October 22, 2018
17 mins read

አንድ ሕዝብ ነን ወይስ አይደለንም – nፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

“እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ሕዝብ ነን” ከሚሉት አንዱ ነኝ። አንድ ከሆንን ለምን እንጋጫለን?  “በልዩነት አንድነት” የሚል አነጋገርም አለን። በልዩነት አንድነት ይቻላል ወይ? ልዩነታችንን ጠብቆ አንድ የሚያደርገን ምንድን ነው? ያንን አንድ የሚያደርገንን ሁላችንም ካልተቀበልነው፥ አንድነትን ምንም ያህል ብንሰብከው እንደማግኔት አሉታ ተራርቀን እንኖራለን እንጂ አንቀራረብም።

ባልና ሚስት የተለያዩ ናቸው። እሱ ወንድ ነው፤ እሱዋ ሴት ናት። “አንድ ነን” ሊሉ የሚችሉት ትዳር ለመመሥረት ስለተስማሙ ነው። የተለያዩ ሆነው ሳለ፥ አንድ የሚያደርጋቸው ሁለቱም የተቀበሉት ምክንያት አገኙ ማለት ነው። ክርስቲያኖች የተለያዩ ሰዎች (ከተለያዩ ነገዶች) ሊሆኑ ይችላሉ። “አንድ ነን ሊሉ” የሚችሉት ሁሉም የተቀበሉት አንድ ዓይነት የአምልኮ ሥርዓት ቢኖራቸው ነው። አንድ ዓይነት ያልሆኑ ሕዝቦችን ሃይማኖት አንድ አደረጋቸው። ቋንቋም አንድ ያልሆኑ ሕዝቦችን አንድ የማድረግ ኀይል አለው። ኦሮሞችን አንድ ያደረጋቸው ቋንቋ ነው። አማሮችንም አንድ ያደረጋቸው ቋንቋ ነው። ጎጥና ዘርም አንድ ያደርጋሉ። አንድ የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ከሌላው ይለያሉ። “እኛ አንድ ነን” ማለት “ከሌላው የተለየን ነን” ነን ማለት ነው።

አንድ ምክንያት አንድ ያደረጋቸውን ሕዝቦች፥ ሌላው ምክንያት መጥቶ ይበትናቸዋል፤ የተለያዩ ሕዝቦች ያደርጋቸዋል። ቋንቋ አንድ ያደረጋቸውን ሃይማኖት የተለያዩ ያደርጋቸዋል። ባህል አንድ ያደረጋቸውን ሰዎች የትውልድ ቦታ የተለያዩ ያደርጋቸዋ። በዚህ ምክንያት እኮ ነው፥ “ተጋብተናል፥ ተዋልደናል፥ ደማችን አንድ ነው” የምንለው እውነታ ሁሉ ልብ ለመማረክ አቅም ያነሰው። በዚያ ላይ መናናቅ አለ። የጎሳን ስም እየጠራን የስድብ ቃል የምናደርገው አለን። ከኦሮሞች ጋር በነበርኩበት የልጅነት ጊዜ “ሲዳምቲቲ እነና” እየተባልኩ ነው ያደግሁት። አማሮቹም ስድብ አላቸው። ዋናው እዚያም ቤት እሳት መኖሩን አለመዘንጋት ነው።

ኢትዮጵያዊ ሥነ ጽሑፍ የዳበረው፥ ኢትዮጵያዊ መንግሥት የተቋቋመው ኦሮሞዎች ማህል ኢትዮጵያን ከመውረሳቸው በፊት ከወደሰሜን በኩል ስለሆነ፥ ይህ ታሪክም እንደ ሃይማኖትና እንደ ቋንቋ፥ በሰሜኖች (ትግራይ-አማራ) እና በኦሮሞዎች መካከል ከሁሉም የከፋ ልዩነት ፈጥሯል። የኦሮሞ ፖሊቲከኞች፥ “ሥነ ጽሑፉም መንግሥቱም ምናችን ናቸው?” ሲሉ ይሰማሉ። ያለፈ ታሪክንና ጊዜን ጠርቶ በፈለጉት መንገድ ማስኬድ አይቻልም። ከሰዓት በኋላ የደረሱ ሁሉ፥ ኢትዮጵያን ገናና ያደረጋትን ከሰዓት በፊት የተፈጸውን ማክበር ውዴታችንም ግዴታችንም ነው።  ግን እኮ ኦሮሞዎች ወደማህል ኢትዮጵያ ከገቡ ወዲህ በሁለቱም ሥርዓቶች (በመጻፍም፥ መንግሥቱን በማካሄድም) እኩል እንደተሳተፉ ያፈጠጡ ማስረጃዎች አሉ። ሥራ ማስኬጃው (ቋንቋው) አልተቀየረም እንጂ ሠራተኞቹ ተለውጠዋል። አስተዋፅኦው የሁሉም ሆኗል።

“አንድ ሕዝብ ነን”  እንዳንል፥ አንድ ሕዝብ እንዳይደለን የሚከለክሉን ምክንያቶች ከላይ ተዘርዝረዋል። አዲሶቹ መሪዎቻችን ቢቸግራቸው፥ “ብሔር፥ ብሔረ ሰብ፥ ሕዝቦች ሆይ” እያሉ ይጠሩናል። እልዩነታችን ላይ ስለሚያተኩር፥ ጥሩ መፍትሔ አይደለም። “ብሔር፥ ብሔረ ሰብ፥ ሕዝቦች” ሲባል፥ የትኛው መጠሪያ ነው የትኛውን ኢትዮጵያዊ የሚያመለክተው? “ብሔር” ሲል፥ “አቤት” የሚል፥ “ብሔረ ሰብ” ሲል፥ “ብሔረ ሰብ” እስከሚባል ጠብቆ፥ “ሕዝቦች”  ሳይባል ቀደም ብሎ፥ “አቤት የሚል”፥  “ሕዝቦች”  እስኪል ሲል ቆይቶ “ሕዝቦች” ሲል “አቤት” የሚል ኢትዮጵያዊ ማነው? በሌላ አነጋገር፥ “መጠሪያየ ይኼኛው ነው” የምንለው የትኛውን ነው? “አቤት” ለማለት ተራችን መቸ ነው–“ብሔር” ሲባል፥ ወይስ “ብሔረ ሰብ” ሲባል፥ ወይስ “ሕዝቦች” ሲባል?

ከዚያም አልፈው፥ ሰፍረን የተገኘንበትን ቦታ ለሁላችንም ሳይሰጡን፥ “ለሁላችሁም ሰጥተናችኋል” ብለው፥ ትንሾችን የትልቆች ሰለባ አደረጓቸው። ብዙዎቻችንን የአማራ፥ የትግራይ፥ የኦሮሞዎች ጥገኞች አደረጉን። ይህ መፍትሔ እሌላ አገሮች ተሞክሮ አልሠራም፤ እዚህም ሳይሠራ እያየነው ነው። የወደዱት አሉ፤ እነሱ በውስጣቸው የሚኖሩ አናሳ ጎሳዎች መብት ቢጣስ ግድ የሌላቸው ትልቆች ግን ኋላ-ቀር ነገዶች ናቸው።

የአንድ አገር ሕዝቦች ሆነን መኖር በግድም በውድም ከወሰንን፥ የአንድ ሀገር ሕዝብ የሚያደርጉንን ምክንያቶች ፈልገን መኮትኮት ይኖርብናል።  አለባብሰን አንረስ፤ እንደማየው፥ “በባህል በዘር አንድ ነን” ማለቱ ብቻውን አላዋጣንም። ምክንያቱም፥ በባህል በዘር አንድ አይደለንም። በባህል ረገድ ሱማሌዎች ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ይልቅ ለነዚያዎቹ ሱማሌዎች ይቀርባሉ። ጉሙዞችና ጋምቤላዎች ከትግሬዎች ይልቅ ለደቡብ ሱዳኖች የበለጠ ይቀርባሉ። ከዓሥር ዓመት ግድም በፊት ዋሺንግቶን ዲሲ ስብሰባ አድርገን ነበር። ከተናጋሪዎቹ አንዱ ጥቁር አሜሪካዊ በከተማው አስተዳደር ውስጥ ባለሥልጣን ነበር። “እንኳን ደኅና መጣችሁ” ካለ በኋላ፥ “እኛ እንቀበላችኋለን፤ እናንተ ግን አትቀበሉንም” አለን። እኔም ደርሶብኛል፤ አንድ ስብሰባ ላይ ጸሐፊያችን አፍሪካዊት ነበረች፤ ላይቤሪያዊት ትመስለኛለች። ሁሉን ስታነጋግር እኔን ትሸሸኝ ነበር። ሲያጋጥመኝ፥ “ብታነጋግሪኝ ቁንጅናሽን እንዳልነካብሽ ቃል ልግባልሽ” ብላት፥ “ደግሞ እናንተ ኢትዮጵያውያን ከመቸ ወዲህ ነው በጥቁር ሰው ላይ ቁንጂና የምታዩት?” አለችኝ።  “አየሃት ያቺን ልጅ? ልክ አበሻ/ኢትዮጵያዊት ትመስላለች” እንላለን። የትኛዋን ኢትዮጵያዊት ነው የምትመስለው?  ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም አንዲት ኤርትራዊት ለማግባት ቢፈልጉ፥ ኦሮሞ ስለሆኑ፥ ዘመዶቿ እንደከለከሏቸው እትዝታ መጽሐፋቸው ውስጥ መዝግበውታል።

በአንድ ሕዝብነት አብሮ መኖር ግዴታችን ሆኗል። ግዴታችን ከሆነ፥ ግዴታችንን በሰላም የምንወጣውና በደስታ የምንኖረው ስንከባበርና አንዱ የሌላውን ችግር ሲገነዘብ፥ ተገንዝቦም አብሮ በሰላም እንዳንኖር ላደረገን ችግር አብረን መፍትሔ ስንፈልግ ብቻ ነው። እንደመናቅ (“ና” ትጠብቃለች) የሚያስቆጣ ነገር የለም፤ ክብር ይነካል። መናቅ እንኳን ሕዝብን አንድን ሰውም ቢሆን ሊታገሡት የማይገባ ጠባይ ነው። ወያኔዎችን  ከምንጠላበት ምክንያቶች አንዱ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ዎች ሊያደርጉን ሲሞክሩ በማየታችን እንደሆነ አንረሳም። ንቀት ኃጢአት ነው፤ እግዚአብሔርን ያስቆጣል። ክርስቲያን የሆነ ሌላውን ከናቀ ንስሐ መግባት አለበት። “ወንድሙን ደንቆሮ የሚል ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል” ይላል ቅዱሱ መጽሐፍ። ሌላውን የሚንቅ ራሱን የናቀ የሰላም ጠላት ርኩስ ሰው ነው። ካህናት መገናኛ ብዙኃን ፊት ቀርበው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ሲገዝቱ መስማት እንፈልጋለን። ሆኖም፥ አንዱ በናቀ በነገዱ መቀየም ስሕተት ነው። አሜሪካን አገር ለጥቁሮች መከበር ብዙ ነጮች መሥዋዕት ሆነዋል።

ከላይ እንዳልኩት፥ የአንድ አገር ሕዝቦች ሆነን መኖርን አምላክ ከወሰነልንና እኛም ውሳኔውን ከተቀበልን፥ አንድ ሕዝብ የማያደርጉን ምክንያቶች የሚወገዱ ከሆኑ መወገድ፥ የማይወገዱ አመሎች ከሆኑ በጉያችን መያዝ፥ አንድ የሚያደርጉንን ምክንያቶች ፈልገን መኮትኮትና ማዳበር ይኖርብናል። ሥልጡን ሕዝብን ከኋለ-ቀር ሕዝብ የሚለየው ይህ ተግባር ነው። የአሜሪካን መንግሥት የተለያዩ ሕዝቦቿን በአንድ ሕዝብነት ለማስተዳደር የሚያሳየውን ጥረት እንመልከት። ጥረቱ ልጆች ከሚያድጉበት ትምህርት ቤት ይጀምራል።

ደግነቱ፥ እኛንም የአንድ ሀገር ሕዝብ የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉን። የተፈጥሮ መኖሪያችን በኢትዮጵያ ምድር ላይ ከሆነ ሁላችንም እኩል ኢትዮጵያውያን ነን። የጋራ ሀገር አንድ ሕዝብ ስለሚያደርግ፥ ኢትዮጵያዊነት አንድ ሕዝብ ያደርገናል። የሌላ አገር ዜጋ ካልሆነ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ሊል አይችልም። ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ካለ ደግሞ፥ አገሬ ነው ወደሚለው አገር መሄድ ወይም በሀገር-አልባነት መመዝገብ ይኖርበታል። ሌላ ሰላማዊ አማራጭ የለውም።

ሰዎችን አንድ ሕዝብ የሚያደርገው ሌላ ምክንያት ታሪክ ነው። የዚህ ምክንያት ባለጸጎች ነን። የውጪ ወረራን የነገዶች አባቶቻችን አብረው መክተዋል። በዘመነ መሳፍንት ወድቃ የነበረችውን ኢትዮጵያን የነገዶች አባቶቻችን አብረው አንሥተዋታል።

ሌላው የአንድነታችን ምልክት አንድ አገራዊ ቋንቋ (አማርኛ) በሁሉ ቦታ መታወቁ ነው። የመስፋፋቱን ታሪክ ትኩር ብለን ስንመለከት በዘመን ብዛት ቋንቋው ወደ ጎሳዎች፥ ጎሳዎች ወደ ቋንቋው መጥተው እንደተገናኙ እናያለን። ውጤቱ ሁለት ዓይነት  ሆኗል፤ ቋንቋውና ቋንቋውን የማያውቁ ጎሳዎች በመገናኘታቸው ምክንያት የተገናኙትን ቋንቋ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያደረጉ ሰዎች ወይ አማራ ሆነዋል ወይም የጥንት ጎሳቸው አባላትነት ይሰማቸዋል። አማራ የሆኑት የአማራውን ቍጥር አብዝተውታል። ዛሬ “አማርኛ ተናጋሪ እንጂ፥ አማራ የሚባል ዘር የለም” የሚባለው ስለዚህ ነው። ሌሎቹ የጎሳ ቋንቋቸውን ባያውቁም፥ የዚያ ጎሳ ሰዎች መሆንን ይመርጣሉ። አሜሪካን አገር እንግሊዝኛ ብቻ እየተናገሩ፥ “አየሪሽ ነኝ”፤ “ጀርማን ነኝ”፤ “ጣልያን ነኝ”  እንደሚሉት አሜሪካኖች ማለት ነው። ቋንቋ መነጋገሪያ መሣሪያ ስለሆነ፥ በማንኛውም ቋንቋ ቢጠቀሙ ከመሣሪያነቱ ያለፈ ዋጋ የማይሰጡ ኢትዮጵያውያንም አሉ።

ታላቁ የምሥራች፥ ሁሉን እኩል በሚያደርገው በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር (በዳምጠው) የማይምል ፖለቲከኛ ኢትዮጵያዊ  አላጋጠመኝም። ዲሞክራሲን ሁላችንም ተቀብለነዋል። ዲሞክራሲ ምድራዊ ሃይማኖታችን  መሆኑን ከተቀበልን፥ ቅዱስ መጽሐፋችን አብረን የምናረቀው ሕገ መንግሥት ይሆናል። እዚያ ላይ እናትኩር። ዲሞክራሲ ሥር የሚሰድበትን ማሳ እናለስልስ። የሚቆምባቸው ተቋማት እስኪቋቋሙ አንተኛ አናንቀላፋ። ዶክተር ዐቢይ የሚቀጥለው ምርጫ ማጭበርበር የሌለበት ይሆናል ብሎናል፤ አምነዋለሁ።

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop