ሸንቁጥ አየለ
አንዳን የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያነሷቸዉ ጥያቄዎች ስህተት ናቸዉ ባይባልም የዲሞክራሲ ግንባታ ዉልን በአግባቡ ከመረዳት የዘገዩ ናቸዉ::አንዳንዱ የሚመስለዉ ስለ ትናንት እናዉም ሆነ ስለነገዉ ሂደት በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ዉስጥ አንድ የሚጠየቅ ሀይል ያለ ይመስለዋል::ሌላዉ ደግሞ እርሱን የሌላዉን ጥያቄ መላሽ ያደርግና የማይመልሰዉን ጥያቄ ለመመለስ ደፋ ቀና ሲል ይስተዋላል::
ትናትናም ሆነ ዛሬ የሆኑ ክስተቶች ዉስጥ የፖለቲካ አመራር ጨብጠዉ የሀገሪቷን ስልጣን የዘዎሩ እና እየዘወሩ ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች በነገይቱ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ዉስጥ ቁልፍ ሚና አይኖራቸዉም::ቁልፍ ሚና የሌለዉ ሀይል ደግሞ ነገ ስለሚኖረዉ የዲሞክራሲ ቅርጽ እና ይዘት ምንም አይነት የዉሳኔ ጉልበት አይኖረዉም::
በነገይቱ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ዉስጥ ቁልፍ ሚና የሚኖረዉ ለዉጥ ፈላጊዉ የአሁኑ ትዉልድ እና ለዉጡን አስቀጣይ የሆነዉ የነገዉ ትዉልድ ናቸዉ:: እነዚህ ሁለት ትዉልዶች ደግሞ ትናት ለተሰሩ ስህተቶች ወይም ዛሬ በአንባገነኑ እና ዘረኛዉ ሀይል እየተከናወኑ ላሉ ወንጀሎች መልስ መስጠት አይችሉም::
አንዱ የለዉጥ ፈላጊ ቡድን ጥያቄ አቅራቢ ሌላዉ የለዉጥ ፈላጊ የፖለቲካ ቡድን ጥያቄ መላሽ ለመሆን በመሞከር በእኩልነት እና በጋራ የነገይቱን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ የተዛባ መሰረት ላይ ማቆም አይጠበቅባቸዉም::የለዉጥ ፈላጊ ሁላ በነጻ ህሊና በነጻ መሰረት ላይ በመጀመር ነጻይቱን እና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በምትመች መልኩ መገንባት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነዉ::
እነ እገሌ የሚባሉት ብሄሮች አሁንም የእኛን ብሄር ጥያቄ አያከብሩም በማለት ከሌላዉ ብሄር ማስተማማኛ ለማግኘት መሞከር ወይም ደግሞ ሌላዉ ብሄር ትናት ስለተሰሩ ስህተቶች ሀላፊነት እንዲወስድ በመሞከር የነገን ብሩህ የዲሞክራሲ ግንባታ በትናንት የማይጨበጥ ማስረጃ ከረጢት ዉስጥ በመቀርቀር የነገን የጋራ የዲሞክራሲ ግንባታ ማዛባት በራሱ የነገዉን የእኩልነት መሰረት የተንሸዋረረ መሰረት ላይ ያቆመዋል:: ሌላዉ የፖለቲካ ቡድንም የሌሎች የፖለቲካ ቡድኖችን ጥያቄ ሁሉ መላሽ እና ተንታኝ በማድረግ እራሱን ለማቅረብ ከሞከረ አሁንም የእኩልንተ መሰረቱን በመናድ የነገይቱ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዳትገነባ እንቅፋት ይሆናል::
በመሆኑም የለዉጥ ፈላጊ ሁላ በነጻነት እና በእኩልነት መንፈስ በሚመራ ነጻ ህሊና እና በነጻ መሰረት ላይ በመጀመር ነጻይቱን እና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በምትመች መልኩ መገንባት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነዉ:: ይሄም የሚከናወነዉ የእኩልነት መሰረት ላይ በመቆም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን በእኩል ሀላፊነት ቀንበር በመጠመድ ሲከናወን ብቻ እዉን ይሆናል::