበራቸው አልፈው ሌሎች አገሮችን አተራምሰዋል። የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች መነሳትና አገሮችን ወሮ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን በመግደል የታሪክን ጎማ ወደ ኋላ ለማሽከርከር መሞከር የኃይል አሰላለፍ መቀየር ውጤትና ሌሎች አገሮችን እንደተፎካካሪና እንደጠላት ከማየት የመነጨ አደገኛና ትናንሽ ጭንቅላት ያላቸው ሰዎች አስተሳሰብ ውጤት ነው። እኛ ብቻ ነን መሰልጠንና ማደግ፣ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂን መቀዳጀት ያለብንና የምንችለው ብሎ መዝናናትና ግብዝ መሆን ዋናው ምክንያት ትናንሽ አስተሳስቦች እየነገሱ ሲመጡ ነው። በተለይም የፋሽዚምን አነሳስ ስንመለከት ዋናው ምክንያት የዝቅተኛ መንፈስ ማየሉ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ ዝቅተኛ ስሜት ይሁዲዎች ለአውሮፓው በተለይም ለጀርመን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ያደረጉትን ታላቅ አስተዋፅዖ እንዳለ የካደ ነው። በ19ኛው ክፍለ-ዘመንና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ላይ ጀርመን በዕድገት እየመጠቀች ለመምጣት የቻለችው የይሁዲዎች ፈጠራ ስለታከለበት ነው። ሌላው ትልቁ የታሪክ ወንጀል ናዚዎች የአውሮፓው ስልጣኔ መሰረት የሆነውን የግሪኩን ስልጣኔ በመዘንጋታቸውና የአርያን ዘር ከሁሉም ይበልጣል ብለው በማሰባቸው ነው። እነሱ ብቻ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች እንደሆኑ አምነው መቀበላቸው ግብዝ እንዲሆኑና በአውሮፓው ምድር ሁለ-ገብ የሆነ ጦርነት እንዲያውጁ ገፋፍቷቸዋል።
ይህ ዐይነቱ የተሳሳተ ወይም የተበላሸ አስተሳሰብ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነቱን ከተቀዳጀ ወዲህ ጎልቶ የወጣና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን መቀስቀሻ መሳሪያ የሆነ ነው። የአሜሪካንን የበላይነት ያልተቀበለ ወይም ለእሱ ያላጎበደደ ሁሉ እንደጠላት እየታየ ጦርነት የሚካሄድበት የውጭ ፖለቲካ ስትራቴጂ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አሜሪካን በዓለም አቀፍ ደረጃ የበላይነቱን ለማስፈን ሲል የግዴታ በየአገሮች ውስጥ አምባገነናዊ አገዛዞችን በመደገፍና በተዘዋዋሪ የየመንግስታቱን የመንግስት ፖለቲካ በመቆጣጠር የአመጽ ፖለቲካ ለማስፋፋት ችሏል። በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ከኢኮኖሚው መሰረት ጋር ሊጣጣሙ የማይችሉ የሚሊታሪ፣ የፀጥታና የፖሊስ አውታሮች በመዘርጋታቸው ለኢንዱስትሪ ተከላና ለስራ መስክ ፈጠራ፣ ለተቋማት መገንቢያና ለከተማዎች መቆርቆሪያና እንዲሁም ለሌሎች ለአገር ግንባታ ነገሮች ላይ ሊውል የሚችለው ገንዘብ በእነዚህ ምርታማ ባልሆኑ ተቋማት ላይ እንዲውል ተገዷል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየአገሮች ውስጥ የፈረጠሙ የመንግስት ባለስልጣናት ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር በማበር ከውስጥ የተስተካካለና ሰፊውን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይመጣ ለማገድ በቅተዋል። ከዚህም በላይ እንደዚህ ዐይነት መሪዎችና መንግስታት ስትራቴጂካሊ ስለማያስቡ ህዝቦቻችው ሊወጧቸው የማይችሏቸውን የተወሳሰቡ ችግሮችን አስታቅፈዋቸው ይሄዳሉ። የአሜሪካ መንግስት የሚከተለው የውስጥም ሆነ የውጭ ፖለቲካ በሆበስ ፍልስፍናዊ አመለካከት ላይ የተመረኮዘ ሲሆን፣ እንግሊዝና አሜሪካ፣ እንዲሁም አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ሌሎችን አገሮች ለመቆጣጠር ሲሉ እንደጠላት በመፈረጅ የሚከተሉት ስትራቴጂ ነው። እዚህ ላይ ግን ሆበስ የሰውን ልጅ አስተሳሰብ እንደ ቀበሮ ሲያመሳስልና፣ አንዱ በሌላው ላይ የሚነሳና እንደጠላት አድርጎ ነው የሚያየው ብሎ ሲሰብክ የአስተሳሰቡን አደገኛነትና ወደ ርዕዮተ-ዓለም በመለወጥ የጥቂት ኃይሎች መሳሪያ ሊሆን እንደሚችል የተገነዘበ ነበር ብሎ ለመናገር በፍጹም ያስቸግራል። ያም ሆነ ይህ አሜሪካም ሆነ የተቀሩት የአውሮፓ አገሮች የሚያራምዱት ፖለቲካ የሚያረጋግጠው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ታላላቅ ጭንቅላቶች ቢፈጠሩም፣ እንዲሁም ደግሞ ፖለቲካን ከፍልስፍናና ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ ጋር አጣምረው ቢያስተምሩም፣ የፖለቲካ ስልጣንን የሚቀዳጁ ኃይሎች ምሁራዊ መሰረት የሳሳና በርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ ብቻ የሚሽከረከር በመሆኑ በተለይም የውጭው ፖለቲካ ሌሎች አገሮችን ማዳከሚያና እንዲያም ሲል መበተኛ መሳሪያ ወደ መሆን ተለውጧል። ይህ ዐይነቱ የበላይነትን ማረጋገጫ ፖለቲካ ሰሞኑን እንደምንከታተለው በአገራችን ላይም እየታየና ብዙዎቻችንን እያነጋገረ ይገኛል። የአሜሪካን መንግስት የህዳሴውን ግድብ አስታኮ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚያደርገው ጫና የዚህ ዐይነቱ የማን አለብኝነትና፣ እናንተ ሳትሆኑ እኔ ነኝ የእናንተን የመኖርና ያለመኖር ዕድል መወሰን የምችለው ከሚለው የግብዝ ፖለቲካ የመነጨ አስተሳሰብ ነው። ይህንን ዐይነቱን ግብዝነት የሰማነው ደግሞ ሁላችንም እንደ አቅማችን 124ኛውን ዓመት የአደዋ ድል በዓል እየተዝናናን በምናከብርበትና በነጭ ወራሪ ኃይል ድልን የተቀዳጀች ጥቁር አፍሪካዊ አገር ኢትዮጵያችን ብቻ ነች ብለን በምንኮራበት ወቅት ነው። ለማንኛውም የአሜሪካንም ሆነ የተቀሩት የአውሮፓ የመንግስታት መኪናዎች ሙሉ በሙሉ በሚሊታሪ-ኢንዱስትሪ ውስብብስብ(Military-Industrial Complex) ቁጥጥር ስር ስለወደቁና በሎቢይስቶችም ስለተሰገሰጉ የመንግስታት መኪናዎች የጦርነት መቀስቀሻና ማስፈራሪያ መሳሪያ ለመሆን በቅተዋል። ወደ ውስጥ ስንመጣ ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው ፖለቲካ ዘረኞችንና የፋሺሽት ኃይሎችን እንዲፈለፈሉ በማድረግ በውጭ አገር ሰዎች ላይ ጦርነት እንዲያውጁ ለማድረግ በቅቷል። በተለይም ንዑስ ከበርቴው የዚህ ዐይነቱ ዘረኛ አመለካከት ሰለባ በመሆን ሳያውቀው አገሩን ወደ አደገኛ ሁኔታ ላይ በመለወጥ ይገኛል።
ትናንሽ ጭንቅላቶች በምን ይገለጻሉ!
በተለይም ካለፉት አርባ ዐመታት ጀምሮ በአገራችን ምድርም ሆነ በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና በአንዳንድ የካፒታሊስት አገሮች የሚታየው ግብዝነት የተሞላበት ፖለቲካ ዋናው ምክንያት ጭንቅላት በትናንሽ አስተሳሰብ እየተወጠረ ስለመጣ ነው። ትናንሽ አስተሳሰብ እንደየሰውና እንደየአገሩ ቢለያይም፣ በተለይም ፊደል ቆጥረናል በሚሉት ላይ ጎልቶ የሚታይና ለዕድገትና ሰፋ ላለ ህብረተሰብአዊ ለውጥና የሃሳብ ለሃሳብ መለዋውጥ እንቅፋት በመሆን በተለይም እንደኛ ያለውን አገር ወደ ጦር አውድማነት በመለወጥ ላይ ነው። ይህንን ዐይነቱን ችግር ለመረዳት በአገራችን ላይ ማትኮሩ ነገሩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል።
ባለፉት አርባ ዐመታት የአገራችን ህዝብ ሰላምን አግኝቶ አያውቅም። በአብዮት ስም፣ ለብሄረሰቤ መብት እታገላለሁ በሚል ሳቢያና፣ ጉግ ማንጉግ መጣ ብሎ ያለ የሌለውን ኃይል በማስተባበር በተንኮልና በጦርነት ላይ የተሰማራውና፣ ከንጉሳዊ አገዛዝ መውደቅ በኋላ ስልጣንን የተቀዳጁት ሁለት አገዛዞች፣ እነዚህ ሁሉ ኃይሎች በሙሉ ህዝባችንን ፍዳውን አሳይተውታል። የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መሳሪያ በመሆን ዛሬ ላለው ትርምስ ሁኔታ አመቻችተው አልፈዋል። የተቀሩት ደግሞ አሁንም ቢሆን አገርን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ለማውደም እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ። ዋና ዓላማቸውም ስልጣኔን ማምጣት ሳይሆን ስልጣን ላይ ቁጥጥ ለማለት ብቻ ነው። በተለይም የህወሃት አገዛዝ አገራችን ዛሬ ለደረሳባት የውስጥና የውጭ ጭንቀትና ግፊት ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን እንደ አገሩ ሳይሆን እንደጠላት በመፈረጅ ህዝብን ከህዝብ ሲያጋጭ ከርሟል። እነዚህ ዐይነት አሳዛኝና አደገኛ ድርጊቶች በሙሉ ከትናንሽ ጭንቅላቶች የሚፈልቁ ናቸው።
ከአብዮቱ በፊት የነበረውን የተማሪውን እንቅስቃሴ ታሪክ ለተመለከተ፣ የዲሞክራሲንና የመሬት ላራሹን መፈክር አንግቦ ቢነሳም፣ እዚያው በዚያው ከፊዩዳል አሰተሳሰብ የፀዳ አልነበረም። ግልጽ ለሆነ ውይይት የተዘጋጀና፣ የነገሮችን ሂደትና መተሳሰር፣ እንዲሁም የመንግስቱን መኪና አወቃቀርና ፖለቲካውን በኢንላይተንሜንት መነጽር በመረዳት ጠቅላላውን ሁኔታ በመገምገም የትግል ስትራቴጂ ለመቀየስ የሚችል ኃይል አልነበረም። አስተሳሰቡ በጣም ጠባብ ስለነበር ሌላው የሚለውን ለመስማት የሚፈልግ አልነበረም። እራሱን ከሌላው አጉልቶ በማሳየትና ወጣቱን በማሳሳት ህዝባችን የራሱን ታሪክ እንዳይሰራ ዕንቅፋት ለመፍጠር ችሏል። ይህ ማለት ግን እንደዚህ ዐይነቱ አደገኛ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያሳስቡ ግለሰቦች አልነበሩም ማለት አይደለም። የአንዳንድ ድርጅቶችና የግለሰቦች ጥረት ቢኖርም ሁልጊዜ በአሽናፊነት ለመውጣት የሚችለው የተሻለ አስተሳሰብ ያለውና የረጋ ትግል ማድረግ የሚፈልግ ኃይል አይደለም። እንደተለመደው በፖለቲካ ትግል ውስጥ ሁልጊዜ በአሸናፊነት የሚወጡት የሰብአዊነት አመለካከት ያላቸውና የተስተካከለ ዕድገት አራማጆች ሳይሆኑ ህዝብን የሚያታልሉና የሚያወናብዱ ኃይሎች ብቻ ናቸው።
ለማንኛውም የአገራችንን የምሁር እንቅስቃሴ ታሪክ ለተመለከተ ትላንትም ሆነ ዛሬ በአገራችን ምድር የተከሰተው አስቀያሚ ሁኔታ ካለምክንያት አይደለም። በህብረተሰባችን የተበላሸ አወቃቀር ምክንያት የተነሳና አገራችንም ከውጭ ለሚመጣ የተሻለና ጭንቅላትን ብሩህ ለሚያደርግ አስተሳሰብ የተዘጋ ስለነበር የህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ግብታዊ በሆነና እጅግ በቀጨጨ የአስተሳሰብ ክልል የሚወሰን ነበር። በስራ-ክፍፍልና በንግድ እንቅስቃሴ የሚገለጽ ህዝባዊ ግኑኝነትና የሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጥ ለመዳበር ባለመቻሉ በአገሪቱ ምድር ይከሰቱ የነበሩ አደጋዎች በሙሉ የእግዚአብሔር ቁጣ ተደርገው የሚወሰዱ ነበሩ። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና ተደጋጋሚና አሰልቺ ኑሮ በህዝቡ አስተሳሰብ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። ስለሆነም ሰፊው ህዝብም ሆነ ምሁሩ ወደ ውስጥ የመመልከትና በነገሮች መሀከል ያለውን መተሳሰር የመገንዘብና ጥያቄ የማቅረብ ባህልም ሆነ ኃይል አልነበራቸውም። ማሰብ፣ የነገሮችን አፈጣጠር መመልከት፣ መመራመር፣ ጥያቄ መጠየቅና መልስ ለመፈለግ መሞከር…ወዘተ. እንደነዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ የሳይንስና የፍልስፍና መሳሪያ የሆኑ መሰረተ-ሃሳቦች ስላልተለመዱ አብዛኛው ነገር ይደረግ የነበረው በደመ-ነፍስ በመመራት ነው ማለት ይቻላል። በተለይም ደግሞ የሃሳብ ሞኖፖል በሰፈነበት፣ ወይም ደግሞ ከዚህ ውጭ ማሰብ ስህተት ነው ተብሎ ተቀባይነትን ባገኘበት አገር ምሁሩም ሆነ ሰፊው ህዝብ ወደ ውስጥ የመመልከትና ጥያቄ የመጠየቅን ባህል ማዳበር አይችሉም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በተለይም በዛሬው ወቅት አይሎ ይገኛል። አብዛኛው የሚፈልገው ስርዓት ያለውና ሳይንሳዊ ጥናት እንዲካሄድ ሳይሆን የተወሰኑ ሰዎችን በመጋበዝ በተደጋጋሚና በሚያሰለቹ ነገሮች ላይ ብቻ መነታከርን ነው የሚመርጠው።
ከዚህ ስንነሳ በየካቲት 66 ዓ.ም አብዮት ሲፈነዳ እንደዚያ ዐይነቱ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ መከሰቱ የሚገርም አይደለም። ትላንትም ሆነ ዛሬ የግንባር ቀደምትነትን ሚና ይዘናል የሚሉ አንዳንድ ግለሰቦች በአብዮቱ ወቅት የደረሰውን የወንድማማቾች እልቂት ከግራ አስተሳሰብ ጋር ለማያያዝ ነው የሚሞክሩት። በእኔ ዕምነት ይህ ዐይነቱ አመለካከት በፍጹም ትክክል አይደለም። በጣም አደገኛ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካን ትርጉም የማይረዱ የቀኝ ኃይሎች ስልጣንን እንዲጨብጡ በማድረግ አጠቃላይ ጦርነት እንዲፈጠር የሚጋብዝ አደገኛ አካሄድ ነው። እንደዚህ ዐይነቱን ውንጀላ የሚሰነዝሩ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የአገራችንን የህብረተሰብ ታሪክ አወቃቀር ያልተረዱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት አገር ውስጥ የሰዎች አስተሳሰብ ነገሮችን በጥልቀት የመመልከት ኃይሉ የጠበበ እንደሆነ ያልተረዱና ሊረዱ የማይችሉ ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ ምሁራዊ አስተሳሰብ በዳበረበትና ግልጽ ክርክር በተለመደበት አገር የሰዎች አስተሳሰብና የነገሮችን አመጣጥ ለመረዳት የሚኖረውን አዎንታዊ ሚና ያልተገነዘቡና ለመገንዘብም የማይፈልጉ ናቸው። የእነዚህ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ዋናው ችግር የሚጠሉትን ርዕዮተ-ዓለም የቲዎሪ መሰረት በደንብ አላማጥናቸው ነው። የተለያዩ አዋቂዎች የጻፉትን በማንበብ የራሳቸውን ፍርድ ለመስጠት የሚችሉ አይደሉም። በሌላ ወገን ደግሞ ያላደጉበትን፣ ከመንፈሳቸው ጋር ያላዋሃዱትንና በደንብ ያላብላሉትን የነፃ ገበያ ፖሊሲና የሊበራል ዲሞክራሲን ፖለቲካ እንከተላለን በማለት በተለይም ወጣቱን ሲያሳቱት ይታያል። ይሁንና ግን በአውሮፓ ምድር ውስጥ ካፒታሊዝምና የሊበራል ዲሞክራሲ እንዴት እንዳደጉና ወደዛሬው የዕድገት ደረጃ ላይ እንደደረሱ በጽሁፍ ሀተታ ሰጥተውም ሆነ ገለጻ አድርገው አያውቁም። በእነዚህ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ዕምነት ካፒታሊዝምና የሊበራል ዲሞክራሲ ስርዓት ካለምንም ግጭት የተፈጠሩ ናቸው። በየአገሮች ውስጥ በአንድ በኩል የአሪስቶክራሲውን ስርዓት በሚደግፉና እንዳይፈርስም አጥበቀው በሚታገሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሊበራል ዲሞክራሲንና የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በሚፈልጉ ኃይሎች መሀከል ምንም ትግል ወይም ጦርነት አልተካሄደም። በእነሱ አስተሳሰብና ግምት የሊበራል አስተሳሰብ ከሰው ልጅ ጋር የተፈጠረ አስተሳሰብ ስለሆነ በህብረተሰብ የታሪክ ሂደት ውስጥ ቀስ በቀስ ንቃተ-ህሊና ሲዳብር የሚያድግና የበላይነትን የሚይዝ አስተሳሰብ አይደለም። ስለሆነም በተለይም ቀደም ብሎም ሆነ ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ የተፈጠረውን የገጠሩን ህዝብ ከመሬቱ ማፈናቀልና ወደ ከተማዎች እንዲሰደድ ማድረግ፣ እነዚህ ሁሉ ለካፒታሊዝም ዕድገት መነሻዎችና የሀብት ክምችት መሳሪያዎች እንደሆኑ በፍጹም አይገነዘቡም። ከዚህም በላይ ካፒታሊዝም በማደግ ላይ እያለ በብዙ አገሮች ድህነትና በሽታ የተስፋፉ ለመሆናቸውና፣ ለአቅመ-አዳም ያልደረሱ ሴቶችም ሆነ ወንድ ልጆች በኢንዱስትሪ ውስጥ ተገደው ይሰሩ እንደነበር የሚያውቁት ነገር የለም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ካፒታሊዝም ካደገና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተስፋፋም በኋላ በየአገሮች ውስጥ ያስከተለውን ያልተስተካከለ ዕድገት በደንብ ያላጠኑና፣ የካፒታሊዝምን ዕድገት ከግጭትና ከብዝበዛ ነፃ እንደሆነና ሁሉም ነገር በስምምነትና በሰላም እንደተፈጠረ አድርገው ነው የሚረዱት። ያም ሆነ ይህ፣ አንድን ድርጊት በጥቁርና በነጭ እየሳሉ ጥፋቱ ከዚህ የመነጨ ነው፣ የግራ አስተሳሰብ መከተል ከጀመርን ወዲህ ነው ነገሮች ሁሉ እየተበላሹ መምጣት የጀመሩት ብሎ መናገርና አደገኛ ቅስቀሳ ማካሄድ ወደ ጤናማ ውይይትና የአገር ግንባታ ሙኩራ እንዳናመራ የሚያግደን ነው። ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ ትንሽ አስተሳሰብና ትንሽ ጭንቅላት መላቀቅ በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ አገር ሊያድግና ሊበለጽግ የሚችለው የተለያዩ አስተሳሰቦች ክርክር ሲደረግባቸውና በደንብ ሲብላሉ እንጂ በጭፍን አንድን አስተሳሰብ ወይም ርዕዮተ-ዓለም በመከተል አይደለም።
ለማንኛውም በዚህ ላይ በሰፊው ሳልቆይ፣ በሁላችንም ዘንድ ያለው ትልቁና ዋናው ችግር እኔንም ጨምሮ በዕውነተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ መንፈስ አለመታነፃችን ነው። በፕላቶናዊ ወይም በላይብኒዛዊ ዕውቀት ሳይሆን በትናንሽና በተበጣጠሰ ዕውቀት በታነፀ ጭንቅላት በመነሳትና ግብዝ በመሆን ታላቁን የሰውን ልጅ ፕሮጀከት መንደፊያ የሆነውን ፖለቲካ አገር መገንቢያ ሳይሆን፣ መነታረኪያና አገር ማፍረሻ መሳሪያ ማድረጋችን ነው። ይህ ዐይነቱ አደገኛ አስተሳሰብ የአምባገነንነትና የፋሺዝም መነሻ ምክንያት ነው። እንደተከታተልነውና አገራችንና ህዝባችን ያሉበት ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው ይህ ዐይነቱ ግብዝነት የተሞላበት ፖለቲካ አገራችን ውስጥ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብርና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የሚመረኮዝ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ እንዳንገነባ አግዶናል። አሁንም ድረስ ዕውነተኛ የፖለቲካ ዲስኮርስ ለማዳበር አልቻልንም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ችኮ ባህርይና አልበገርም ባይነት ጥርጣሬንና አለመተማመን ማሳደሩ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ጥንካሬና ትብብርም እንዳይኖረን ለማድረግ በቅቷል። ይህ ሁኔታ በራሱ የውጭ ኃይሎች በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ገብተው እንዲፈተፍቱና እንዲከፋፍሉን አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
ያም ሆነ ይህ ትናንሽ ጭንቅላት ያላቸውና በትናንሽ አስተሳሰብ የታነፁ ሰዎች የአንድን ህብረተሰብ ታሪክ በተጣመመ መልክ ያቀርባሉ። የታሪክን ውጣ ውረድነትና፣ በየኤፖኩ የሚሰሩ ስራዎችንና አላግባብ ድርጊቶችን በዚያን ጊዜ ከሰፈነው ዝቅተኛ ንቃተ-ህሊና ሁኔታ የመነጨ መሆኑን በፍጹም ለመረዳት አይችሉም። በአገራችን የተፈጠረውን ችግር ከግራ ርዕዮተ-ዓለም ጋር ለማያያዝ ይሞክራሉ። ሌሎች ተበድለን ነበርን የሚሉ ኃይሎች ደግሞ የህብረተሰባችንን ታሪክ እንዳለ የጨቋኝ ስርዓት የሰፈነበት ነበር በማለት ወደ ተሳሳተ ድምዳሜና የትግል ስልት ተሻግረዋል። ስለሆነም በጊዜው በግብታዊነት የተሰሩ ጥሩ ድርጊቶችንና ባህሎችን እንዳለ ይዘነጋሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ከአምስት መቶና ከስድስት መቶ ዐመት በፊት ቆሜለታለሁ የሚሉት ብሄረሰብ በምን ዐይነት የማቴሪያል ሁኔታ ይኖር እንደነበረና፣ ከተፈጥሮ ጋር የነበረውን ግኑኝነት ለመረዳት አይጥሩም። በትናንሽ አስተሳሰብ በታነፁ ሰዎች ዕምነት አንድን ማህበረሰብ ወደ ፊት እንዳይራመድና የስልጣኔ ባለቤት እንዳይሆን የሚያግቱት ነገሮች እንዳሉ በፍጹም አይታወቅም። በሌላ ወገን ደግሞ ባህል ቆሞ እንደሚቀር(Static) ነገር አድርገው በመቁጠር ከሌላ አካባቢ የሚመጣ ባህል የማዳበር ኃይል እንዳለው በፍጹም አይረዱም። በህዝቦችና በብሄረሰቦች መሀከል በተለያየ መልክ በሚደረጉ ግኑኝነቶች አንድ ባህል ዕምርታን እንደሚያገኝና በሰውም አስተሳሰብ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በፍጹም ለመረዳት አይፈልጉም። በመሆኑም የሌላውን ባህል የወራሪ ባህል አድርገው በመቁጥር የባህልን ውስጣዊ-ኃይል የዕድገት አጋዢነት በማይሆን መልክ በመተርጎም በህዝብ ዘንድ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። በዚህ መልክ የአንድን ህብረተሰብ ታሪክ እንዳለ በመካድና የውጭ መሳሪያ በመሆን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር በቅተዋል። በአጭሩ አንድ ህዝብ የዝንተ-ዓለሙን በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ሳያውቁት ከባድ ጥፋት ሰርተዋል፤ እየሰሩም ነው። እጅና እግር ወይም የፍልስፍና መሰረት የሌለው ፖለቲካቸው እንደምናየው እያጋለጣቸው ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ድንቁርናቸውን እያስመሰከሩ ነው። አማራጭ መፍትሄ ለማቅረብ የማይችሉም መሆናቸውን እያሳዩን ነው።
በአለፉት አርባ ዐመታት በኢትዮጵያ ምድር በፖለቲካ ስም የተፈጸመውን ወንጀል ካለብዙ ምርምር በምንቃኝበት ጊዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ የቱን ያህል ትናንሽ ጭንቅላት ባላቸው ሰዎች ተይዞ እንደነበረና ዛሬም እንደተያዘ መረዳቱ ከባድ አይሆንም። ስለሆነም በዚህ ዐይነቱ ትናንሽ ጭንቅላት ባላቸው ሰዎች አማካይነት ነው አገርና ባህል ሊፈራርሱ የቻሉት። በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ህይወቱ እንዲሰዋ ለመደረግ የበቃው። የመቶ ዓመት የቤት ስራ እንሰጣችኋለን ብሎ መነሳትና ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር በራስ ታሪክና በአገር ላይ ጦርነት ማወጅ እነዚህ ሁሉ የሚያረጋግጡት ፖለቲከኛ ነን ባዮች የቱን ያህል በትናንሽ አስተሳሰብ እንደተያዙና ትናንሽ ጭንቅላቶችም እንዳላቸው ነው የሚያረጋግጠው። የአንድን አገር ታሪክ የመቶ ዐመት ታሪክ ብቻ ነው ብሎ በመናገርና በማስፋፋት ብሄረሰብን ከብሄረሰብ፣ ግለሰብን ከግለሰብ ማጋጨትና የማይፈልጉትን ሰው እንዲጠፋ ማድረግ ዋናው ምክንያቱ ፖለቲከኞቻችን በትናንሽ ዕውቀት ስለታነፁና ትናንሽ ጭንቅላቶች ስላላቸው ነው። ትናንሽ ጭንቅላቶች ያላቸው ሰዎች በዚህ ዐይነቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ለዝንተ-ዓለም ስልጣን ላይ የሚቆዩ ስለሚመስላቸው አንድ ቀን ከታች በሚነሳ ህዝባዊ ማዕበል ተጠራርገው እንደሚጠፉ በፍጹም ሊገነዘቡ አይችሉም። ትናንሽ ጭንቅላቶች ያላቸው ሰዎች በራሳቸው ስለማይተማመኑ የአገርን ገበና ለውጭ ኃይል አሳልፈው በመስጠት አንድ ህዝብና አገር ታሪክን እንዳይሰሩ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ ትናንሽ ጭንቅላት ያላቸው ሰዎች በተንኮል የታነፁ ስለሆነ ስለሰው ልጅ ምንም ዐይነት ርህራሄ የላቸውም። በቅናት የተወጠሩም ስለሆነ ይበልጠኛል ብለው የሚገምቱትን ሰው ለማጥፋት የማይፈነቅሉት ዲንጋይ የለም። እንደዚህ ዐይነት ሰዎች በልባቸው ውስጥ ምንም ዐይነት ፀፀት የሌላቸውና ድርጊታቸውንም ወደ ውስጥ በመመልከትና በማመዛዘን ራሳቸውን ለመመርመር የሚችሉ ስላይደሉ ቀን ከሌት ሆን ብለው የሚሰሩትና የሚያስቡት ስለተንኮል ነገር ብቻ ነው። ስለሆነም ማንኛውንም ግለሰብንም ሆነ አገርን ከሚጎዳና ከሚበታትን ተግባር በፍጹም አይቆጠቡም። በውሸት ዓለም የሚኖሩ፣ ወንጀል ሰርተው የሚክዱና፣ ትልቅና አሳቢ ሰው እንደሆኑ ለማሳመን የሚሞክሩ፣ እነሱ ተበዳዮች ሌላውን ተበዳይ አድርገው የሚናገሩና የሚወነጅሉ ናቸው። ስለሆነም በትናንሽ አስተሳሰብ የታነፀ ጭንቅላት በምንም ዐይነት ሊቃናና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም። ስራው ሁሉ ጥፋትና ተንኮል ነው። አንድ ሰው ዲሞክራትና ሊበራል ለመሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ከዚህ አስተሳሰብ ጋር ማደግ አለበት። ጭንቅላቱ ልክ ፍሬ እንደሚሰጥ ችግኝ በየጊዜው መኮትኮትና እንክብካቤ ማግኘት አለበት። ይህ ብቻ ሲሆንና በአንድ አካባቢ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሲያብብ ታዳጊ ትውልድም ዲሞክራሲና ነፃነት ምን እንደሆኑ መገንዘብ ይችላል።
ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ዐይነቱ ትናንሽ ጭንቅላትና አስተሳሰብ በአገራችን ምድር ከተስፋፋና አገርንና ባህልን ማውደም ከጀመረ ዘመናት አልፈዋል። በየጊዜው እየተሻሻለ የሚመጣ ሳይሆን አዳዲስ አዋካቢዎች በመፈጠር አገራችን የጦርነት አውድማ እንድትሆን የማይሰሩት ስራ የለም። እነዚህ ዐይነት ሰዎች ዲግሬ ጨብጠናል፣ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አለን ቢሉም በስልጣን ጥማት የታወሩ ስለሆነ አገር ተበታተነ አልተበታተነ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አለቀ አላለቀ ጉዳያቸው አይደለም። በውሽት ዓለም ውስጥም ስለሚኖሩና አስተሳሰባቸውም ቁንጹል ስለሆነ ምንም ዐይነት ጉዳት ካላደረሰባቸው ጋር ሳይሆን ዕድሜያቸውን ሁሉ ሲያሰቃየቸው ከሰነበተ ሰው ወይም ኃይል ጋር ቁጭ ብለው ቢበሉ ይወዳሉ። የደረሰባቸውን ወንጀል በሙሉ በመርሳትና በመካድ በዝቅተኛ ስሜት በመወጠር ምንም ጉዳትና በደል ያላደረሰባቸውን በጅምላ ይጠላሉ። የእነዚህ ሰዎች ትልቁ ችግር ጭንቅላታቸው በዝቅተኛ መንፈስ ስለተወጠረ የአንድን ህብረተሰብ ታሪክ በተሳሳተ መልክ በመተርጎምና በማስተጋባት ትላልቅ ሰዎች ሆነው ለመቅረብ መሞከሩ ላይ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ ትናንሽ ጭንቅላት ያላቸው ሰዎች ታሪክን ሊሰሩ የሚችሉ አይደሉም። በራሳችው ላይ ዕምነት የሌላቸው ናቸው። በአንድ በኩል ራሳቸውን ከፍ አድርገው ለማሳየት ይጥራሉ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ለውጭ ኃይሎች በመሰለል ታዳጊ ትውልድ እንዲዘናጋ ያደርጋሉ። እዚያው በዚያው ደግሞ የራሳቸውን ዜጋ ዝቅ አድርጎ በማየት የውጭ ኃይሎች ተገዢ ሆኖ እንዲቀር ያደርጋሉ። በተለይም በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስም አንድ አገር በተስተካከለ መልክ እንዳያድግ በማድረግ የአገር ሀብት እንዲዘረፍ ያደርጋሉ። በገበያ ኢኮኖሚ ስም ጤናማና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ዕድገት እንዳይመጣ እንቅፋት በመፍጠር ወይም በማሳሳት በሀብታምና በደሀ መሀከል ትልቅ የገቢ ልዩነት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ትናንሽ ጭቅላትና አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ቴክኖሎጂ፣ ፀረ-ጥበብና ፀረ-ስነጽሁፍ ናቸው። አንድን ህብረተሰብ ሊያያይዙና ጥንካሬ ሊሰጡ የሚችሉ ጥበባዊ ስራዎችን በሙሉ ይጠላሉ። በአንፃሩ በህዝባቸው ድህነትና ደካማነት ይደሰታሉ። በተለይም የመንግስት መኪናን ተገን በማድረግ ሰፊው ህዝብ፣ በተለይም ወጣቱ የእነሱን ኢ-ሳይንሳዊ ፈለግ እንዲከተል በማድረግ አንድ አገር በተሟላ መልክ እንዳያድግና በሁሉም መልክ የሚገለጽ የአስተሳሰብ ዕድገት እንዳይፈጠር ያደርጋሉ። ባጭሩ ትናንሽ ጭንቅላቶች ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ስግብግብነትን ያስቀድማሉ። የስራ ባህልና ፈጠራ ስራዎች እንዲዳብሩ ሳይሆን፣ ማታለልና ኃላፊነት የጎደለው ስራ እንዲስፋፉና የአንድ ህዝብ ባህልና የአሰራር ኖርም እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር የአንድ አገር እሴትና ባህል እንዲጠፋ ያደርጋሉ።
በዚህ መልክ የአገራችን ፖለቲካ በውሸታሞች፣ በከሃዲዎች፣ በአገር ሻጮች፣ በሰላዮችና የበሉበትን ወጪት ሰባሪዎች፣ በአጠቃላይ ሲታይ ርህራሄ በሌላቸው ሰዎች ተይዟል። ይህ ዐይነቱ አስተሳስብ በሁሉም ዘንድ የሚንፀባረቅና በአወቅኹኝ ባይነት ህብረተሰቡን የሚያዋክብ አደገኛ አካሄድ ነው። የምሁራዊ ኃይልና መሰረት የመነመነ ስለሆነ ወደ ውጭ በመውጣት እንደዚህ ዐይነቱን አደገኛ አስተሳሰብና ግብዝነት ለማጋለጥና ለመዋጋት በፍጽም አይቻልም። የአገራችንን ሁኔታና የሰፈነውን አደገኛ አስተሳሰብ ሳወጣ ሳወርድ የደረስኩበት ድምዳሜ ከዚህ ዐይነቱ አሳሳቢ ሁኔታ ለመውጣት በጣም አስቸጋሪ ይመስለኛል። በስልጣን ላይ ያለውም ኃይል በትናንሽ ነገሮች የተወጠረና የራሱን ስልጣን ለመጠበቅ ደፋ ቀና የሚል ስለሆነ በአገራችን ምድር የተንሰራፋውን አደገኛ አመለካከትና ሁኔታ በመገንዘብ የእርማትና የመንፈስ ተሃድሶ ዘመቻ ለማካሄድ ጊዜም ሆነ ችሎታ ያለው አይመስልም። ከእንደዚህ ዐይነቱ የቀጨጨ አስተሳሰብ ለመላቀቅ ከተፈለገ የግዴታ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል። አንድን አገርና ህዝብ፣ እንዲሁም ተከታታዩን ትውልድ የሚመለከት በመሆኑ የነገሩን አደገኛነት ከራስ ጥቅምና ዝና ባሻገር መመልከቱና በቂ ዝግጅት ማድረጉ ሊታለፍ የሚችል ጉዳይ አይደለም። መልካም ግንዛቤ!!