ሰው መሆናችንን ካልተገነዘብን፣መጨረሻችን አያምርም –  በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርሰ

 ( ግጥሜ   አዲስና ሁሉንም ቋንቋ ተናጋሪ በአባልነት የሚይዝ  ለምሳሌ፣  “የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የመደመር ፓርቲ”  (ኢአመፓ) ዓይነት  እሥካልተመሰረተና ከዶ/ር አብይ አእምሮ ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዜጎችን በፓርቲ አባልነት  እስካላሳተፈን ጊዜ ድረስ፣   ሌላው ዓለም ላይ በሌለ “በአግላዮችና እና በሤረኞች በተሞላ  የቋንቋ ፓለታካ” ሀገር ተረጋግታ አትቀጥልም።” የሚል አንድምታ ያለው ነው። )
     ” የሤራ ቦጠሊቃ”
“እኔ ሰው አይደለሁም!”ዕወቅ ” ትግራዊ” ነኝ!
እኔም” አማራ ነኝ።” ሰው ነህ አትበለኝ !
ለምን ሰው ትለኛለህ?”ኦሮሞ!” ብለህ ጥራኝ።
አቤት አልልህም፣”አንተ ሰው! “ስትለኝ።
እኔ ብሔረሰብ፣ጎሣና ክልልነኝ።
ወላይታ ጋሞ፣እኔ ሲዳማ ነኝ!
አገው፣ኩናማ ዕወቅ መዠንገር ነኝ።
የወል መጠሪያዬን ጎሣዬ ወስዶታል
በጎሣና በቋንቋ መጠራት ግዴታዬ ሆኗል።
ኦባማ፣ ኬኒያዊ ዘር  ኖሮት አሜሪካንን ሲመራ
ትራፕ ከጀርመን ፈልሶ፣ ሲሆን እሱም አውራ
አንተ ኢትዮጵያዊው፣ወደኋላ ተመልሰህ
ዘመነ መሳፋት ውስጥ መክሊትህን ቀብረህ
“ሰው ከቶም አይደለሁም _ቋንቋ ነኝ “ትላለህ።
ለሆድህ ተገዝተህ
ቋንቋ፣ጎሣ እያልክ …
በዘውግ ፖለቲካ…
ህዝብን ታባላለህ…
” መልኬን ቁመናዬን፣እርሳው ሰውነቴን
ከአለም ህዝብ ጋር፣ያለው አንድነቴን።
ወግድ! አጨቅጭቀኝ፣በቃ! እኔ አገውነኝ!
ጉራጌ ወላይታ፣አፋር ቅማት ነኝ!
ራያ፣አርማጮህ፣ቤንችና ማጂነኝ!
ቦዲ፣ሀመር፣ሸካ፣በርታ፣ሲዳማነኝ!”
እንዲል ፣
ቀዬው ድረስ ወርደህ ትቀሰቅሳለህ
በማህበራዊ ሚዲያ እሳት ትጭራለህ።
ይህ ብቻም አይደለም፣ያንተ ተንኮልህ
ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር ግንባር ፈጥረህ
በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ውስጥ ልዩነትን አጉልተህ
ታስብላለህ፣
“እኔ ሰው፣አይደለሁም !”የጠራው መንዜ ነኝ
የተጉለት የቡልጋ…እኔ የሸንኮራ ነኝ!
ከጎጃምም የደጀን… የደብረማርቆስ ነኝ።
ከጎንደርም ጎደር !ደብረታቦሬ ነኝ።
እውቅ ፈሪ  ሁላ!እኔ አርማጮህ ነኝ።
እኔ ያባ ጃሌው…ዕወቅ የቋራ ነኝ !!
ዕወቅ” ሰው ነኝ! ” ባይ ሁላ!!
ከኦሮሞም ኦሮሞ እኔ ወለጋ ነኝ!
የነቀምቴ !የነጆ…የደምቢ ዶሎ ነኝ !!
“እኔ ሰው አይደለሁም! “በቃ አሩሲ ነኝ !!
