የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

በሰባት ዓመት እድሜዬ አካባቢ ተቤታችን አጥር ግቢ ውጪ ስጫወት ሁለት አስርና አንድ አምስት ሳንቲሞች አገኘሁ፡፡ የአገኘኋቸውን ሳንቲዎች በቀኝ እጄ ያዝኩና ወደ ቤታችን ሮጬ እናቴን “እቴቴ ሃያ አምስት ሳንቲም አገኘሁ!” ስል ጮህኩ! ተዚያም የልጅ ጣቶቼን ፈልቅቄ ሳንቲሞቹን አሳየሁ፡፡ እናቴ ተእጆቼ ያሉትን ሳንቲሞች ላለመንካት እግዜርን እንደሚለማመን እጇን ወደ ሰማይ ዘረጋችና ሁለት ሜትር ያህል ወደ ኋላ ተስፈነጠረች፡፡ እጆቿን ወደ ጣራው እንደዘርጋችም “የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው!! ሂድ ታገኝህበት ጣልና እጅህን በሳሙና ሶስት ጊዜ ታጠብ!” ስትል አዘዘችኝ፡፡ በታዘዝኩት መሰረት ሳንቲሞቹን ታገኘሁበት ጣልኩና ሶስት ባለችው ላይ አራት ጨምሬ ሰባቴ ታጥቤ ቁንቋኑን ተእጆቼ አጸዳሁ፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የአብዛኞቻችን ወላጆች ሃይማኖትና ባህል እንደዚህ የተቀደሰ ነበረ፡፡

ከብዙ ዓመታት በኋላ ዛሬም “የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው!” የሚለው የእናቴ ድምጥ እንደ ቤተክርስቲያናችን ደወል ይሰማኛል፡፡ በዚህ የእናቴ ቅዱስ ቃል የቤተክርስቲያንን ገንዘብ የሚዘርፉ ወሮበላ ካህናትን ስመዝናቸው ዲያብሎስ ያሰገዳቸው ውቃቢዎች መስለው አንደ አባጨጓሬ በሃምሳ እግር አፈር ላፈር ሲርመሰመሱ እንደ ምስጥም የሰው ሥጋ እያነከቱ ሲበሉ ይታዩኛል፡፡ እነዚህ ለዲያብሎስ የገበሩ ካህናት እንኳን የሰው ገንዘብ ቁንቋን መሆኑን አምነው የሰው ኪስ ሊምሩ ተክርስቶስ ኪስም እየዘረፉ ምድራዊ ፍላጎታችውንና ስስታቸውን ሊያረኩ ተገዳማቸው ወጥተው እንደ ፓስተሮች በየከተማው ሲቅበዘበዙ ይታያሉ፡፡

ብዙው እነደሚታዘበው እነዚህ ከንቱ ካህናት እንኳን እንደ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ነፍሳቸውን ለመስቀል ሊገብሩ፤ እንኳን እንደ አምስቱ ዘመን የደብረ ሊባኖስ ካህናት በመሳሪያ ወራሪን ሊተናነቁ፤ እንኳን እንደ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ተፋኖ ጋር ሊዘምቱ የቤተ፟ክርስቲያኗን ቋንጃ ተሚሰብሩት ጋር ለሰላሳ ዓመታት አብረዋል፡፡ እነዚህ የሰው ገንዘብ ቁንቋን መሆኑን የማያምኑ ካህናት እናቶች ተድሃ መቀነታቸው እየፈቱ ተክርስቶስ ኪስ ያስገቡትን ገንዘብ በአካፋ እጅ እየዘረፉ የራሳቸውንና ዘመዶቻቸውን መንደላቀቂያ በማድረግ ስንት ቅዱሳንና ሰማእታት የወጡባትን ቤተክርስትያን ክብር አዋርደዋል፡፡ ለማኝ በቁስል እግሯ ለምና ታገኘችው የከፈለችውን አስራት እየላፉ የሉመዚን መግዣና የፎቅ መስሪ እያደረጉ የሰማዩን ህይወት ረስተዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰሞነኛ ጉዳዮችን በወፍ በረር አንቀጾች ስንቃኛቸው - ከይሄይስ አእምሮ

ተከታዮች እንደሚያውቁት በአንድ አምላክ መመለክ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሊቃውንትንና ብፁዓንን ሲያፈልቁ የኖሩት ቤተምኩራቦችና የተዋህዶ ቤተክርስትያናት በአሁኑ ዘመን በልተው በማይጠግቡ አሳማዎች ባይወረሩ የተራቡትን የማብላትና የታረዙትን የማልበስ ችሎታ ይኖራቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ቅድስት ቤተክርስትያን “የሰው ገንዘብ ቁንቋን” መሆኑን በሚያምኑ ፓትርያሪክና ጳጳሳት ብትመራ ኖሮ በመላ አገሪቱ ያሉት የአብነት ትምህርት ቤቶች ወደ ዩንቨርስቲ ተቀይረው የዓለም ሕዝብ በውድድር ለመግባት የሚሽቀዳደምባቸው የሃማኖትና የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ማድረግ ይቻል ነበር መተንበይ ይቻላል፡፡

የሃይማኖት መሪዎች “የሰው ገንዘብ ቁንቋን” መሆኑን አምነው የሞራል ልእልናና የሥነ-ምግባር አርአያ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ላለፉት ሰላሳ ዓመታ የእምነት ተቋማት የሰው ገንዘብ ቁንቋን መሆኑን በማያምኑ ገንዘብና ስልጣን አሳዳጆች ተሞልተው የመንፈስ ልእልናና የሥ-ምግባር ሚዛኖች እንደ ሸክላ ተሰበሩ፡፡ የሚዛኖች መሰበርም ወንበር ለተቆናጠጡት ነፍሰ-ገዳይ ባለስልጣኖች፣ ነፍሰ-ገዳዮችን እናስወግዳለን ለሚሉት አንዳንድ ተቃዋሚዎችና ራሳቸውን አክቲቪስት እያሉ በመጤ ቃል ለሚጠሩ ዘራፊዎችም ጠቀመ፡፡

እንደሚታወቀው ወንበር የተቆናጠጡት ነፍሰ-ገዳይዎች በድሃ ጉረሮ እንጨት እየሰደዱና የአገሪቱን ሀብት እየዘረፉ የውጭ አገር ባንኮችን አድልበዋል፡፡ ባደኸዩት ጎስቋላ ሕዝብ ሥም እየተበደሩና እየለመኑ ልጆቻቸውን በውጪ አገር ሽቅብ እስተመሽናት አድርሰዋል፡፡ ሚስቶቻቸውን በሰዓታት ውስጥ እስከ አንድ ሚሊዮን ያሜሪካ ዶላር ለሸቀጥ ልብስ ሺመታ እንዲያጠፉ አስችለዋል፡፡ የጎሰጎሱት ቁንጣንና ቁርጠት በሆናቸው ቁጥር “በቻርተር” አውሮፕላን  እየበረሩ አሜሪካ፤ አውሮጳ፣ ኤሽያ፣ እስራኤልና ደቡብ አፍሪካ መታከሚያ አድርገውታል፡፡ የንግድ መርከብ እስከመግዛትም ደርስዋል፡፡ ቁንቋኑ የሰው ገንዘብ እንደ ሂትለር፣ ኢዲ አሚን፣ ጋዳፊና ለገሰ ትቢያ ተመሆን የማይድነውን ገላቸውን ንሶላቸዋል፡፡

እነዚህን ነፍሰ-ገዳዮች ለማስወገድ ተደራጀን ተሚሉት ተቀዋሚዎች አንዳንዶቹም ቁንቋኑ የሰው ገነዘብ ቦርጫቸውን እንደ ድርስ እርጉዝ ሲገፋውና መቀመጫቸው እንደ እማማ ታንቺ ወዲያ ጋን ሲያሰፋው ይታያል፡፡ እነዚህን ያዩ አንዳንድ ግልገል ዘራፊ ሕዝብ አደራጅ ነን ባዮችም “ጎፈንድ” እየከፈቱ ገንዘባችንን ሞጭልፈው የቁንቋን ኑሮ መኖርን ብልጠት አድርገውታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወሳኝ ጥያቄዎች ለአብይ አህምድ አፍቃሪዎች - ሰርፀ ደስታ

ለቤተክርስቲያን የሚያስገባው አስራት በዘራፊ ካህናት እንደሚሞጨለፍ ሕዝብ ያውቃል፡፡ ዳሩ ግን ይህ ሕዝብ ተቤተክሲያን መልስ በእየቤቱ ያማና ዝም ይላል ወይም “እግዜር ይቅጣቸው!” ይልና የራሱን ሐላፊነትና ግዴታ ለእግዚአብሄር ሰጥቶ ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለገንዘብ የሚገዙ ዘራፊ ካህናትን እየቀለበ ይኖራል፡፡ ለመንግስት አፍንጫውን ተይዞ ግብር ይገብርና በከፈለው ግብር ባሩድ እየገዙ ሲጨፈጭፉትና ሲገርፉት ለጥ ብሎ ይገዛል፡፡ ተሞት የተረፈው እንደገና መረሸኛውንና መገረፊያውን ግብር ይገብራል፡፡ ተቃዋሚና አደራጅ ነን ለሚሉትም መልካም ነገር የሚያመጡ እየመሰለው ያዋጣል፡፡ ዳሩ ግን ገንዘቡን ተቀብለው ለምን እንዳዋሉት ለመጠየቅ ይሰንፋል፡፡ ይህ እየተለመደ የመጣ ከንቱ ባህል የሰው ገንዘብ ቁንቋን መሆኑን ለማያምኑ የሰይጣን ተከታዮች ሰርግና ምላሽ ሆኗል፡፡

መጣፉ እንደሚለው ሰይጣን ክርስቶስን ወደ ተራራ ወስዶና ንብረት አሳይቶ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ ማቴ 4፡9” ሲል ክርስቶስን የፈተነው በገንዘብ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ሰይጣን ምን ያህል ገንዘብን በመሳሪያነት እንደሚጠቀምበት ነው፡፡ ገንዘብ የሰይጣን መሳሪያ መሆኑን የካዱ የሃይማኖት አባቶች የድሃን አስራት አግበስብሰው ተፎቅ ሲያድሩ አስራት ከፋዩ ቤቱ እየፈረሰበት ተመንገድ እያደረ ነው፡፡ ባለስልጣኖች ተመንገድ የጣሉትን ሕዝብ ንብረት እየዘረፉና በሥሙ እንደ ዓለም ባንክ፣ አይ ኤም ኤፍ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ ያሉትን ባንኮችና አገሮች እየለመኑ የራሳቸውን ቤተሰቦች በውጪና በአገር ውስጥ እያንደላቀቁ ነው፡፡ እናቴ ቁንቋን ያለቸው የሰው ገንዘብ ለሰይጣን ተከታዮች ምቾችና ቅንጦት እየሆነ ነው፡፡

 

ቅዱሱ መጽሐፍ “ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴ 6፡24“ ባለውና እናቴም በዚህ ተመርኩዛ “የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው” ባለቸው በሚያምኑ ቤተክርስቲያንም ሆነ አገር ካልተመራች ሰይጣን በገንዘብ የሚያማልላቸው አረመኔዎች ሲያተራምሱን መኖራቸው ነው፡፡ ሰይጣን በገንዘብ የሚያማልላቸውን አሪዎሶች ተቤተ-መንግስትም ሆነ ተሃይማቶች ተቋማት እስካልወጡ ድረስ የአገራችንም ሆነ የቤተክርስቲያናችን መከራ እየከፋ መሄዱ እማይቀር ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጎሽ ፋኖ! የአምስቱ ዘመን ፋኖች እነ በላይ ዘለቀም ጥምጣም ቆልለው የመጡ ተላላኪ ባንዶችን ወንፊት የፋሽሽት አሽከር እያሉ ልክ ያስገቧቸው በዚህ መንገድ ነበር!

እንኳን በገንዘብ ሊታለሉ ነፍሳቸውን እየገበሩ አርበኞች በአጥንታቸው በገነቧት አገር ባለስልጣን፣ ተቃዋሚ ወይም ህዝብ አደራጅ ተመሆን በፊት የሰው ገንዘብ ቁንቋን መሆኑን ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ ብፁአን ሰማእታት አንገታቸውን ተቀልተው በአለት ተመሰረቷት ቤተክርስቲያን ፓትርያቲክ፣ ጳጳስ፣ መነኩሴ፣ መሪጌታ፣ ቄስና ዲያቆን ከመሆን በፊት “ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አለመቻሉን” ማመን አስፈላጊ ነው፡፡

ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት ስለማይቻል ውዷ እናቴ እንዳለችው የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው፡፡ የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው! የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው! የሰው ገንዘብ ቁንቋን ነው!

 

አመሰግናለሁ!

የካቲት ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

 

2 Comments

  1. One billion dollars aid is urgently needed for Ethiopians mostly for those who are residing in Oromia region since the Oromia regional government of Ethiopia has completely failed to properly protect the citizens from the locust invasion which was not disclosed publicly to protect the images of ODP, the extent of the locust disaster had been undermined by the authorities in Oromia region which is known to be plagued by conflicts from Ambo to Wollega, where now is said to be in a brink of starvation being feared to cause uncontrollable migrations to major cities such as Hawassa and Finfine in search of food.

    If the aid is not gotten in time from foreign donors the only choice left is said to be borrowing from international financial institutions such as World Bank and IMF in a form of loan, by securing the development projects that are already underway.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share