የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ (ኢውመመ) በኢትዮጵያ ላይ ስለሚካሄደው ሕዝባዊ እምቢተኛነትና የገዢው ፓርቲ የጭካኔ እርምጃዎች ያወጣው መግለጫ

pastedGraphic.png

የኢትዮጵያ፤የውዪዪትና፤መፍትሔ፤መድረክ

Ethiopian Dialogue Forum

9900 Greenbelt RD.  E#343 –  Lanham, MD 20706

__________________________________

የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ (ኢውመመ) በኢትዮጵያ ላይ ስለሚካሄደው ሕዝባዊ እምቢተኛነትና የገዢው ፓርቲ የጭካኔ እርምጃዎች ያወጣው መግለጫ

August 28, 2017

የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ (ኢውመመ) ከተመሰረተበት ወቅት ጀምሮ አስኳል በሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ችግሮች ላይ በመረጃ በተደገፈ ትንተና ውይይቶችን እያካሄደ አማራጮችን ሲያቀርብ ቆይቷል። የአገራችን ሁኔታ ሲያስገድድ አግባባ ያላቸውን የአቋም መግለጫዎች ለኢትዮጵያና ለመላው ዓለም ሕዝብ በመግለጫ መልክ በማቅረብ ላይ ይገኛል። ለምሳሌ፤ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ተቋማችን የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የሰብአዊ መብቶች አፈና በመቃወም የምክር ቤቱ ተወካዮች ያረቀቁትን  H. Res. 128 “Supporting respect for human rights and encouraging inclusive governance in Ethiopia” ተብሎ የሚጠራውን ሕግ በሚመለከት የምንደግፍ መሆናችን ለሚመከታቸው ባለሥልጣናት ገልጸናል።  ይህን ረቂቅ ሕግ ከስድሳ በላይ የምክር ቤቱ አባላት እንደሚደግፉት አረጋግጠናል።

ይህ መግለጫ ትኩረት የሰጠው በአሁኑ ወቅት እንደገና በመላው ኢትዮጵያ፤ በተለይ በኦሮምያና በአማራ ክሎሎች እየተስፋፋ ለሄደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል፤ በተለይ እምቢተኛነት ይሆናል።  በዚህም መስረት፤ ተቋማችን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሙን እየገለጸ፤ ገዢው ፓርቲ በሕዝብ ላይ የሚያካሂደውን ጭፍጨፋ፤ በደል፤ አፈና፤ ግድያ፤ እስራት፤ ማሳደድና ሌላ ወታደራዊ እርምጃ እንዲያቆም እናሳስባለን።

ኢውመመ በአገር ቤትና በውጭ ለሚገኘው ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚከተሉትን አበይት ጉዳዮችና መፍትሄዎች ያቀርባል፤

1. በአሁኑ ወቅት በሃገራችን በኢትዮጵያ የሚታየው ሕዝባዊ እምቢተኛነት የህወሓት/ ኢህዓዴግ “ከፋፍለህ ግዛው” ስርዓት የሚያከትምበት ጊዜ መቃረቡን የሚያመለክት ነውና ኢትዮጵያውያን ሁሉ፤ ለኢትዮጵያ ሃገራቸው፤ ለመብታቸውና ለዴሞክራሲ ምስረታው ትግል በጽናት፤ በመተባበርና በመደጋገፍ ሕዝባዊ አመጹን፤ እምቢተኛነቱንና  ትግሉን እንዲቀጥሉበት አደራ ይላል፤ ድጋፉን ይገልጻል፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  የባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ሠራዊት ወደ ግንባር ሽኝት ተደረገለት

2. የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲና መንግሥት መብታቸውን ሊጠይቁ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ወታደራዊና ሌላ የኃይል እርምጃ እንዲያቆም እናሳስባለን፤

3. ከጭካኔና ከብሶት የተጸነሱና የተወለዱ ሕዝባዊ ኣመጾች በየትኛውም አካባቢ ሲነሱ የእነዚህ ዐመጾች ስትራተጅና ግብ የሃገራችንን አንድነት፤ ነጻነት፤ እርጋታ፤ ደህንነት፤ ቀጣይነትና ሉዐላዊነት ዋስትና የሚያሳጣ መሆን እንደሌለበት ተቋማችን ያምናል፤ ያሳስባል፤

4. ልዩ ልዩ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርብ እየተከታተሉና እያጠኑ ለዜጎቻቸው የሚሰጧቸው የጉዞና የጸጥታ ማስጠንቀቂያዎች አግባብ አላቸው። ሆኖም፤ አሁንና ወደፊት፤ ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያዎችን ሲሰጡ በተመሳሳይ ደረጃ ለአደጋው ዋና መንስኤ የሆነውንና በኢትዮጵያውያን ላይ ኢ-ሰብአዊ የሆኑ እርምጃዎችን  የሚወስደውን የኢትዮጵያን መንግሥት በጽኑ እንዲያወግዙና ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ የኢትዮጵያውያንን የዴሞክራሲ ትግል እንዲደግፉልን በትህትና እንጠይቃለን፤ እኛም የበኩላችን እንደምናደርግ እናረጋግጣለን።

5. በአገር ቤትና ከአገር ውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎች ጥቃቅን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው በብሄራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ተሰባስበው አግባብ ላለው የፖለቲካ ስልጣን ሽግግርና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል እንዲያቀነባብሩና እንዲመሩ ጥሪ እናደርጋለን።  በጋር ጉዳዮች ላይ በግልጽነትና በድፍረት መወያየትን እንዲጀምሩ እንጠይቃለን።

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የዜግነት መብታቸውን ተጠቅመው H.R. 128 የአሜሪካ ሕግ እንዲሆን ተወካዮቻቸውን ሁሉ በያሉበት እንዲያነጋግሩ እናሳስባለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

Share