ባሌ!ጮሬ …ሸዋ ! ጅማ፣ኢሉአባቦራ
ከረዩ፣ቦረና፣ቆቱ…ሐረርጌ ነኝ !
“ሰው ነኝ !!” ባይ ሁላ ፣ በቃ አፍህን ዝጋ !!
በቋንቋ ፖለቲካዬ  ላይ፣ አታምጣ አደጋ።
ከ27 ዓመት በፊት ለሥልጣን ስበቃ
ተገን አድርጌ ነው የቋንቋን ጠበቃ !!
እንደሥልጥኑ ዓለም ፣ በሀገር ሰው ብመካ
ይኑር ብል አንድ ቋንቋ ሀገሬን የሚያስመካ
ልራመድ ብሞክር፣በምዕራቡ ፖለቲካ
107 ፖርቲ፣አይኖርም ነበር ፣ወሬውን እየከካ!
ቋንቋ ሥልጣን መሥሎት፣በግብዝነት እያስካካ!
መች ይኖር ነበር፣ተቧድኖ ፣ እየተላላሰ ሲያወካ!
አልገብቶህ እንደሆን፣የሴራ ነው የእኛ ቦጠሊቃ!!
በማለት የሚጀምር “ብርሌ ከነቃ፣አይሆንም ዕቃ !”
ተራምደህ እለፈው፣አትቁም፣ አጋርህን ጥበቃ !
ያለና የሚኖር ነው ግጭትና ሥንጠቃ !
ወርውረና ጣለው ብርሌው ከነቃ !
ለዘመድ አዝማድህ ሰብስብ እንጂ ጥሪት
ግዛ እንጂ አዲስ ዕቃ !
ብዝበዛህን አጣድፈህ ፣ህዝብ ከእንቅልፉ ሳይነቃ!!!…
መኮንን ሻውል ወ/ጊ (ጥቅምት 14/2011 ዓ/ም)
107 ፖርቲ እና የትርፍ ዳቦ ፍለጋ ትንቅንቅ በኢትዮጵያ
      በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
     በኢትዮጵያችን የዳቦ ጥየቄ ለዘመናት መልስ አላገኘም፡፡መልስ ያላገኘውም፣በየዘመናቱ የመጡ እና ወደ  አፈርነት የተለወጡ ጥቂት መንግሥታት ፣ዳቦ ሰራቂዎች እንጂ ዳቦ አምርተው ለህዝብ በአግባቡ የማያከፋፍሉ በመሆናቸው ነው፡፡
      የፈውዳሉ ሥርዓት፣መለኮታዊ ሥልጣን፣አለኝ ብሎ፣ ከእግዜር በታች ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ መሆኑን ሃይማኖትን ጠቅሶ፣በብሉይ እምነት መሰረት  ̋ ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ ̋ በማለት፣ ̋ የሀገር ዳቦ የእኔና የቤተሰቤ ብቻና ብቻ ነው፡፡በፍቃዴ፣ለወደድኩት ያሻኝን አደርግለት ዘንድ ሥልጣን አለኝ፡፡ ከፀሐይ በታች የስልጣን ባለቤትም እኔ ነኝ፡፡ “ ባይ በመሆኑ፣በግልፅ የተትረፈረፈ ዳቦ በግሉ ቢያከማች  ከቶም አያስገርምም፡፡
   የሚስገርመው ደርግ “ይህ ደም መጣጭነት ነው እንጂ መለኮታዊ ስልጣን አይደለም።”  በማለት ፣ቀኃሥን ከዙፋን አውርዶ  ሲያበቃ ፣አባላቱ በሂደት ራስ ወዳድ ፣ግብዝ፣ትምክህተኛ እና አምባገነኖች እየሆኑ  መጡ።… ፣በመጨረሻም ቁንጮው መሪ ሳይቀሩ፣ በህዝቡ የጋለ የሀገር ፍቅር ስሜት ላይ፣ ቀዝቃዛ ውኃ ቸልሰው መኮብለላቸው አይረሳም።
    ከዚህ እኩል  የሚያስገርመው ና የሚያሳዝነው፣በደርግ የአገዛዝ ዘመን ፣ለወያኔም ሆነ ለሻቢያ ከኢትየጵያ ጦር እኩል ስንቅና ትጥቅ፤በማከፋፈል፣ በዜጎች ህይወት የነገዱ፣ በእህቶቻችን እና በወንድሞቻችን  ደም የጨቀየ ዳቦ የግበሰበሱ መኖራቸው ነው፡፡ ዛሬም ከታሪክ አልተማርንም።
