አንዱን የዘመናችንን ትልቁን ብሔራዊ ችግር ለመፍታት ያስችል የመሰለኝን ሐሳብ ከጥቂት ቀናት በፊት “በኢትዮጵያ ሰላም የሚያመጣ የአማራ የተራድኦና የዕርቅ ድርጅት ያስፈልጋል” በሚል ርእስ አንድ ጽሑፍ በ ethiomedia ለሕዝብ አቅርቤ ነበር። በጽሑፉ ጥቂት ሰዎች የተወያዩበትን ወዳጆች ልከውልኝ አነበብኩት። በስልክ ያወያዩኝም አሉ። ትችቶቹን ሁሉ ስላላየኋቸው ይሆናል እንጂ፥ ያየኋቸውን ሳጠናቸው፥ ከዶክተር ፀሐይ ብርሃነ መስቀል በቀር ፍሬ ነገሩ ላይ ያተኮረ ሐሳብ የሰጠ አላጋጠመኝም።
የተቺዎችን ቀልብ የማረከው “አማራ የሚባል ሕዝብ አለ ወይስ የለም?” የሚለው ነው። ይኸንን መተቸት ደስ ይላል መሰለኝ፥ ተተችቶ ባለቀ በስንት ዓመቱ፥ ትችቱ እንዲያገረሽበት ጽሑፌ ምክንያት ሆነ። እኔ ግን ጽሑፌን የደመደምኩት እንዲህ ብየ ነበር፤
ለዚህ ድርሰት አስፈላጊነቱ ስላልታየኝ፥ “አማራ ማነው?” ከሚል፥ መልሱ ብዙ ገጽ ከሚፈጅ ጥያቄ ውስጥ አልገባሁም። ሁሉም ራሱን ስለሚያውቅ፥ “አማራ ነኝ” የሚል ሁሉ በሙሉ አባልነት፥ በድርጅቱ የዕርቅና የሰላም ዓላማ የሚያምን፥ ግን “አማራ ነኝ” የማይል ኢትዮጵያዊ ደግሞ በደጋፊ አባልነት መመዝገብ ይችላል።
እንዲህ ያልኩት መተቸቱ ተስኖኝ አይደለም። እንዲያውም ካሁን በፊት ማስረጃ እየሰጠሁ በሰፊው እንደተቸሁት የሚያስታውስ አይጠፋም። አሁን እንደገና ያልተቸሁት፥ ታኝኮ የተዋጠን በማመስኳት፥ የኔንም የአንባቢውንም ጊዜ ላለማጥፋት መርጬ ነበር። “አማራ አለ” የሚሉም “አማራ የለም” የሚሉም፥ እንደየመነሻቸው ተቀባይነት ያለው ምክንያት አላቸው። በዘር ከሄድን የዘመን ብዛት ስላዳቀለን፥ ዛሬ አማራ የሚባል ዘር አለ ለማለት አይቻልም፤ የለም። በባህል ከሄድን ግን አለ። አማራ ከማለት አማርኛ ተናጋሪ ማለት የሚመረጠውም ስለዚህ ነው። ይህ የባህል ሕዝብ ለመኖሩ ማስረጃው ቀላል ነው፤
አንደኛ፥ “አማራ ነን” የሚሉ ሰዎች አሉ። “አማራ አይደላችሁም” ብንላቸው ግራ ይጋቡና፥ “ታዲያ ምን ልታደርጉን ነው፤ ዶርዜ፥ ወይስ እስላም?” ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ።
ሁለተኛ፥ ብዙ ሰዎች “አማራ ናችሁ” ተብለው ተገድለዋል፥ ከሀገራቸው ተፈናቅለዋል፥ ንብረታቸው ተዘርፏል። “አማራ አይደላችሁም” የተባሉ ጎረቤቶቻቸው፥ ወይም በአውቶቡስ ላይ አብረዋቸው የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ግን አማሮች አይዶሉም ተብለው ድነዋል።
ሦስተኛ፥ በየዘመኑ የሚደረገው የሕዝብ ቈጠራ ሕዝቡን በጎሳ ሲመድብ አማራውን የለህም ብሎ አልዘለለውም። የአማራው ቍጥር መቀነሱን ያወቅነው፥ በቈጠራው አማካይነት ነው። ቈጣሪዎቹ በዚህ መንገድ መሄዳቸው ተሳስተዋል እንዳንል፥ በማንም አገር የሚደረግ ነው። አሜሪካ ረዘም ያለ ጊዜ እየኖረ፥ ይኸንን ልምድ ያልደረሰበት ያለ አይመስለኝም።
አራተኛ፥ አንድ ቋንቋ ለሌለ ነገር ስም አያወጣም፤ “አማራ” የሚል ቃል ወይም መጠሪያ ስም በቋንቋችን ውስጥ ካለ፥ በዚያ ስም ተጠሪ ሕዝብ አለ ማለት ነው።
አምስተኛ፥ “ኢትዮጵያውያንን በዘር መከፋፈል ይሆናል” ተብሎ ቀረ እንጂ፥ የቀድሞ መታወቂያ ደብተር ላይ “ዘር” የሚል መሥመር ነበረበት፤ ያለምክንያት አልነበረም። ምንጮቹ “ቤተ አምሐራ” ይሏቸዋል።
ግን አንድ እውነታ አለ። አማራው (ወይም አማርኛ ተናጋሪው) ራሱን እንዳንድ የተለየ ሕዝብ ቈጥሮ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ራሱን አላገለለም። ማለት፥ አንድነቱ በኢትዮጵያዊነቱ ነው እንጂ በአማራነቱ ላይ አይደለም። በሀገር ጉዳይ ላይ ጎሳ ሳይለይ ከሁሉም ጋር አብሮ ይሠራል። እንዲቀጥልበት ማበረታታት የሁላችን ግዴታ ነው። ግን ጥቃትን ለመከላከል መጠራራትና ዘዴ መፍጠር እንኳን በሰዎች በእንስሳት ዘንድም ያለ ነገር ነው። እንድ ኢትዮጵያዊ፥ “አማራ ነህ” እየተባለ ሲጨፈጨፍና ማንም ሰው ሳይደርስለት ዝም ብሎ ይታይ ወይ? ሌላው ቢቀር “ነግ በኔ” አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ ተነሥቷል። ጥያቄው ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? አማርኛ ተናጋሪው እንዳይደርስለት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተለይቶ የአማራ ወገን መፍጠር ሆነበት። ምን ይሻላል?
ለዚህ መልስ ሳሰላስል ችግሩ በተለይ የአማራው ሕዝብ ሳይሆን የሀገሪቷ ሆኖ ታየኝ። አገሪቷ አማርኛ ተናጋሪውን በጎሳዎች የሚያስጠላ ጠላት (ጸላኤ ሠናያት የሚባለው ሰይጣን) ገብቶባታል። ስለዚህ የጥላቻውን ምንጭና ምንጩን መድፈኛ ዘዴ ወደመፈለግ ሄድኩት። ምንጩ ወያኔ ብዙዎቹን ጎሳዎች በአማራው ላይ በጠላትነት ማስነሣቱ፥ መፍትሔው ደግሞ፥ “በኢትዮጵያ ሰላም የሚያመጣ የአማራ የተራድኦና የዕርቅ ድርጅት” መሆኑን ለሕዝብ አቀረብኩ። ከአንባቢዎቼ የጠበቅሁት፥ ሐሳቡ የማያዋጣ ከመሰላቸው፥ ምክንያት ሰጥቶ ውድቅ ማድረግ፤ የሚያዋጣ ከሆነ፥ ተከታትለነው ከዚህ ትልቅ ብሔራዊ በሽታ እንፈወስ የሚል ነበር። ሰው ግን የጽሑፌን ቁም ነገር ወደጎን ትቶ፥ የሚያውቀውን ለመናገርና ብሶቱን ለመተንፈሻ አጋጣሚ አደረገብኝ። (1) አማራ አለ፤ (2) አማራ የለም፤ (3) አማራ በዘር መዘጋጀት የለበትም ለማለት ብዕር መዘዛ መጣ። ግን ሦስቱም የጽሑፌ የኅዳግ ነጥቦች እንጂ አስኳሎች አይደሉም።
ዶክተር ፀሐይ ብርሃነ መስቀል ብቻ የዕርቅ ድርጅ የማቋቋሙን ሐሳብ ደግፋ፥ ድርጅቱ በአካባቢ (regional) ቢሆን ይሻላል የሚል አማራጭ አቅርባለች። ግን ሐሳቧ የችግሩን መንሥኤ ይስታል። የተከሰሰው በአንድ አካባቢ ያለ ሕዝብ ሳይሆን፥ አማራው ተለይቶ ነው።
ሌላ ወዳጄ፥ በድርጅቱ ውስጥ አማራ ያልሆኑ ቢገቡበትስ የሚል ሐሳብ አቀረበልኝ። ይኸም የችግሩን መንሥኤ ይስታል። የተከሰሰው አማራው ተለይቶ ነው። ሌሎች እንደ አማራው ተከስሰው እንደ አማራው አልተጨፈጨፉም። ጽሑፌ ያተኮረው ወያኔ በሚያጠቃው ላይ ሳይሆን፥ ወያኔ በሚያስጠቃው ላይ ነው።
ፕሮፌሰር ሀብተ ጊዮርጊስ በዘር መደራጀትን (ከሞተበት) አናስነሣው የሚል ተማፅኖ አቀረበ። ጽሑፌን ባይጠቅስም የተማፀነው የኔ ሐሳብ ተቀባይነት እንዳያገኝ መሆኑ ግልጽ ነው። ይህን ጽሑፍ ያረቀቅሁት የሱን ጽሑፍ ስላየሁ ነው። የምናካሂደው ውይይት ሀገር የሚጠቅም መፍትሔ ለማግኘት ስለሆነ፥ ስሜትን ገታ አድርገን ከተወያየን፥ ልንግባባ እንዲያውም ከአንዳች ስምምነት ላይ ልንደርስ እንችላለን።
የፕሮፌሰር ሀብተ ጊዮርጊስ ተማፅኖ እንደገባኝ፥ በጎሳ ከመደራጀት በዲሞክራሲ ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች እንሥራ የሚል ነው። የዕርቅ ድርጅት ማቋቋምና በዲሞክራሲ ላይ የተመሠረቱ ሥራዎችን መሥራት ሲስማሙ እንጂ ሲጋጩ አይታየኝም። ልብ አላልነውም ይሆናል እንጂ፥ በባህል መደራጀት ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የተፈጠረ ነው። ለምሳሌ፥ ክርስቲያኖች በሃይማኖት ተደራጅተው ከፓርትያርክ (ከፖፕ) እስከ ዲያቆን የራሳቸው አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች አሏቸው። ከዚያም አልፎ፥ የዓለም-አቀፍ አብያተ ክርስቲያን ማኅበር አለ። ሙስሊሞችም ተመሳሳይ ድርጅት አላቸው። የአንድ ሰፈር ሰዎች እድር አላቸው። የነጋዴዎች ምክር ቤት አለ። በዓለም ላይ በሚደርስ ድንገተኛ አደጋ ለሚጎዱ ችግረኞች ፈጥነው የሚደርሱላቸው እንደ ቀይ መስቀል ያሉ የክርስቲያኖች የተራድኦ ድርጅቶች ናቸው። ዕርቅና ሰላም ለማምጣት አማሮችን ማደራጀት የሚኮነን ከሆነ፥ መጀመሪያ እነዚህ ድርጅቶች መኮነን፥ ቤተ ጸሎቶችም መዘጋት አለባቸው።
ዲሞክራሲ ያወጀልን ትልቁ ፍልስፍና ሰዎች ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳያቋቁሙ በሕግ መከልከልን ነው። ጽሑፌን የደመደምኩትም፥ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚቋቋም የፖለቲካ ፓርቲ መሠረት የሚያደርገው ሁሉን እኩል አብሮ በሚያሳድግ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ላይ ነው፤ ሕዝብን በዘርና በባህል የሚከፋፍል ድርጅት ግን “በሕግ መከልከል፥ መኰነንም አለበት። ለመረዳዳት፥ ከዚያም አልፎ ሌሎችን ለመርዳት ከሆነ ግን፥ በሕግ መፈቀድ፥ መደገፍም አለበት” በማለት ነው። እባብ ያየ ልጥ ቢያይ በራየ፤ የጎሳ ድርጅትን ጉዳት ያየ የተራድኦና የዕርቅ ድርጅትን ቢያይ በራየ ሆኖ ነው እንጂ፥ ድርጅቱ ስሕተት ኖሮበት አይደለም። ያልመከተ ተፈነከተ፤ ያልተደራጀ ተፈጀ የምለው ኢትዮጵያን ነው።