March 28, 2019
47 mins read

ጢሰኛ ባለ እርስት የሆነባት ሀገር ኢትዮጵያ! (በገ/ክርስቶስ ዓባይ)

የሦስት ሺህ ዘመን አንጋፋዋ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ መሠረተ ድርሳኗ የሚያጠነጥነው በነገሥታትና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጥርት ያለ ሃይማኖታዊ ባህሏዋና ትውፊቷ ተገንብቶ ነው። ለዚህ ገናናነትዋና የክብሯ መገለጫ የሆነው ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላት ሀገር ጭምር መሆኗ ነው። ስለሆነም ማንኛውንም ፍጡር እንሳስትን ጨምሮ ታከብራለች፤ ትራራቸዋለች። ቀሪው ዓለም በአካባቢው የነበሩትን እንስሳት ሁሉ ቁርጥም አድርጎ ጨርሷቸዋል። ኢትዮጵያ ግን ከፈጣሪ ትዕዛዝ ፈቀቅ ሳትል በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት በስተቀር ሌላውን እንስሳ አትበላም። በመሆኑም እጅግ በርካታ ድንቅዬ እንስሳትን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በእንክብካቤ ጠብቃ የያዘች ብቻኛ ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች። ይሁን እንጂ ይህንን የተረዱት የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በተለይ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ዙሪያዋን በመክበብ፤ በምዕራብ ሱዳንን፤ በደቡብ ኬንያን እና በምሥራቅ ሶማሌ ላንድን ተቆጣጥረው እንደነበር አይዘነጋም። ከዚህም የተነሳ በስውር ድንበር እየዘለሉ በመግባት በሄሊኮፕተር ጭምር ዝቅ ብለው በመብረር እየነዱ ወደ ጎረቤት ሀገር በማስገባትና ተመልሰው እንዳይወጡም በአጥር በመከለል አግደው አስቀርተዋቸዋል።

የዓለም ሕዝብ በአብዛኛው አሳማ ይበላል፤ አሳማ የማይበላው የአይሁድ፤እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሲሆኑ፤ ከክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ውስጥ ብቸኛዋ ቅድስት ኢትዮጵያ ብቻ ናት። መቼም ዕድሜ ያማያሳየው ነገር የለምና ሀገራችን በታሪክ አጋጣሚ የሀገር ፍቅርና የወገን ክብር በሌለው፤ የወያኔ ዘራፊ ቡድን ሥር በመውደቋ፤ ለዘመናት ለጭነት ብቻ ሲያገለግሉ የኖሩ አህዮች፤ በዚች የተቀደሰች ሀገራችን ለእርድ እየቀረቡ እንደሆኑ በታላቅ ውርደት የምናስታውሰው ጉዳይ ነው። ሰው ክብሩን እስካልጠበቀ ድረስ ይዋረዳል።

ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ራሱን ብቻ ሳይሆን የተገኘበትን የትግራይን ሕዝብ ጭምር አዋርዶ ወደ እማይቀረው ዓለም ገና በጉልምስና ዕድሜው ተቀስፎ ሄዷል። ነገር ግን በእርሱ የተረጨው በዘርና በጎሣ የማሰብ መርዝ፤ አገራችንን አሁንም እንደበከለ ይገኛል። ሌሎቻችንም ከዚህ ሁኔታ ተነስተን ትምህርት በመቅሰም መርዙን ማርከስና አገራችንን ማንጻት ሲገባን፤ እንዲያውም የእርሱን እኩይ መንገድ በሚያሳፍር ሁኔታ እየተከተልነው እንገኛለን።

አንድ ባለሥልጣን እንዲሁ ደርሶ ለሹመት አይበቃም፤ ወደድንም ጠላንም አመንም አላመንም፤ ከፈጣሪ ትዕዛዝ ውጭ የሚሆን ጉዳይ አይደለም። ለዚህ ማስረጃ ከታላቁ መጽሐፍ ብዙ እንማራለን። የእሥራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ ሳዖል ከብት ጠፍቶበት በመፈለግ ላይ እንዳለ ለንጉሥነት እንደተቀባ ያትታል። ሳዖልም ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ፈቀቅ ባለ ጊዜ ከክብሩ ተዋርዷል፤ መንግሥቱም ለሌላ (ለቅዱስ ዳዊት) ተላልፎ ተሰጥቶበታል።

የማንኛውም ሰው ዕድሜ አጭር እንደሆነ በመገንዘብ በዚች የዓይን ጥቅሻ የምታክል ጊዜያችን ለሀገርና ለወገን የሚበጅ መልካም ሥራ ሠርተን ብናልፍ ስማችን በታሪክ መዝገብ በመልካም ምሳሌነቱ ሲወሳ ለትውልድ ትውልድ ሕያው ሆኖ ይኖራል። መጥፎ ከተሠራ ደግሞ እንዲሁ በተቃራኒው በትውልድ ትውልድ የእርግማን ናዳ ሲወርድበት ይኖራል።

መሬት ከተረገመች በኋላ እሾህና አሚካላ፤ ጉመሮና ቆንጥር አብቅላላች። ሰውም ሲረገም እኩይ ዘር ይወልዳል። በመሆኑም ኢትዮጵያችንም የተለያዩ እኩዩችን አፍርታለች። ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የኢትዮጵያ ታሪክ የነገሥታት እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በመሆኑ ፈሪሃ እግዚአብሔር ስላላት፤ እስካለንበት ዘመን ድረስ በነፃነቷ ታፍራና ተከብራ እንደዘለቀች ይታወቃል። ለዚህም እጹብ ድንቅ የሚባሉና የዓለማችን ጠቢባን ገና ያልደረሱበት የዕውቀት ባለቤት መሆኗ ግልጽ ነው። ይህንንም በመረዳት እኒሁ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች፤ ሰላዮችን አስርገው በማስገባት ውድ ንብረቷ የሆኑትን ታሪኳን እና ጥበቧ የተመዘገቡበትን ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት በሀገር ከሃዲዎች ስግብግብነትና ጊዜያዊ ጥቅም ተባባሪነት ሲመዘብሩ ቆይተዋል። ይህንን ስንል እንደሌሎቹ በአፈታሪክ ላይ ተመሥርተን ሳይሆን በየወቅቱ በተዘገቡ ‘ዜና መዋዕል’ የጽሑፍ ማስረጃ ተደግፈን ነው።

ይህንን ያህል ለመንደርደሪያ ከገለጽን ወደ ዋናው ቁም ነገራችን እንመለስ። ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ እንደሆነ ይታወቃል። እንግዳን ሲያስተናግድ እግር አጥቦ፤ ምግብ አብልቶ፤ ዓልጋውን ለቆ፤ አክብሮ ያስተናግዳል። ይህ ዓይነቱ መስተንግዶ ከሞላ ጎደል በማንኛውም ማኅበረሰብ እንደ ባህል ሠርጾ የገባ በመሆኑ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሲተገበር ቆይቷል።

ቀደም ሲል እንደተጠቆመው የኢትዮጵያ ታሪክ የነገሥታት ታሪክ እንደሆነ ገልጸናል። ንጉሥ ማለት በከፍተኛ ጾም እና ጸሎት እንዲሁም ሱባዔ ተገብቶ በፈቃደ እግዚአብሔር ቅባዕ መንግሥት ተቀብቶ የነገሠ ማለት ነው። ስለሆነም ሥዩመ እግዜአብሔር በመባል ይታወቃል። ይህም ማለት የሚያስተዳድረውን ሕዝብ በዘር፤ በቋንቋ ወይንም በሃይማኖት መድሎ ሳያደርግ፤ ፍትህንና ርትዕ ሳይጓደሉ፤ በእኩልነት የሚዳኝ ስለሆነ ነው። ንጉሥ ከእግዚአብሔር በታች ያለ፤ ለሕዝቦች እኩልነት፤ለሀገር ሉዓላዊነት፤አንድነትና ሰላም በትጋት የሚሠራ ተቋም ዘርግቶ እውነተኛና ሐቀኛ አስተዳደር የሚያሰፍን ማለት ነው።

ንጉሥ የመሾምና የመሻር ሙሉ ሥልጣን ያለው ኃያል አካል ነው። የሚሾመው ፈጣሪውን የሚፈራ ሰባዊ ፍጡርን የሚያከብርና ብሩህ አእምሮና ራዕይ ያለውን ሲሆን፤ኃላፊነቱንም በታማኝነት ለመፈጸም እስከመጨረሻው በጀግንነትና በጽናት የሚቆም፤ ለሌላው አርአያ የሚሆን ጠንካራ መንፈስ ያለውን ሰው ነው። በአንጻሩም የሚሻረው ደግሞ ለተቸገሩት የማይራራ፤ እግዚአብሔርንን የማይፈራ፤ ሥልጣኑን መከታ በማድረግ ድሆችን የሚበድል፤ ፍርድ የሚገመድል፤ ጨካኝና ከሀዲ ሆኖ ሲገኝ ሲሆን፤ንጉሡ ከነበረው ሥልጣን ያስወግደዋል። የንጉሥ ሥርዓት የባላባት ሥርዓት ነው። የባላባት  ሥርዓት ደግሞ የእርስት ሥርዓት አለው።

ይህም ማለት ሀገር በጠላት በተወረረች ጊዜ፤ ንጉሡ አዋጅ ያውጃል፤ ነጋሪት ያስጎስማል፤ ጥሩንባ ያስነፋል፤የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ክተት ሠራዊት ይላል። በዚህ ጊዜ ባላባቶቹ ስንቃቸውን አዘጋጅተው መሣሪያቸውን ወልውለው፤ ጦራቸውን ሰብቀው፤ጎራዴያቸውን ስለው፤ቀስታቸውን ደግነው፤ በሥራቸው የሚገኙትን ለአቅመ አዳምና ሔዋን የደረሱ ወንዶችንም ሴቶችንም አሠልፈው ለዘመቻ ይወጣሉ፤ ከንጉሡም ጋር በመሆን ይዘምታሉ። ወንዶቹ ከጠላት ጋር ሲፋለሙ፤ሴቶቹ ደግሞ ምግብ በማዘጋጀት፤ ቁስለኞችን በማስታመም ይሳተፋሉ። በዚህም ኅብረታቸውና ያላሰለሰ አገልግሎታቸው ጠላታቸውን ድባቅ ይመታሉ።

በጥንት ጊዜ የሰው ቁጥር እንደ አሁኑ አልነበረም እና እነዚህ ጀግኖች፤ በዘመቱበት ጦርነት ደማቸውን ላፈሰሱበት፤ አጥንታቸውን ለከሰከሱበትና፤ልጆቻቸውን መስዋዕት አድርገው ጧሪ ቀባሪ ላጡበት፤ መካካሻ ይሆን ዘንድ ለመተዳደሪያ እንዲሆናቸው፤ አልምተው የሚጠቀሙበት ጠፍ መሬት በንጉሡ ይሰጣቸው ነበር። እንዲህ ያለው ጀግንነት፤ ዘማቾችን ባላባት ሲያደርጋቸው ያገኙት መሬት ደግሞ እርስት (ቋሚ መተዳደሪያ) ይሆናል ማለት ነው።

እንግዲህ ከዚህ ተነስተን የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመረምር፤ ከአጼ ካሌብ ሥርወ መንግሥት 22ኛው የኢትዮጵያ ንጉሥ በነበሩት በአፄ አርማህ ዘመነ መንግሥት፤ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ  ማለትም ከ613-615 ዓ/ም ባለው ጊዜ የነቢዩ መሐመድን ስደተኞች ተቀብለው በኢትዮጵያ እንዳሠፈሩ ይታወቃል። በአንጻሩም በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ንጉሥ በነበሩት አፄ ልብነ ድንግል መንግሥት ላይ የክርስትናን እምነት ከምድረ ኢትዮጵያ ለማጥፋትና አገራችንን ወደ እስልምና ሃይማኖት ተከታይነት ለመለወጥ ይፈልግ የነበረው ግራኝ መሐመድ፤ በኦቶማን ቱርክ እየተደገፈ ዘመተባቸው። ከዚህ የተነሳ ‘አገሬን በጠላት አላስደፍርም!’ በማለት ዘምተው 1521 ዓ/ም ሽምብራ ኩሬ ላይ በተደረገ ጦርነት መስዋዕት መሆናቸውን በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚያን ዘመን ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዓብያተ ክርስቲያናት ተመዝብረዋል ተቃጥለዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ማኅበረሰብ ይኖሩበት ከነበረው የደቡባዊ ምሥራቅና ደቡባዊ ምዕራብ የኢትዮጵያ ግዛቶች በወረራው ምክንያት ሀብት ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፤ተገድለዋል፤ ከብቶቻቸው ተነድተዋል፤ በሕይወት የተረፉትም ወደ ሰሜኑና የአገሪቱ ማዕከላዊው ክፍል ተገፍተዋል።

በወቅቱ የአማራው ማኅበረሰብ በደቡብ እስከ ኬንያ ድንበር፤በምሥራቅ እስከ መቅደሰ ማርያም (አሁን መቋድሾ) በምዕራብ ደግሞ እስከ ኢሉባቦር ድረስ ሰፍሮ ይኖር እንደነበር ይታወቃል። በተለይ ደግሞ ቀደም ሲል በ13ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ አቡነ ተክለሃይማኖት በደቡብ በኩል የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማስተማርና በማጥመቅ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን ማሳነፃቸው የተረጋገጠ ሐቅ ነው። በዚህ ጊዜም የቡናን ተክል በዘመናዊ መንገድ በማስፋፋትና በመትከል፤ እንዲሁም ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎችን በማልማት ሕዝቡ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንደነበር ይታወቃል። ይሁን እንጂ አገር ሰላም ብሎ በሚኖርበት ወቅት የክርስትና ሃይማኖት ጸር የሆነው የግራኝ መሐመድ አረመኒያዊ ወረራ በድንገት በመከሰቱ ኗሪው ቀየውን እየለቀቀ ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ከፍል እንደተፈናቀለ ግልጽ ነው።

እስከዚህ ጊዜ ድረስ በደቡብ በኩል ያሉት ሁሉም ማኅበረሰቦች ቁጥራቸው እጅግ አነስተኛ ቢሆንም መኖራቸው ሲታወቅ የጋላ (ኦሮሞ) ማኅበረሰብ ግን ፈጽሞ እንዳልነበረ የተረጋገጠ ነው። ነገር ግን በአንዳንድ ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ እንደ ፕሮፌሰር አስመሮም ያሉ ምሁራን ተብየዎች ከሐቅ የራቀ የፈጠራ ታሪክ እየጻፉ ነባሩን የአማራውን ማኅበረ ሰብ ለማሳነስና ለማኮሰስ ብሎም ኢትዮጵያዊነቱን ለማሳጣት ከፍተኛ ሤራ እየተደረገ ይገኛል። እንደ ፕሮፌሰር አስመሮም ጦር ቀስቃሽና ኢትዮጵያን የማፍረስ ትርክት ከሆነ ኦሮምያ የሚባል ካርታ ከመንደፍ ባሻገር የጋላ (ኦሮሞ) ማኅበረሰብ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ300 ዓመተ ዓለም ጀምሮ በኢትዮጵያ ይኖሩ እንደነበር የሐሰት ድርሰት በመጻፍ ሕዝቡን ግራ በማጋባት ላይ ናቸው።

እንዲህ ዓይነቱ የፈጠራ ትርክት ለኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ለሌላው የኢትይጵያ ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲገዳደል ጠብ ከመጫር ያለፈ የሚፈይደው አንዳችም ነገር አይኖርም። ከአሁን ቀደም ተስፋየ ገብረአብ የሚባል ከሐዲ የጻፈውን አማራ ጠል የሆነ ‘የቡርቃ ትዝታ’ ልብወለድ መጽሐፍ መሠረት በማድረግ በሕዝቦች ደም ተረማምደው ጥቅም ለማግኘት የሚቋምጡ እበላ ባይ የወያኔ ጋሻ አጃግሪዎች የሆኑት የኦሕዴድ ሹመኞች ሐቁን እያወቁ ጌቶቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ ብቻ የአኖሌን ሐውልት አርሲ ውስጥ በመትከል ቁመንልሃል በሚሉት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የፖለቲካ ቁማር ተጫውተዋል።

የኢትይጵያን ታሪክ ስናነሳ በአፈታሪክ ሳይሆን በብራና መጻሕፍት የተደጎሰ መሆኑን ማንም የሚስተው አይደለም። ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ በእነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት ውስጥ የጋላ (የኦሮሞ) ማኅበረሰብ ታሪክ ከግራኝ መሐመድ ወረራ በፊት የሚታወቅ ዘገባ አልተገኘም።

ይሁን እንጂ የጋላ ማኅበረሰብ ይኖርበት በነበረው የማዕከላዊ አፍሪካ አካባቢ በአውሮፓ ቅኝ ገዝዎች የመስፋፋት እንቅስቃሴ የሚደርስበትን ወከባ መቋቋም ባለመቻሉ ዘላን እንደመሆኑ መጠን የከብቶቹን ጅራት ተከትሎ ግጦሽ ፍለጋ ወደ ሰሜኑ የአፍሪካ ክፍል ማለትም በመጀመሪያ ወደ ታንዛንያ፤ከዚያም ወደ ሩዋንዳና ኬንያ፤ ቀጥሎም በ1518 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ተገዷል። በወቅቱ በግራኝ መሐመድ አረመኔያዊ ወረራ ተማረው ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን መኖሪያ ቀየ በመቆጣጠር መስፈር እንደጀመሩ አባ ባህሬይ የተባሉ መነኩሴ መዝግበውታል።

የጋላ ወረራ በጌዴኦ፤በሲዳማ፤በሀዲያና በሌሎችም በደቡብ ክፍል በሚኖሩ ሕዳጣን ማኅበረሰቦች ላይ በየስምንት ዓመቱ በሚያደርጉት ድንገተኛና የማያባራ የገዳ ሥርዓት የመስፋፋት ወረራ፤ ከብቶቻቸውን በመንዳት፤ሀብት ንብረቶቻቸውን በመዝረፍ፤ ወንዶችን በመስለብ፤ ሴቶቻቸውን በመድፈር ለብዙ ዘመናት ሲያስጨንቋቸውና ሲያፈናቅሏቸው እንደኖሩ ይታወቃል።

የጋላ (ኦሮሞ) ማኅበረሰብ ብዙ የተለያዩ እምነቶችና ባህሎችን ይዘው መጥተዋል። በወቅቱ የጠራ እምነት አልነበራቸውም፤ አረማዊ ነበሩ። ዛፍን አድባር በማለት የሚያመልኩ፤ ቅቤ የሚቀቡ፤ ዶሮ አርደው የሚያንጠለጥሉ፤ ለውቃቤ በማለት ልዩ ልዩ ዕቃ  ማለትም ጮጮና ቁዲ የሚባሉትን፤ በዛጎልና በጨሌ እየሸለሙ አቴቴ የሚሉ፤ ፍየል አርደው በሞራው የሚጠነቁሉ፤በሰው ላይ ሠፍረው የሚያስጓሩ፤ የዛር መናፍስት ሠራዊት አስከትለው እንደመጡ የሚካድ አይሆንም።

ይህንንም ልማድ እስከ አሁኑ ወቅት ድረስ እንኳ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሕዝብን ሲያታልል የነበረውን ታምራት ገለታን ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል። በዚህም መሠረት ወደ ደቡብ ምሥራቅ የሠፈረው የጋላ (ኦሮሞ) ማኅበረሰብ ቀስ በቀስ የእስልምና ሃይማኖትን ሲከተል ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሠፈረው ደግሞ የክርስትናን ሃይማኖት ተቀብሏል።

የአሁኑ ወለጋ፤ በከፊል ከፋና ኢሉባቦር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ይተዳደር እንደነበር ሲታወቅ፤ከአፄ ምኒልክ ጋር በ1874 ዓ/ም እምባቦ ላይ ከተደረገው ጦርነት በኋላ መቋረጡ ተመዝግቦ ይገኛል። ይህ ሁሉ ሲሆን ጋላ (ኦሮሞ) መጤ እንጂ ባላባት አልነበረውም። የሠፈሩበትም መሬት የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ቦታ የነበረ በመሆኑ ኑሯቸውም እስከ ደርግ ሥርዓት ድረስ በአብዛኛው የጢሰኝነት ነበር።

በተሰውት አባታቸው በአጼ ልብነ ድንግል ምትክ በወቅቱ የነገሡት አፄ ገላውዴዎስና ቀጥለውም የተነሱት የኢትዮጵያ ነገሥታት፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ስለነበራቸው በሰላም እስከኖሩ ድረስ የጋላን (ኦሮሞ) ማኅበረሰብ ሊያባርሯቸው አልፈለጉም። ቀስ በቀስ ግን ከአማራው ጋር በፈጠሩት መግባባት እስከ ቤተ መንግሥት ለመግባት ችለዋል። ለምሳሌም የአፄ ኢዮአስ ባለቤት ወ/ሮ ውቢት (ወለተ በርሳቤህ) ጋላ (ኦሮሞ)  እንደነበሩ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ  ምንም እንኳ የጋላ (ኦሮሞ)  ማኅበረሰብ ከብት የማገድ እንጂ ሌላ የግብርና ሙያ ባይኖራቸውም በአገሪቱ ከነበሩ ባላባቶችም እየተጠጉ በመቀጠርና በጢሰኝነት የመኖር ዕድል ማግኘታቸው ተመዝግቧል።  ቆይቶ ግን ከአድዋ ጦርነት በኋላ ብዙ ጋሎች (ኦሮሞዎች)  ዘምተው ስለነበር የጀግንነት ማዕረግና በስፋት ባላባት የሚያደርጋቸውን የመተዳደሪያ መሬት ከአፄ ምኒልክ እንደተሰጣቸው ይነገራል። ሆኖም እንዲህ ያለውን የአፄ ምኒልክ ፍትሐዊ ፍርድና ፈሪሀ እግዚአብሔር የተላበሰ አስተዳደር፤ የፖለቲካ ቁማርተኞች እውነቱን በመካድ የሐሰት ጥላሸት በመቀባት ሆነ ብለው የታላቁን መሪ የአፄ ምኒልክን  ስም የማጥፋት ዘመቻ ላይ ተጠምደው ይታያሉ።

በ1966 ዓ/ም የፈነዳው የኢትዮጵያ አብዮት የዘውዱን ሥርዓት በማስወገድ ‘መሬት ላራሹ’ በሚል መፈክር የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሲያራምዱት የነበረውን አስተሳሰብ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ጠልፎ ለፖለቲካ ትኩሳት ማብረጃ ሲል በደንብ ባልተመረመረና ባልተጠና ሁኔታ በግብታዊነት የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ/ም የገጠር መሬትን በአዋጅ መውረሱ አይዘነጋም። ቀጥሎም ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ/ም የከተማ ቦታ እና ትርፍ ቤትን እንዲሁ ያለ በቂ ጥናትና ዝግጅት በመውረስ አገራችን እስከ አሁን ለደረሰችበት የማኅበራዊ ቀውስ ከፍተኛ አስተዋጸዖ እንዳደረገ አይካድም።

እንግዲህ ይህንኑ ተከትሎ የጋላ (ኦሮሞ)  ማኅበረሰብ በጢሰኝነት ሲጠቀሙበት የነበረውን መሬት እንደያዙት እንደቀሩ ግልጽ ሲሆን፤ምን ጊዜም ቢሆን ሕጋዊ የባለቤትነት መብት እንዳልነበራቸው ግን መረዳት አይከብድም። የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያ የምትባለዋን ገናና ሀገራችንን እንደ ዩጎዝላቪያ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት  ከመቶ ዓመታት በላይ ሲያሴሩ ቢቆዩም ሊሳካላቸው አልቻለም። እንደ አለመታደል ሆኖ የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተምና ሀገር በቀል የባንዳ ልጆች ከአደዋ ትግራይ በተገኙ ከሀዲ ቡድኖች አማካይነት ሕልማቸውን ለማሳካት የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። በዚህም እራሱን እንደ ኢትዮጵያዊ የሚያየውን የአማራ፤የአፋር፤ጉራጌና የደቡብ ሕዝቦች ያልታደሙበትን ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ሕገ መንግሥት፤ በወያኔ፤ ሻዕቢያና፤ ኦነግ ድርጅቶች ተሳትፎ ብቻ አዘጋጅተው ወደ ሥልጣን እንዲወጡ አደረጓቸው።

በታሪክ አጋጣሚ በትረ መንግሥቱን የጨበጠው ወያኔ፤ አገሪቱን ዘርና ቋንቋን ማዕከል ባደረገ ክልል በመሸንሸን በሰላም እና በፍቅር ተባብሮና ተከባብሮ ይኖር የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሐሰት ትርክት እየፈበረኩ በማጣላት፤ እርስ በእርሱ እያፋጁ፤ሆድና ጀርባ ሆኖ የጎሪጥ እየተያየ ሲናቆር፤ እነርሱ ፀረ አንድነት የፕሮፓጋንዳ መርዛቸውን እየረጩ የዝርፊያ ሥራቸውን ሲከውኑ ቆይተዋል።

‘ደሀ በሕልሙ ቅቤ ባይጠጣ ንጣት በገደለው ነበር’ እንዲሉ የአድዋ ወያኔዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብት ለሃያ ሰባት ዓመታት በገፍ ሲዘርፉ ቆይተው፤ ለመገንጠል የሚያስችላቸውን ግዛታቸውን አስፍተው፤ የሕዝብ አመጽ እየጠነከረ መሔዱን ሲረዱ ማዕበሉ እንዳይጠርጋቸው በመፍራት የዋሁን የትግራይ ሕዝብ እንደምሽግ በመጠቀም መቀሌ ገብተው መሽገዋል። እንደ ዕቅዳቸው ሉዓላዊ ሀገር የመሠረቱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ከስድሳ ሺህ በላይ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ሠራዊት በተጠንቀቅ አቁመው የመጣውን ለመጋፈጥ በመጠባበቅ ላይ ለመሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

በአንፃሩም ‘ሞኝ ያስያዙትን አይለቅም’ እንዲሉ ለዘመናት የበታችነት ስሜት እንዲያሰቃያቸው፤ከአማራ ማኅበረሰብ ጋር ያላቸው መልካም ግንኙነት እንዲሻክር የሌለ ትርክት ሲሰበክላቸው፤ የግዕዝ ፊደላቸውን ሳይቀር በላቲን እንዲቀይሩ ሲታዘዙ፤ ‘ለምን?’ ብለው ሳይጠይቁ ሁሉንም እያግበሰብሱ ለሃያ ሰባት ዓመት ሲቀረጹ የቆዩት የሕወሃት ጥፍጥፍ ‘የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት’ (ኦሕዴድ) ዓባላት የሥልጣን ኮርቻው ላይ ተፈናጠዋል።

ኦሕዴድን ወክለው ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑት ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በወያኔ ዘመነ መንግሥት የተረሳችውን ኢትዮጵያ እንደ ዳዊት በመድገም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አማለሉት። ይቅርታ ነው እንጂ ጥላቻ የትም አያደርሰንም በማለት የሕዝቡን ልብ አቀለጡት። ሕዝቡም  የወደፊቱን ተስፋ በመመልከት፤ ይሁን በማለት ተከተላቸው። ነገር ግን ይቅር ማለቱ ቀደም ሲል የሠሩትን የማያውቅ ሆኖ አይደለም። አቦ ለማ መገርሣ የጸጥታ ሹም በመሆን ብዙዎችን ሲያሳስሩ፤ሲያሳፍኑና ሲገድሉ እንደነበር ጠፍቶት አይደላም። ዶ/ር ዓቢይም የኢንሣ ዳይሬክተር በመሆን የንጹሐን ዜጎችን ስልክ፤ኮምፒውተርና የመገናኛ መንገዶችን በመጥለፍ በመሰለልና የተለያዩ መሠረተ ቢስ ትንተና በመስጠት ሕዝብን ሲያሳስሩ፤ሲያስገርፉና ሲያሰድዱ እንደነበር ዘንግቶት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ይህንን ልባዊ ይቅር ባይነት እንደ ድንቁርና እና ስንፍና መመዘን ግን እጥፍ ድርብ ዋጋ ያስከፍላል።

እየዋለና እያደረም የቲም ለማ ቡድን የለውጥ ሐዋርያ እንደሆነ በስፋት ይስተጋባ ጀመር። ዶ/ር ዓቢይ የልጅ አዋቂ፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ለመታደግ ከላይ እንደ ነቢዩ ሙሴ  የላካቸው ናቸው እየተባሉ ተሞካሹ። ነገር ግን ቃልና ተግባር እንደ ሰሜን እና እንደ ደቡብ ዋልታ እየተራራቁ መጡ።

ምንም እንኳ የፖለቲካ እስረኞች ቢፈቱም፤ወደ ሀገር መግባት የማይችሉ፤ በስደት የነበሩ ኢትዮጵያውያንም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ቢደረግም፤ ለዓመታት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ የነበረውን አለመግባባት ቢያለዝቡም፤ በትጥቅ ትግል ወያኔን ለማምበርከክ በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎችም ወደ ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ መታገል እንዲችሉ ቢፈቅዱም፤ ውሎ አድሮ ግን ሂደቱ ሲታይ ‘ውስጡ ለቄስ!’ ሆኖ አረፈው።

ዝም ብለን በይሆናል መላምት ሳይሆን እስቲ በታዋቂው እንግሊዛዊ የዲቴክቲቭ ጸሐፊ ሰር አርተር ኮናን ዶይል፤ የሸርሎክ ሆምስ ገጸ ባሕርይ የምርመራ ዘዴ፤ እስከዛሬ የተሠራውን በጥቂቱ ደረጃ በደረጃ እንመልከተው።

ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ/ም የተጣለው የማስመሰያ ደካማ ቦንብ እንዲፈነዳ መደረጉ፤ የኢንጅነር ስመኘው በቀለ ምስጢራዊ አገዳደል፤ ብዙ ቢሊዮን ብር የፈሰሰበት የዓባይ ግድብ መቋረጥ፤ ከደንብ ውጭ የኢንጅነር ታከለ ኡማ ለአዲስ አበባ ከተማ በም/ከንቲባነት መሾም፤ የኦነግ ትጥቅ አለመፍታት፤ በተቀነባበረ መልክ በአንድ ቀን የ18 ባንኮች መዘረፍ፤የቡራዩ ዘር ለይቶ የማፈናቀል ወረራና ግድያ፤የለገጣፎ አረመኔያዊ ቤት የማፍረስና የማፈናቀል እርምጃ፤ የአዲስ አበባ የማንነት ጥያቄና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሤራ፤ የኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ አመሠራረት እና ሰላማዊ የኦሮሞ ወጣቶችን ለጥፋትና ለዕልቂት የመቀስቀስ ሂደት፤ በአዲአ አበባ ሕዝብ ላይ የሽብርና ያለመረጋጋት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፤የጀዋር መሐመድ በአባገዳ አስታራቂ ኮሚቴ በጸሐፊነት መሰየም፤ የአቶ ለማ መገርሣ በሚኒሶታ ከተለመደው ደንብ ውጭ ቆንስል የማቋቋም ሂደትና በኦሮምኛ የሚነገሩና በአማርኛ የሚሰበኩት ዲስኩሮች ፈጽሞ ሊጣጣሙ አለመቻል፤ ወዘተ. ወዘተ……. ፤ የለውጥ ደጋፊዎችን ስሜት እየሞገተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ እጅግ በጣም ተናዷል፤ ተበሳጭቷል፡ቲም ለማ የኢትዮጵያን ሕዝብ ‘ዋቴ’ ሠርቷል።  ዶ/ር ዓቢይም እንዲሁ የቁጭ በሉ ተግባር እየፈጸሙ ይመስላል፤ የሚለው ጥርጣሬ እያየለ መጥቷል። አላወቁትም እንጂ አዲስ አበቤ አራዳ ነው። እንኳን ሲሸጡት ገና ሲያስማሙት ያውቃል። እንደ እውነቱ ከሆነ ዶ/ር ዓቢይ አሁንም ከሕወሀት መንገድ ፈቀቅ አላሉም፤ አሿሿማቸው ሁሉ በዘር ላይ የሚያጠነጥን እና ልክ እንደ ሟቹ መለስ ዜናዊ በዙሪያቸው ያሰባሰቧቸው ሰዎች ሁሉ እጅግ በጣም ደካማዎችና ለቦታው የማይመጥኑ ሰዎችን ነው በመባል ወቀሳው በርትቷል። ይህም ዶ/ር ዓቢይ በራሥ መተማመን እንደሌላቸው ይሳብቃል ይላሉ ታዛቢዎች። ብዙ ብዙ ድብቅ አጀንዳዎች እንዳላቸው ተጨማሪ ማስረጃ ማቅረብም አይከብድም ይላሉ ተቆርቋሪዎቹ።

የወልቃይትና የራያን ጉዳይ በተመለከተ የድንበርና ወሰን አጥኚ ኮሚሽን አቋቁመዋል። እንደገናም የአዲስ አበባን የማንነት ጥያቄም በተመለከተ በተመሳሳይ ሌላ ኮሚቴ አቋቁመዋል። የኮሚቴ አሿሿማቸው ጉዳይ ሲታይ ገለልተኛ መሆን ሲገባው፤ ትኩረትን ከማስቀየስ ያለፈ አይደለም፤ ከወዲሁ አድሏዊ እንደሆነ ማስረገጥ ይቻላል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይፈልጋቸውን፤ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለውን የኢሉሚናቲ አርማ የሆነውን ኮከብ አላነሱም፤ የአገር ሉዓላዊነትንና የሕዝብ አንድነትን የሚጻረረውን አንቀጽ 39 ባለበት እንዲቀጥል ይደግፋሉ። በሐሰት ትርክት ላይ ተመሥርቶ የአማራን ሕዝብ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለማቃቃር የቆመውን የአኖሌ ሃውልት አላፈረሱም፤ እጅግ በጣም የሚገርም ጉዳይ ነው፤ ሕዝብን መናቅ ውጤቱ የከፋ ውርደት ላይ መውደቅ ይሆናል በማለት ትዝብታቸውን ይሠነዝራሉ።

‘ለማ-ዋቴ’ እና ‘ዓቢይ-ቁጭ በሉ’ እስከመቼ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያታለሉ እንደሚዘልቁ ለማየት ያብቃን። የኦነግን እና የወያኔን የመገንጠል አጀንዳ እያራመዱ ናቸው። ጃዋር መሐመድ ደም የሚያፋስስ፤ ሕግ የሚጥስ፤ ሀገር የሚያተራምስ ስብከቱን በየጊዜው ሲያናፍስ ዝም ተብሏል። በአንፃሩም ጠ/ሚንስትር ዓቢይ አህመድ፤ የአዲስ አበባን የማንነት ጥያቄ በተገቢው መንገድ ለማረጋገጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙትን እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ፤ ማስፈራሪያና ዛቻ፤ ለአዲስ አበባ ሕዝብም ‘ጥሩ ሥንሠራ አሞግሱን፤ ስንሳሳት ደግሞ አርፋችሁ ቁጭ በሉና በመጭው የምርጫ ጊዜ አትምረጡን’ ካልሆነ ግን ማሰርም መቅጣትም እንጀምራለን በማለት ማስጠንቀቃቸው ብዙ ደጋፊዎቻቸውን አሳዝኗል።

እንግዲህ ዶ/ር ዓቢይ ፍትሀዊ ናቸው ለማለት እጅግ በጣም ይከብዳል። ከአሁን በፊት ያልታየ አምባገነን እየሆኑ ነው። ‘ቁጭ ብሎ የሰቀሉት ቆሞ ሊያወርዱት ይቸግራል’ እንዲሉ ከአሁኑ ሕዝቡ በአንድ ላይ ተባብሮ እንዲህ ያለውን ጋጠወጥነትና የሥልጣን ብልግና ማስቆም ይኖርበታል። ዶ/ር ዓቢይ እንዲህ ዓይነት ዓይን ያወጣ መድሎ የሚያራምዱ ከሆነ፤ እስከ ምርጫው ድረስ በተለይ በአዲስ አበባ አካባቢ ምንም ዓይነት ልማታዊ እንቅስቃሴ ሳይደረግ አሁን በአለው ሁኔታ መቆየት አለበት። እንዲህ የማይሆን ከሆነ ግን በልማት ስም በሚካሄዱ ሕገወጥ ዘረፋዎችና አድሏዊ ውሳኔዎች መንግሥትንና የአዲስ አበባ ሕዝብን ለከባድ ችግርና ፈተና የተጋለጠ እንደሚያደርጋቸው አይጠረጠርም።

የአዲስ አበባ እና የኦሮምያ ድንበርን በተመለከተ እንደጎረቤት አጥር ገፋኸኝ፤ ገፋኸኝ ክርክር ሆኗል። ይህ በጣም የወረደ ተግባር ነው። አዲስ አበባ ለወደፊቱ ቢያንስ ለቀጣዩ አንድ መቶ ዓመት የሚመጥን የዕድገት ፕላን የሚያካትት ሠፋ ያለ ክልል ያስፈልጋታል።

አዲስ አበባን በተመለከተ እንዲያውም ጨረታ ወጥቶ የከተማ ልማትና ዕድገት ጥልቅ ዕውቀት ያለው የውጭ ኩባንያ በነፃነትና በገለልተኝነት፤ ያለአድሎ ቢያጠናውና ለመጭው መቶ ዓመት የሚጠቅም ዕቅድ ቢወጣ መልካም ይሆናል። ምክንያቱም የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት በጨመረ ቁጥር ከተማው በየጊዜው እያደገ ስለሚሄድ ከአሁኑ ሠፋ ብሎ መከለል ይኖርበታል። ቢያንስ ቢያንስ ከ40-50 ኪሎሜትር ዙሪያ በከተማው አስተዳደር ስር መሆን ይኖርበታል። ለምሳሌም ደብረዘይት (ቢሾፍቱ) በአዲስ አበባ ሥር መሆን ይኖርበታል። እንደዚህ ያሉ አካባቢዎች ኮስሞፖሊታን በመባል ይታወቃሉ። ነገር ግን አዲስ አበባን ኦሮምያ ክልል ለማድረግ ማቀዱ ቀርቶ ማሰቡ እንኳ ከመሃይምነት የዘለለ ከቶ ሊሆን አይችልም። ዋቴ ለማና ቁጭበሉ ዓቢይ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያተላላችሁ መቀጠል እንደማትችሉ ልታውቁት ይገባል።

ታላቅ ፍቅር እምነትና እና አክብሮት የቸራችሁን የኢትዮጵያን ሕዝብ በመካድ፤ ዕልቂትና ዘረፋ የሚሰብከው ጀዋር ሞሐመድ የሚያዋጣችሁ ከሆነ ቀጥሉበት። ሰው ለክብሩ ይሞታል፤ አንድ የራስ መተማማን ያለው ሰው እንኳን ሕዝብን፤ ጓደኛውን እንኳ ለማታለል ኅሊናው አይፈቅድለትም። ሕዝብን ማታለል ማለት ለዘለዓለም በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ተግባር መፈጸም ነው። እንዲህ ያለው ታሪክ ለልጅ ልጅ የሚተላላፍ ትውልድን የሚያሳፍርና አንገትን የሚያስደፋ ይሆናል። ስለዚህ እየተስተዋለ ቢሆን መልካም ነው።

‘….. ላይ ቁጭ ብሎ ፈስ ገማኝ’ ፖለቲካ የሚያዋጣ አይደለም። ተወደደም ተጠላም ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያን ሕዝብ በኃይል ማስተዳደር ሕልም መሆኑን መረዳት አዋቂነት ነው። ያለፈውን እያነሳን በዚያ ጌዜ ሳናጠፋ  ጠቃሚውን እየያዝን በአሁኑ ላይ ተመሥርተን የነገውን እያሰብን ብንሠራ ይሻላል፤ ያሉት ሁላችንንም ያስማማናል። ነገር ግን የሐሰት ትርክት ላይ ተመርኩዞ የታየውን ሁሉ የኔ የኔ ማለት፤ ወይም የሥልጣንን መዋቅር መከታ በማድረግ በስውር አንዱን ማኅበረሰብ ለመጥቀምና ሌላውን ለመጉዳት ማሴር ኅሊና ባይሞግትም ከፈጣሪ እይታ ውጭ የሚሆን ነገር የለምና፤ ውጤቱ የሥልጣን ዘመንን ብቻ ሳይሆን ዕድሜንም ለቅስፈት መዳረግ ይሆናል። ለዚህም ምንም ማስረጃ አያስፈልግም፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊና በአቡነ ጳውሎስ የደረሰውን የኢትዮጵያ አምላክ ፍርድ አሁንም አይደገምም ብሎ ማሰብ ብልህነት ሳይሆን ጅልነት ነው። እንኳን የሚታየውን ገና በሰዎች ልብ የተጸነሰውን ተንኮል የሚያውቅና የሚያከሽፍ፤ ኃያል የኢትዮጵያ አምላክ ክብር ምስጋና ይድረሰው።

 

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop