ወገኖች ተረጋጉ፣ ቆም ብላችሁ አስተውሉ። በዚህ ፈታኝ ወቅት ቀጥ ያለ የሚመስለው ጠማማ፣ ላይ ላዩን ሲያዩት አገር ወደ ሞት አፋፍ እየከነፈች ያለ ነው የሚመስለው። ይህ ደሞ የሆነው ሆን ተብሎ ነው። እንደዛ እንድናስብ ሌት ተቀን እየተሰራብን ስለሆነ። የኢትዮጵያ ጠላቶች ብዙ ናቸው። እየተናበቡ ነው የሚሰሩት። እየተመካከሩም። በገንዘብም ፣ በጉልበትም በደንብ እየተደጋገፉ ነው። ይህ የጥፋትና የጽልመት ሀይል ከባድ ጥፋት እያደረሰ ለመሆኑ የሞቱት ወገኖቻችን፣ የወደሙት ንብረቶቻችን፣ የታገቱት ልጆቻችን ህያው ምስክር ናቸው። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው የአቢይን አስተዳደር ሆን ብሎ ለመስበርና በዚህ ግርግር አገርን ዳግም ለመመዝበር ነው። የዚህ ሁሉ ጥፋት ዘዋሪዎች ደግሞ ያው በዚህ ጉዳይ ለአመታት የተካኑትና የስራ ልምድ ያካበቱት ወያኔዎች ናቸው። አዎ ይዘውሩታል እንጂ በስራቸውና በሚመሩት የጽልመት ብርጌድ ብዙ አማሮች፣ ዖሮሞዎች፣ ሲዳማዎችና ሌሎች አሉበት። ባብላጫው ለዚህ መርዝ ተልእኮ ያልተመቹት ሱማሌዎች፣ ጋሞዎችና ሌሎች የደቡብ ወገኖቻችን ናቸው።
ውድ ኢትዮጵያውያንና ውያት!
ቆም በሉ፣ ሰከን በሉ፣ ለመፈረጅ አትቻኮሉ። ዶር አቢይ ገና መቶ ፐርሰንት ማንዴቱ የላቸውም ለአመታት የጎበጠውን ለማቅናት። ውስጣቸው ያሉት ሰዎች ባብላጫው በደመነፍስ ያሉ ፣ አጥር ላይ ተንጠልጥለው ወዴት እንደሚዘለል እያሰለሰሉ ያሉ ሀሞተቢሶች ናቸው። ድንገት ህውሀት በሚመጣው ምርጫ ይሁን የጉልበት ቅርጫ በለስ ከቀናው ተሽቀዳድመው እጅ ለመንሳት አሰፍስፈው እየጠበቁ ያሉ ናቸው የሚመስለኝ። ለዚህም ነው መንግስት ስለመኖሩ እስክንጠራጠር ድረስ ላይታቹ እየታመሰ ያለው። ግን ግን ሆን ብሎ ላየው፣ እንደቁጥራችንና እንዳሳለፍነው መከራ ጥልቀት አገሪቱ ጠላቶችዋ እንደጠበቁት አልፈራረሰችም፣ የፈራረሰች ያህል ግን ከፍተኛ የሚዲያ ዘመቻ እየተካሄደባት ነው። ወገኖቼ ስራ እየተሰራ ነው። አገሪቱ አለምአቀፍ ቢዝነሶችን እያካሄደች በህይወት ያለች፣ ወደፊትም የምትኖር የዋዛ ያይደለች ናት። ዝም ብዬ አስተዋልኩት። አቢይና ጥቂት ደፋር ከየጎሳው የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን መልካም ስራቸውን እየሰሩ ነው። የነዚህን ጥቂት ሰዎች መልካም ስራ ለማጠልሸት ከውስጣቸው ለሆዳቸው ያደሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይሰማኛል። የታገቱት ልጆች የዚህ ስራ ውጤት ይመስለኛል። በአቢይ ላይ ከባድ ድራማ እየሰሩባቸው ያለ ይመስለኛል። ለምን? አቢይ እራሳቸው መግለጽ እስኪቸግራቸው ድረስ ልጆቹን ሳይወዱ በግድ እነዛ ክፉ ዘዋሪዎች ወይም አክራሪዎች የተረከቡዋቸው ይመስለኛል። በቃ ከባድ ጥርጣሬ በሰውዬው ላይ ለመፍጠር የታቀደች ስልት ናት።ወያኔዎቹና አክራሪዎች ይህ ስልት ብቻ ይመስላል የቀራቸው። ፖሊሶችና ምንደኛ መለዮ ለባሾች የጥቅም ተባባሪዎች ብዙ ናቸው። ሰውዬው አላስር፣ አልገድል፣ አላሰቃይ አሏቸዋ። ምን ያድርጉ? ጓዳቸው ገብተው፣ በገንዘብና ጥቅማጥቅም ደልለው የቅርብ የሚሏቸውን ድረስ ያስኮበለሉ ይመስላል ። አቢይ እንዲህ እንደዋዛ የሚረቱላቸው አልሆኑም እንጅ ። ከባድ ስልተኛ ናቸው። ክፋቱ ባብላጫው አገር ወዳድ የተባለ ሁሉ ስሜታዊ ነው። ላይላዩን ነው የሚጋልበው። ሰከን ብሎ ለምን ይህ ሆነ የሚል የለም። ለመሾምና መሻር መቻኮል ብቻ። አሳዛኝ ዘመን። ታድያ ምን ይሆን መፍትሄው? እንዴት አገራችንን ከጥፋት እንታደጋለን? እስቲ የምክሬን ያህል በነጥብ ላስቀምጥ። ቢረዳም ባይረዳም፣
፩) አስሩ ቦታ እየገባችሁ ወሬ አትቀላውጡ። ካነበባችሁ ወይም ከሰማችሁ በሁዋላ ደግም የወሬውን መሰረትና ፍሬ ነገር ገምግሙ። ስሜታችሁን ከነካው ነገር አለና ሼር ከማድረጋችሁ በፊት በደንብ መርምሩ። ጁዋር የተባለው ምንደኛ በወያኔ ዘመን የፈዘዙና የነፈዙ ልጆቻችንን አይምሮ በስሜት እየነካካ ነው ጉድ እያደረገን ያለው።
፪) ሌላው እጅግ የሚደንቀኝ እንደምን አድርገው አቢይ አህመድ የ መቶ ሚሊዮን ህዝብ በነፍስ ወከፍ እምባ አባሽ እንደሚሆኑ ነው። ሰውዬው ጓዳም እራሳችሁን እያስገባችሁ ተረዱላቸው እንጅ። ባለፈውም ደቡብ ላይ ይህንኑም ብለዋል።
፫) ከዚህ ቀደምም ብያለሁ፣ አሁንም ልድገመው። ይህን ምርጫ ስጋ እንዳየች ቀበሮ አድፍጠው የሚጠብቁት ወያኔዎቹና በስራቸው የሚዘወሩት አክራርያን ናቸው። ይህን ምርጫ “በሞተ ” ህገመንግስት አሳቦ ቀኑን ማስተላለፍ አይቻልም የሚሉት ጫወታ አይገባኝም በበኩሌ። በቅርብ አቶ ልደቱና ዶር ኦባንግም ይተላለፍ እያሉ ነው። መፍትሄው እነ ኢዜማን ሌሎችንም ጨምሮ ፔቲሺን ማድረግ ነው ምርጫ ቦርድን።ማንን ለመጥቀም ነው ምርጫው?ደሞስ ምን ፖሊሲ ሰማንና ነው ምርጫው? እነብልጽግናን እንዲወስኑ ተጠብቆ እንደሆነ ህዝቡ ገና ምን እንደሚፈልግም የገባው አይመስልም ።
፬) የፖለቲካ ድለላን መና ማስቀረት። እንዴት? የነ መረራ፣ በቀለን ከጁዋር ጥምረት ዎንኛ ምክንያት ማጋለጥ። እዚህ ላይ ብልጽግናዎች ብዙ ይቀራችሁዎል። በቅርብ ጀግናው ታዬ ደንደአ እንዳደረገው ሌሎችም በብርቱ ታገሉ እንጅ ። አንድ ታዬ ብቻ እንዴት ብቻውን ይፍጨረጨራል? ሌሎችም በብልጽግናው የታቀፋችሁ እህትና ወንድማማቾች ዝም አትበሉ እንጅ ። ይህ ጁዋር የተባለው ጠንቅነቱ ለኦፒዲ ብቻ መስሏችሁ ከሆነ ተሸውዳችሁዋል።ምንም እንኳ ምኞቱ አማሮችንና ዖሮሞዎችን ለማባላት ቢሆንም ዳፋው ለአገር ነውና በህብረት ይሁን በተናጠል አጥብቃችሁ መታገያ ጊዜው አሁን ነው። ሁዋላ መቆምያው ይቸግራል ይህ ጉዳይ በጊዜ ካልተመከተ።
ፈጣሪ በቃችሁ ብሎ አገራችንና ህዝባችንን ከክፉ ይጠብቅልን።