(ግርማ ካሳ)
Muziky68@yahoo.com
ሰኔ 26 ቀን 2005 ዓ.ም
ያለ መታደል ጎንደርን በአካል አላውቃትም። ነገር ግን እንደ ማንም ኢትዮጵያዊ በልቤ ዉስጥ ልዩ ቦታ አላት። ያለ ጎንደር ኢትዮጵያ የምትባል አገር ትኖር ነበር ለማለት ያስቸግራል።
ግራኝ መሃመድ በቱርኮች እየተረዱ፣ አብዛኛዉ የኢትዮጵያን ክፍል ተቆጣጥረዉ በነበረ ጊዜ፣ ስመ ጥሩ ያልነበሩ፣ ብልሹዉ የሸዋ ንጉስ፣ አጼ ልብነህ ድንግል ይሞታሉ። አጼ ገላዉዲዮስ ይተኳቸዋል። የግራኝ ጦር በመጠንከሩ ሽሽት ወደ ሰሜን፣ ወደ ጎንደር ይጀመራል። አጼ ገላዉዲዮስ ያሸንፋሉ። ግራኝ መሃመድ ይሞታሉ። ጎንደር የኢትዮጵያ የፖለቲካ መዓከል ትሆናለች። ከአጼ ገላዉዲዮስ በመቀጠል ፣ አጼ ሱስኒዮስ፣ አጼ ፋሲል እያሉ በጎንደር፣ ገዢዎች መፈራረቅ ጀመሩ። የጎንደር ገዢዎች አገሪቷን በአንድ ላይ አድርገዉ ማስተዳደር ስላልቻሉ ዘመነ መሳፍንት የሚባለው ዘመን መጣ። ኢትዮጵያ ተበታተነች። በወሎ፣ በሸዋ፣ በትግራይ በጎጃም …የተለያዩ ገዚዎች መግዛት ጀመሩ።
ትዉልዳቸው ቋራ የሆነ፣ መይሳው ካሳ፣ የኢትዮጵያ አባት፣ ብቅ አሉ። መሳፍንቱን እያስገበሩ ንጉስ ነገስት ዘኢትዮጵያ ቴዎድሮስ ተባሉ። አጼ ቴዎድሮስ፣ ከጎንደር የጀመሩት ዘምቻ፣ ኢትዮጵያን አንድ አደረገ። አዎ ጎንደር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ልዩ ቦታ አገኝች።
መሃዲስት ደርቡሾች ታሪካዊዋን የጎንደር ከተማ አጠቁ። ጀግናዉ አጼ ዮሐንስ ተንቀሳቀሱ። የደርቡሾችን ጦር እየመነጠሩ ከኢትዮጵያ ምድር አስወጡ። የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ላይ፣ በመተማ፣ ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ወደቁ። ለኢትዮጵያ አንድነት ለግዛቷ መከበር፣ እኝህ ታላቅ ሰው በጎንደር ደማቸው ፈሰሰ። መስዋእት ሆኑ። ጎንደር ታሪክ የተሰራባትና ወደፊትም የሚሰራበት ሆነች።
ጎንደር በርግጥ ሕወሃት ከኢሕአፓ ካፈነገጠዉ፣ በአቶ ያረድ ጥበቡ (ከዚያም ታምራት ላይኔ) ይመራ ከነበረዉ አንጃ ፣ ኢሕዴን( የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ጋር በመተባበር ኢሕአዴግን መሰረተ። «ሕወሃት ሚሊተሪዉን ይቆጣጠራል፤ ኢሕዴን ደግሞ ሕዝቡን ለማግባባት የፖለቲካ ሥራ ይሰራል» በሚል ስምምነት።
የሕወሃት ጦር በጎንደር በኩል ወደ ደቡብ ሲያልፍ «ዘመቻ ቴዎድሮስ» በሚል ነበር። አጼ ቴዎድሮስ እንዳደረጉት ፣ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የተደረገ ዘምቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ባህር አልባ ለማድረግ፣ ሕዝቧን በዘር ለመከፋፈል የተደረገ ዘመቻ ነበር። «ቴዎድሮስን» መጥቀስ ያኔ የተፈለገዉ፣ የሕወሃቶችን እዉነተኛ ከፋፋይና ዘረኛ ገጽታቸውን ለመሸፈንና ሕዝቡን ለማታለል ነበር።
አጼ ቴዎድሮስ መሳፍንትን ያስገበሩት በጦርነት መሆኑ ይታወቃል። የመጀምሪያዉ ዘመቻ ቴዎድሮስ፣ የነፍጥ ዘመቻ ነበር። ሁለተኛው የሕወሃት «ዘመቻ ቴዎድሮስ» ግን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሆን ተብሎ የተካሄደ፣ ቴዎድሮሳዊ ያልነበረ ዘመቻ እንደሆነ በሂደት ተረጋገጠ። አገሪቷ በዘር ተከፋፈለች። ኢትዮጵያዊነት እንደ ሐጢያት መቆጠር ተጀመረ። ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸዉ ሳይሆን በዘራቸው እንዲለዩ ተደረገ። አንዱ ግዛት ለአንዱ ዘር፣ አንዱ አካባቢ ለሌላው ዘር ተሰጠ። ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗ ቀረ። በማንም አገር ያልታየ፣ ግዛቶች ከፈለጉ እንዲገነጠሉ በሕግ ተደነገገ። አሉላ አባ ነጋ እንደራሴ ሆነው ያስተዳደሯትን፣ ባህር ምድሪ ተብላ ትታወቅ የነበረችዉን፣ ኤርትራን፣ ለተባበሩት መንግስታ ደብዳቤ ሁሉ በመላክ፣ እንድትገነጠል ግፊት ተደረገ። «ኢትዮጵያ የባህር በር አያስፈልጋትም» በሚል ወደብ እንዳይኖራት በማድረግ፣ ለጅቡቲ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚሆን ገንዘብ በየጊዜው በገፍ መክፈሉ ግዴታ ሆነ። የጅቡቲን ወደብ በኮንትራት የሚያስተዳደሩት፣ የዱባይ ኩባንያዎች በመሆናቸው፣ በተዘዋዋሪ መንገድ አረቦች ኢትዮጵያን ማነቅ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጠረላቸው።
ከሃያ አመታት በፊት የጎንደር ሕዝብ ሕወሃትን ከትግራይ ወደ ደቡብ እንዲያልፍ ያደረገዉ፣ በአንድ በኩል የደርግ የግፍ አገዛዝ መሮት ስለነበረ ሲሆን በሌላ በኩል ፣ «ኢሕአዴግ ዲሞክራሲን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን ያሰፍናል፤ የኢትዮጵያ አንድነትን ያስከብራል» በሚል፣ ኢሕዴኖች የሕወሃት አፍ ሆነው፣ አታለዉት ስለነበረ ነዉ።
ያኔ ለጎንደር ሕዝብ የተገባዉ ቃል ግን፣ እንኳን ተግባራዊ ሊሆን፣ ጭራሹን የግፍ አገዛዙ ብሷል። መሬቱ ለሱዳን እየተሰጠ ከፍተኛ ስቃይና መከራ እየደረሰበት ነዉ።
በኢትዮጵያ ያለዉን የግፍ አገዛዝ በመቃወም፣ ሕዝቡን በማደራጀትና በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኘዉ፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፣ ከጎንደር ሕዝብ ጋር ሆኖ፣ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲከበር፣ ሕዝቧ በሰላም በእኩልነት እንዲኖር፣ የሕግ የበላይነትና የሰብአዊ መብቶች መከበር እንዲሰፍን የሚደረገዉን ትግል ለማገዝ፣ የሚሊዮች ድምጽ ለነጻነት በሚል መርህ፣ እዉነተኛ ዘመቻ ቴዎድሮስን አዉጇል። የጠመንጃ ዘመቻ ሳይሆን የሰላማዊ፣ የሰለጠነ፣ የሕዝባዊ ንቅናቄ ዘመቻ !
ሰኔ 30 ቀን በጎንደር ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል። በታሪክ እንዳነበብነው፣ አባቶቻችን እንደነገሩን፣ የጎንደር ሕዝብ እንደገና ታሪክ ይሰራል። «ዘረኝነት ይብቃ ! የግፍ አገዛዝ ይብቃ! ኢትዮጵያ ትቅደም! » እያለ ድምጹን ያሰማል። የነጻነት ደዉል ከፋሲለደስ አገር ይሰማል።
በጎንደር ወዳጆች፣ ዘምዶች ያሉን፣ በስልክ፣ በኢሜል፣ በፌስቡክና በትዊተር የሰልፉ ተካፋይ እንዲሆኑ እናበረታታ። በአካል የሰልፉ ተካፋዮች ባንሆንም፣ በመንፈስ ግን ከጎንደሬ ወገኖቻችን ጎን እንቁም ! ዘመቻ ቴዎድሮሶን እንቀላቀል ! ወገኖቻችን፣ ሊታሰሩ ፣ ሊገደሉ እንደሚችሉ እያወቁ ደፍረው ሰልፍ ለመውጣት ከተዘጋጁ፣ እኛ እንዴት ድምጻችንን ማሰማት እንፈራለን ? የአንድነት ፓርቲ ይፋ ያደረገዉ ፔትሽን እንፈርም። የትግሉ አካልና አጋር እንሁን ! አንፍራ ። አንደንግጥ። አንታለል። ከበስተጀርባ ሌላ አላማ ባላቸው የዉጭ ኃይሎች አንተማመን። እኛው እንበቃለን። የተባበረ የኢትዮጵያዉያን ኃይል ከተነሳ፣ አምባገነኖች ወደዱም፣ ጠሉም ለሕዝብ ፍቃድ ይገዛሉ።
ፔቲሽኑን ለመፈረም ወደ ሚከተለዉ የድህረ ገጽ አድራሹ ይሂዱ
http://www.andinet.org
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !