ዳንኤል ተፈራ
ዛሬ የነበረው የፓርላማ ውሎ ከቀደሙት በይዘት፣ በአጠያየቅ፣ በመልስ አሰጣጥና በማፅደቅ ከቀደሙ ስብሰባዎች ምንም የተለየ ነገር አልነበረውም፡፡ የሚንስትሮች ሹመትም ቢሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ ግን እንዲህ በጨረፍታ ሳይሆን በደንብ የሚያነጋግረን ነው፡፡ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አይነት፡፡ ወደ ፓርላማው ስመጣ እንደከዚህ በፊቱ የማሻሻያ ሞሽን ይቀርባል በአብላጫ ድምፅ ውድቅ ይደረጋል? የፓርላማው ጥርስ የማብቀል ጉዳይ ከምኞት ባሻገር ገቢራዊ እንዳልሆነ ለማየት የቻልን ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ ፓርላማው ጥርስ ማብቀል ካልቻለ ያው ‹‹በገንፎ›› መኖር ነው፡፡
የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ያቀረቧቸው ሁለት ሞሽኖች ተገቢነታቸው የሚያከራክር አይደለም፡፡ አንደኛው መንግስት ከሀገር ውስጥ ለመበደር ያሰበውን ገንዘብ ወደ ግሉ ሴክተር ቢዞር የግሉን ዘርፍ እንሚያበረታታ የሚጠይቅ ሞሽን ነበር፡፡ በአንድ ድጋፍ ብቻ ውድቅ ተደረገ፡፡ ታዲያ የበቀለው ጥርስ የታለ???
ሁለተኛው ብሮድባንድ የተባለውን ፕሬስ አፋኝ መስሪያ ቤት የሚመለከት ነው፡፡ አቶ ግርማ እንዳቀረቡት ባለስልጣኑ አንድ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ መክፈት ያልቻለ ነው፡፡ ይሄ ማለት የብሮድካት ባለስልጣን አብያ በሬ ነው እንደማለት ነው፡፡ አብያ በመባል የሚታወቀው በሬ ከፍተኛ መኖ የሚጠቀም ሲሆን ሰውነቱን ከማደንደን ባለፈ ለእርሻ ሲጠመድ መልገም ይጀምራል፡፡ ይተኛል፡፡ ሰነፍ ነው፡፡ በማሻሻያ ሞሽኑ ላይ እንደቀረበው ለብሮድካስት ባለስልጣንም የተመደበለት በጀት ከደመወዝ ውጭ ያለው መኖ መቀነስ አለበት፡፡ ማንኛውም መስሪያ ቤት የታለመለትን ዓላማ እያሳካ ካልሆነ መዘጋት ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ብሮድካስትም መፍረስ አለበት ማለት ነው፡፡ ይሄ ተገቢ ሀሳብ ነው፡፡
ምክንያቱም ብሮድካስት የተባለው የባለስልጣን መ/ቤት እኛ የምናውቀው በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ የነበሩትን ጋዜጣና መፅሄቶች ሲዘጋ ነው፡፡ እነ አዲስ ነገር፣ ፍትህ፣ ፍኖተ-ነፃነት፣ አዲስ ታይምስ፣ ልዕልናና ከ1997 ዓ.ም በፊት የነበሩ በርካታ ጋዜጦች ተዘግተዋል፡፡ በርካታ ወዳጆቼ የጋዜጣ ፈቃድ ለማውጣት ደጅ ጠንተው የገንዘብ ምንጫችሁ ይጠና በሚል ተልካሻ ሰበብ ፈቃድ ተከልክለዋል፡፡ እና ለዚህ መስሪያ ቤት በጀት ምን ይሰራለታል? የአቶ ግርማ የሞሽን ማሻሻያ ጥያቄ ትክክል ነበር፡፡ ብሮደካስት ብቻ ሳይሆን ህዝብን የማያገለግሉ ድርጅቶች ሁሉ መዘጋት አለባቸው፡፡