“ዋ! ከታሪክ ያለመማር፣ታሪክን ለመድገም ያስገድዳል።”
     እዚህ ላይ ፣ አንባቢ ልብ ሊለው የሚገባ እውነት አለ፡፡ይኸውም በየዘመናቱ በሥልጣን ኮርቻ ላይ የወጡ፣የኢትዮጵያ መንግስታት የየራሳቸው በጎና ጥሩ ጎን እንዳላቸው የሚክድ የታሪክ ፀሐፊ ያለመኖሩን ነው፡፡ይሁን እንጂ ለህዝብ ዳቦ ከማከፋፈል አንፃር፣አንዳቸውም ሚዛናዊ አልነበሩም፡፡ይልቁንም፣በሚስጥርና በግለፅ፣ለግላቸውና ለጥቅም ሸሪኮቻቸው፣የተትረፈረፈ ዳቦ በማደል፣ህዝብን የሚያስርቡ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ገበናቸውን በማስጣት ሥንፈትሸው፡፡
     ሁሉም፣የኢትዮጵያ ገዢዎች፣  ይነስም ይብዛ፣የሀገርን ሀብት ወይም ዳቦ፣ለራሰቸው ና በተዋረድ ላሉ የሥርዓቱ አውራዎች ሲየከፋፍሉና ኑሯቸውን ሲያደረጁ እንጂ፣ህዝብ ና ሀገርን በተገቢው መንገድ በማሳደግ ቢያነስ በቀን ሦስት ጊዜ ዜጎች  እንዲበሉ ሲያደርጉ አልተሰተዋሉም፡፡
   (እናስ በዳቦ ጥያቄ ሥልጣንን ያገኛት፣የአፍሪካ ፖለቲከኛ፣ዳቦ ያለጠባቂ ሜዳ ላይ ተበትኖ ሲያገኘው ላያግበሰብስልህ ነው?…)
      በየሰርዓቱ የነበሩ ቱባ ባለስልጣነት ሁሉ፣በህዝብ ሥም፣እየማሉና እየተገዘቱ የህዝቡን ዳቦ የሚሰርቁ፣ሌቦች ነበሩ፡፡ሰርቀውም ሲያበቁ፣በሀገርና በውጪ፣የሚምነሸነሹ ብቻ ሳይሆኑ፣የበዛ ዳቦ በስማቸው በባንክ በማከማቸት ህዝብን የሚያስርቡ እነደነበሩ ታሪክ መስክሮባቸዋል፡፡( የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ባለሥልጣናት  ዘረፋ ግን በዛ! )
     ዛሬም ልዩ የቁጥጥር ሥርአት ባለመዘርጋቱ  የተነሳ በፌደራልና፣በየክልልሉ ያሉ አንዳንድ አገልግሎት ሰጪዎች (፣በቀበሌ የተመደቡ የፖለቲካ ሹማምነት ፣የማዘጋጃ ሹማምነት፣ህግ አስፈፃሚ አካላት፣ገቢዎች ወዘተ)በጨረታ ሥም፣በህገወጥ ግንባታ ሥም፣የመንግስት ገቢ በማስገባት ሥም፣የቀበሌ ቤትን በመቆጣጠር ስም፣ህግን እና ህገመንግስትን በመጠበቅ ሥም፣የሚደረገው ብዝበዛ አላባራም።
    ዛሬም፣በተዋረድ ያሉ፣አንዳንድ ባለሥልጣናት፣(አገልጋይነታቸውን የዘነጉ)ተገልጋዩን፣ያለጉቦ አንገለግልም በማለት እያንገላቱት ነው።በቀበሌ ነዋሪነት፣መታወቂያ ሥም ሳይቀር እየዘረፉት እነደሆነ ታዛቢ ያወራል፡፡
     ታዛቢ ሲያወራ የመንግስት ጆሮ በመስማት እውነትን በረሱ መንገድ በማግኘት ፣ሳይዘገይ መፍትሄ መስጠት አለበት የምንልበት የመንግስት አወቃቀር ሥርዓት ላይ ገና አለደረስንም፡፡ዛሬ እና አሁን፣ የመንግስትን ሥልጣን የያዘው የለውጥ ኃይል ፣አንዚህን የህዝቡን ዳቦ፣እጁን እየጠመዘዙ የሚቀሙ፣ (ትንሾን ጣት ሳይቀር የሚቆሩጡ)ዘራፊዎችና ሌቦች ላይ ጨከን ያለ የህግ ቅጣት እንዲያገኙ የሚያደርግ ህግና የቁጥጥር ሥርአት ለመዘርጋት ፣ቀና ደፋ ማለቱን የሚሳዩ፣ተጨባጭ መንግስታዊ ሥራዎች መኖራቸውን ባንክድም ፣የቀደመው ታሪካችን ትርክት እንደ በጋ ጉም፣በአብይና በቲም ለማ ሃሳብ እንደ በጋ ጉም ታይቶ እብስ የሚል ባለመሆኑ፣ሁሉም ፖለቲከኛ ሰው ሆኖ መቆሙን በውል ሊገነዘብና፣ሰው ለሆነው ወገኑ በሞላ ከልቡ ለማገልገል ቅን፣በጎና፣በፍቅር የተሞላ ህሊና ሊኖረው ይገባል፡፡ይህ ካልሆነና 107 ፖርቲ ትርፍ ዳቦ ለማግበስብስ በሴራ የሚራኮት ከሆነ ነገራችን ሁሉ “የእምቦይ ካብ ” ሆኖ ይቀራል።
    ያለፈውን የጭቆና እና የብዝበዛ ሥርዓት ፣ሙሉ ለሙሉ በአዲስና በትወራ ብቻ ፣ሆዳችንን በማይነፋ፣በቅን ዜጎች የሚመራ እና ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው ሥርዓት ለመቀየርም፣ከአዲሱ የለውጥ ኃይል ጎን ከመሰለፍ ውጪ አማራጭ የለንም፡፡
       ያለፈው ሥርዓት፣ ሙሉ ለሙሉ እስታለተቀየረ ድረስና ‘የፓርቲና የመንግስት አሰራር መቀላቀሉ እስካለከተመ ድረስ” ፤ቀበሌ “በመዘጋጃ አገልግሎት “እሰካልተተካና ለሠላማዊ የሰልጣን ሽግግሩ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ በጠቅላላ ተጠቃሚ ለሚያደርግ የዴሞክራሲ፣የሰላም እና የመቻቻል መድረክ፣ በራችን ክፍት እስካልሆነ ድረስ፣አሁን ከምናየው የከፋ ትርምስ በዚች ሀገር እንደሚከሰት መገመትም ከለውጥ ኃይሎች ጋር እንድንሰለፍ ያስገድደናል፡፡
      እንደምታውቁት፣ “ሴጣኑ ያለው በዝርዝሩ ውስጥ ነው፡፡ “ ከህዝብ ጋር ሁሌም የሚገናኝ የስልጣን መቀመጫ ወይም ወንበር ያለው እታች ነው፡፡ቀበሌ ነው፡፡የለውጥ ኃይሉ መቀመጫውን ከምስጦች ሳያፀዳ ፣ተደላድሎ መቀመጥ አይችልምና የኢትየጵያ መንግስት ልክ እንደአውሮፓና አሜሪካ የተደላደለ እንዲሆን እታች ያለው ህዝብ ከዳቦ ዘራፊዎች ነፃ መውጣት ይኖርበታል፡፡ለዚህም ላይ ያለው መንግስት  አዳዲስ የቁጥጥር ሢሥተም ለመፍጠርና ለመተግበር  ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል፡፡
    ሁሉም ዜጋ ወዛደሩ፣ወታደሩ፣ገበሬው፣የመንግስት ሰራተኛው ፣ነጋዴው፣ተማሪው ፣አስተማሪው፣በተለያየ ሥራ የተሰማራ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፣ከመሞቱ በፊት ፣ለትውልዱ የሚያስተላልፈው ሀብት ከሀገሩ  ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማግኘት እንዲችል ፣የህግ ልእልና መታወቅ እና ህግ መከበር ይኖርበታል፡፡ይህንን ዕውቀት ማሥረፅ  እና መተግበር የሚቻለው ደግሞ፣ሰው ሁሉ በህሊናው እንዲገኝ የሚያደርግ ተከታታይ የሆነ በጥበብ የተሞላ እውቀት፣ሁሉም በሚገባው ቋንቋ እንዲያገኝ በማደረግ እና በድፍን ኢትዮጵያ ተዞዙሮ በመሥራት ሀብት የማፍራት መብቱ ሲረጋገጥለት ነው።
ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ህሊና እና ሞራል ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጉናል።
   ለህዝብ ጥቅም መከበር እንታገላለን የሚሉ  በ107 የፖለቲካ ፖርቲ ውስጥ የምናስተውላቸው ፖለቲከኞች እንደኔ ሃሳብ  በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከመመዝገባቸው በፊት፣  አሥቀድመው  “ያለምንም ሸፍጥ” እውነተኛ ተሐድሶ እና ንስሐ     ገብተው ፣ በጋብቻ  የተቀላቀለውን እና እንደጨው በድፍን ኢትዮጵያ በዜግነቱ ኮርቶ   የሚኖረውንም ሆነ በአንድ አካባቢ የሚኖረውን ዜጋ  ፈፅም የማይወክል ሃሳብ  እርግፍ አድርገው መተው ይኖርባቹዋል ።
    በዜግነታቸው እምነት ሳይኖራቸው ፣ (ህወሓትን ጨምሮ ) በባህልና ተወራራሽ በሆነው ቋንቋ የተሳሰረውን አንድ ህዝብ በሤራና በጠመንጃ ጉልበት   ለመገንጠል እንደሚፈልጉ ሥማቸው ጮኾ እያሣበቀባቸው ” ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ነን ። ” ማለት ፣ ከቶም አይችሉምና !   ለማያባራ ዳቦ ሢሉ ተቧድነው የሙሰረቱትን የጎሣና  የዘር ፣ቋንቋን ማዕከል ያደረገ አደረጃጀትን በመተው ፣ለሀገሪቱ ዜጎች  እኩል  ጥቅም ሲሉ ፣ ተዋህደው ርእዮተ ዓለማዊ ፓርቲ  ማቋቋም” ኢትዮጵያ !ኢትዮጵያ !” በቃል ማለት ብቻውን እንደማይበቀ በተግባር የሚመሰክሩበት ብቸኛው አማራጫቸው እንደሆነ አሥባለሁ።ቢያንሥ ለእኔ እና  በሚሊዮን ለሚቆጠሩ መሰሎቼ ዓለም ላይ የሌለ በቋንቋ፣ በዘርና በጎሣ የተመሰረተ ፓርቲ ግዜውን ጠብቆ የማፈነዳ አውዳሚ ቦንብ ነው። ለቀጣዩ ትውልድ ይህንን ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ቀብረን ማለፍ የለብንም።ይህንን የጎሣ፣የቋንቋ ፣የዘር ፣ክፍፍልን፣ኢትዮጵያዊያን የፈጠርነው አይመሥለኝም።የታሪክ ባለሙያዎች ደጋግመው እንደመሰከሩት ፣የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ለብዝበዛ  አመቺነት ሲሉ የፈጠሩት ዜጎችን እርስ በእርሥ ማናቆርያ ሥልት ነው ።ሥለዚህም ነው በግጥሜ ሰው መሆናችንን አበክረን እንድንገነዘብ ለማሳየት የፈለኩት።ሰው መሆናችንን መገንዘብ ካልቻልን የዚች ሀገር ዜጎች መጨረሻችን አያምርም።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያን እናድን::
Share