October 21, 2018
21 mins read

ብሔራዊ የእርቅ ጉባኤ አሁኑኑ!!!!! – ጌድዮን በቀለ

ጌድዮን በቀለ Gedionbe56@yahoo.com

ከ3 ወር በፊት “ የሽግግር መንግስት ወይስ ብሄራዊ እርቅ ጉባኤ” በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሑፌ ላይ የዶ/ር አብይ መንግስት የሽግግሩ ጊዜ መንገስት እንደሆነ መቀጠሉ ተገቢና ትክክል ስለመሆኑ አንድ ሁለት ብየ ምክንያቶቼን አስቀምጨ ነበር። ይሁንና በዚያው ጽሁፌ ውስጥ ከዶ/ር አብይ መንግስት ጎን ለጎን የሽግግሩ ሂደት የተሳካና ህዝብ በሚፈልገው አቅጣጫ ይጓዝ ዘንድ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ባለድርሻ አካላት በወኪሎቻቸው አማካኝነት ተሳታፊ የሚሆኑበት “ ብሔራዊ የዕርቅ ጉባኤ አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም ሊኖረው የሚገባውን ድርሻና አገሪቱን ከሚያስተዳድረው የዶ/ር አብይ መንግስት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለውይይት መነሻነት የሚሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን መጠቃቀሴን አስታውሳለሁ።የዛሬው ጽሁፌ ታዲያ ያለፈውን ሃሳቤን የሚያጠናክሩ ሁናቴዎች መፈጠራቸውን ከመጠቆም አልፎ ጥያቄው ለነገ የማይባል መሆኑን ለማሳየት አልሞ የተነሳ ነው።

ጊዜ የለንም!፤ እያንዣበበ ያለው የጥፋት ሞገድ ጨርሶ ሳይጠራርገን ፈጥነን እርምጃ ልንወስድ ይገባል። ላለፉት 6ወራትና ከዚያም እምብዛም የላቀ እድሜ ያላስቆጠረው የመነቃቃትና የነጻነት መንፈስ ጸሀይ በደንብ ሳትሞቀን ብርሃኗ ጥላ እያጠላበት ስለመሆኑ ለመናገር የህይወት ልምዳችንን አገላብጦ ማየት በቂ ነው፡፡ እጅግ በፈጠነ መቀራረብ የከሸፉ ስርዓቶችን ላስተናገደና በውስጡ ላለፈ እንደኔ ላለ የዚያ ትውልድ ትራፊ  “የበለስ ጫፍ ማቆጥቆጧን” አይቶ የበጋን መቃረብ  ለመናገር አያስቸግረውም።

የተወደሰውና ከአማልክት እንደአንዱ ከሰማየ-ሰማያት ወርዶ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ሊታደጋት ነው የተባለለት የነዶ/ር ዓብይ ቡድን  “ከእባብ እንቁላል መሃል የተፈለፈለ እርግብ” ሆኖ በመገኘቱ ብቻ ፤ በብዙ ዘመን አንዴ እንደሚገኝ መሲህ “ባንተ መጀን!” ያልተባለለትን ያክል “ሰው መሆንክን አትዘንጋ” እንዲል መጽሃፉ ሰማየ-ሰማያት የረገጠው መተማመንና ተስፋ ቀስ-በቀስ የቁልቁለት መንገድ እየጀመረ መሆኑን እዚህም እዚያም ምልክቶች እየታዩ ነው።

በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ያገዛዝ መንግስትነት ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ከደቂቅ እስከ ልሂቅ፤ ከማይም እስክ ሊቅ ፤ ከአጽናፍ እስካጽናፍ በተባለ ደረጃ ይበል- ይበጅ የተባለለት፤ የንግስና ስርዓት በፈረሰ ባርባ ዓመቱ ፤ ባንደበቱ የነገሰና የከበረ መሪ በማግኘቱ እንደየምነቱ ለፈጣሪው ምስጋና ያደረሰውን ኢትዮጵያዊ ቤቱ ይቁጠረው። እኔን ጨምሮ ሳንመርጠውና ሳይቀባ እንዲነግስ ከልባችን የፈቀድንለት መሪ ካንደበቱ የሚወጡት ማናቸውም ቃላት የሚጣፍጡለት ፤እንደመና የህይወትና የመዳን ተስፋ ምግብ ሆነው ኢትዮጵያውያንን በነቂስ ሲመግቡ የነበሩበት ጊዜ አልቆ ቀስ በቀስ እንደጥላ እየቀለሉ በመንከባለል ተዳፋቱን ከመጀመራቸው በፊት መላ መፈለጉ ሁላችንንም ለውጡ እንዳይደናቀፍ የምንሻ ወገኖች ሃላፊነት ነው። እርግጥ ይሄ ጥሩ ምልኪት አይደለም፤ ለኢትዮጵያም፤ በይበልጥ ደግሞ ለራሳቸው ለእነ ዶ/ር አብይ ጭምር፤  ከበጣም መጥፎ መጥፎ ይሻላል በሚባለውም ብሂል ቢሆን የዶክተር አብይን መንግስትና የጀመሩት የለውጥ ጎዳና አቅጣጫውን እንዳይስት ማገዝ ራሳችንን የማገዝ አንዱ ክፍል ነው። ስለዚህ ነው መጻኢውን ያገራችንን እጣ ፈንታ ለመወሰን የሚያስችል ብሔራዊ እርቅ ጉባኤ እንዲጠራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ግፊት ማድረግና የሚጠራበትን ሁኔታ እንዲመቻች ጥያቄ ማቅረቡ ለነገ የማይባል የሚሆነው።

እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ የምንፈስበት አቅጣጫ ተለይቶ ባልታወቀበት፤ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በዘር ልክፍት በተመረዙ ግለሰቦችና ቡድኖች የመንግስትን ስልጣን ተገን ባደረጉ፤ “ባለጊዜነት” የተጣባቸው ግብዞች አስተባባሪነት፤ እትብታቸው ከተቀበረበት፤ ሁለት ሶስትና ከዚያ በላይ ያስቆጠረው ትውልዳቸው ከኖረበት ምድር በተፈናቀሉበት፤ህጻናትና አረጋውያን ሳይቀሩ ከጎስቋላ መኖሪያ ቤታቸው እንደውሻ እየተጎተቱ እዚህም እዚያም የሚታረዱበት ፤ የሚሰለቡበት፤ የሚደፈሩበት አገር ይዘን ስለልማት፤ ዕድገትና ብልጽግና ወዘተ… የምናወራበት ወቅት ላይ አለመሆናችንን መገንዘብ ብልህ መሆንን አይጠይቅም።

ከስድስት ወራት በፊት በዕምነታቸው ፤ባመለካከታቸውና ፤ በሚከተሉት የፖለቲካ መስመር የተነሳ የወንጀለኛ ታርጋ እየተለጠፈባቸው ወደ እስር የተወረወሩ፤ የተወሰነ ዘርና ጎሳ አባላት በተለይም ከኦሮሞና አማራ ጎሳ የመጡ፤ በገፍ ከታጎሩበት እስር ቤት ያለካሳ “በነጻ” በመለቀቃቸው ብቻ  መነቃቃት የጀመረው ህዝብ ፤ ትናንት የደረሰው በደል  “ዳግመኛ ሊታሰብ አይችልም” እንዳልተባለ ፤  ግፉን የፈጸመው መንግስት አካል ስለፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት በይፋ ይቅርታ እንዳልጠየቀ ሁሉ ፤ ዛሬ ከስድስት ወራት በኋላ “ ያ ሁሉ ተረስቶ የያኔ ታሳሪና አበሳ ተቀባይ” የነበሩ ግለሰቦች ሳይቀሩ የመሪነት ቦታውን ከያዘው ቡድን ጋር በጅምላ ተደምረው “የለውጥ ሀይላት” በሚለው መከተሪያ እየታገዙ ልክ እንደትናንትናው በባለጊዜነት “ግብዝ” አስተሳሰብ ሌሎች ጎሳዎችን ፤ ከነሱ የተለየ የፖለቲካ አመለካከትና እምነት ያላቸውን ወገኖችን ማሳቀቅ መጀመራቸው፤ ትናንት እነሱ ላይ ሲደረግ በነበረው መንገድ ፤  በተመሳሳይ ውንጀላና ፍረጃ፤ በጅምላና በተናጠል ያለማስረጃና ያለፍርድ ማጎር መጀመራቸው በምንም መለኪያ ጤናማ ነው ብሎ ለማሰብ የሚያዳግት ነው።

ሌላው ቢቀር ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ ህግና ስርዓትን ለማቆም ቁርጠኛነት አለኝ ለሚለው የዶር አብይ መንግስት በራሱ ድርጅታዊ ጉባኤ በሙሉ ድምጽ በሚባል ደረጃ ተመርጫለሁ ባለበት ማግስት መከሰቱ ጥሩ ምልኪት ሊሆን አይችልም። ሰሞኑን በቴሌቪዥን መስኮት ለፓርላማቸው ካደረጉት “ቁጭትና ብሶት” ከተሞላበት ንግግር ለመረዳት እንደቻልነው “የሳቸውን በጎና ቅዱስ ዓላማ ለማጨናገፍ” በውጭ ከሚታየው አፍራሽ እንቅስቃሴ በበለጠ ውስጣዊ ፍልሚያው እንደምኞታቸው እንዳላስሮጣቸው የሚያረጋግጥ ነው።

የነገሩንን ሁሉ ከእነህጸጹ እንደውነት ወስደን ያለጥርጣሬ ብንቀበለው እንኳ አብረናቸው አደጋውን ለመከላከልና ባሸናፊነት ለመወጣት፤ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋእትነት ለመክፈል እጅግ ቢያንስ ካንደበታቸው የሚውጡትን ቃላት የሚመጥኑ ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ መነሳታቸውን አስረግጠው ሊያሳዩን ይገባል። ቢያንስ ቢያንስ  በነጻነትና በባለተራነት ስሜት ተነሳስተው በህዝብ ላይ ዘርንና ጎሳን መሰረት ያደርገ የጥላቻ ቅስቀሳ ባደባባይ የሚያሰራጩ ወገኖች አደብ እንዲያደርጉ ሃይ ለማለት   ያልተገዳደረው መንገስታዊ ተቋማቸው ፤ መነቃቃቱን ተከትሎ ከተፈጠረው የነጻ ህዝብነት ስሜት የመነጨ የመብት ጥያቄ  ያነሱ ቡድኖችን “በሽብር ፈጣሪነትና በዘረፋ ተግባር አስተባባሪነት “ ክስ እየወንጀለ ወህኒ ለመወርወር መጣደፉን ቀለል አርገው ማየታቸው ወይም አበክረው ባለመሞገታቸው አድሎና ሚዛን አልበኛነት ዳግም እየተንሰራራ መምጣቱን አመላካች ነው የሚሉ ወገኖች ሲነሱ መንግስታቸው  እዚህ ግባ የሚባል የማስተባበያ አቅም ሊያቀርብ  አለመቻሉን ለተመለከተ የጥርጣሬ ሽንቁር ቢያበጅ አያስገርምም።

ዞሮ ዞሮ መንግስትና ህዝብ ተማምነው ለመቀጠል የጀመሩት በለሆሳስ የተፈጸመ መግባባት፤ ሰሞኑን በታየው ሁናቴ ንፋስ እንደገባበት ከቀጠለ እዚህም እዚያም የጥፋት ማእበል ለማስነሳት ሌት ተቀን ተግተው በመስራት ላይ ለሚገኙትና “ እየተንኮታኮተ ነው” የሚባልለት ዘረኛና ጎሰኛ ስራት ፊታውራሪዎችና አጫፋሪዎች ወይም በጎሳ ልክፍት ተወልደው፤ክህነት ተቀብለው፤ደቁነው የቀሰሱና የጰጰሱ ቡድኖች ተባባሪነት “የባለተረኛነት” አደጋ መጋረጡን አለማስተዋል ከየዋህነትም የበዛ ጅልነት ይመስለኛል።

ስለሆነም ፤ ጊዜው ከፊታችን የተደቀነውን ፤ ሁላችንንም ሊያጠፋን የቀረበውንና፤ “አልፏል ስንለው” መልኩን ቀይሮ እያቆጠቆጠ ያለውን፤ መነሻው ምንም ይሁን ምንም በጥላቻ ላይ የተመሰረተ አደጋ ለማስቀረት ፤ ተቻችለንና ተደጋግፈን ለሁላችን በሚመጥን ጤናማና ሰላማዊ ጎዳና ለመጓዝ ፤ልዩነታችንን የምናስተናግድበትን፡ የሰለጠነ ስርዓት የምናቆምበት፤ ጫፍና-ጫፍ የረገጡ ሸውራራና ጠንጋራ አስተሳሰቦችን ሳይቀር በሰላማዊ፤ ዴሞክራሲያዊና ይበልጥ ደግሞ በትዕግስትና በማስተዋል የምናስተናግድበት መጫዎቻ ሜዳ ለመመስረት የሚያበቃን፤ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያካትትና የሚያሳትፍ ብሄራዊ እርቅ ጉባኤ የሚያዘጋጅ ኮሚሲዮን የማቋቋም ስራ የሽግግሩን ስርዓት እየመራ ካለው መንግስት የሚጠበቅ ወቅታዊና ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።

ጥድፊያው፤ መቼ በተናገረና “ በሰማነው” የሚባልለት የዶ/ር አብይ፤ ቃል ቀስ-በቀስ እየተቀዛቀዘ ከመሄዱ በፊትና ባንጻራዊ ደረጃ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ እምነትና ተስፋ የጣለበት መሪ ከማጣታችን በፊት መሆን ስለሚገባው ነው።  ነገ ወይም ከነገ ወዲያ የተወደደውን ያክል “ ደሞ መጣ”… የሚባልበትን ቁልቁለት የጀመረ እንደሆን  ሊከተል የሚችለውን ጫጫታና ትርምስ መገመት ስለማይቻል  ፤ ከወዲሁ  ይህንን ወርቃማ እድልና ተስፋ ተጠቅሞ ያስፈጻሚ አካላትን ለማደራጀት ከሚያደርገው ተፍ-ተፍ ጎን ለጎን የብሄራዊ ዕርቅ ጉባኤን ለመጥራት የሚያስችል የአዘጋጅና አደራጅ ኮሚሲዮን ማቋቋም ለነገዬ የማይለው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተረድቶ ሊያተኩርበት ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ። የእርቅ ጉባኤን መጥራት ባንድ ጀምበር የሚጠናቀቅ ስራ ባለመሆኑም ከወዲሁ ዝግጅቱን መጀመሩ ተገቢ ነው።

የኮሚሲዮኑ ሃላፊነትና ተግባር በህግ ተደንግጎ ፤ ባደራጅ ኮሚሲዮኑ ውስጥ የሚካተቱት ግለሰቦች ነጻነትና ገለልተኝነት፤ ተጠሪነትና ተጠያቂነት ታውቆ ሁሉም ወገን ከሞላ ጎደል በሚስማማበት ደረጃ ፤ሙያን የትምህርት ብቃትን፡ የስራ ልምድንና ችሎታን ብቻ መሰረት ባደረገ መስፈርት በማደራጀት ለጉባኤተኛው የሚቀርቡ ጥናታዊ የመነጋገሪያ ሰነዶችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት፤ ለጉባኤው መጠራት አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ ፖለቲካዊ፡ ማህበረሰባዊና ስብአዊ ጉዳዮችን በተወሰነ ጊዜ ገደብ በጥናትና በመረጃ የተሰበስቡ ሃሳቦችን አደራጅቶ ጉባኤውን እስከሚጠራ የሚወስደው ጊዜ ቀላል ባለመሆኑ ቡድኑን የማቋቋሚያ ጊዜው አሁን ነው።

የዶ/ር አብይ መንገድ የጸዳ ጎዳናን በመከተል ፤ በኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎች ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ የሚኖሩበት ስርዓት ማደራጀት ከሆነ ፤ የወጀቡን አመጣጥና አቅጣጫ ተገንዝበው በይሁን ይሁን የጸደቀላቸውን የሽግግር ጊዜ መሪነት( እሳቸውም አሜሪካ በመጡበት ጊዜ እንደተናገሩት) ሁሉ ከመደበኛው መንግስታዊ ሰራ በላቀ ትኩረት ይሰጡታል የሚለው እምነቴ ጨርሶ አልደበዘዘም። ስለዚህም ነው የማረጋጋት ስራውን እንዳጠናቀቀና እንደተረጋጋለት መንግስት ፤ መደበኛ መንግስታዊ ስራን በማከናወን ከመጠመድ ይልቅ አብላጫውን ጊዜያቸውን ሽግግሩ ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ተቋማትን በመፍጠርና በማጠናከር፡ የተቋማቱም ቅቡልነትና ተአማኒነት ሰፊ ሀዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማካተት ተሳታፊ የማድርግን ስራ በትጋት መስራት ይገባቸዋል የምለው።

የብሔራዊ እርቅ ጉባኤ ጥሪም እጅግ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን የማነሳበት ምክንያትም ይሄው ነው። ወቅቱ ላለፉት 6 ወራት በተፈጠረው የነጻነት ንፋስ ተሳክሮ የነበረው የህዝብ መንፈስ ወደ መስከኑ የተቃረበበት፡ በኢትዮጵያውያን መካከል ያሉ ልዩነቶች በጉልህ ነጥረው የወጡበት በመሆኑ እነዚህን ልዩነቶች ለማስተናገድ የሚችል የጨዋታ ሜዳ የማበጀቱን ተግባር የመከወን ሃላፊነት ሊጣልባቸው ከሚገቡ የሽግግር ጊዜ ተቋማት አንዱና ወሳኙ ይሄው ብሄራዊ የዕርቅ ጉባኤ ነው ቢባል ስህተት ሊሆን አይችልም።ከሁሉም በላይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ፤ የኢትዮያውያን ሁሉ አገር ትሆን ዘንድ አምርረው የታገሉ፤ ህይወታቸውን ፤ እድሜአቸውንና ሃብታቸውንና ክብራቸውን የሰጡ ግለሰቦች፤ ቡድኖች፤ አክቲቪስቶች፤ የፖለቲካና የሲቪል ማህበራት ሁሉ፤ አስቀድመው ሲጮሁለት የነበረው ብሔራዊ እርቅ ጥያቄ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በዶ/ር አብይ በሚመራው መንግስት ላይ የተጠናከረ ግፊት የሚያደርጉበት ጊዜው አሁን ነው።

 

4 Comments

  1. ቀላጁ እንዳለው አገራችን የመንግስት ለውጥ ሳይሆን የህዝብ ለውጥ ነው የሚያስፈልጋት ያለው እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እኔም የሽግግር ለውጥ በአፋጣኝ ፈላጊ ነበርኩ አሁን ግን የሚታየው ሁኔታ ቀላል ስላልሆነ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ ፕ/ሚሩን የምርጫው ጊዜ እስኪመጣ መደገፍና መጠበቅ የግድ ነው፡፡ ሰራዊት ይዞ አይን ያወጣ ቅልበሳ ለማካሄድ ቤተመንግሥት የሄደ ዜና ከመስማት አሰደንቃጭና የሚያሳስብ ጉዳይ የለም፡፡

    የፕ/ሚሩ አስተዳደር ግልጽና እውነትነት የተመርኮዘ ዜና ማስተላለፍና ህዝቡን ማደናገር ቢያቆሙ የተሻለ ነው፡፡ በእርግጥ ፓለቲከኞቹ እንደተክፋፈሉና ብዙ ፍልሚያ እንዳለ ባይነግሩንም በምናየው ብዙ ነገር ይጠቁማል፡፡ እውነቱን ለመናገር አንዳንድ የሚታየው ነገር ላይ መሪ መኖሩን ያስጠረጥራል፡፡ ሆኖም የግድያ ሙክራ የሚባለው ዜና በጣም እየተደጋገመ ስለሆነ ህዝብን ማረጋጋት የሚቻለው እውነቱን በመንገር እንጂ ሁለት የተለያየ ተቃራኒ መረጃ በመስጠት አይደለም፡፡

    ፕ/ሚሩ እንደአነጋገሩ ክሆነ ገና ከአሁኑ በስልጣን የተስላቸና የመረረው ነው የሚመስለው፡፡ ህዝቡ እንደሙሴ አምኖ
    የተቀበለው መሪ፣ ግለሰቦች ነፍሳቸውን በአደባባይ ከፍለዋል፣ አካለስንኩላን ሆነዋል እሱን ለመደገፍ ወጥተው እንደዚህ የህዝብ ፍቅርና ድጋፍ እያለው ህዝብን ትራስ አድርጎ መረጋጋት ካልቻለ ከአሁኑ መሰላቸቱና መማረሩ አሁንም ህዝብ የማያውቀው ለእሱ ብቻ ግልጽ የሆነ ነገር እንዳለ ነው የሚያሳየው፡፡

    አገራችን በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ላይ እያለች የተስፋ መቁረጥና የመሰላችት ፀባይ ማሳየት ክበሰለ መሪ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለው ይሄ በየጊዜው የምንሰማው የግድያ ሙከራ የሚያመለክተው ነቅቶ ለጸብ፣ ለሽብር ጠዋት ማታ የሚያቀነቅን የውስጥ ሃይል እንዳለ ነው የሚጠቁመው እና ወደድንም ጠላንም ፕ/ሚሩን መደገፍና ሁለቱን አመት ጠብቆ ምርጫ ማድረግ ነው ያለን አማርጭ፡፡

  2. Kuni የአቅዋም ለውጥ ማድረግህ ለሀገርህ ፍቅር ማስቀደምህን ነው የሚያሳየው:: ሁላችንም የምንወተውተው
    ይህ ስጋት ስላለ ነው:: እኔ በግሌ እንኳን ሊገረሰስ የህውሀት ሰንሰለት ገና አልላላም:: እጅግ ብዙ ቢሊዮኖች በእጁ ያለድርጅት
    የራሱን የሚንቀሳቀስ አፋኝ የማፊያ ቡድን ማሰማራት ይችላል:: እኔ ሶስት መንግስት ይታየኛል:: ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ያላቸው ምርጫ እሰከምርጫ ከዐቢይ ጋር መቆም ነው:: ዶክተር ብርሀኑ ወልቂቴ የተናገረው እኛ የዐቢይን መንግስት ለመታገል ሳይሆን ለመደገፍ ነው የመጣነው!! ቃለ ህይወት ያሰማልን:: ለመወዳደር ይደረስበታል:: ዶክተር ዐቢይ የሰለቸው የሚመስለው የሚተማመንበት ደጋፊው የማያስፈልጉ ነቀፌታ ሲያዘንቡበት ነው:: ሰው ነው::ሺ ቦታ ሊሆን አይችልም:: ሙሴም እኮ በ40 ቀናት ነፃ ምድር ህዝብን ሳያደርስ 40 አመታት ወስዶ ህዝቡም ተነስቶበት ነበር:: ደጋፊው ህዝብ በከፉም በደጉም ከአቢይ ጋር መቆም አለበት:: ከሁሉም ሰው የበለጠ እጅግ ያሳዘነኝ በአማራነቴ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ አስፈላጊ ያለሆነ ተቃውሞ ማድረጉ የህውሀትን ቡድን ማጠናከር እንጂ የሚጨምረው ነገር አይኖርም:: ከዐቢይ ጋር መቆም ውሳኝ ጥሪ ነው::

    • ውንድሜ ተስማ! እኩልነት፣ ፍትህ፣ እድገት እያልን በባዶ ሜዳ እንጮሃለን፡፡ እንዲህ ናት ጨዋታ! ሲያደናግሩን ለካ አማራ ሆኗል ጨዋታው? አንዳንዱ ከድንቁርና የተነሳ ከእምዬ ሚኒሊክ ዘመን ገና አሁን ከኮማ የነቃ የሚያስመስለው፡፡ አንዳንዱ በጡንቻው ነው የሚያስበው፡፡ ለግርግር ለሌባ ያመቻል አማራን ጥቢጥቢ ሊጫወቱበት ነው የሚዶልቱት ማኖ አስነክተው፡፡ የኔ ወንድም ውሻ ቀንድ ልታወጣ ሄዳ ጆሮዋን ተቆርጣ መጣች መሆን አንፈልግም፡፡ ክፕ/ሚሩ ጋር ቀሪዋን 2 ዓመት ያድርሰን እንጂ መንቃት፣ መማር፣ የሚበጀንን ማጥናት ከዛም መደገፍ አልብን፡፡ ለጊዜው ያለን G7 ነው ሌላ የሚያስንቅ ዘር አልባ ተኣምር ድርጅት ክሰማይ እንደመና ካልተወረውልን በስተቀር።
      ቀልድ አቁመናል! ትግላችን lol ከጠ/ሚሩ ዐቢይ ጋር ወደፊት ነው!!!✌ ብስቅም መቀለዴ አይደለም፡፡ kiss my amhara ass! ዝምታ ለበግም አልበጃት!!

  3. ህወሃት ባለፈው ሰሞን ቤቱን ዘግቶ በተቀረው የአገራችን አካባቢ ሲደርግ በነበረው ትርምስ ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ፌዴራል መንግስቱን ሲሳስብ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ለምሳሌ ሶማሌ ክልል ላይ በጅግጅጋና አካባቢው በደረሰው እልቂት ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባቱና ህዝብን በመታደጉ የትግራይ ክልል አስተደዳደር በመግለጫ መንግስት ለምን ጣልቃ ይገባል ብሎ ሲወተውት ነበር፡፡ ዛሬ በአዋሳኝ ድንበሬ ላይ ተደጋጋሚ ግጭትና መፈናቀል እየደረሰ እኔንም ችግር ውስጥ የከተተኝ በመሆኑ ፌዴራሉ መንግስትና የትግራይ ክልል አስተደዳደር በአፋጣኝ መፍትሄ ይሰጠው ብሎ የአማራ ክልል መግለጫ በማውጣቱ ጣልቃ ገባህብኝ ብሎ ጫጫታ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ችግር ቢደርስ፣ ምንም እልቂት ቢፈጠር ክልሎች መንግስት ስለሆኑ ምንም አያገባቸውም ዝም ብሎ መመልከት ነው ማለት ሰው መሆናችንን ከመዘንጋት፣ የጋራ ቤታችንን በጋራ ለመመልከት አለመፍቀድ ሲፈልጉ ደግሞ በረጅም እጃቸው መነካካት መሻት ድብልቅልቅ ያለ ተራና አስተዛዛቢ ውሳኔና ድርጊት ነው፡፡ ሰው እየሞተ በዛኛው ክል ያለህው በክልሌ አያገባህም፣ እኔ ግን በአንተ ክልል እንደፈለኩ መወሰን እችላለሁ ብሎ ትዕቢትና ማደናገሪያ ጊዜው ያለበት ይመስለናል፡፡ በአንተ ክልል ገብቼ ልወስንልህ ሳይሆን ችግሩን ተገንዝቦ እረ አንድ በሉት ለምን ትሉናላችሁ ማለት ማንአለብኝነት ነውና ምግለጫውን ሰውኛ አልባ፣ የዘቀጠ ብለነዋል፡፡

Comments are closed.

92062
Previous Story

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስምምነት ከተደረገባቸው አገራት ውጪ የሚደረግ ሕገወጥ ጉዞ መቆም እንዲቆም ማሳሰቢያ ሰጡ

Next Story

አንድ ሕዝብ ነን ወይስ አይደለንም – nፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop